Saturday, September 30, 2023

የጠቅላይ ሚኒስትሩና የተቃዋሚዎች የሁለት ቀናት ውሎ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቅርቡ አዲስ ካቢኔ ያዋቀረው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ አደርግበታለሁ ያለውን የሁለተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ላይ ነው፡፡ ዕቅዱን ለማዳበር ይረዱኛል ያላቸውን ውይይቶች በማካሄድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በመገኘት ገለጻ በመስጠትና አስተያየቶችን በመሰብሰብ መጠመዳቸውን ከተለያዩ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያማከለ የውይይት መድረክ ከፍቶ በዕቅዱ ላይ ለመወያየትና ግብዓት ለመሰብሰብ መዘጋጀቱን የቀድሞው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ሰኔ ይፋ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ከዜጎች፣ ከተለያዩ ማኅበራት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች ጋር ውይይቶች ተካሂዷል፡፡

በዕቅዱ ዙርያ እንዲወያዩና ግብዓታቸውን እንዲያበረክቱ ከተካተቱት መካከል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበረ፡፡ በዚህም መሠረት ከ22 ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮችና አባላት ባለፈው ሳምንት መስከረም 28 እና 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

እያንዳንዱ በውይይቱ ላይ የሚሳተፈው ፓርቲ 20 አባላትን ለውይይት መላክ እንደሚችል በደረሳቸው ጥሪ መሠረት፣ ከየፓርቲው የተውጣጡ በርከት ያሉ ታዳሚዎች ውይይቱ ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት የቆየው የውይይት መድረክ ላይ የነበረው የውይይት ነጥብ የአገሪቱን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ነበር፡፡ በመጀመርያው ዕለት ውይይት በመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ፣ በቀጣዩ ቀን ደግሞ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ የተለያዩ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ጥያቄዎችም ተነስተው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አማካይነት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በመጀመርያው ቀን ውሎው በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም አማካይነት የመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ማብራርያ የተሰጠ ሲሆን፣ በዚህ ማብራርያ መሠረትም የዕቅዱን አጠቃላይ መነሻዎች፣ ያጋጠሙ ውጤቶችና ተግዳሮቶች ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹የመጀመርያው አምስት ዓመት የዕቅዱ መሠረታዊ ዓላማዎች ኢኮኖሚውን በየዓመቱ ቢያንስ በአማካይ በ11 በመቶ በማሳደግ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ሽፋንን በመጀመርያ ጥራትን በማረጋገጥ ላይ የተመሠረተ ማኅበራዊ ልማት በማካሄድ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን ማሳካት፣ የተረጋጋ፣ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግሥትን በመፍጠርና በማጠናከር በቀጣይ የአገር ግንባታ ሥራ ምቹ መደላድል በመፍጠርና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ በማስፈን የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ…›› የሚሉ እንደበሩ አስታውሰዋል፡፡

በዕቅዱ አጠቃላይ አፈጻጸም ረገድም፣ ‹‹መልካም ተሞክሮዎች መገኘታቸው ለቀጣይ ዕቅዶች ደግሞ መደላድል ሆነዋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ ‹‹የዓለም የምግብና የነዳጅ ዋጋ በመጀመርያዎቹ ሁለት የዕቅዱ የትግበራ ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት ያሳየበት በመሆኑና አጠቃላይ የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገትም ዕቅዱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ከነበሩ ሁለት ዓመታት ብዙ መሻሻል ሳያሳይ የቆየ በመሆኑ፣ በአገር ውስጥ ዋጋ ንረትና በውጭ ምርት ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበር፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ የዕቅዱ አጠቃላይ መነሻዎች አማካይነት በፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡት ጥያቄዎች ደግሞ አንዳንዶቹ ከዕቅዱ ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው፣ የዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ በደሎችንና ከመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚመነጩ ብልሹ አሠራር ላይ ያተኮሩ ነበር፡፡

በዕለቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተሰጡት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ የዕቅዱን አጠቃላይ ሒደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም ስኬቶችን በማስረዳት የመጀመርያው ቀን ውይይት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ተጠናቀቀ፡፡

በውይይቱ ሁለተኛ ቀን ውሎ እንዲሁ አቶ ጌታቸው የሁለተኛውን የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችና ዝርዝር የዕቅዱ መርሐ ግብሮች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የያዛቸውን ነጥቦች አብራርተዋል፡፡ እነዚህም የዕቅዱ መነሻዎች፣ መለያዎች፣ ዓላማዎችና መሠረታዋ አቅጣጫዎች፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅድ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች ልማት ዕቅድ፣ የባለብዙ ዘርፎች የልማት ዕቅድ፣ በዕቅዱ አፈጻጸም ሒደት የሚጠበቁ ዕድሎችና ሥጋቶች፣ እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ሥርዓት የተባሉት በመጥቀስና በነጥቦቻቸው ላይ ዝርዝር ማብራሪያ በመስጠት መድረኩን ለውይይት ክፍት አደረጉ፡፡

ከዕቅዱ አጠቃላይ ምሰሶዎችና መነሻ ነጥቦችን መሠረት በማድረግ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ ከተወሰኑት በስተቀር የፖሊስና የዕቅድ ድክመትና ጥንካሬን በመነጠል በዕቅዱ እንዲካተቱ ወይም እንዲቀነሱ የሚፈልጓቸውን ነጥቦች ከማጉላት ይልቅ፣ በተለመዱት የቢሮክራሲና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ላይ በማተኮር አጠቃላይ አገራዊ ዕቅድ ነድፈው አገርን ሊመራ የሚችል አቅጣጫቸውን ማሳየት ተስኖአቸዋል፡፡

በሁለተኛው ዕቅድ ትግበራ ላይ መጨመር ያለባቸውንና መስተካከል ወይም መቀነስ ይኖርባቸዋል የሚባሉ ነጥቦችን ነቅሶ ለማውጣት ይረዳቸው ዘንድ ፓርቲዎቹ 81 ገጽ የዕቅዱ ጭማቂ ሐሳብ ተልኮላቸው የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ጠያቂዎች ግን ከዕቅዱ ሰበዞችን እየመዘዙ እንዲህ ይሁኑ አልያም እንዲያ ከማለት ይልቅ ስለታሠሩ አባሎቻቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ስለሚያጋጥማቸው ችግር፣ እንዲሁም ስለብልሹ አሠራር ትኩረት በመስጠት አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫቸውን ማሳየት አልቻሉም፡፡

ምንም እንኳ የተነሱት ነጥቦች በአጠቃላይ በሚያሰኝ ሁኔታ ዕቅዱን ከግምት ያላስገባ ነው ማለት ባይቻልም፣ በመድረኩ ከዚህ የተሻለ ነገር ይጠበቅ እንደነበር በሥፍራው የነበሩ ግለሰቦችም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳን ለውይይቱ ግብዓት መሆን የሚችሉ ነጥቦች በብዛትና አማራጭ ሐሳቦች በበቂ ሁኔታ ተንፀባርቀዋል ማለት ባይቻልም፣ የተነሱት ነጥቦች ግን መጥፎ የሚባሉ አይደሉም፤›› በማለት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የስብሰባው ተሳታፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ እሳቸው ግንዛቤ፣ ‹‹ከዕቅዱ ውይይት ውጪ ሐሳቦች ወደተለያየ አቅጣጫ መሄዳቸው የሚመነጨው ደግሞ ተደጋጋሚ መድረክ ካለማግኘት ሊሆን ይችላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሆኑ አባላት በተለያዩ ጊዜያት በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በቢሮክራሲ መንዛዛት ላይ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲያገኙ እነዚህን አስተያየቶች በማስቀደም ለመተንፈስ የሞከሩ ይመስለኛል፡፡ ወደፊት እንዲህ ዓይነት ውይይት የሚካሄድ ከሆነ ችግሮቹ የሚቀረፉ ይሆናል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሁለት ቀናት ውሎ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥልጣን ላይ ከወጣ ወዲህ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ ደረጃ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአገራዊ የልማት ዕቅድ ላይ ለመወያየት ሲቀመጡ ይህ የመጀመርያው ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተሞከሩ የውይይትና የስብሰባ ተሞክሮዎች በስተቀር፣ ሁለት ቀናትን የፈጀ ያውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት እንዲህ ዓይነት ስብሰባ መደረጉ መልካም መሆኑን የጠቀሱት አብዛኞቹ ታዳሚዎች፣ እንዲህ ዓይነት ውይይት ሊዘወተር የሚገባው እንደሆነ ከማሳሰብ ባለፈ ተማፅኖም አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዲህ ዓይነት መድረኮች ቀጣይ እንደሚሆኑ ቃል ገብተውላቸዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት መድረኮች ለጋራ ተጠቃሚነት ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ እኔ እንኳን ባልገኝ በሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የውይይት መድረኮቹ ይቀጥላሉ፤›› በማለት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

