Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ወጣቶችን ማን አለሁላችሁ ይበላቸው?

  በዚህ ዘመን ወጣትነትን በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ነው የምንመለከተው፡፡ በአንድ በኩል ወጣቱ በዘመናዊ ትምህርት እየተኮተኮተ፣ በሞራልና በሥነ ምግባር እሴቶች እየተገራ ለቁም ነገር የሚበቃባቸው መልካም አጋጣሚዎች ወይም ዕድሎች ይታዩናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወጣቱን ትውልድ ተስፋና ራዕይ የሚያጨናግፉ አጓጉል ድርጊቶችን እንታዘባለን፡፡ መልካሙን እያበረታታን አደገኛውን ጉዳይ አብጠርጥረን ልንመለከት ግድ ይለናል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚስተዋሉ አጓጉል ድርጊቶች መላ ካልተፈለገላቸው የወጣቶቻችንን ተስፋ ይቀጫሉ፡፡ የአገሪቱንም ተስፋ ያደበዝዛሉ፡፡

  አሁን ባለው ግምት መሠረት ከአገሪቱ 96 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ በታዳጊነትና በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የአገሪቱ ተስፋ በመሆኑ፣ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ያሻዋል፡፡ ወጣቶች በትምህርትና በሥነ ምግባር ታንፀው ሲያድጉ የአገራቸው ተስፋ ናቸው፡፡ የነገው አገር ተረካቢ ትውልድ የሚባሉትም ለዚህ ነው፡፡ ይህንን ተስፋ የሚያደበዝዙ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ብዙዎችን ወጣቶች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየነዱ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ ኅብረተሰቡን ይዞ እስከ መንግሥት ድረስ ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቁ ጊዜ የማይሰጣቸው ችግሮች ናቸው፡፡

  ዋና ዋና ከሚባሉት ችግሮች መካከል ተጠቃሾቹ መጠጥ፣ ጫት፣ ሺሻና አደንዛዥ ዕፆች ናቸው፡፡ እነዚህ የወጣቶችን ተስፋ የሚያጨልሙ ነገሮች በመኖሪያ ሥፍራዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በሥራ አካባቢዎች በብዛት ይታያሉ፡፡ የግል ጥቅም ብቻ በተፀናወታቸው ራስ ወዳዶችና ኃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች አማካይነት በወጣቶች ላይ ያነጣጠሩት እነዚህ አስከፊ ሕገወጥ ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ አድማሳቸውን አስፍተዋል፡፡ በተለይ የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ አውሬ የከበቡዋቸው እነዚህ የጥፋት ኃይሎች፣ በኅብረተሰቡና በመንግሥት ትብብር አደብ እንዲገዙ ካልተደረገ በስተቀር ከፊታችን ከፍተኛ አደጋ ተደቅኗል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

  በአገሪቱ ውስጥ እንደ አሸን የፈሉት የጫት ማስቃሚያና የሺሻ ማጨሻ ቤቶች፣ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ሹማምንትን ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር እንዴት አገር ይወራሉ? የትምህርት ተቋማትን ዙሪያ ጥምጥም ከበው ሲሠፍሩ የተቋማቱን አመራሮች ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር እንዴት ይበራከታሉ? ከ18 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች እንዳይቀምሷቸው ማስታወቂያ የሚያስነግሩ የመጠጥ ፋብሪካዎች፣ በእነሱ ስፖንሰርሺፕነት በሚዘጋጁ ፌስቲቫሎች ላይ ወጣቶችና ታዳጊዎች አልኮል ሲጋቱ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸው የት ነው ያለው? በየሥርቻው የቀን ፓርቲ እየደገሱ ወጣቶችን በአልኮል የሚመርዙ ጉዶች ለምን የዜግነት ኃላፊነት አይሰማቸውም? ለወጣቶች መዳሪያ በየቦታው የተኮለኮሉ ፔንሲዮኖችና የማሳጅ አገልግሎት ሰጪ ተብዬዎች ዓላማ ምንድነው? ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

  በዚህ ዘመን ኃላፊነት የሚሰማቸው የንግድ ተቋማት ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ፣ ከዚህ በተቃራኒ የተሠለፉት ግን የወጣቱን ትውልድ ተስፋ እያጨለሙት ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ እነዚህ ወገኖች የራሳቸው ልጆች የሌሉዋቸው ይመስል አገር እያጠፉ ነው፡፡ ከእነዚህ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ የመንግሥት ተሿሚዎችም የጥፋቱ ተባባሪ በመሆን ወጣቱን እየገደሉት ነው፡፡ እነዚህ ኃላፊነት የማይሰማቸው የጥፋት ኃይሎች በወጣቱ ተስፋና ራዕይ ላይ ሲቆምሩ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡና መንግሥት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ወጣቱ ትውልድ እየጠፋ አገር መገንባት የማይታሰብ ነው፡፡ ወጣቶቿን ገድላ የለማች አገር የለችም፡፡ ፈጣን የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡

  ዜጎች ለአገራቸው ከሚያበረክቱዋቸው አስተዋጽኦዎች መካከል አንዱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ በተለይ በአክሲዮንም ሆነ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተመሠረቱ ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸው ከበድ ያለ ነው፡፡ ከሚያገኙት ትርፍ ላይ ቀንሰው ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ ያለው አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ኃላፊነታቸውን ተወጡ ይባላል፡፡ በሚዲያ የገጽታ ግንባታ ለማካሄድ ሲሉ ብቻ የተረጂነት ስሜትን የሚያባብሱ እየበዙ ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር ዓላማውን እየሳተ ነው፡፡ ይልቁንም የተቸገሩትን እየረዱ ነገር ግን ለወጣቶች አብያተ መጻሕፍትን፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን፣ የክህሎትና የልቀት ማበልፀጊያዎችን፣ ለአዛውንቶች ማረፊያዎችን፣ የሕክምና ድጋፎችንና የመሳሰሉትን ማድረግ ያስመሰግናል፡፡ ለታይታ ያህል እዚህም እዚያም እየረገጡ ‘አለን’ ማለት ቀልድ ነው፡፡ በየሚዲያው የምናያቸውና የምንሰማቸው ድርጅቶች ቀልዱን ትተው የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች መቅረፍ ላይ ቢያተኩሩ ይመረጣል፡፡ በዓላትንና አጋጣሚዎችን እየጠበቁ የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ፋይዳ የለውም፡፡ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ሳይሆን እዩኝ እዩኝ ማለት ነው፡፡ ውጤቱም ተረጂነትን ማባባስ ነው፡፡

  ወጣቶችን ለአደጋ ከሚዳርጉ አላስፈላጊ ድርጊቶች ለመታደግ ከተፈለገ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በአዳራሾች ውስጥ የሚዘጋጁ የክህሎት ውድድሮችን መደገፍ ጠቃሚ ነው፡፡  በመደበኛ ትምህርቶች፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በኪነ ጥበብ፣  በስፖርትና በመሳሰሉት የተለያዩ ዘርፎች ቢሠራባቸው ዕምቅ ክህሎቶች ጎልተው ይወጣሉ፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የባላገሩ አይዶል ዝግጅት፣ በድምፅና በውዝዋዜ ለአገሪቱ ሙዚቃ የወደፊት ተስፋዎችን አሳይቷል፡፡ ይህንንና መሰል የክህሎት ማበልፀጊያዎችን በመደገፍ ወጣቶችን ለማብቃት ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ ለአልባሌና የፈለገውን ያህል ቢመዘኑ አገራዊ ፋይዳ ለሌላቸው ተግባራት የሚባክነው ገንዘብ ያሳዝናል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ከአገሪቱ የነገ ተስፋ ከበለጠ ባለቤቶቹ ራሳቸውን ይጠይቁ፡፡ በተለይ እኛስ ከማን እናንሳለን የሚሉ የንግድ ተቋማት የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራቸውንና ውሎዋቸውን ቢያጤኑት መልካም ነው፡፡ አሁን ግን አያያዛቸው አያምርም፡፡

  ኅብረተሰቡም መንግሥትም የወጣቱ ጉዳይ ከማንም በላይ ሊያንገበግባቸው ይገባል፡፡ ወጣቱን የማብቃት ሥራ የእነሱ ኃላፊነት ነው፡፡ ወጣቱ በዝንባሌ፣ በአስተሳሰቡ፣ በማኅበራዊና በባህላዊ ግንኙነት መስኮች በሚገባ ተቀርፆ ሊወጣ ይገባል፡፡ የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች ሲኖሩት ትምህርቱን በሚገባ ይከታተላል፡፡ ኃላፊነት ለመረከብ ዝግጁ ይሆናል፡፡ ወጣቱ ብቃትና ንቃት ሲኖረው በገዛ ራሱ ሕይወትም ሆነ በአገሪቱ መፃኢ ዕድሎች ላይ የመወሰን አቅሙ አስተማማኝ ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሳል አስተያየታቸውን የሚያሰፍሩ ጠንካራና ብቁ ወጣቶች እየታዩ ሲሆን፣ በተቃራኒው ከስድብና ከአሉባልታ የዘለለ ዕውቀት የሌላቸው ብዙ ናቸው፡፡ የእነዚህ ድክመት የሚመነጨው በትምህርት ባለመብሰል፣ በሥነ ምግባር ባለመኮትኮትና በተለያዩ ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ኅብረተሰቡና መንግሥት በጋራ ተቀምጠው በችግሮቹ ላይ መክረው ተገቢውን መፍትሔ ማቅረብ ያለባቸው፡፡ ወጣቱን ተላላኪ ከማድረግ ይልቅ የመሪነትና የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማው ያድርጉ፡፡

  ማኅበራዊ ኃላፊነት አለብን የሚሉ ወገኖችም የራሳቸውን ገጽታ ግንባታና የታይታ ሥራ አቁመው በቁርጠኝነት ከተነሱ ውጤት ይገኛል፡፡ ወጣቱን በተሻለ መንገድ ላይ ለማራመድ ሲፈለግ ዘለቄታዊ ጉዳዮች ይታሰብባቸው፡፡ ወጣቶች እየተማሩ አካባቢያቸውን እንዲመለከቱ ማገዝ ይገባል፡፡ ከሚኖሩበት አካባቢ ጀምሮ ተሳትፎአቸው እየጎለበተ አገር ለመረከብ የሚያስችላቸው ደረጃ እንዲደርሱ ሲፈለግ፣ መንግሥትም ሆነ ይመለከተናል የሚሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እገዛ በመርህ ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ወጣቶች እንደ ዝንባሌያቸው እንዲማሩና የበቁ እንዲሆኑ ድጋፍ የሚያደርጉ ኃይሎች አስተዋጽኦዋቸውን ማቀናጀት አለባቸው፡፡ ይህ የተቀናጀ አስተዋጽኦ በመርህ ሲመራና ዘለቄታዊ አስተማማኝነት ሲኖረው ለውጥ ይገኛል፡፡ ይህ ለውጥ ይገኝ ዘንድ ግን ወጣቶችን ማን አለሁላችሁ ይበላቸው ነው ዋናው ጥያቄ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...