Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮምባይነርና የትራክተር ማሠልጠኛ ተቋም ተቋቋመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ተስፋዬ ተክለ ሃይማኖት የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ሲሠሩበት ከቆዩት ሙያ ጎን ለጎን ወደ ንግድ ሥራ ለመግባት ያስቻላቸው አንድ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር በኩል ክላስ የተባለ የጀርመን ኮምባይነር አምራች ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ዕድል ያገኛሉ፡፡ ወደ ቢዝነስ ሥራ ለመግባትም ካሌብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባለውን ኩባንያ በ1986 ዓ.ም. አቋቋሙ፡፡ ይህም ኩባንያቸው በኢትዮጵያ የክላስ ኮምባይነር ወኪል በመሆን ሥራ ጀመረ፡፡ መጀመሪያ ያስመጡዋቸውን ኮምባይነሮች በኢትዮጵያ በስንዴ አምራችነት በሚታወቁት አርሲና ባሌ አካባቢ ሸጡ፡፡ ሦስት ኮምባይነሮችን በመሸጥ የጀመሩት ሥራ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺሕ በላይ የክላስ ኮምባይነሮች በኢትዮጵያ ማሳዎች ላይ እንዲሰማሩ አስችሏቸዋል፡፡ እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ በአርሲና ባሌ አካባቢ የመካናይዜሽን እርሻ እንዲስፋፋ ኩባንያቸው ያደረገው አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአካባቢው በኮምባይነር ማረስ በመለመዱም ያልታረሱ መሬቶች እንዲታረሱ፣ የምርት ውጤት እንዲጨምርም ማስቻሉን ይናገራሉ፡፡ ከአካባቢው አርሶ አደሮችና ዩኒየኖች ጋር የጠበቀ ግንኙነትም ፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴያቸው ከግብርናና ከግብርና መሣሪያዎች ጋር የተያያዙ ሥራዎቻቸውንም እዲያሳድጉ ሰፊ በር ከፍቶላቸዋል፡፡

“እኔ ሀብትና ንብረት ያፈራሁት በአርሲና ባሌ አርሶ አደሮች ነው፡፡  ምንም ሳንቲም ሳይኖረኝ ሀብትና ንብረት ያገኘሁበት አካባቢ በመሆኑ፣ አንድ ማስታወሻ ማኖር አለብኝ ብዬ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን መኖር ያለበት ያልኩትን ተቋም በሻሸመኔ ከተማ አቋቁሜያለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ተቋም ደግሞ የኮምባይነርና የትራክተር አሽከርካሪዎች ማሠልጠኛ ተቋም ነው፡፡ ካሌብ ሰርቪስ ፋርመርስ ሃውስ የሚል ሥያሜ አለው፡፡ የአርሲና የባሌ ማዕከል ናት በተባለችው ሻሸመኔ ከተማ የተቋቋመውን ማሠልጠኛ ተቋም የአዲሱ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በክብር እንግድነት በተገኙበት ባለፈው ሳምንት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡

እስካሁን ባለው የአገሪቱ የአሽከርካሪዎች ፈቃድ አሰጣጥ የኮምባይነርና የትራክተር አሽከርካሪዎችን በተለየ የሚያሠለጥንና ለዚህም ብቃት ማረጋገጫ እየተሰጠ እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፣ ማሠልጠኛ ተቋሙ ይህንን ክፍተት ይደፍናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ እስከዛሬ ትራክተሮችንና ኮምባይነሮችን እያንቀሳቀሱ ያሉት በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ የሠሩ ሾፌሮች መሆናቸውም፣ መካይናዜሽን ግብርናው ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደነበረውም ያምናሉ፡፡

ኮምባይነሮችና ትራክተሮች ከሌሎች ተሽከርካሪዎች በተለየ የሚታዩ በመሆናቸው አሽከርካሪዎቻቸውም የግድ ለነዚሁ ተሽከርካሪዎች ተብሎ በተዘጋጀ የሥልጠና ማኑዋል መሠልጠን ይገባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በግል ዘርፍ የመጀመሪያው መሆኑ የተነገረለት ይህ ማሠልጠኛ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ጠይቋል፡፡

ለመካናይዜሽን እርሻ መሠረት የሆኑትን ኮምባይነሮችና ትራክተሮች ለማንቀሳቀስ ልምድ ያላቸው የሚባሉ ሰዎች ጥቂትና ዕድሜያቸው የገፋ በመሆኑ፣ በዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ የባለሙያዎች እጦት እርሻን በወቅቱ ለማረስ ችግር የሚፈጠርበት አጋጣሚዎች እንደነበሩም ተነግሯል፡፡ ከ20 ዓመት በፊት በተለያዩ መካናይዜሽን እርሻ ላይ ይሠሩ የነበሩ ሰዎችን ማግኘትም የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱም፣ ተቋሙ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመቅረፍም ትልቅ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡ የግብርናው ዘርፍ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት የሚያሻ ቢሆንም፣ የኮምባይነርና የትራክተር አሽከርካሪዎች የሚሠለጥኑበት አሠራር ስላልነበር በውድ ዋጋ የሚገቡት ተሽከርካሪዎች ያለ ዕድሜያቸው ከሥራ ውጭ ይሆኑ እንደነበርም አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የአንድ ኮምባይነር ዋጋ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ነገር ግን በብቁ ባለሙያ የማይሽከረከር በመሆኑ፣ የአንድ ኮምባይነር ዕድሜ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት እየሆነ መምጣቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያመላክታልም ተብሏል፡፡