በመጀመርያው ቀን የውይይት መድረክ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሁለተኛው ቀን በተለየ ከዕቅዱ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን፣ ከጥያቄዎች መካከል የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጀት (አይኤምኤፍ) የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአገሪቱን ዕድገት በተመለከተ የተለያየ አኅዛዊ መረጃ ይፋ ያደርጋሉ የትኛውን እንመን? በዕቅድ ዘመኑ ድህነትን ለመቀነስ የተደረገው ጥረት አነስተኛ ነው፡፡ የሥራ አጥ ዜጎች ቁጥር መብዛቱ ሥራ እንዲያገኙ ምን ተሠርቷል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹የፓርቲዎቹ ተወካዮች በእነዚህ ነጥቦች ላይ ትኩረት ሰጥተው አስተያየት የሰጡትና ጥያቄዎችን ያቀረቡት፣ ዕቅዱን ስለሚያውቁትና አፈጻጸሙ ተገምግሞ ውጤቱ ምን እንደሆነ የሚገልጽ መረጃ ስላላቸው ሊሆን ይችላል፤›› በማለት ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የውይይቱ ታዳሚ አስረድተዋል፡፡

‹‹በሁለተኛው ዕቅድ ዙሪያ ግን ገና ጅማሮ ላይ ያለ ከመሆኑና የተላከውን 81 ገጽ ሰነድ በአጭር ጊዜ አንብቦ ዝርዝር ነጥቦችን ከማውጣት አንፃር ጉድለት ያለ ይመስላል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛው ዕቅድ ላይ ገለጻ ከተደረገ በኋላ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጣቸው 30 የፖለቲካ አመራሮችና አባላት ሲሆኑ፣ በአብዛኛው በሚባል ሁኔታ ይነሱ የነበሩት ጥያቄዎች የአፈጻጸም ጉዳዮችን የተመለከቱ ነበሩ፡፡

ለአብነት ያህልም በመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፕሬዚዳንት አቶ መሳፍንት ሽፈራው የተነሱትን ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ አቶ መሳፍንት የመጀመርያ ጥያቄያቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጤና ሁኔታ መጠየቅ የተጀመረ ሲሆን፣ ‹‹የእርስዎን ጤንነት ለመጠየቅ የግድ ጋዜጠኛ መሆን አይጠብቅኝም፤›› በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤንነት ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ‹‹ሁሉም ሰላም ነው፤›› በማለት ታዳሚዎችን ፈገግ ያሰኘ ምላሽ ወዲያውኑ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአቶ መሳፍንት ጥያቄ በክረምቱ ተገንብተው በመስከረም ስለፈራረሱ መንገዶች ተጠያቂ የሆኑት ለምን እንደማይጠየቁ፣ በቀድሞው የዕቅድ ዘመን ጥፋት የሠሩ ሰዎች ሳይጠየቁ እንዴት ሁለተኛው ይጀመራል? ካሉ በኋላ ስለ አሳሳቢው የትራንስፖርት ዘርፍና አደጋ ያነሱት ጥያቄ ተጠቃሽ ነው፡፡

በተለይ የትራንስፖርት ዘርፍ አደጋን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ለየት የለ ነበር፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ውስጥ መኪና ሰው እየፈጀ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎች እየወደሙ ነው፡፡ ለዚህ ዋናውና ቁልፉ ጉዳይ ሲቪል ሰርቫንቱና የፖለቲካ ሹመኛውን መለየት ስላልተቻለ ነው፡፡ በድርጅት ስለሚመደቡ ነው፤›› በማለት ችግሩ ሙያተኛ በፖለቲከኛ መመራቱ ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡

