የታክሲን ትዕይንት ሳስተውል ሁሌም የምመሰጥበት ነገር አላጣም፡፡ በተለይ በመዲናችን በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት ነዋሪው ከሚጠቀምባቸው የመጓጓዣ ዓይነቶች አንዱ ታክሲ እንደመሆኑ መጠን የነዋሪውን አመል፣ ፍላጎት፣ መግባባት፣ አለመግባባትና ጭቅጭቅ ማየት የተዘወተረ ተግባሬ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ለባለታክሲዎችና ለታክሲ ተጠቃሚዎች በመልካም መተሳሰብ የተገነባ ሰላማዊ ግንኙነት ብመኝም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን በተራ ነገር በሚፈጠር እንካ ሰላንቲያ ወይም ንትርክ ፈገግ እያልኩኝ መንገዴን አወራርድበታለሁ፡፡
ተሳፋሪው የሚደርስበትን ቦታ እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለሥራው በማውጠንጠን በአንድ የጉዞ ጣሪያ ሥር ተሰባስቦ ታክሲውን ጉዞ አስጀምሯል፡፡ ወያላው ልጅ እግር ቢጤ ሲሆን፣ ተሳፋሪ እንዲገባለት በመጣራት ብዙ እንዳይደክም የእሱ ታክሲ ብቸኛ ሆና በአካባቢው መታየቷ ጠቅሞታል፡፡ ‹‹ብትፈልጉ ግቡ ባትፈልጉ ተውት›› ዓይነት አስተያየቱን ችላ ብለንና በታክሲዋ መገኘት ፈጣሪን አመስግነን ጉዟችንን ከመርካቶ ወደ አራት ኪሎ ጀምረናል፡፡
የታክሲያችን ውስጣዊ ይዞታ በትርፍ ሰዓቱ ፊልም ቤት እየሆነ የሚያገለግል ይመስል፣ በተለያዩ የፊልም ተዋንያን ምሥል ተዥጎርጉሮ የወያላውን ወይም የሾፌሩን ፊልም አፍቃሪነት ልናገር ይላል፡፡ የሚገርመው አንድም አገር በቀል ተዋናይ አለመለጠፉ አሳዘነኝ፡፡ የአገሬው ተዋንያን ምሥል ሊለጠፍ ያልቻለበትን ምክንያት ካገኘሁ ብዬ፣ ከተለጠፉት ተዋንያን መካከል ቢገኙ በማለት አተኮርኩ፡፡ እያንዳንዱን ተዋናይ በጥልቀት አስተዋልኩ፡፡ ሁሉም ላይ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር የተክለ ሰውነት መፈርጠምን ነው፡፡ ታዲያ የአገራችን ተዋንያን ጡንቻ አልባ መሆን ይሆን ይህችን በመሰለች ‹‹የሆሊውድ መንደር›› ውስጥ እንዳይኖሩ የከለከላቸው ስል አሰብኩ፡፡
ሆነም ቀረ ጠፋም ለማ ጉዟችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ ታክሲያችን ውስጥ ከተለመደው ለየት ባለ ሁኔታ ጨዋታ ደርቷል፡፡ በወሬ ሳንጠመድ እየተጓዝን ያለነው እኔና ሾፌሩ ብቻ ነን፡፡ ሾፌሩን በከፊል ከከለለው መቀመጫው ጀርባ ለማስተዋል ስጥር፣ በቀይ እስኪቢርቶ የተጻፈ ጥቅስ ካይኔ ገብቶ ሐሳቤን ገዛው፡፡ ‹‹አባቴን የምታውቀው እናቴ ብቻ ናት!›› ይላል፡፡ ከጥቂት የግርምት ፈገግታዬ ግርጌ ጥያቄ ተቀጣጠለ፡፡ እንደ ማንኛውም የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች ሁሉ ይኼኛው በታክሲ የጥቅስ ጸሐፊ በሆነው ሰው አልተጻፈም፡፡ ምናልባት የወያላው ወይም የሾፌሩ የበርካታ ዓመታት ታሪክ በዚህች ጥቅስ ውስጥ ከንፈር ያስመጠጠች እውነት ሆና ቀርታ ይሆን ስል አሰብኩ፡፡ አፍታም ሳልቆይ እንዲህ ይሆን ወይ እያልኩ መቀጠል እንደማይኖርብኝ ገባኝና ወያላውን ‹‹እንዴት ነው የወጣለት ፊልም ተመልካች ትመስላለህ?›› ስል ጨዋታ አስጀመርኩት፡፡
‹‹ምን ታደርገዋለህ? በዙሪያህ ያለውን ነገር ለመርሳት ግድ የምትሸሽበት ሥፍራ ያስፈልጋል፤›› አለኝ፡፡ ወሬያችንን በነፃነት ለመቀጠል የተሳፋሪው እርስ በርሱ በወሬ መጠላለፍ ረድቶናል፡፡ ‹‹እንዴት?›› አልኩት፡፡ የእርሱን ዓለም የሕይወት ፍልስፍና ለመስማት ጓጉቼ፡፡ ‹‹ያስጠላላ!! እዚህ ስንት ዓይነት ሰው እየተጫነ ይወርዳል መሰለህ? ከፍሎ ስለተጓዘ ብቻ አንተን የፈጠረህ ሁሉ የሚመስለው ብዙ አለ፤›› አለኝ፡፡ ‘ያልተማረ ሀብታም ደሃን የፈጠረው ይመስለዋል’ የሚለውን አባባል እያሳየኝ፣ ‹‹ግማሹ አውቆ እንዳላወቀ ይሆንና ታክሲዎች ስትባሉ . . . እያለ ይወቅጥሃል፡፡ ኧረ አንዳንዱማ ካልደበደብኩህ እያለ ለያዥ ለገላጋይ ያስቸግራል፤›› አለ በተመረረ ስሜት፡፡ ‹‹ፊልም ተመልካችነትህ ታዲያ ለዚህ ያለው አዎንታዊ ጥቅም ምንድነው?›› አልኩት፡፡ ከልቡ በተሳፋሪ የሚደርስበትን የበደል ብዛት እያሰላ ሲበሳጭ አቋርጨው፡፡ ‹‹ምን ነካህ? ቢያንስ ለምሳሌ እኔ በበኩሌ ፊልም ውስጥ የራሴን ኑሮ አላይም፡፡ ምክንያቱም በሌሎች አገሮች እንደኛ ዓይነት የታክሲ አገልግሎት ስለሌለ፡፡ ስለዚህ የቀን ውሎዬን ሳላስታውስ ቀረሁ ማለት አይደል?›› አለ፡፡
‹‹ያችን ጥቅስ አንተ ነህ የጻፍካት?›› አልኩት፡፡ ‹‹አዎ ጥቅስ እንኳን አይደለችም፣ ግን ራሴ የፈጠርኳት አባባል ናት፤›› ጥቂት እንደ ማቅማማት እያለ፣ ‹‹ኑሮ ብዙ ያሳስብሃል፣ የሚገርምህ አባቴን አላውቀውም፡፡ ባለውቀውም ግን እወደዋለሁ፡፡ አንድ ቀን አንዲት ልጅና አባቷ ተሳፍረው ሳለ እኔም በአባትና በልጅነታቸው መሀል ጥልቅ ብዬ ገብቼ አባቴን ማወቅ አሰኘኝ፡፡ እንደዚያ ቀን ተነጅሼ አላውቅም፡፡ እናም ያቺን አባባል ጻፍኳት፡፡ ጸሐፊዎች ብዙ ነገር ሊጽፉ ቢችሉም አንዳንድ ጊዜ የራስህን ጉዳይ እንደ ራስህ አይጽፉልህም፤›› ሲለኝ፣ ይኼ ወያላ የገባው መሰለኝ፡፡
እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ከእንደዚህ ዓይነት ተራ መሳይ ሰዎች ስሰማ ሁሌም ቢሆን ድንጋጤ ካሸለብኩበት የንቀት ዓለም ይቀሰቅሰኛል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ዕጦትና ግኝት እንዳለው ለማሰብ ብሞክርም፣ ይህን ያህል በሐዘን የሚበላ ምትኃት ይኖረዋል ብዬ አላስብም ነበር፡፡ የታክሲዋ ተሳፋሪዎች ጨዋታ እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ሳቅ፣ ጨዋታና ፍቅር ነግሶበት በፍልቅልቅ ገጾች ታጅቦ ታክሲያችን እየተጓዘ ነው፡፡ እንዲህ ሁሉም ከተጣደበት የኑሮ እሳት ላይ እየፈላና ፈልቶ እየተንከተከተ በፍቅር ሲኖር ሲታይ፣ አንዳች ከደስታ ጋር የተሳከረ ስሜት ከውስጥ ካልፈነቀልኩ እያለ ይታገላል፡፡ አጠገቤ የተቀመጡት እናትም በሳቃቸው ላይ የእርጅና ውበት በድምቀት ተስሎ በስልክ የያዙትን ጨዋታ ይኮመኩማሉ፡፡
