Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት የብድር ዕዳ ክምችት እንደማያሳስበው አስታወቀ

መንግሥት የብድር ዕዳ ክምችት እንደማያሳስበው አስታወቀ

ቀን:

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ በየፊናቸው ሲያወጡ በተደመጠው ሪፖርት መሠረት፣ አገሪቱ የብድር ዕዳ እያሻቀበ በመምጣቱ በብድር ዕዳ ክምችት ላይ መንግሥት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሲያስጠነቅቁ ቢቆዩም፣ መንግሥት ግን የብድር ዕዳው አሳሳቢ አለመሆኑን አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ይፋ የሚደረገውን የዓለም የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርትን ተንተርሶ በተሰጠ መግለጫ ላይ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አብርሃም ተክስተ እንዳሉት መንግሥት የሚበደረውን ገንዘብ በምርታማ መስኮች ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡ መንግሥት ወደፊት የግሉን ዘርፍ በሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ላይ ኢንቨስት እያደረገ እንደሚገኝ ሲገልጹም፣ የሚያገኛቸውን ብድሮች በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በመንገዶች ግንባታ፣ በባቡር መስመሮች ዝርጋታ፣ በትምህርትና በጤና በመሳሰሉት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በሚረዱ መስኮች ላይ እያዋለ በመሆኑ፣ የአገሪቱ የብድር መጠን በየትኛውም መለኪያ ተከፋይና ኢኮኖሚውን መሸከም የሚችለው ነው ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት የሚያካሂደው ኢንቨስትመንት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ መሠረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ክህሎት፣ ግብርና እንዲሁም ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በርካታ ኢንቨስትመንት ይፈልጋሉ፡፡ ኢንቨስትመንቱ ወሳኝ ነው፡፡ የዓለም ባንክ ምን እያለ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መሥራት የጀመርነውን እየሠራን እንቀጥላለን፤›› ያሉት ዶ/ር አብርሃም፣ ከውጭ እየመጣ ያለው ብድር የኢኮኖሚውን ዕድገት ለማስቀጠል በሚረዱ ተግባራት ላይ እየዋለ በመሆኑ የዕዳ መጠን አሳሳቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይልቁንም አገሪቱ ለአሥር ዓመታት ያህል በየዓመቱ የአሥር በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ስታስመዘግብ ብትቆይም፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እንድትበር የሚፈቅድላት የገንዘብ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳይሆን ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጉን ዶ/ር አብርሃም ኮንነዋል፡፡ መንግሥት በንግድ ሎጂስቲክስና በትራንስፖርት መስክ ኢንቨስት ለማድረግ ብዙ ገንዘብ እንደሚፈልግም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ መንግሥታቸው ሲሶውን ወይም አንድ አራተኛውን በጀት ለትምህርትና ለክህሎት የሚያውለው የግሉን ዘርፍ ለመደገፍና ለማገዝ ጭምር በመሆኑ፣ የመንግሥት የብድር ሥርዓት ጤናማ መሆኑን በመግለጽ አብራርተዋል፡፡

ይህንኑ የአገሪቱን የብድር መጠን በመንተራስ ማብራሪያ የሰጡት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የንግድና የልማት ጉባዔ የአፍሪካ ዲቪዥን ዳይሬክተርና በማደግ ላይ ያሉ አገሮችና የልዩ ፕሮግራሞች ተጠሪ ዶ/ር ተስፋቸው ታፈረ፣ ብድር በአግባቡ ሥራ ላይ እስከዋለ ድረስ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም ብለዋል፡፡ አገሮች የሚበደሩት ለልማት እስከሆነ ድረስ የብድር ዕዳ ችግር እንደማይሆን ጠቅሰው፣ ከዚህ ተፃራሪ በሆነ መንገድ እንደ ግሪክ ያሉ አገሮች የገቡበት ቀውስ ብድርን ለፍጆታ በማዋል ጭምር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ የአቴንስ ኦሎምፒክ ውድድርን ለማዘጋጀት ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በብድር ወስደው ወጪ ሲያደርጉ፣ እንዴት እንደሚመልሱት ባለማሰባቸው ችግር ውስጥ መግባታቸውን ዶ/ር ተስፋቸው አስታውሰዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የብድር ዕዳ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) አንፃር ሃምሳ ከመቶ በመድረሱ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባሻገር እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ግሽበትም ትኩረት እንዲሰጠው አሳስቧል፡፡ የዓለም ባንክ ከጥቂት ወራት በፊት ይፋ ያደረገው ሪፖርትም የአገሪቱ የብድር መጠን ከጂዲፒው አኳያ በሁለት ዓመት ውስጥ 65 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል መተንበዩ አይዘነጋም፡፡ ይህም ሆኖ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በማደግ ላይ በመሆኑ አገሪቱ ዕዳን የመሸከም አቅሟና የመመለስ ብቃቷ ጥያቄ እንደማይፈጥር የባንክ ባለሙያዎችና ኢኮኖሚስቶች የሚስማሙበት ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጠቅላላ የብድር መጠን ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወይም ከ1.2 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱን የዓለም ገንዘብ ድርጅት ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ የተደረገው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ የዘንድሮው ሪፖርት፣ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚያሳስብ ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ላይ እየደረሰ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ እንደ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ እስካሁን መፍትሔ ሊያገኝ ካልቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የዓለም የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚደረግ ጠንካራ ቁጥጥር ባለመኖሩ እንደሆነ ዶ/ር ተስፋቸው አብራርተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎችን እንደሚቆጣጠረው እንደ የዓለም የንግድ ድርጅት ያለ ተቋም ለፋይናንስ ዘርፉ ባለመኖሩ የብድር አሰጣጥ፣ የዶላር የመግዛት አቅም ማንሰራራትን ተከትሎ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል ግምት የሚሰጡ ብድሮችና የንግድ እንቅስቃሴዎች፣ ፈንድ በሚሰጡ ተቋማት በሚደረግ አግባብነት የሌለው የፋይናንስ ገበያ ንግድ ሳቢያ የኢኮኖሚ ቀውሶች እየተባባሱ ለመምጣታቸው ምክንያት ተደርገዋል፡፡

የቡድን ሃያ አገሮች የዓለም የገንዘብ ድርጅት ላይ ቁጥጥር ከማድረግ ባሻገር ሪፎርም እንዲደረግበት ሲወተውቱ ቢቆዩም፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት ተግባራዊ ለውጥ አልመጣም ያሉት ዶ/ር ተስፋቸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቻይና የተመራው የእስያ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ እንዲሁም ብራዚል፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ አፍሪካ በጋራ የመሠረቱት ‹‹ብሪክስ›› ያቋቋመው ባንክ ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ጥሩ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በርካታ አገሮች በፋይናንስ ቁጥጥር አለመኖር ሳቢያ ከ200 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ለመሸከም ሲገደዱ፣ በርካታ አገሮችም 40 በመቶ የመጠባበቂያ ክምችታቸውን ከብድር ባገኙት ገንዘብ ለመሸፈን ተገደዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የዓለም ኢኮኖሚ ዘንድሮ ከ2.5 በመቶ በላይ ሊያድግ እንዳልቻለ፣ በዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና ባልረገበው ቀውስ ሳቢያ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ልጓም እየሳበ እንደሚገኝ ባለሙያዎች አብራርተዋል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያና አንጎላ ያሉ አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ላይ መቀዛቀዝ እየታየ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የአፍሪካ ጽሕፈት ቤቱን የከፈተው የተመድ ንግድና የልማት ጉባዔ ለአፍሪካ መንግሥታት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ከመስጠት ጀምሮ የጉምሩክ አሠራሮች ላይ፣ የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ልማት ላይ፣ የትንታኔ ሥራዎችና ሌሎች ተግባራትን በሚመለከት ድጋፍ እሰየጠ እንደሚገኝ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር ጆይ ካፌጋካዋ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...