በተጨማሪም ሙሰኞች ለምን ቶሎ ቶሎ አይቀጡም? በሙስናና በመልካም አስተዳደር ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰቦች ለምንድነው ጠበቅ ያለ ዕርምጃ የማይወሰድባቸውና የመሳሰሉት ከውይይት አጀንዳው ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህንን መሰል አስተዳደራዊ ጉዳዮች መድረኩን ተቆጣጥረውት ነበር፡፡

ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንድ አስተያየት ብሰጥ ደስ ይለኛል፤›› በማለት አስተያየት ይሰጡ የነበሩ ታዳሚዎችን አቋርጠው ገለጻ የሰጡት፡፡ ‹‹ከዕቅዱ ውይይት ይልቅ ወደ አፈጻጸሙ እየገባን ነው፡፡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ካሉ አብረን እናጣራለን፡፡ ማን ጥፋተኛ እንደሆነ እንለይ፡፡ ስለዚህ አሁን ምላሽ ማግኘት በማይቻልበት ጉዳይ ላይ ጊዜ ባይጠፋ ጥሩ ይሆናል፤›› ሲሉ የስብሰባውን አቅጣጫ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ለመመለስ ሞክረዋል፡፡

ወደ ዕቅዱ እናተኩር የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ ተከትሎም ቢሆን፣ አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች ከዕቅዱ ይልቅ የግልና የፓርቲ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ስለታሰሩ አባሎቻቸው፣ በበታች የፖለቲካ ሹሞችና ካድሬዎች ስለሚደርስባቸው በደልና ሌሎች ጉዳዮችን በመዘርዘር ተጠምደው ነበር፡፡

ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ የተሳኩ ናቸው ባይባልም፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን (ኢዴፓ) ወክለው የተገኙ ተሳታፊዎች፣ በአንፃራዊነት የዕቅዱን ዝርዝር ሒደቶች የሚሞግቱ እንዲሁም ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡

‹‹80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍል አርሶ አደር በሆነበት ሁኔታ፣ የዚህ ኅብረተሰብ ክፍል አካል ወደ ኢንዱስትሪውና ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ካልመጣና በግብርና ዘርፍ ላይ ያለው ኅብረተሰብ እየቀነሰ ካልመጣ፣ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አሁንም በታለመለት ጊዜ ሊሳካ ይችላል የሚለው ነገር በእኛ በኩል በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የምናምነው፤›› ሲሉ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ኢዴፓ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ምን በማድረግ ማፋጠን እንደሚቻልና እንደሚገባ ለተሳታፊውም ለሕዝቡም ቢገልጽ ጥሩ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍ እኔ የምከተለው ይኼ ይኼ ነው የሚል ተጨባጭ ነገር ቢኖር ለእኔም ምላሽ ለመስጠት መልካም ይሆናል፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልሰው አቶ ኤርሚያስን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስም፣ ‹‹ኢዴፓ ከኢሕአዴግ የተለየ የመሬት ፖሊሲ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ግብርናው በሚቀንስበት ሁኔታና ሰፋፊ የሆኑ እርሻዎችን በመፍጠር ለማኑፋክቸሪንግና ለኢንዱስትሪው ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶችን በማምረትና ካፒታል በመፍጠር ወደ ዘርፉ የሚገባበት ሒደት አለ፡፡ መከራከር የምንችልባቸው መድረኮች ከተዘጋጁ በቀጣይ ዝርዝሩን በማቅረብ በደንብ ልንከራከር እንደምንችል ለማስገንዘብ እወዳለሁ፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ቀናት መድረክ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ዕቅዱን የተመለከቱ ጠንካራና ሞጋች አስተያየቶችን ከመሰንዘር ይልቅ፣ ፓርቲዎች በአብዛኛው በአስተዳደራዊና በአፈጻጸም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ውይይቱ ተጠናቋል፡፡ ለወደፊቱ ፓርቲዎች እንዲህ ዓይነት መድረኮች ሲኖሩ ያላቸውን የፖሊሲ አማራጭ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የፓርላማውን ሙሉ ወንበሮች በተቆጣጠሩበት የአሠራር ሒደት ላይ እንዲህ በአጋጣሚ የሚገኙ መድረኮችን በቅጡ በመጠቀም፣ ሕዝቡን ስለአማራጭ ፖሊሲው ግንዛቤ ማስጨበጥ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ትልቁ ቁም ነገርና የቤት ሥራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -