Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰንደቅ ዓላማው

ሰንደቅ ዓላማው

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጥንታዊ፣ ዘመን ተሻጋሪና የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ካላቸው አገሮች ጋር የሚመደብ ነው፡፡ ማዕከላዊ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊትና ከተመሠረተም በኋላ በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ እስከአሁን ዘልቋል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ለስምንተኛ ጊዜ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ዘመን›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ዙፋኒያስ ዓለሙ እንደሚሉት፣ ከማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታ በፊት በነበረው ዘመነ መሳፍንት፣ እያንዳንዱ መስፍን የተለያየ ቀለም ያለውና የራሱ የሆነ ሰንደቅ ዓላማ ነበረው፡፡ እርስ በርስ በሚያካሂዱት ጦርነት ላይ አሸናፊ የሚሆኑት መሳፍንት የየራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበልቡ ነበር፡፡ በወቅቱም፣ የአሸናፊነት፣ የጦር ኃያልነት፣ የሃይማኖት የበላይነት መገለጫ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡

ማዕከላዊ መንግሥት ተመሠረተ የሚባለው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ነው፡፡ ይህ ወቅት የተሰፋ ሰንደቅ ዓላማ የተዘጋጀበት ነው፡፡ አሁን ያለው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን የያዘው ሰንደቅ ዓላማ የመጣውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማው ለአገር ሉዓላዊነትና ለነፃነት ክብር ሲል ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፈው፣ በ1888 ዓ.ም. በዓድዋ ጦርነት ላይ ነው፡፡ ታላቁ ዓድዋ የዓለም ሕዝቦች ሰብአዊ ክብርና የመንፈስ ኩራት ከፍ ብሎ ከታዩባቸው የዓለም ኩነቶች ሁሉ የመጀመርያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር እስከወዲያኛው መሰበሩ በታሪክ ሊመዘገብ የቻለውም በሰንደቅ ዓላማ መሪነት በተደረገ ውጊያ አሸናፊ በመሆን ነው፡፡

ሰንደቅ ዓላማው፣ በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን እንደገና አገራዊ ቅርጽ አሲዞና የጀግንነት ሥራ ሠርቶ ትልቅ መስዋዕትነት በመክፈል አገሪቱን ከዚህ ወረራ በማላቀቅ ነፃነቷን እንድትቀዳጅ አድርጓል፡፡ በእነዚሁ ሁለት ታላላቅ ጦርነቶች ላይ ሰንደቅ ዓላማ ባስመዘገበው ድል የተነሳም ብዙ የአፍሪካ አገሮች እምነት እንደጣሉበትና ተምሳሌታቸውም ለመሆን እንደበቃ አስረድተዋል፡፡

ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመላቀቅ ወይም ነፃ ለመውጣት እንዲችሉና የአፍሪካ አንድነት እንዲመሠረት በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የሶማሊያና የኤርትራን ወረራዎች በማንኮታኮት ወረራው እንዲቀለበስ አድርጓል፡፡ አገርንና ሕዝብን ከባዕዳን ወረራ ነፃ አውጥቷል፡፡ የአገር ውስጥ የነፃነትና የእኩልነት ትግሉንም መርቷል፡፡ በፊውዳሉና በደርግ ሥርዓቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ ተስኗቸው፣ በነበረውም ብልሹ አስተዳደር ሳቢያ አገሪቷ ወደ ገደል አፋፍ እየተመራች ባለችበት ጊዜ ሰንደቅ ዓላማው ግዴየለም፣ ሰላም ይኖራል፣ አንድ እንሆናለን በማለት ከፍተኛ የሆነ ድልን አንጸባርቋል፡፡

እንደአቶ ዙፋኒያስ፣ የ1983ቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮት፣ ለሕዳሴው ጉዞ በር ከፋች የሆነውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ብዝኃነትን በአግባቡ በሚያስተናግድ መልክ እንዲቀረጽ አድርጓል፡፡

የሕዳሴው መሪ በሆነው ሰንደቅ ዓላማ መሃል ላይ ያረፈው ብሔራዊ ዓርማ፤ የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የሃይማኖቶችን እኩልነት ያረጋግጣል፡፡ ተፈጻሚነቱም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ በሙሉ፤ በክልል መንግሥታትና በሁለት ከተሞች አስተዳደር ውስጥ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ በኤምባሲዎችና ቆንስላዎች፣ አውሮፕላኖች፣ መርከቦች፣ ጀልባዎችና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

በሰንደቅ ዓላማው መሃል ላይ ያለው ክብ፣ አረንጓዴውና ቀዩ መስመሮች በግማሽ ያርፉበታል፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ መስመሮች ደግሞ እኩል ሆነው ወርዱ የቁመቱን እጥፍ ይሆናል፡፡ የብሔራዊ ዓርማም ሆነ የሰንደቅ ዓላማው ጠቅላላ ቀለማት ብሩህ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በብሔራዊው ዓርማ ላይ ከየአቅጣጫው መጥተው የሚገናኙ ቢጫ ጨረሮች ይኖሩታል፡፡ ቁመታቸው እኩል ነው፡፡ እንደሁም እኩል ቁመት ያላቸው መስመሮች ተዋቅረው አንድ ኮከብ ይሆናሉ፡፡ በተገጣጠሙት ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ቀለም ይኖራል፡፡

