– ጠቅላላ የሚያስፈልገው የዕርዳታ መጠን 12 ቢሊዮን ብር ደርሷል
– አራት ቢሊዮን ብር ከመንግሥት ካዝና ወጪ መደረጉ ተጠቁሟል
በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት ይፋ አደረገ፡፡ ለጋሾች አስፈላጊውን ዕርዳታ እያቀረቡ አለመሆኑን መንግሥት ሲያስታውቅ፣ በጠቅላላው አስከፊነቱ እየተባባሰ ለመጣው ድርቅ 12 ቢሊዮን ብር ወይም 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚያስፈልግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ይፋ አድርገዋል፡፡
ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ከለጋሽ አገሮች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ለጋሾች ጋር በተደረገ የሁለትዮሽ ስብሰባ ላይ የብሔራዊ አደጋ መካከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ምትኩ ካሳ እንዳስታወቁት፣ በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት በበልግና በመኸር (ክረምት) የዝናብ ሥርጭት በመዛባቱ 8.2 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
‹‹የበልግ ዝናብ መዛባት ከመኸር ዝናብ መስተጓጎል ጋር ተዳምረው የፈጠሩት ችግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በልግ በሚዛባበት ወቅት መኸር ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ለወትሮው በመኸር አምራች የሆኑ አካባቢዎች ለችግር ስለማይጋለጡ የተረጂዎች ቁጥር ዝቅ ያለ ነበር፡፡ አሁን ግን የሁለቱም መዛባት ችግሩን ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከጥር እስከ ሰኔ ወር በሚተገበረው ሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው የነበሩ 4.4 ሚሊዮን ሰዎችም በ8.2 ሚሊዮን አኃዝ ውስጥ ይገኛሉ፤›› ያሉት አቶ ምትኩ፣ ከጥር ወር በኋላ በመደበኛው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑት ሰዎች ከዕለት ደራሽ ተረጂዎች ሲለዩ፣ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚቀርብላቸው ሰዎች ቁጥር እንደሚቀንስ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው የበልግ ግምገማ ተካሂዶ ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው አኃዝ መሠረት የተረጂዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን እንደነበር መገለጹን ያስታወሱት አቶ ምትኩ፣ ይህ አኃዝ ይፋ ከተደረገ በኋላ መንግሥት በአብዛኛው ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን፣ በተወሰነ ደረጃ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ያልሆኑ ድርጅቶች ማለትም በካቶሊክ ሪሊፍ ሶሳይቲ ሥር የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ለድርቅ ጉዳተኞች ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡ የበልጉ ዝናብ በመዛባቱ የተከሰተው የምግብ እጥረት 4.5 ሚሊዮኖችን ጉዳት ላይ ጥሏል ቢባልም፣ የክረምቱ ዝናብም በኢልኒኖ ሳቢያ ዘግይቶ ከመግባት ባሻገር በመጠንና በሥርጭት ስለተዛባ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ከ4.5 ሚሊዮን ወደ 7.4 ሚሊዮን፣ ቀጥሎም ወደ 7.7 ሚሊዮን ሊደርስ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱ ታይቷል ያሉት አቶ ምትኩ፣ ይህ ቁጥር ከዚህ ቀደም በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉት 4.4 ሚሊዮን ሰዎች ያካተተ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
አቶ ምትኩ በሪፖርተር ተጠይቀው እንዳብራሩት፣ መንግሥት ከራሱ መጠባበቂያ ፈንድና ከክልሎች በተዋጣ በጀት አራት ቢሊዮን ብር ወይም 192 ሚሊዮን ዶላር ለዕርዳታ ማዋሉንና እንደሚቀጥልበትም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለአስቸኳይ ዕርዳታ እየዋለ ካለው ገንዘብ ውስጥ አብዛኛውን ከፌደራል መጠባባቂያ ፈንድ ቢያወጣም፣ ክልሎችም በራሳቸው ከያዟቸው የመጠባበቂያ ፈንድ በጀት ለድርቁ ሰለባዎች ማዋላቸው ተነግሯል፡፡
የኦሮሚያ ክልል 565 ሚሊዮን ብር በክልሉ ለተጎዱ ሰዎች ሲያውል፣ የአፋር ክልል በበኩሉ 100 ሚሊዮን ብር በመመደብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ተብሏል፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ተመሳሳይ ዕርምጃ በመውሰድ ተጎጂዎችን እየታደገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በከፍተኛ መጠን የድርቅ ተጎጂዎች ካሉባቸው ክልሎች መካከል አፋር ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ሶማሌ ክልልም በተጎጂነት ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙት ክልሎች ውስጥ ሲካተት የደቡብ፣ የአማራና የትግራይ ክልሎችም በድርቅ ምክንያት ተጎጂዎች የሚገኙባቸው ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ለተረጂዎች የተገዛውን 450 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደሚገዛ ይፋ አድርገዋል፡፡ በጠቅላላው ከ620 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ስንዴ ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱን አቶ ምትኩ አስታውቀዋል፡፡
ይህም ቢባል ግን ከዚህ ቀደም በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ጥሪ ያቀረበበት አስቸኳይ የዕርዳታ መጠን 450 ሚሊዮን ዶላር (ከ9.4 ቢሊዮን ብር በላይ) ሊያስፈልግ እንደሚችል የሚጠቁም እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ግን ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አለመገኘቱን መንግሥት አስታውቋል፡፡ አቶ ምትኩ በጽሕፈት ቤታቸው ካነጋገሯቸው የውጭ ዕርዳታ ለጋሾች መካከል የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት መሥሪያ ቤት (ዴፊድ) 45 ሚሊዮን ፓውንድ (ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ)፣ የስዊዝ ትብብር ተቋም ሰባት ሚሊዮን የስዊዝ ፍራንክ (152.74 ሚሊዮን ብር) ለመለገስ ቃል ከመግባታቸው ውጪ፣ ሌሎቹ ተቋማት ዕርዳታ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ከመግለጽ በቀር ቃል የገቡት የገንዘብ መጠን አልነበረም፡፡
መንግሥት ድርቅ ያስከተለው ከባድ አደጋ ከቁጥጥሩ ውጪ እንዳልሆነ ለለጋሽ አገሮች፣ ለተመድ ኤጀንሲዎች ተወካዮችና ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ያብራሩት አቶ ምትኩ፣ በአንፃሩ ከእነዚህ አካላት የተጠበቀውን ያህል ምላሽ አለመገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባቸው ምክንያቶች መካከል፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተከሰቱ ቀውሶች የኢትዮጵያን የድርቅና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ቸል እንዲባል ሰበብ መሆናቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
በዓለም የምግብ ፕሮግራም የቀጣናው አስተባባሪና በብሔራዊ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ጆን አይሊፍ የተመራው የለጋሾች ቡድን፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው አስከፊ የድርቅ አደጋ አስቸኳይ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ከስምምነት በመድረስ፣ በጥቅምት ወር ማብቂያና በኅዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ ተጠቃሎ ይፋ እንደሚወጣ የሚጠበቀውን ሪፖርት በመንተራስ፣ የጉዳተኞች መጠንና የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን በግልጽ እንደሚታወቅ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሆኖ በጠቅላላው ለኢትዮጵያ የድርቅ ሰላባዎች ያስፈልጋል ከተባለው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን 258 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከለጋሾች ቢገኝም ጥቅም ላይ በመዋሉ የምግብ፣ የተጨማሪ ምግብ አቅርቦት፣ የግብርና ዘርፍ ላይ ለህልውና የሚያስፈልጉ ምግብ ነክ አቅርቦቶች ከፍተኛ እጥረት መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መሠረት በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ለሰብዓዊ ድጋፎች በአስቸኳይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 237 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ዩኒሴፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለልማት ከተያዘው በጀት መንግሥት ወደ አስቸኳይ ዕርዳታ መዋል እንዳለበት ዩኒሴፍ አሳስቧል፡፡ የዴንማርክ ኤምባሲም የዩኒሴፍ ጥያቄን አስተጋብቷል፡፡ በዓለም ላይ በተከሰቱት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ የዕርዳታ ሽሚያ በማጋጠሙ፣ መንግሥት ለልማት ሥራዎች ከሚያውለው ፈንድ ውስጥ ለድርቁ ተጎጂዎች የሚውል ገንዘብ እንዲመድብ ጠይቋል፡፡
ሴቭ ዘ ችልድረን ኢትዮጵያ ለለጋሾች ቡድን እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የከረረ መሆኑን፣ መንግሥት ምላሽ የሰጠበት መንገድ ከወትሮው የተለየና ያልተለመደ ፍጥነት የታየበት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ሆኖም አስቸኳይ ዕርዳታ ካልተገኘ ግን አስከፊ የምግብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ሥጋቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የካናዳ ኤምባሲና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) መንግሥት መረጃ በመስጠትና ድርቅ በከሰተባቸው አካባቢዎች ፈጣን ግምገማ በማካሄድ ያገኛቸውን ውጤቶች በማሠራጨት በኩል ጥሩ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ ምትኩ በበኩላቸው ዘንድሮ በተከሰው ድርቅ መንግሥት ትልቁን ድርሻ በመያዝ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ከማቅረብ በተጨማሪ፣ ዕለታዊ መረጃዎችን ለለጋሾች በመስጠት ግልጽነት የተሞላበት ግንኙነት መመሥረቱን አስታውቀዋል፡፡