ኮምባይነሮቹ በብቁ ባለሙያ ቢሽከረከሩ ኖሮ ግን ከ15 እስከ 20 ዓመት ማገልገል ይችሉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የኮምባይነርና የትራክተር አሽከርካሪዎችን ማሠልጠኑ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ፣ ከዕውቀት ማነስ ለሚበላሹ የተሽከርካሪዎቹ አካላት የሚወጣው ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ ለመለዋወጫዎቹ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መቀነሱ ነው፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ሥልጠናው ኮምባይነርና ትራክተር አሽከርካሪዎችን በማፍራት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ከሌሎች አሽከርካሪዎች በተለየ እያንዳንዱ ሠልጣኝ ከአሽከርካሪነቱ ባሻገር በእርሻ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ትምህርቶችንም እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ ስለእያንዳንዱ የእርሻ መሣሪያዎች አጠቃቀምና ብልሽት ቢያጋጥም እንኳን የመጠገን ክህሎት እንዲኖራቸው ተጨማሪ ሥልጠናዎች እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ስለዚህ ማዕከል ግንባታ መረጃዎች እንደነበራቸው የገለጹት አቶ ወንድይራድ፣ ለግብርናው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ በተለይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ምሳሌ ሊሆን የሚችል መሆኑን በማመን ጭምር በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡   

“የአገሪቱ ግብርና በአነስተኛ አርሶ አደሮች ላይ የተመሠረተ ነው፤” ያሉት አቶ ወንድይራድ፣ እንዚህ አርሶ አደሮች ደግሞ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅማቸው አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሁልጊዜ አዲስ ነገር ለመሞከር ተጠራጠሪ የሆነ አስተሳሰብ አለ፡፡ በቴክኖሎጂ ድጋፍ አዲስ አሠራሮችን በማምጣት ተጠቃሚ ለማድረግ ቢቻልም እንኳን፣ ይህንን ለመቀየር እየተሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ሽግግር ስለመጀመሩ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሽግግር አበረታች ቢሆንም በጣም በርካታ ውስንነቶች አሉ ያሉት አቶ ወንድይራድ፣ አሁንም ሊደርስበት ከሚችለው እምቅ አቅም አኳያ ጅምር ላይ በመሆኑ ዘመናዊ እርሻ የግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተፈጥሮ ሀብት እየተመናመነ ከመሆኑ ባሻገር የእንስሳት ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ አጠቃላይ የእርሻ ሥራም ዘመናዊ የአሠራር ሒደትን መከተል የግድ የሚልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግን ዘመናዊ አሠራርን ለማስረጽ የሚያስችሉ ዕቅዶች ተነድፈዋል፡፡ ይህንንም ለማሳካት የፋይናንስ አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂ መረጣና የመሳሰሉትን አስፈላጊ ግብዓቶች በማቅረብ ለመካናይዜሽን አመቺ ሁኔታ በመቀመጡ፣ ይህንን ለማሳካት የዚህ ሥልጠና ማዕከል ሚና ትልቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ከታቀደው አንፃር ተጨማሪ ተመሳሳይ ማሠልጠኛ ተቋማት እንዲከፈቱም ጥሪ አድርገዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ማበረታቻ ይሰጣልም ብለዋል፡፡ ማሠልጠኛው በመጀመሪያው ዓመት 200 ሠልጣኞችን ይቀበላል ተብሏል፡፡

አቶ ተስፋዬ ከዚህ ማሠልጠኛ ባሻገር ሌላም ነገር እያሰቡ ነው፡፡ ከማሠልጠኛ ተቋሙ ጎን “ሻሸመኔ” ትራክተር የሚል ስያሜ ያለው ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደ ትራክተር የመገጣጠሙ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ግን በቀጣዩ ዓመት የአነስተኛ የእርሻ መሣሪያዎች ማምረቻ ሥራ የሚያስጀምሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመስመር መዝሪያ፣ ማረሻና የመሳሰሉትን አነስተኛ የእርሻ መሣሪያዎችም ከአንድ የጣሊያን ባለሙያ ጋር ሽርክና ባቋቋሙት ኩባንያ ምርት የሚጀምሩ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

ወደ ምርት ይገባሉ የተባሉትንና አሁን በመክር ደረጃ ያወጡዋቸውን አነስተኛ የእርሻ መሣሪያዎች ሞዴሎችንም በማዕከሉ ምርቃት ቀን ለዕይታ ቀርበው በጎብኝዎች ታይተዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የክላስ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች