Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የዓለም ፌዴራሊዝምና የእኛ ሁኔታ ንፅፅር

   በገመቹ ዘለዓለም

የፌዴራል ሥርዓት በዓለም ተመራጭ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሲስተም ከሆነ ቢያንስ አራትና አምስት አሥርት ዓመታት አልፈዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ እስካሁን በዓለም ላይ ካሉ አገሮች 29 የሚሆኑት (ከዓለም ሕዝብ 40 በመቶ ያህሉ) የፌዴራል ሥርዓትን ይከተላሉ፡፡ እንደ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ቦስኒያ ሄርዞንቪና፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ኮሞሮስ፣ ኢትዮጵያ፣ ጀርመን፣ ህንድ ማሌዥያ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታንና ሩሲያ… እያሉ መዘርዘርም ይቻላል፡፡

በ1950ዎቹ ገደማ እንደ ኮሙዩኒዝምና ካፒታሊዝም ያሉ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚዎች የዓለምን ጫፍና ጫፍ ይዘው ሲጎትቱ፣ በአንድ አገር የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ሁኔታ ከመጣ የማንነት ጥያቄ እንደ ጉም በኖ ይጠፋል ይባል ነበር፡፡ ያ ሳይሆን ቀረና ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት ከፍተኛ ማንነት የመፈለግና አገር የመሆን ፍላጎት አይሎ ታይቷል፡፡

የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚያስረዱት በዓለም ላይ 200 ከሚደርሱት ሕጋዊ መንግሥት ያላቸው አገሮች ውስጥ ከስድስት እስከ ሰባት ሺሕ የሚደርሱ የቋንቋ፣ የብሔር፣ የአመለካከትና የእምነት ማንነት የፈጠራቸው ስብስቦች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 600 ያህሉ የራሳቸውን አገርና መንግሥት የመፍጠር ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህ አኃዝ ሲታይ በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ጥብቅ ትስስርም በዕድገት ሥልጣኔ አንድ ከሆኑት የሰው ልጅ ብዝኃነቶች በላይ በማንነት አገር የመሆን ወይም በፌዴራል ሥርዓት ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የመኖር ፍላጎት ጎልብቶ እየታየ ነው፡፡

የትኛውም አገር በሕዝቡ ጥንቅር ሲታይ በሁለት ጎራ ይከፈላል፡፡ አንደኛው የብሔር መንግሥት (Nation State) ሲባሉ አብዛኛው ሕዝባቸው የአንድ ብሔር አካል ነው፡፡ ሁለተኛውም የኅብረ ብሔራዊ መንግሥታት ወይም አገሮች ተብለው ሲታወቁ፣ በውስጣቸው ሁለትና ከሁለት በላይ ብሔረሰቦችን ይዘው ያሉ ናቸው፡፡ ይሁንና እነ አሜሪካና ካናዳን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ምዕራባውያን አገሮች ጭምር ኅብረ ብሔራውያን ናቸው፡፡

እንግዲህ ፌዴራሊዝም የምንለው አንድነትን ከብዝኃነት ጋር ያጣመረ የጋራ አስተዳደርና የራስ አስተዳደርን የመመሥረት ጠቀሜታዎችን የሚገልጽና ይህንን የሚያራምድ ነው፡፡ እንዲሁም አንድነትን/ኅብረትንና ያልተማከለ አስተዳደርን እንደ መርህ የሚወስድ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው፡፡

ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የሦስት ሺሕና ከዚያ በላይ ዕድሜ ባለፀጋ ነች የሚለው ብያኔ   (ከነአወዛጋቢ የታሪክ ጭብጦቹ) ወስደን ስናይ፣ አሁን ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በአንድ አገዛዝ ውስጥ የገቡት ከአፄ ምኒልክ ዘውዳዊ አገዛዝ ወዲህ ነው፡፡ እርግጥ ከዚያም በፊት ኢትዮጵያ የለችም የሚሉ የቀን ቅዠት ውስጥ ያሉ ቢኖሩም፣ ይህንን ከመሬት የተነሳ እብደት ትተን ከአፄ ምንሊክ ወዲህ ባለው አሀዳዊ አገዛዝ ግን የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ማንነቶችና ቋንቋዎች የመጨፍለቅ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ የነበሩት የአፄ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ይህንኑ አካሄድ ተከትለዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን 80 የሚደርሱ ብሔረሰቦች፣ ከ13 በላይ ሃይማኖትችና መንፈሳዊ ዕምነቶች፣ የጎሳ፣ የቋንቋና የመልክዓ ምድር ትስስሮች ተፈጥረዋል፡፡ ከ90 ሚሊዮን በላይ የሚገመተው የአገራችን ሕዝብ በሥነ ልቦናውና በአመለካቱ የገነባው የጋራ እሴት (Value) እንዳለ ባይካድም፣ ብዝኃነቱ ጐልቶ መታየቱ ግን ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በየትኛውም ሁኔታ ጥያቄ የሚያስነሳበት አመለካከት ቅቡል እየሆነ የመጣው፡፡

እርግጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ያለፈባቸው ያለፉት 24 ዓመታት ከፍተኛው ውዝግብ የተስተናገደባቸው ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ከቀደመው አሀዳዊ አስተሳሰብ የሚመነጨው አመለካከት ፌዴራሊዝምን አገር ሊበታትን የመጣ ናዳ አድርጎ በመሳል አውግዞታል፡፡ በሌላ በኩል በአሀዳዊነትና በአንድነት ስም ማንነት የመጨፍለቁ ጣጣ መጥፎ ጠባሳ ያሳረፈበት ወገን፣ ጉዞውን በፀጋ ከመቀበል ባሻገር የራስ አስተዳደሩን (Self Rule) ከዚህ በላይም ለጥጦ ማግኘትን ይሻል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተቃዋሚ ጎራ ያለው ኃይል እንኳን ፌዴራሊዝምን የሚያወዛግብበት ድምፁ እየሰለለ መከራከሪያ ጭብጡ እየመነመነ መጥቷል፡፡ ከዚያ ይልቅ ፌዴራሊዝም ተቀብሎ በአፈጻጸሙ ጉድለት ላይ የሚከራከረውን ኃይል መብዛት በየጊዜው እያየን ነው፡፡

በዚህ መነሻ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅም ፌዴራል ሥርዓቱ ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚል የእብደት ንትርክ ውስጥ አይገባም፡፡ አስፈላጊነቱን በአገሪቱ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታም ሆነ ከተዛባው የኖረው ታሪካችን በሚገባ ተምሯልና፡፡ ይልቁንም በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ በሚታዩ የአሠራር ክፍተቶች፣ በጠባብና በትምክህተኛ ግለሰቦች ፍላጎትም ሆነ በራሱ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ማነስ የሚስተዋሉ ችግሮችን ማጋለጥ መርጧል፡፡ ለቀጣይም ሥጋት እንዳይሆኑ በፍጥነት መታረም እንዳለባቸው ምክረ ሐሳብ ለማስቀመጥ ይወዳል፡፡

የጋራ አስተዳደር ጉዳይ ጉድለቶች

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በብሔር ብሔረሰቦችና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን በኅብረት (ፌዴራል) መንግሥት ውስጥም ሚዛናዊ ውክልናቸውን ተሳትፎን ያረጋግጣል፡፡ የጋራ መንግሥቱ የአንድ ብሔር ብቻ ወይም የብሔሮቹ ውህድ ሳይሆን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኅብር (ኅብረት) ነው፡፡ በመሆኑም የኅብረቱ መንግሥት እነዚህን ቡድናዊ ማንነቶች የሚያንፀባርቅ መሆን አለበት ይላል የሕገ መንግሥቱን ትርጓሜ የሚያብረራው ሰነድ፡፡

ከዚህ አንፃር ስናየው የአገራችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት (የሕዝብ ብዛታቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ብሔሮች ላይ ቢያተኩርም) የተሻለ የብሔር ብሔረሰቦችን ስብጥር ይዘዋል ማለት ይቻላል፡፡ በመንግሥት አስፈጻሚው ክንፍ በኩል ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ይኼውም በአንድ በኩል በፌዴራል መንግሥት ሲቪል ሰርቪስ፣ በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ ያሉ መሪዎችና የሥራ ኃላፊዎች ሹመትና ስያሜ ላይ አሁንም እምብዛም የሕገ መንግሥቱን መርህ የጠበቀ አይደለም፡፡

በእርግጥ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የፀጥታ፣ የመከላከያና የደኅንነት መዋቅሩን ባቀደው የትጥቅ ትግል ዲሲፒሊን ለመቅረፅ ቀደምት አዛዦችን ማስቀጠል ተገቢ ነው የሚል ሐሳብ ሲያራምድ ቢቆይም፣ ይህን ሒደት ከ24 ዓመታት በላይ ማስቀጠል አዳጋች ነው፡፡ በሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ወገኖችም ተጨማሪ መከራከሪያ ከማቀበል ወይም ‹‹ማናለብኝነት›› ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡

