Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሪያው አልባሳት አምራች ለሠራተኞች ማደሪያ ቤት ለመሥራት ማቀዱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደቡብ ኮሪያው ሺንትስ ኢትዮጵያ አልባሳት አምራች ኩባንያ፣ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በከፈተው ፋብሪካ ተቀጥረው ለሚሠሩና ወደፊት ለሚቀጠሩ ዘጠኝ ሺሕ ያህል ሠራተኞች የማደሪያ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት 1,500 ሠራተኞችን በመቅጠር ለአሜሪካና ለአውሮፓ የፋሽን ድርጅቶች ምርቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

የፋብሪካው ፕሬዚዳንት ቻ ጆንግ ትናንት በተካሄደው የፋብሪካው አንደኛ ዓመት የሥራ ክንውን ላይ እንደገለጹት፣ ኩባንያው ለሠራተኞች ማደሪያ ለመገንባት ዕቅዱን ለመንግሥት በማስገባት ፈቃድ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙት ጥራት ያላቸው ከፍተኛ ድርጅቶች ውስጥ መንግሥት በቀዳሚነት የሚያስቀምጠው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሺንትስ ኢትዮጵያ ለመገንባት ያሰበው የሠራተኞች ማደሪያ ከክልል ለሚመጡ ሠራተኞች የሚውል ሲሆን፣ ይህም ከአዲስ አበባ የሚቀጥራቸው ሠራተኞች በተደጋጋሚ እየለቀቁበት እጥረት ስላጋጠመው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ሠራተኞች ግን የሚከፈላቸው ደመወዝ እጅግ ዝቅተኛ ስለሆነ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ መሆኑን በመግለጽ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል፡፡ አቶ ታደሰ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት ማብራሪያ ምንም እንኳ ኩባንያው የሚከፍለው ደመወዝና የሚሰጣቸው የሠራተኞች አገልግሎቶችና የሥራ ቦታ ደኅንነት ሥርዓቶች ዓለም አቀፍ ደረጃን መሠረት አድርጎ ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ እየተባባሰ በመጣው በቤት ኪራይና በኑሮ ውድነት ምክንያት የሠራተኞች ደመወዝ ምንም ሊፈይድ አልቻለም ብለዋል፡፡ መንግሥት በዚህ መስክ የሚታየውን ችግር ካላስተካከለ በቀር የደመወዝ መጠን የተሻለ ቢሆን እንኳ፣ ሠራተኛው ከዕለት ኑሮው ተርፎት ለሌሎች ፍላጎቶቹ የሚያውለው ጥሪት ለመቋጠር እንደሚቸገር አሳስበዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የገበያ ፕሮሞሽንና ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ሰሎሞን እንደሚሉት፣ ሺንትስ ለሠራተኞች ለመገንባት ያቀደው ማደሪያ ቤት የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በመኖሪያ መንደሮች ሥር በተካተተው ፕላን መሠረት የሚስተናገድ መሆኑንና ለግንባታ የሚሆነው ቦታ ተከልሎ በወጥ ማስተር ፕላን መሠረት ይስተናገዳል፡፡ እስካሁን በቦሌ ለሚ ቦታ ከወሰዱ 12 ኩባንያዎች ውስጥ የኮሪያው ሺንትስ፣ የታይዋኑ ጆርጅ ሹ ጫማ አምራች ኩባንያዎችን ጨምሮ ስድስት ኩባንያዎች ማምረት መጀመራቸውን አቶ ሽፈራው አስታውቀዋል፡፡

ሺንትስ በኮሪያውያን ቤተሰብ የሚመራ ኩባንያ ሲሆን፣ መንግሥት በቦሌ ለሚ በገነባው ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 35,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ አምስት ማምረቻ ቤቶችን በመግዛት ሥራ ከጀመረ ወዲህ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አልባሳትን ወደ ጣልያን ልኳል፡፡ በአሁኑ ወቅት 30 የማምረቻ መስመሮችን በመዘርጋት እየሠራ እ.ኤ.አ. በ2015 መጨረሻ የሚቀጥራቸው ሠራተኞች ቁጥር 2,500 እንደሚደርስ አስታውቆ፣ ይህ ቁጥር ከአራት ዓመት በኋላ 12 ሺሕ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ ሠራተኞች መካከል ዘጠኝ ሺሕ የሚደርሱት ማደሪያ ቤት ይሠራላቸዋል፡፡

ኩባንያው ለስዊድኑ ኤችኤንዲኤም፣ ለጀርመኑ ሾፌል ኩባንያ፣ ለጣሊያን ድርጅቶች፣ እንዲሁም በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ምርቱን ለሚገዙ ትልልቅ ብራንድ ኩባንያዎች በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ አሜሪካ በሚገኘው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱም የአሜሪካ ኩባንያዎችን ያዳርሳል ተብሏል፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ውስጥ 15 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አልበሳትን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ያስታወቁት የኩባንያው ባለንብረቶች፣ ከአራት ዓመት በኋላ በዓመት 1.9 ሚሊዮን ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን አልባሳት ለውጭ ደንበኞቹ ያቀርባል ብለዋል፡፡

በ47 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ሺንትስ ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ወቅት ካሉት ደንበኞች መካከል ሼርፓ፣ ኤሮስቲሽ፣ ከሊም፣ አይከን፣ ፖላሪስ፣ ሻወር ስፓስ የተባሉ የሞተር ብስክሌትና የብስክሌት እንዲሁም የበረዶ ስፖርት ኩባንያዎች በትዕዛዝ ልብስ የሚያስመርቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከስፔን ትራንጎ ወርልድና ግሪፍዋን፣ ከጀርመን ቢኤምደብሊው፣ ኬቲኤም፣ ማሪን ፑልና ሾፌል ሲጠቀሱ ከስዊዘርላንድ ኦድሎ፣ ከጣሊያን ዴኒስ የተባሉት ኩባንያዎች ከሺንትስ አልባሳት እየገዙ ያሉ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች