Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየሐቻምናው የሰንደቅ ዓላማ ቀን

የሐቻምናው የሰንደቅ ዓላማ ቀን

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ለስድስተኛ ጊዜ በመስከረም 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲከበር በክብር እንግድነት የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ነበሩ፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ መከበር የጀመረው ከኢትዮጵያ ሚሌኒየሙ ጋር ተያይዞ በ2000 ዓ.ም. ነበር፡፡ በየዓመቱ የመስከረም ሁለተኛ ሰኞ እንዲከበር በወጣለት አዋጅ መሠረትም እስከ 2006 ዓ.ም. ሲከበር፣ ከአምና ጀምሮም አዋጁ ተሻሽሎ ክብረ በዓሉ በጥቅምት ወር እንዲከበር መደንገጉ ይታወሳል፡፡ (ፎቶ በታምራት ጌታቸው)

*************

የውርርድ ቅኔ
‹‹እንወራረድ!››
ሲለኝ አጥብቆ – ካምና ጀምሮ
መስሎኝ ነበረ – ልክ እንደድሮ
‹‹እናሲዝ››ም ሲል – አምኘው ነበር
እንደድሯችን – መስሎኝ የፍቅር፤

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹እናሲዝ›› ብሎ – ያስይዘን ገባ
እኛ ስናምነው – በ‹ወንድም› ካባ
ያሁኑ ይባስ – ካምናው ጨምሯል
‹‹እንወራረድ›› – ማለት ጀምሯል፤

ተወኝ ወንድሜ – አንወራረድ
ጣት አንቃሰር – አንፈራረድ
ቢቀር ነው እሚሻል – ባንወራረድ
ብናዳፍነው ከምላስ – ባይወርድ፤

ያለዚያ ግና
እንወራረድ – ማለት ከመጣ
ለኔ ያሰብከው – ላንተ እሚመጣ
የሚወራረድ – ስንት አለ ጣጣ
ምዝዝ እያለ
ጉድ እሚያፈላ – ጉድ እሚያወጣ!!

        በደመቀ ከበደ – መሀል ሸገር

*****

በጐች የተሳተፉበት የሱፍ አልባሳት ኢንዱስትሪ ሳምንት

በለንደን የወንዶች አልባሳት ሰፊዎች በብዛት የሚገኙበት ዝነኛው የሳቬል ጎዳና ለአንድ ቀን የበጐች መናኸሪያ ሆኖ ማሳለፉ ተሰማ፡፡ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ በለንደን ከመስከረም 24 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የእንግሊዝ ብሔራዊ የሱፍ አልባሳት ኢንዱስትሪ ሳምንት ይከበር ነበር፡፡ በእንግሊዝ የሱፍ አልባሳት ኢንዱስትሪ ዕድገት እያሽቆለቆለ መሄድን ተከትሎ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ መከበር በጀመረው የሱፍ ኢንዱስትሪ ሳምንት፣ የዘንድሮው ለየት ያለ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ለሱፍ ጨርቅ መሥሪያነት ተመራጭ የሆኑት ባለፀጉራም በጐች በበዓሉ የመጀመሪያ ቀን በሳቬል ጎዳናዎች በመዋላቸው ነው፡፡

የሱፍ ኢንዱስትሪ ሳምንት አዘጋጆች እንደገለጹት፣ በጐቹ ጐዳና እንዲወጡ የተደረገው በሱፍ ጨርቅ ማምረትና መስፋት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡ በእንግሊዝ ተከስቶ በነበረው የዋጋ ውድቀት በግ አርቢ ገበሬዎች ዘርፉን እየለቀቁ መውጣት ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ የሱፍ ኢንዱስትሪ ሳምንት መከበር ከጀመረ ወዲህ የሱፍ ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ኢንዱስትሪው መልሶ እያንሰራራ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

* * *

ረዥም የእስር ቅጣትና ጋብቻን በአንድ ቀን

የ47 ዓመቱ ግሬግ ሆዋርድ የ20 ዓመት የእስራት ፍርድ በተከናነበበት ዕለት፣ በፍርድ ቤቱ ሌላኛው ክፍል ጋብቻውን ፈጽሟል፡፡

አሶሽየትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ሆዋርድ ለእስራት የተዳረገው፣ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በፔንስልቫኒያ ነዋሪ ለሆነች ሴት የቤት ዕቃዎች እናቀርባለን ብሎ በማታለልና ቤት ከደረሱ በኋላ ሴትየዋን አስረው 13 ሺሕ ዶላርና ጌጣጌጥ በመዝረፍ ነው፡፡

በዕለቱ ፍርዱን ያከናነቡት ዳኛ፣ በሌላኛው የፍርድ ቤት ክፍል የሰርግ ሥነ ሥርዓቱን እንዲፈጽምና በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሰርግ ልብስ እንዲለብስም ፈቅደውለታል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የሚስቱ ልጅና ተጨማሪ አምስት ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡   

