Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልያልተደረሰው የ500 ዓመት ሀብት

ያልተደረሰው የ500 ዓመት ሀብት

ቀን:

ወደ ሱባ ፓርክ እንደደረሱ ለማብሰር ከቆመው የእንጨት ምልክት ጋር ሲደርሱ፣ አንዳች የእፎይታ ስሜት ይወራል፡፡ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ያለው ፀጥታ ፍፁም ሰላም ያሰፍናል፡፡ የአእዋፋቱ ዝማሬና ነፋሻማው አየር መንፈስን የማደስ ኃይል አለው፡፡ ፓርኩን አቆራርጠው በግዙፍ፣ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች መካከል ሲጓዙ ልዩ ቀለም ያላቸው ቢራቢሮዎች ያጅባሉ፡፡ ከቅርብ ርቀት አልፎ አልፎ ድምጻቸው የሚሰማው እንስሳትም የፓርኩ ተጨማሪ ውበት ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሱባ ለመድረስ፣ የሚታለፈው ግርግርና አስቸጋሪ መንገድ በፓርኩ ገጽታ በመጠኑም ይረሳል፡፡ ረዥም ርቀት በእግር መጓዝ የሚችሉ ከፓርኩ በላይ ካሉ ተራራዎች ይደርሳሉ፡፡ ያልቻሉም በየደረሱበት ያለውን የተፈጥሮ መስህብ ይቋደሳሉ፡፡

ከ9,000 ሔክታር በላይ በሆነ መሬት የተንጣለለው ሱባ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታሪካዊ ፓርኮች አንዱ ሲሆን፣ በብዝሀ ሕይወት ከበለፀጉ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ በአፍሪካ ካሉ ፓርኮች ዕድሜ ጠገቡ እንደሆነም ይነገርለታል፡፡ ፓርኩ የተመሠረተው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ ንግሥና ወቅት ነበር፡፡ ንጉሡ በወቅቱ ባዶ የነበረውን አካባቢ በዕፀዋት የሞሉት ወፍ ዋሻ ከተባለ ስፍራ ባስመጧቸው የዕፀዋት ዝርያዎች ነበር፡፡

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ1900 ዓ.ም. የጥብቅ ደን አዋጅ ባስነገሩበት ጊዜ በአዋጁ ከተካተቱ ውስጥ ይኸው ፓርክ አንዱ ነው፡፡ በአገሪቱ ግንባር ቀደም የሚባለው የችግኝ ጣቢያ የተቋቋመው በፓርኩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ፓርኩን ያስጐበኘን አቶ ኃይሉ ጥላሁን በሱባ ሰበታ ዲስትሪክት ፓርክ የኢኮቱሪዝምና የዱር እንስሳት ባለሙያ ነው፡፡ ፓርኩን ልዩ ያደርገዋል በሚል ከሚጠቅሳቸው አንዱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ዘመን የተተከለው ሱክያ (አይረን ውድ) የተሰኘ ዛፍ ነው፡፡ ዛፉ ፍሬ የሚሰጠው በ70 ዓመቱ ሲሆን፣ ለንጉሡ 70ኛ ዓመት የልደት በዓል ከተበረከቱ ስጦታዎች አንዱ ነበር፡፡

በፓርኩ 500 ዓመት የሆነው (በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተተከለ) የፅድ ዛፍ ይገኛል፡፡ በፓርኩ ታሪክ አይረሴ ከሆኑት በ1892 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የገባው የእንጨት መሰነጠቂያ ይነሳል፡፡ በእንፋሎት ኃይል የሚሠራው ማሽኑ የተተከለው፣ ለመኳንንት የሚሆኑ ቤቶችን ለማዘጋጀት የሚውሉ እንጨቶች እንዲሰነጠቁበት ታልሞ ነበር፡፡ ማሽኑ ከተተከለ በኋላ ለ30 ዓመታት ያህል ወደ 1,600 ሔክታር የሸፈኑ ዕፀዋት ተቆርጠዋል፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ደግሞ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ 3,500 ሔክታር የሚሆን ደን እንደተጨፈጨፈ አቶ ኃይሉ ይናገራል፡፡ እንጨቱን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝም የባቡር ሐዲድ ተተክሏል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ በወቅቱ ደኑ የደረሰበት ጭፍጨፋ በፓርኩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እንጨት መሰንጠቂያው በፓርኩ ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ቢጥልም፣ በታሪካዊነቱ ለጐብኚዎች ዕይታ ይቀርባል፡፡

ፓርኩ የሚገኝበት አካባቢ (ማለትም በአቅራቢያው ያሉት ሞግሬ፣ አደሬና ዳሞቻ የተባሉ ተራራዎችንም የያዘው) ወጨጫ ይባላል፡፡ በሆለታ አልያም በሰበታ መስመር ወደ ፓርኩ መሔድ ይቻላል፡፡ ፓርኩ ከጥቂት ዓመታት በፊት በፌደራል አስተዳደር ሥር መናገሻ ሱባ ፓርክ በሚል ይተዳደር ነበር፡፡ አሁን ሱባ ሰበታ ዲስትሪክት ፓርክ የሚል በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ሥር ይገኛል፡፡

ከባህር ወለል በላይ ከ2,200 እስከ 3,385 ሜትር ከፍታ ላይ በሚገኘው ፓርኩ 186 የአዕዋፋት ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ ግንደ ቆርቁር (አቢሲኒያን ዉድ ፓከር)፣ አቢሲኒያን ካት በርድ፣ ብላክ ሔርድ ሲስኪንና የሎ ፍሮንትድ ፓሮት የተባሉት ዝርያዎች አገር በቀል ናቸው፡፡ ፓርኩ ከ32 በላይ የሚሆኑ አጥቢዎች መኖሪያም ነው፡፡ 12 ከሚደርሱት ትናንሽ አጥቢ እንስሳቶች፣ ኋይት ሩትድ ራት (እግረ ነጭ ፍልፍል) እና 20 ከሆኑት ትልልቅ አጥቢዎች ደግሞ የምኒልክ ድኩላ አገር በቀል ናቸው፡፡

በፓርኩ ከ70 ዓይነት በላይ ዕፀዋት ያሉ ሲሆን፣ ጽድ፣ ወይራ፣ ጥቁር እንጨትና ዝግባ ይጠቀሳሉ፡፡ በፓርኩ ያሉ ዕፀዋት እርስ በእርስ ተሳስረው ስለሚታዩ ‹‹ጁኒፈር ኦልያ ቤልት›› የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸዋል፡፡ በፅዶቹ ሥር የበቀሉ ወይራዎች በፅዶቹ ላይ መጠምጠማቸው ይጠቀሳል፡፡  

በፓርኩ አራት ካምፕ ሳይቶች (ጐብኚዎች እንደማረፊያ የሚጠቀሙባቸው) ቦታዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው በፓርኩ መግቢያ የሚገኘው ሳይት ሲሆን፣ ኤግዚቢሽን ሴንተር ሌላው ነው፡፡ ገበር ካምፕ ሳይት፣ መልካ ኢትዮጵያ ሰኚ ለተሠኘው ፕሮጀክቱ የሚጠቀምበት ነው፡፡ ሞሩ ካምፕ ሳይት የተባለው የሎ ፍሮንትድ ፓሮትን የመሰሉ አዕዋፋት እንዲሁም ጅብ፣ ነብርና የዱር ድመትን የመሰሉ እንስሳትን ለመመልከት የተመቸ ነው፡፡ ጃንሆይ ካምፕ ሳይት በሚል የሚታወቀው ሳይት፣ ቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለማረፊያ ይጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡

ፓርኩ አራት ዋና ዋና መንገዶች አሉት፤ በመኪና በእግር ወይም በሳይክል የሚኬድባቸውም ናቸው፡፡ ጦና መንገድ በአንድ ወቅት የፓርኩ ጥበቃ ሠራተኛ በነበሩና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባበረከቱ ግለሰብ ስም የተሰየመ መንገድ ነው፡፡ አራት መንታ የባቡር ሐዲድ መስመርና የእንጨት መሰንጠቂያው የሚገኝበት እንዲሁም የምኒልክ ድኩላ በብዛት የሚታይበት ነው፡፡ ኦልድ ትሪ መንገድ ረዥም ዕድሜ ያለው ዛፍ መገኛ ሲሆን፣ ሜይን መንገድ ወደ አደሬ፣ ሞግሌና ዳሞቻ ተራራዎች ይወስዳል፡፡ በጉዞ ዘለግ ያለ ጊዜ (ወደ 4፡30 የሚወስደው) ደግሞ ወተር ፎል መንገድ ነው፡፡

ጐብኚዎች ለፓርኩ እንዲሁም ለተፈጥሮ በአጠቃላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ከሚተላለፍበት መንገድ አንዱ  በፓርኩ መግቢያ ላይ ያለው ቅርፅ ነው፡፡ ቅርፁ ‹‹ደን አጥፊው አደገኛ አውሬ ተይዞ እዚህ ውስጥ ታስሯል፤ እንዳያመልጥ በጥንቃቄ ይመልከቱ፤›› የሚል መግለጫ የሰፈረበት ነው፡፡ ጐብኚዎች አንዳች እንስሳ የያዘ የሚመስል ቅርፁን ከፍተው ቁልቁል ሲመለከቱ፣ ራሳቸውን በመስታወት ይመለከታሉ፡፡ ጐብኚዎች ካምፕ ፋየር ማዘጋጀት ከፈለጉ ፓርኩ የሚሰጣቸውን እንጨት ገዝተው ይጠቀማሉ፡፡

አቶ ኃይሉ እንደሚናገረው፣ አምና ወደ 9,800 ሰዎች ፓርኩን ጐብኝተዋል፡፡ የውጭ አገር ጐብኚዎች፣ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎችና ለመዝናናት የሚሔዱ ይገኙበታል፡፡ ፓርኩ ካለው የብዝሀ ሕይወት ሀብትና ታሪካዊ አመጣጥ ግዝፈት አንፃር ግን በበቂ ሁኔታ እየተጐበኘ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ በዋነኛነት የሚቀመጠው ምክንያት ደግሞ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት ነው፡፡

ወደ ፓርኩ የሚወስደው መንገድ በበጋ አቧራ በክረምት ጭቃ ይፈታተነዋል፡፡ ፓርኩ የሚሰጠው አገልግሎትም ሙሉ አይደለም፡፡ መብራት የሚሠራው በጄነሬተር ሲሆን፣ በምሽት ብቻ ይሠራበታል፡፡ ፓርኩ የተመሠረተበትን ጊዜ ከግምት በማስገባት ባለፉት ዓመታት ከመሻሻል ይልቅ ባለበት የቆመ ይመስላል፡፡ የፓርኩ የተፈጥሮ ሀብት በተለያየ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች እንደ መማሪያ የሚጠቀስ ቢሆንም ትኩረት የተነፈገው ይመስላል፡፡ 

‹‹ፓርኩ መሠረተ ልማት አልተሟላለትም፤ ማስተዋወቂያም አይሠራለትም፤ በተሠራበት ዘመን ላይ እንዳለ የቆመ ነው፤ መንግሥትም የረሳው ይመስላል፤ ለአገሪቱ መጥቀም ሲችል ብዙ ያልተሠራበት ስፍራ ነው፤›› ይላል አቶ ኃይሉ፡፡

ፓርኩ በመደበኛ መንገድ ሲተዋወቅ አይታይም፡፡ ስለዚህም በስሚ ስሚ የሚጐበኘው ሰው ቁጥር ያመዝናል፡፡ ለጉብኝት የሚሔዱ ሰዎች በቂ መረጃ የሚያገኙበት መንገድ እንዲኖር የሰው ኃይል መሟላትም አለበት፡፡

በፓርኩ ቅርንጫፍ ያለው መልካ ኢትዮጵያ ወደ ሱባ የገባው ከስምንት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ሰኚ በተባለው ፕሮጀክት፣ በተለይም ወጣቶች ከተፈጥሮ ጋር እንዲተሳሰሩ ለጥቂት ቀናት በደኑ ውስጥ እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡ ድርጅቱ በሆለታና ሰበታ ከተሞች ለሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣኖችና የሕግ ባለሙያዎች በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችንም ያዘጋጃል፡፡

ወደ ፓርኩ የገቡት ደኑን ለመጠበቅ እንደሆነ የሚናገሩት የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሚሊዮን በላይ፣ በእንቅስቃሴያቸው የተመዘገበ ለውጥ ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ችግሮች አልተቀረፉም ይላሉ፡፡ ለፓርኩ የሚደረገው ጥበቃ መጠናከር፣ በፓርኩ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎትም መሻሻል እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

በተያያዥም ፓርኩ በጀት ተመድቦለት ያለበት ሁኔታ መሻሻል አለበት፡፡ ‹‹አሁን ያለበት ሁኔታ ያሳዝናል፤ በከተማ አካባቢ አረንጓዴ ስፍራ የለም በሚባልበት ሁኔታ ሱባ ውስጥ ግን የሚያምር ገፅታ አለ፤›› በማለት ሰዎች በስፋት በፓርኩ የሚጠቀሙበት መንገድ እንዲፈጠር ያሳስባሉ፡፡

ፓርኩ በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማ ካለው ቅርበት በመነሳት በብዙዎች አለመጐብኘቱን አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የፊንፊኔ ቅርንጫፍ የዱር እንስሳት ልማትና አጠቃቀም አስተባባሪ አቶ ተከተል ፈጠነ፣ ፓርኩ በቱሪዝም መስህብነት የበለጠ እየታወቀ የመጣው ከ2001 ዓ.ም. ወዲህ በመሆኑ አበረታች ጅማሮ እንዳለ ጠቅሰው፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላቱ ግን የጐብኚዎችን  ቁጥር በማሳነስ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይናገራሉ፡፡

ጐብኚዎች አሁን ካለው የተሻለ ቆይታ እንዲኖራቸው የማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀትና ካምፕ ሳይቶችን ለማሻሻል የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ወደ ፓርኩ የሚወስዱ መንገዶች ያልተሠሩት በአቅም ማነስ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ፓርኩ የሚያገኘው ገቢ ውስን በመሆኑ ለመንገድ ግንባታ በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር መንገዱን ለማሠራት ጥረት ቢደረግም አልተሳካም፡፡

በመብራት ረገድ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ክፍያ ከፈፀመ ሦስት ዓመት ቢሆንም ሥራው እንዳልተጀመረ ጠቅሰዋል፡፡ ፓርኩን ለማሻሻል ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር የቢዝነስ ዕቅድ ማውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ ዕቅዱ ለፓርኩ እገዛ ማድረግ ከሚችሉ ሦስተኛ ወገኖች ጋር የመተባበር ዓላማ ያነገበ ነው፡፡

‹‹አሁን ባለው አገልግሎት ብዙዎች ቅሬታ ያሰማሉ፤ ለምን ለውጥ አልመጣም የሚሉ ጥያቄዎችም ይሰነዘራሉ፤›› የሚሉት አቶ ተከተል፣ የቢዝነስ ዕቅዱ ሲተገበር ለውጥ እንደሚኖር ያምናሉ፡፡ ፓርኩን ለማስተዋወቅ የተዘጋጁ ብሮሸሮች ጥቅም ላይ ሲውሉ እንዲሁም ከመሠረተ ልማት ዝርጋታው በኋላ ለውጥ እንደሚኖርም ያክላሉ፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...