በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት ሹም ሽር ለማካሄድ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡበት መላኩን ምንጮች ገለጹ፡፡
ማን እንደሚሾምና ማን እንደሚሻር የሚተነትነው ሰነድ በአስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አማካይነት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
ሰነዱ በዋናነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባላት በሆኑ 16 ቢሮዎችና 84 የተለያዩ ኤጀንሲዎች ውስጥ ከፍተኛ ሹም ሽር እንዲካሄድ ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚህ የሹም ሽር ሰነድ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡበት የተላከ መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ለመምከር በቅርቡ የሚመለከታቸውን አካላት ስብሰባ ይጠራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ሹም ሽር እንዲደረግ የተወሰነው፣ የከተማው ነዋሪዎች በየጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩንና መረን የለቀቀ ሙስና መስፋፋቱን በመግለጽ ላይ በመሆናቸው ነው፡፡
የከተማው አስተዳደርና የከተማው ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ለረዥም ጊዜ ከመከሩ በኋላ እነዚህ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የአመራሮች የአቅም ማነስም አለ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የከተማውን ዕድገት ለማስቀጠል የአመራሮች ሹም ሽርና በአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች ላይ መጠነ ሰፊ የመዋቅር ለውጥ ማካሄድ እንደ አማራጭ መወሰዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረትም ሹም ሽር የሚካሄድበት ሰነድ ተዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲላክ፣ የመዋቅራዊ ለውጡን እንዲያጠና ደግሞ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሟል፡፡
‹‹የአዲስ አበባ አስተዳደር የአደረጃጀትና የመዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት›› በሚል ስያሜ ራሱን የቻለ ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ተቋቁሟል፡፡ ከንቲባ ድሪባ ኩማ የአዲስ አበባ ከተማ የመዋቅርና የአደረጃጀት ለውጥ እንዲያደርግ ያስፈለገበትን ምክንያት በቅርቡ በደሳለኝ ሆቴል በተጠራ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የምትገኝ ቢሆንም፣ ነገር ግን ይህንን ፈጣን ዕድገት የሚሸከም መዋቅር ባለመኖሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መዋቅሩ ዕድገቱን መሸከም ብቻ ሳይሆን፣ ከዕድገቱ ጋር እያደገ ላለው የኅብረተሰብ ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ መዋቅር አይደለም በማለት ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሹም ሽሩን ሰነድ ካፀደቁት የከተማው አስተዳደር የ2008 ዓ.ም. የመጀመርያውን የምክር ቤት ጉባዔ በመጥራት፣ የሚሾማቸውን አባላት ያፀድቃል ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል፡፡