በአንድ ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ‹‹አገራዊ አስተሳሰብ ለገዥው ፓርቲ ዓላማ፣ ስኬትና ለሕዝብ ጥቅም መሠለፍ እንጂ የአንድ ቤተሰብ አባላትም የካቢኔ አባላት ቢሆኑ አያስጨንቀንም፤›› በማለታቸው የሕገ መንግሥቱን የጋራ አስተዳደር (Shared Rule) መርሆ ገደል ገባ ያሉ ተችዎች በዝተው ነበር፡፡ ምክንያቱም ከ80 በላይ ለሚሆን ብሔረሰብና ማንነት በጣጥቆ የፌዴራል ሥልጣን ማከፋፈል ባይቻል እንኳን፣ ተመጣጣኝና ሚዛናዊ የሆነ ተሳትፎን መዘርጋት ለመተማመንና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በፀና መሠረት ላይ ለማቆም ይረዳል፡፡

እዚህ ላይ አጽንኦት ልሰጠው የምፈልገው በቀደሙ የተዛቡ ሥርዓቶች አካሄድ ጠገግም ሆነ ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ለአናሳው (Minority) ማኅበረሰብ ከሚሰጠው ቅድሚያ ትኩረት አንፃር፣ ብዘኑኃኑ (Majority) ማኅበረሰብ እንዳይደናቀፍም ሊታይ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የአማራና የኦሮሞ ብሔሮችን ወስደን ብንፈትሽ ከ65 በመቶ በላይ የሕዝብ ብዛትና ከ56 በመቶ በላይ የቆዳ ስፋት እንደመያዛቸው ብቻ ሳይሆን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከፈጠሩት ሰፊ መስተጋብር አንፃር ለሕዝቦቹ ማንነትና የጋራ አስተዳደር ውክልና ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል እስላለሁ፡፡ ሁሉም መመጣጠን አለበት፡፡

የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ ፍትሕ እንቅፋቶች

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከአገሪቱ ልማት እኩል ተጠቃሚነት መብት እንዳላቸው የሚደነግጉ አንቀጾችን ይዟል፡፡ ይህን አስመልክቶ አንቀጽ 43 ሁሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተናጠል ኑሯቸውን የማሻሻልና የማያቋርጥ ዕድገት የማግኘት መብታቸውን ይደነግጋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራትንም መብት እንዲሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ግዴታ እንዳለበት (በአንቀጽ 89) ተቀምጧል፡፡

እስካሁን በሄድንበት መንገድ በአገሪቷ የመንገድ፣ የትምህርትና ጤና ወይም ሌሎች የስልክና የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን የማዳረስና ፍትሐዊ ሥርጭትን የማረጋገጥ ሥራ በጥንካሬ ይጠቀሳል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሀብት አጠቃቀም ድክመት ሊኖር ቢችልም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎች በጀት ድልድል ቀመር በጥንካሬ የሚወሳ ነው፡፡

ከዚህ ጭብጥ አንፃር የሚታየው የአፈጻጸም ሆነ የፖለቲካ ዝንፈት የሚመነጨው ከዜጎች በሕጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በአሀዳዊ ሥርዓትም ስም እንበለው ለዘመናት በዘለቀ የዜጎች አብሮነት ሥነ ልቦናዊ ትስስር ተጋብተውና ተዋልደው ብቻ ሳይሆን፣ በክፉም በደግም ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች በማንነታቸው (በብሔርና ቋንቋ) ያለምንም ወንጀልና ጥፋት ሲፈናቀሉ፣ ጉዳት ሲደርስባቸውና ሀብታቸው ሲወድም ብቻ ሳይሆን እስከ ሕልፈተ ሕይወት የደረሰ ጉዳት ከአንዴም ሁለት ሦስት አራት ጊዜ ተፈጽሟል፡፡

በነገራችን ላይ ሰሞኑን የፌዴራሉ ፍርድ ቤት የክስ ሒደት ይፋ ሲደረግ እንደሰማነው፣ በጋምቤላ ክልል ሦስት ወረዳዎች ለ30 ዓመታት ይኖሩ የነበሩ የአማራ ማኅበረሰብ ተወላጆችን በግፍ ያስወጡና የገደሉ ከ30 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለፍርድ ቀርበዋል፡፡ ጉዳዩ በወቅቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍና ገለልተኛ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ሲነገር ቢደመጥም፣ ዛሬ ግን በመንግሥት የክስ መዝገብ ጭምር የ147 ሰዎች የሕይወት ሕልፈት ይፋ መሆኑ የአደጋውን መክፋትና የመጪውን ጊዜ ፈተና እንደ ተራራ አጉልቶ ያሳያል፡፡

ይህ ድርጊት በኦሮሚያ (ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ አምቦና ሌሎች የምዕራብ ሸዋ አካባቢዎች አሁንም ቀጥሏል)፣ በደቡብ ክልል (እንደ ጉራፈርዳ፣ ዲላ፣ ካፋ ሸካና ጋሞ ጎፋ) በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁኔታው ያሳሰበው የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በጠባብነት እየወቀሰና ወደ ፍርድ ቤት እየወሰደው ቢሆንም፣ በሕዝቡም ውስጥ ሆነ በመንግሥት አካላት ዘንድ ጠንከር ያለ የግንዛቤና የኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንዛቤ ካልተፈጠረ ዜጎች እኩል ሊሆኑ አይችልም፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ መሬት፣ የመሥሪያ ብድር፣ ቴክኖሎጂ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሥራ ምደባና ሹመት በዜግነት ከፍ ያለ ወግና ማዕረግ ሊታዩ ይገባል፡፡ ከዚያ ወረዳ አኳኋን ብቃት፣ ችሎታም ሆነ የመሥራትና የመለወጥ ፍላጎት ሳይመዘን፣ በብሔር ብቻ እየተመዘነ ዕድል መፈጠርና መዘጋት ከተጀመረ ማጠፊያው ማጠሩ አይቀርም፡፡

በሕገ መንግሥቱም በግልጽ እንደተደነገገው በታሪክ አጋጣሚ ወደኋላ የቀሩ ክልሎችና ብሔረሰቦችን መደገፍና የሀብትም ሆነ የሥልጣን ክፍፍሉ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ይገባል፡፡ ነገር ግን እዚህም ላይ ቢሆንም ከብሔሩ (ከክልሉ) የወጣ ‹‹ገዥ መደብ›› መሰል ሥልጣን ላይ የተቆናጠጠ ግለሰብ ወይም ቡድን ሀብቱን እንዳይቦጠቡጠውና የዜጋውን ጥቅም እንዳያሳጣው መሥራት ግድ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ኃላፊነት የወደቀው ደግሞ የፌዴራሉ ሥርዓት ዋነኛ ምሰሶ የሆኑት ሕዝብና መንግሥት ላይ ነው፡፡

ፌዴራሊዝምን የሚያበለፅገው ዴሞክራሲ እንዳይኮላሽ

ማንም ፊደል የቆጠረ ሰው እንደሚገነዘበው የዴሞክራሲ መሠረቱ ነፃነት ነው፡፡ በነፃነት ማሰብ፣ በነፃነት መደራጀት፣ በነፃነት የፈለጉትን የፖለቲካ አቋም ማራመድ፣ ተንቀሳቅሶ መሥራትም ሆነ መኖርን ይይዛል፡፡ ከዚህ በላይ ዓለም የተግባባባቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ በአፈጻጸም እየዳበሩ እንዲሄዱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ይህ ካልሆነ የፌዴራል ሥርዓት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ብዝኃነትን ለተሸከመ አገር እኩልነት፣ ነፃነትና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በትምኩ የተጠቃሚነት መበላለጥ፣ የመብት ረገጣና አፈና ወይም የግለሰቦች ወይም የፓርቲ አምባገነንነት ከመጣ ያለጥርጥር የተገነባው ይፈርሳል፡፡ የመጣንበት በጎ መንገድም ቢሆን ወደኋላ ይመለሳል፡፡

አሁን በአገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ቢመረመር ክልል ከክልልም ሆነ ቦታ ከቦታ የተለያዩ ዝንባሌ መታየቱ አይቀርም፡፡ ዛሬም ቢሆን በአንዳንድ እስር ቤቶች  በሕገ መንግሥቱ የተቀበረው ማሰቃየትና የታራሚዎች መንገላታት አለ፡፡ በተለይ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞችና አንዳንድ በልዩ ሁኔታ (እንደ ሽብርተኝነት ባለ) የተጠረጠሩ ዜጎች ተፅዕኖ እንደሚደረግባቸው ፍርድ ቤት ሲቆሙ ብቻ ሳይሆን በመጻሕፍት እየከተቡት ይገኛሉ፡፡

