Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየአባ ታጠቅ ካሳ 150ኛ ዓመት ከቋራ እስከ መቅደላ

የአባ ታጠቅ ካሳ 150ኛ ዓመት ከቋራ እስከ መቅደላ

ቀን:

‹‹ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም

ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም…

‹‹መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከት

- Advertisement -

የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ…››

ለዘመናዊት ኢትዮጵያ፣ ለ19ኛው ምእት ዓመቷ ኢትዮጵያ በር ከፋች፣ ለአሐዳዊት ኢትዮጵያ መነሳት በቀዳሚነት ለሚጠቀሱት በዱሮ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣ በንግሥና ስማቸው አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በዘመናቸው አዝማሪዎች ካንጎራጎሩት፣ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከ150 ዓመት በፊት ነበር መቅደላ አፋፉ ላይ በጄኔራል ናፒር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብለው በራሳቸው ላይ የፈረዱት፡፡

አሐዳዊት ኢትዮጵያን በማስረፅ የሚታወቁትና ‹‹አባ ታጠቅ›› በተሰኘው የፈረስ ስማቸው የሚጠሩት አፄ ቴዎድሮስ፣ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. መቅደላ ላይ ራሳቸውን መሰዋታቸው እምቢኝ ለአገሬ ብለው፣ ‹‹ሽጉጣቸውን አጉርሰው መጉረሳቸው›› ይታወሳል፡፡ እንግሊዞች እንደደረሱም ሙተው ያገኟቸዋል፡፡ በገና ደርዳሪውም እንደደረደረው፣

‹‹ገደልን እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው

ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው፡፡››

ይህን የንጉሠ ነገሥቱን ኅልፈት 150ኛ ዓመት መታሰቢያ በማድረግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር እንቅስቃሴውን ጀምሯል፡፡

በሚያዝያ ወር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሚከናወነው ዓለም አቀፍ ጉባዔ አስቀድሞ ቢሮው ከአፄ ቴዎድሮስ ሕይወት ጋር በተቆራኙት ታሪካዊ ሥፍራዎች ከቋራ እስከ መቅደላ ከመጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ጉብኝት አዘጋጅቷል፡፡ ጉብኝቱ ‹‹150ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ነው፡፡

ቢሮው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውና የሚጎበኙት ሥፍራዎች፣ አፄው ተወልደው ያደጉበት ቋራ እና አካባቢው፣ ጎንደር፣ ዘውድ የደፉበት በጃን አሞራ ወረዳ የምትገኘው ደርስጌ ማርያም፣ ዋና ከተማቸው አድርገዋት የቆዩት ደብረታቦርና የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ መንደር የነበረው ጋፋትና አካባቢው ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንዲሁም ንጉሠ ነገሥቱ የተሳተፉበት ከጋፋት እስከ መቅደላ ያሠሩት የመጀመርያው መንገድና የሴባስቶፖል መድፍን ያስጎተቱበት ከጋፋት እስከ መቅደላ ታሪካዊ የጉዞ መስመር ሌላው ተጎብኚ ሥፍራ ነው፡፡ በተጨማሪም የመጨረሻው ቤተ መንግሥትና ቤተ መዘክር የተመሠረተበት፣ ሕይወታቸው ያለፈበት የመቅደላ አምባ ከመጎብኘቱም ሌላ የጦር አዛዡ ፊታውራሪ ገብርዬ ከእንግሊዝ ጦር ጋር ሲፋለሙ የተሰዉበት እሮጌ የጉብኝቱ አካል ነው፡፡

የመይሳው ካሳ ዝክረ ዓመታት በማድረግ ‹‹የመቅደላ 150 ዓመት›› በሚል መሪ ቃል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚከበረው የጥናት መሰናዶ ላይ የንጉሡን አስተዳደግ፣ ርዕይና አሟሟት፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘመናዊነትና የዕውቀት ሽግግር ያመጡትን ለውጥ፣ ያጋጠሟቸው ፈተናዎች  ይፈተሻሉ፡፡ በሌላ በኩልም ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በአገራዊና በውጭ ጸሐፍት፣ በኢትዮጵያ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ አሻራዎቻቸው ለአሁኑ ትውልድ ያሏቸው አበርክቶ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ኅልፈት በኋላ ወደ እንግሊዝ የተወሰዱ ብሔራዊ ቅርሶች ዕጣ ፈንታ ማስገንዘቢያ እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

በ1810 ዓ.ም. በቋራ የተወለዱት አፄ ቴዎድሮስ የልደታቸው 200ኛ ዓመት በጎንደር መከበሩ ይታወሳል፡፡

ከ50 ዓመት በፊት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ያረፉበት 100ኛ ዓመት በ1960 ዓ.ም. ሲዘከር፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የመታሰቢያ ቴምብር አሳትሞ ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱን ምስል በተለያየ መልክ ይዘው ከወጡት ቴምብሮች መካከል በጎንደር ቤተ መንግሥታቸው ከአንበሶች መካከል ተቀምጠው የሚታዩበት አንዱ ነበር፡፡

የዘንድሮውን ክብረ በዓል አስመልክቶስ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የጎንደር፣ ደብረ ታቦር፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካላት ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር ለ150ኛው ዝክር ቴምብር ያሳትሙ ይሆን!?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...