ብሔራዊ ዓርማ ላይ የተቀባው ሰማያዊ ቀለም ሰላም፤ ከየአቅጣጫው የሚመጡት ጨረሮች የሕዝቦችን፣ የሃይማኖቶችን፣ የሐሳቦችንና የባህሎችን እኩልነትና ነፃነትን ያረጋግጣል፡፡ ኮከቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ብሔሮች ብሔረሰቦች የመሠረቱትን አንድነት የሚያሳይ ሲሆን ቢጫው በዚህ አንድነት የፈነጠቀውን ብሩህ ተስፋን ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሚፈቀደው ትልቁ 210 ሳንቲ ሜትር ከ420 ሳንቲ ሜትር፣ ከዛ ወረድ ሲል 150 ሳንቲ ሜትር በ300 ሳንቲ ሜትር፤ ቀጥሎ 135 ሳንቲ ሜትር በ280 ሳንቲ ሜትር ነው፡፡ የመጨረሻውና ለጠረጴዛ የሚውለውና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚውለበለበው 21 ሳንቲ ሜትር በ42 ሳንቲ ሜትር ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በየቀኑ መውለብለብ አለበት፡፡ በሌሎች መሥሪያ ቤቶችም እንዲሁ፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሚሰቀልበትም ሥፍራ በመሥሪያ ቤቱ ወይም በሕንፃው መሃል ለመሃል ባለው ቦታ ላይ መሆን አለበት፡፡

የሚሰቀልበት ጊዜ ከንጋቱ 12 ሰዓት፣ ከተሰቀለበት የሚወርድበት ደግሞ ከማታው 12 ሰዓት ነው፡፡ ሲወጣና ሲወርድ ተገቢው ክብር ሊሰጠው ግድ ይላል፡፡ ትምህርት ቤቶች ግን ተማሪዎች ለትምህርት ሲገቡ ብሔራዊ መዝሙሩን እየዘመሩ እንዲሰቅሉ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ የሚወርደው ግን ከማታው 12 ሰዓት ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከክልሎች ጋር ሲያያዝ የሚኖረው አሰቃቀል ሲያወዛግብ የቆየ መሆኑን አቶ ዙፋኒያስ ገልጸው፣ በዚህም የተነሳ በጣም ትልቅ የሆነ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማው ከአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ጋር ሲሰቀል የፌዴራሉ ሁልጊዜ በስተቀኝ በኩል መሰቀል አለበት፡፡ ሁለት ሲሆኑ የፌዴራሉ መሃል ላይ ይሆናል፡፡ በቁመትም አጠገቡ ከሚኖሩት ከፍ ይላል፡፡ ከሁለት በላይ ወይም ብዙ በሚሆኑበት ጊዜ የፌዴራሉ ወይም የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በስተቀኝ በኩል ይሆንና ሌሎች በክልሉ ስም የአማርኛ ፊደል ቅደም ተከተላቸውን ይዘው ይሰቀላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን የሚመለከት ወደ 11 የሚጠጉ የተከለከሉ ተግባራት ተቀምጠዋል፡፡ ከተከለከሉት ተግባራት መካከልም ብሔራዊ ዓርማ የሌለውን ወይም ያልተደረገበትን ሰንደቅ ዓላማ መስቀልና የንግድ ማስታወቂያ ማድረግ ከተከለከሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ክልከላውን ለሚተላለፉም ቅጣት ተቀምጧል፡፡ ከፍተኛ አምስት ሺሕ ብር እና አንድ ዓመት ተኩል እስራት ሲሆን፣ ሕጋዊ  ሰውነት ያላቸው ተቋማት ግን ከተጠቀሰው ገንዘብ እጥፍ በላይ ይቀጣሉ፡፡

አቶ እውነቱ ብላታ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብሮ ለመኖር በልዩነት ውስጥ ያለውን ማንነታቸውን ለማጠናከር ቃል ኪዳን የገቡበት የቃል ኪዳን ሰነድ ስዕላዊ መግለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር የተቆራኘ ፍቅርና ታሪክ አላቸው፤›› ብለዋል፡፡

ጥንት ገናና ታሪክ የነበረው ሕዝብ ለዘመናት በችግር ሲናጥ የቆየው ልዩነትን ማክበር ባለመቻሉ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሁለት አሠርታት በተደረገው ትግል፣ በተለይም በተደረገው የፀረ ድህነት ትግል ቀና ማለት እንደተጀመረ፣ በዓለም አደባባይም ኢትዮጵያውያን ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...