ፒያሳ ስንደርስ ወያላው ሾፌሩን ‹‹ወራጅ አለ!›› ብሎ እንዲቆም አዘዘውና ትኩረታችን እንደተለመደው የሚወርደውን ሰው ፍለጋ ማማተር ጀመረ፡፡ በዚህ መሀል ያለማንም ከልካይና ሰቀቀን ሙቆ የነበረው ጨዋታ በአንዴ ቀዘቀዘ፡፡ ወያላውን ማንም ወራጅ ያለው ባይኖርም ምናልባት በምልክት የነገረው ይኖራል ብሎ ሁሉም አጠገቡ የተቀመጠውን ሰው ለማሳለፍ ያማትራል፡፡ ይኼኔ ነበር ሰው ግራ ተጋብቶ እርስ በርስ በሚፋጠጥበት ጊዜ ወያላው ራሱ ወራጁን የመረጠው፡፡ አጠገቤ ወደተቀመጡት ሴት እያፈጠጠ፣ ‹‹ቶሎ በይ ውረጂ፣ ሰዓት የለም፤›› አላቸው፡፡
ሴትዮዋ ሳያስበው በመከራ ተፈልጎ እንደተያዘ ሌባ ደንዝዘው ተራ በተራ ተሳፋሪውን ያያሉ፡፡ ‹‹ኧረ ቶሎ በይ፤›› ይላል ወያላው፡፡ ለማመን ከብዷቸው፣ ‹‹እኔን ነው?›› አሉት፡፡ ‹‹አዎ አንቺን ነው ፈጠን በይ፤›› አላቸው፡፡ ሴትዮዋ አጠገቤ እንደ መቀመጣቸው መጠን ወራጅ አለማለታቸውን እርግጠኛ ነኝ፡፡ ታዲያ ምን ማለቱ ነው ይኼ ወያላ? ‹‹ለምንድን ነው የምወርደው?›› አሉት፡፡ ‹‹የከፈልሽው እኮ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ነው፣ ከቀጠልሽ ያስጨምርሻል፤›› ሲላቸው፣ ‹‹ለዚህ ነው ሾፌሩን አስቁሞ ውረዱ የሚላቸው? ታዲያ ያስጨምርዎታል ብለህ እንዲጨምሩልህ መጠየቅ ይቀላል ወይስ ታክሲዋን አስቁመህ ኑ ውረዱ ማለት?›› አለችው አንድ ወጣት ነግ በእኔ በሚል ስሜት፡፡ ሴትዬዋ አሁንም በወያላው ሥራ ከመገረም አልፈው በዝምታ ተውጠዋል፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎችም በየፊናቸው በወያላው ወጣ ያለ ድርጊት ተደንቀው እርስ በርስ ይንሾካሹካሉ፣ ምን ዓይነቱ የማይረባ ነው ይልቅ ደህና ጨዋታችን አደፈረሰብን በሚል መንፈስ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ሾፌሩ ዝም ብሏል፡፡ ከዚህ ከሾፌሩ ሁኔታ እንደተረዳሁት ይህን መሰል የወያላው ድርጊት ተደጋግሞበት ማማረር ደረጃ ላይ እንደ ደረሰ ነው፡፡
ከአፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት ምንም መሸማቀቅ ሳያሳየን፣ ‹‹እኮ መጨመር ነዋ፣ ከመርካቶ አራት ኪሎ እኮ ሁለት ብር ከሰባ አምስት ሳንቲም ነው፤›› አለ ለጥፋቱ ምንም የይቅርታ ቃል ሳይጋብዘን፡፡ ‹‹ታደያ ነግረኸኛል ልጄ? እኔ እኮ ለመንገዱም ገና አዲስ ነኝ፡፡ የሚገርምህ…፤›› አሉኝ ወደኔ ዞረው፡፡ ይኼኔ ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ የተቋረጠው የተሳፋሪው የሞቀ ጨዋታ በወያላው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ትኩረቱ ወደ ሴትዮዋ ስሞታ ዞረ፡፡ ‹‹…የሚገርምህ እንዲህ እንደ ዛሬ ልጆች ባይሆንም የመቸኮልና የእሳትነት ዕድሜ ላይ ሳለን የማውቃትን ወዳጄን ልጠይቅ ከመምጣቴ በቀር ያለ ዛር ሠፈሩን አላውቀውም፤›› አሉ፡፡ ወደ ወያላው ዞር ብለው ‹‹ይኼውልህ ሒሳብህ ልጄ፤ ግን አትቸኩል እሺ!! አይዞህ በሕይወት ውስጥ ዋናው ቁምነገር ዕድሜን መብለጥ መቻል ነው፡፡ እኔ ቢያንስ ወልጄ አደርስሃለሁ፡፡ አንቺ የምባል ሴት አይደለሁም፡፡ አክብሮትን መንፈግ ዘመናዊ አያሰኝም፡፡ የዛሬ ልጆች መቼም ከእኛ በላይ ላሳር ብላችኋል፡፡ ምን እንደሚሻላችሁ እንጃ? የግብራችሁ እንዲህ ዘሎ ቀንድ መንከስ አባቱ ማን ይሆን?›› አሉት ረጋ ብለው በእናትነት ቃና፡፡
ተሳፋሪዎች በሴትየዋ የንግግር ለበቅ አንጀታቸው ቅቤ እንደ ጠጣ ሁሉ ተደሰቱ፡፡ በእሰይ ዓይነት ማብሸቅ ሾፌሩም እያሳየው ሳቀበት፡፡ ይኼኔ የተጨመረለትን ቀሪውን ሒሳብ በኃፍረት ተቀበላቸው፡፡ በሴትዮዋ ጥልቅ የመረጋጋትና ብዙ የማየት ተሞክሮ በብዙ ተገርመን በብዙ ቀናን፡፡ በቅናታችን ውስጥ ችኮላችንን ጠልተን የስክነት ዕድሜን ናፈቅነው፡፡ ቁጣንና ተግሳጽን በመልካም ምላስ ማብረድ ማለት ይኼ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ጥቅስ ለማግኝት ዓይኖቼን በእነዚያ ነጭ ተዋንያን መሀል በችኮላ አስሮጥኳቸው፡፡ አጣሁት፡፡ ልጅ እግሩ ወያላ ያለኝን አሰብኩ፡፡ ‹‹ጸሐፊዎች ብዙ ነገር ሊጽፉ ቢችሉም አንዳንድ ጊዜ የራስህን ጉዳይ እንደ ራስህ አይጽፉልህም፤›› ያለኝን፡፡ እኔም እንዲህ አልኩ፣ ‹‹አንዳንድ ጊዜ የራስን ጉዳይ እንደ ራስ አስበን፣ እንደ ራስ ብንጽፈውም ድክመታችንን አያወጣውም፡፡›› ቆይ፣ ቆይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ድክመታችንን ለመደበቅ ለምን እንሯሯጣለን? ጠንካራው ሥራችን ሲወሳ፣ ድክመታችን ለምን ይደበቃል? እንዲህ ከኑሮ መንገዳችንና ከታክሲ ውስጥ የማይረሱና አስተማሪ አጋጣሚዎችን አለማጣት በእውነት መታደል ነው፡፡ መዳረሻችን ሲደርስና መውረድ ስንጀምር ትንፋሽ ሳይቆይ ቢረሳንም ቅሉ፣ በታሰበን ቀን ሁሉ ያላንዳች ትርጉም አይተወንም፡፡ አራት ኪሎ ደርሰን በየፊናችን ስንበታተን ‘የአራዳ ልጅና የጣት ወርቅ አንድ ነው፣ ሹልክ ያለ እንደሆን ፈላጊው ብዙ ነው’ የሚል ዕድሜ ጠገብ ዜማ ከአንዱ ካፌ ድምፅ ማጉያ ይሰማል፡፡ ‹‹አራዳ ድሮ ቀረ እባካችሁ…›› እያለ አንዱ ሲጣደፍ ሌላው ደግሞ ‹‹ወሬ ብቻ…›› አለ፡፡ አራት ኪሎ ሆነን ከወሬ የበለጠ ምን ልናገኝ ኖሯል? ሥራማ ድሮ ቀረ፡፡ ሥራ ሌላ ወሬ ሌላ፡፡ መልካም ጉዞ!!