* * *

ሰንደቅ ዓላማችን በኦሜድላ ሰማይ

በስደት ባሕር ማዶ ተሻግረው የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሱዳን በኩል በሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጠረፍ በምትገኘው ኦሜድላ ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀሉበት ቀን ከሰባ ሁለት ዓመት በፊት ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. ነበር፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርሮ የቆየበት ዓመታት ማብቃት መጀመሩም የተበሰረበት ነበር፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጠላታቸውን ለመደምሰስ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ካደረጉት የበረሃ ጉዞ በፊት በ1932 ዓ.ም. ማለቂያ ላይ ለአበርኞች በሬዲዮ ካሰሙት ንግግር የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹ይህ የምትሰሙት ድምፅ የኔ የንጉሣችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው፡፡ ያገሬ የኢትዮጵያ አርበኞች፣ አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው በነፃነት ያቆዩልንን አገራችንን ወደ ከፍተኛው የሥልጣኔ ደረጃ ለማራመድ የምንደክምበት ጊዜ ከጥንት ዠምሮ ስለ ሆነ ደመኛ ጠላታችን ኢጣሊያ ይህንን አይታ ወሰናችንን ጥሳ የግፍ ጦርነት እንዳደረገችብን ሁላችሁም የምታውቁት ነው፡፡ እኛም በተቻለን ከተከላከልን በኋላ እርዳታ ለመጠየቅ ወደ መንግሥታት ማኅበር ወደ ወዳጆቻችን መንግሥቶች መጣን፡፡ እዚህ ስንነጋገር በቆየንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ሰይፋችሁን ሳትከቱ ፊታችሁን ሳትመልሱ ሰንደቅ ዓላማችሁን ሳታጥፉ ለባዕድ አንገዛም በማለት በመሣሪያ ብዛት ከሚበልጣችሁ ጨካኝ ጠላት ጋራ የባህርይ የሆነውን ዠግንነታችሁን መሣሪያ አድርጋችሁ በኢትዮጵያ አምላክ ብቻ ተማምናችሁ በዠግንነት ቀንና ሌሊት በዱር በገደል ስትጋደሉ ቆይታችሁ ይኸው አሁን እንደምታዩት የማያቋርጥ የአምስት  ዓመት ትግላችሁ የድካማችሁንና የመሥዋዕትነታችሁን ፍሬ ለማየት እንድትበቁ አደረጋችሁ፡፡

ኢጣሊያ ወሰናችንን ጥሳ አገራችንን በወረረች ጊዜ በገንዘብ ችግር እንድትቀጣ ባደረጓት በታላቋ ብሪታኒያና በፈረንሳዊ ላይም ጀርመንን ተጠግታ ጦርነት ስላነሳች እነርሱም እርዳታቸውን ስለሰጡን የተመኘነውን አግኝተን ደረስንላችሁ፡፡ የእንግሊዝና የፈረንሳዊ ኃይለኛ የጦር አይሮፕላኖች በኢጣሊያ ግዛት በኢትዮጵያ አየር ውስጥ ያንዣብባሉ፡፡ ኢጣሊያም በአውሮፓ በአይሮፕላን በመድፍ ምላሹን ትቀበላለች፡፡ እግረኞች ወታደሮቿም ከምታምንባችሁ ከኢትዮጵያ ዠግኖች አያልፉም፡፡ በማናቸውም ስፍራ ያለህ የኢትዮጵያ አርበኛ ኢጣሊያን በርትተህ ውጋ ደግሞ በውድም በግድም ቢሆን በኢጣሊያ ውስጥ ያላችሁ የሀገሬ ሰዎች ኢጣሊያ እንግሊዝና ፈረንሳዊ ድል ይሆናሉ እያለች በሐሰት የምትሰብክላችሁን አትመኑ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የኢጣሊያ መሣሪያ በመሆን አገራችሁን የምትበድሉ ለዘራችሁ ከታሪካችሁ የማይፋቅ እርግማን ታቆያላችሁ፡፡››

በሱዳንም ሳሉ ከኢትዮጵያ ያርበኞች ሹማምንቶች ጋር እየተላላኩ ለጦርነት ተዘጋጅተው ከጨረሱ በኋላ በጥር ወር 1933 ዓ.ም. ግርማዊነታቸው ያንን ሁሉ በረሃ ቆርጠው የጠላታቸውን ምሽግ እየጣሱ ከጎጃም ግዛት ገቡ፡፡ በዚሁም ዓመተ ምሕረት በጥር 12 ቀን ኦሜድላ በሚባል ስፍራ ላይ በመዠመሪያ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ፡፡

የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ጎጃም መግባት በቃልና በደብዳቤ በያለበት ተሰማ፤ በዚህ ጊዜ ኢጣሊያኖች ድንጋጤና ፍርሀት አድሮባቸው ሲቀዘቅዙ በያውራጃው ያለ አርበኛ በደስታ ተሞልቶ ልቡ ደነደነ፡፡ የደከመው ሰውነቱ ጠነከረ ካርበኛው በቀር ከኢጣሊያኖች ጋራ አምስት ዓመት በሥቃይ የተቀመጠው ሕዝብ በየቤቱ ውስጥ እየገባ ነገሩን እየተወያየ ደስ ብሎት እርስ በርሱ ይሳሳም ዠመር፡፡ ለስለላ ወዳዲስ አበባ የሚመጡትንም የእንግሊዝ አይሮፕላኖች ቦምብ ይጥሉብናል ብሎ በመፍራት ፈንታ ነፃነትን እንደሚያበስሩ መላእክት እያሻቀበ በናፍቆት ዓይን ይመለከታቸው ዠመር፡፡ ከዚህ በኋላ በሸዋ በትግሬ በጎንደር በጎጃም [ኦሮሞ] አገር ያለ አርበኛ በያለበት መሽጎ የተቀመጠውን የኢጣሊያን ጦር እየከበበ ይዋጋው ዠመር፡፡ ከዚህ ጊዜ ዠምሮ ኢጣሊያኖች በራሪ ኢትዮጵያውያን አባራሪ ሆኑ፡፡  

ምንጭ፡- ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (1936 ዓ.ም.)፤ ‹‹የኢትዮጵያ ድል 25ኛ ዓመት›› (1958 ዓ.ም.)

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...