Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበከተማ ዳርቻ ሲካሄድ የቆየው የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ወደ መሀል ከተማ ሊመለስ ነው

በከተማ ዳርቻ ሲካሄድ የቆየው የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ወደ መሀል ከተማ ሊመለስ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ዳርቻ ሲያካሂድ የቆየውን የቤቶች ግንባታ መርህ በመቀየር፣ በመሀል ከተማ በርካታ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱ ተሰማ፡፡

አስተዳደሩ ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ በመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች በድጋሚ በሚለሙ ቦታዎች ላይ ረዣዥም ከፍታ ያላቸውን ኮንዶሚኒየም ቤቶች የመገንባት ዕቅድ አውጥቷል፡፡

አስተዳደሩ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ ቢያንስ 300 ሔክታር በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ለማልማት ማቀዱን፣ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐረጎት ዓለሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ሐረጎት ጨምረው እንደገለጹት፣ በማስፋፊያ ቦታዎች የመሬት አቅርቦት እያነሰ በመምጣቱ በመካከለኛው የአዲስ አበባ ክፍል ግንባታውን ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹እንደ በፊቱ በማስፋፊያ ቦታዎች የመሬት አቅርቦት የለም፡፡ በአንፃሩ በመካከለኛው የከተማው ክፍል መልማት የሚችል ቦታ በብዛት መኖሩ ታይቷል፤›› ሲሉ አቶ ሐረጎት ቀጣዩን የአስተዳደሩ አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረት በመልሶ ማልማት ቦታዎች ያለውን መሬት በሚገባ በመጠቀም፣ ረዣዥም ከፍታ ያላቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ እንደሚካሄድ አቶ ሐረጎት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአምስት ዓመታት ውስጥ ለሚካሄደው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ 2,200 ሔክታር መሬት እንደሚዘጋጅ አስታውቋል፡፡

በዚህ መሬት ላይ የከተማው አስተዳደር 200 ሺሕ የ20/80 ፕሮግራም ቤቶችን፣ በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ደግሞ 62,322 ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡ በ10/90 ፕሮግራም ለተመዘገቡት ነዋሪዎች እስካሁን የተገነቡት መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ባይተላለፉም፣ በቂ በመሆናቸው በተዘጋጀው አዲስ ዕቅድ ውስጥ አልተካተቱም፡፡

አስተዳደሩ ለመልሶ ማልማት ፕሮግራምና ለተለያዩ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ወሰን ለማስከበር ለሚነሱ 23 ሺሕ ተነሽዎች 6.2 ቢሊዮን ብር ካሳ ለመክፈልና 404 ሔክታር መሬት ምትክ ቦታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ለ51 ሺሕ ተነሽዎች ምትክ ቤቶችን ለመስጠት መዘጋጀቱንም አስተዳደሩ በዕቅድ ሰነዱ አስታውቋል፡፡

በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይመራ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮግራም በጀመረበት ወቅት ግንባታው በመሀል ከተማ እንዲካሄድ ዕቅድ ነበረው፡፡

ዶ/ር አርከበ መሀል ከተማውን በማፈራረስ ይህንን ግንባታ የጀመሩ ቢሆንም፣ በወቅቱ በተነሳው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከተማውን እንዲያስተዳድር የተሰየመው በአቶ ብርሃነ ዴሬሳ የሚመራው የባለአደራ አስተዳደር ከመሀል ከተማ ነዋሪዎችን የማንሳት አቅም በማጣቱ፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታው ከከተማ ውጪ እንዲከናወን ተደርጓል፡፡

ቆይቶ ሥልጣን የተረከቡት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳም በአነስተኛ መጠን የመካከለኛውን ክፍል ለማልማት ከመሞከር ባሻገር፣ ሙሉ ትኩረታቸውን በማስፋፊያ ቦታዎች ላይ አድርገዋል፡፡ በማስፋፊያ ቦታዎች ከተገነቡት መካከል የካ አባዶ፣ ቦሌ አራብሳ፣ ቱሉ ዲምቱ፣ ገላን፣ ጀሞና ሚኪ ሊላንድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የከንቲባ ድሪባ ኩማ አስተዳደር ዘግይቶም ቢሆን መካከለኛውን የከተማውን ክፍል፣ በተለይ የመኖሪያ ቤቶችን በስፋት ለመገንባት አዲስ ዕቅድ መያዙ ተሰምቷል፡፡

አቶ ሐረጎት እንዳሉት ሰነዱ ባለመፅደቁ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም የታቀፉ አካባቢዎች መዘርዘር ባይቻልም፣ ግንባታው የሚካሄደው ግን እጅግ አሮጌና በተጎሳቆሉ መንደሮች ነው፡፡ እነዚህ ቦታዎች የሚገኙት በመሀል አዲስ አበባ የሚገኙ ነባር መንደሮች ውስጥ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...