በአገሪቱ ያለው የፕሬስና የሐሳብ ነፃነት ጤናማ አይመስልም፡፡ በአንድ በኩል የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ልሳን ብቻ የመሰሉ ‹‹የሕዝብ ሚዲያዎች›› ቀን ከሌት የሚያደነቁሩት ልማትና ስኬት ብቻ ሆኗል፡፡ ይህ አካሄድ ተገቢ ነው ቢባል እንኳን ከታች ያለውን ሕዝብ ያላሳተፈ፣ በመንግሥት ተሿሚዎችና ፕሮፓጋንዲስቶች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ፣ ድክመትና የለውጥ እንቅፋትን የማይነቅፍ፣ የሕዝቡን የልብ ትርታና ስሜት የሚያዳምጥ … በመሆኑ ሥራውን ሁሉ ፉርሽና የማይታመን ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል በጋዜጠኝነት የሙያው ሥነ ምግባርና በአገሪቱ ሕግ የሚመራ የግል (ነፃ) ጋዜጣ፣ መጽሔትም ሆነ ኤሌክሮኒክስ ሚዲያ ሊበራከት አልቻለም፡፡ ከሁለትና ከሦስት የማይበልጡ ለረዥም  ጊዜ በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ የዘለቁ ቢኖሩም ብዙዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ዕጣ ፈንታቸው መዘጋት ሆኗ፡፡ ሙያተኛውም ስደት፣ እስር ወይም ‹‹በቃኝ!›› ብሎ መቀመጥን መዋያና ማደሪያው ካደረገ ከራርሟል፡፡ ስለዚህ ነፃ ፕሬስ በዴሞክራሲ ዕድገት ውስጥ ሊጫወተው የሚገባው ሚና አንገቱ ታንቋል፡፡ ሊታይም ይገባዋል፡፡

በነፃ የመደራጀትና የፖለቲካ ትግል የማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብትም አንካሳ ሆኖ ታይቷል፡፡ በአገሪቱ በ70 እና 80 የሚቆጠሩ በየመንደሩ በቤተሰብ፣ በጓደኝነትና በብሔር ልጅነት የተደራጁ ‹‹ወፈ ሰማይ›› የፖለቲካ ማኅበራት (ፓርቲዎች) አሉ፡፡ ነገር ግን ተጠናክረው በኅብረ ብሔራዊ ደረጃ መደራጀት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሕዝብን ማንቃትና ተከታይ ማፍራት፣ ብሎም በየአካባቢው ጽሕፈት ቤትና ቋሚ የዴሞክራሲ ትግል መድረክ መፍጠር አልቻሉም፡፡ በዚያ ላይ የመንግሥትና የአውራው ገዥ ፓርቲ አካሄድ መደበላለቅና መንታ ገጽታ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አምልኮ በስተቀር ሌሎች አማኞችን የሚያፈናፍን እንዳልሆነ፣ በውስጥም ሆነ በውጭ የተለያዩ ኃይሎች እየተተቸ ነው፡፡

በሲቪክ ማኅበራት፣ በሙያም ሆነ በተለያዩ ማንነቶች እየተቋቋሙ ያሉ አደረጃጀቶችም ቢሆኑ ምን ያህል በአባላት ነፃ ምርጫና ከፖለቲካዊ ቅንበባ ውጪ ናቸው? የሚለውም ጥያቄ በቂ ምላሽ አላገኘም፡፡ በተለያዩ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገሮች የሥልጣኔና የዕድገት ጉዞ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ነፃነት ባለመረጋጋቱ የተሰነካከሉ በርካታ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሶቪየት ኅብረት በ1980ዎቹ ከአሜሪካ በእጥፍ የበለጠ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ ማዳበሪያ ወይም የነዳጅ ዘይት ምርት ነበራት፡፡ በጦር መሣሪያ ተፎካካሪነቷም ትታወቅ ነበር፡፡ ይሁንና ነፃነትና የዴሞክራሲ ባህልን መገንባት ባመቻሏ 15 የተበጣጠሱ አገሮች ለመሆን ተዳርጋለች፡፡ አሜሪካ ግን ያው ቁንጮነቷ ጠንክሮ ቀጥሏል፡፡

በአጠቃላይ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረታችንም ሆነ እስካሁን ያመጣነው ተስፋ ሰጪ ልማትና እየታየ ያለው ሰላም አበረታች ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ግን ‹‹ከአብዮታዊ›› ካባ ቀስ በቀስ እየተላቀቀ ነፃነትና እኩልነት ይጎናፀፍ ዘንድ ግድ ነው፡፡ የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም አስተሳሰብ በ1920ዎቹ የእነ ሌሊንና ስታሊን የማይበጅ ፍልስፍና ላይ ተጣብቆ ወደ ውድቀት እንዳይገፋንም ዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊ አገርን ለማቋቋም መትጋት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የሚታየው የአንዳንዱ ወገን ዝምታም ሆነ፣ ድልና ስኬት የመዘመሩ የመንግሥት አባዜ እየታረቁ ድክመቶችና ቀሪ ተግባራት ላይ ሊተኮር ይገባል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles