Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊባለ አውሮፕላን የመሆን ጉጉት

  ባለ አውሮፕላን የመሆን ጉጉት

  ቀን:

  ዓርብ መስከረም 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነው፡፡  የአባ መጫ ግቢ ሦስት አጥሮች አሉት፡፡ በመጀመሪያው አጥር በብዛት ሸንኮራና ተክል ይገኛል፡፡ በሁለተኛው ቡና ብርቱኳን፣ ማንጎ፣ አቩካዶና ሌሎች ተክሎች አሉ፡፡ ከአንደኛው ጥግም ሰፋ ያለ በብረት የተሠራ አግዳሚ ወንበር ይገኛል፡፡ ወንበሩ አባ መጫን ፈልጎ የሚመጣ እንግዳ የሚያርፍበት ነው፡፡ እሳቸውን ለማግኝት የፈለገ በመጀመሪያ ለጠባቂው ስለ ማንነቱና ስለመጣበት ጉዳይ ማስረዳት ይኖርቦታል፡፡ አባ መጫ አባደጋን  ስናገኛቸው ቁርስ በመመገብ ላይ ነበሩ፡፡

  የ75 ዓመቱ ሃጂ አባ መጫ ተወልደው ያደጉት በኢሉባቦርና በአጋሮ መካከል በምትገኝ ኪሎሌ በተባለች ቦታ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በቦታው ስያሜ አባ መጫ ኪሎሌ ይሏቸዋል፡፡ አባታቸው አባ ደጋ ሀብታም የቡና ገበሬ ነበሩ፡፡ ከሃያ ጋሻ የሚበልጥ የቡና መሬት ነበራቸው፡፡ ከቡናው ጎን ለጎንም የተለያዩ አዝርዕቶችን ያመርቱ ነበር፡፡ በወቅቱ የላቀ ገቢም ነበራቸው፡፡ ይህንን ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ቤት ንብረት የማስተዳደር ኃላፊነቱ ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ በሆኑት አባ መጫ ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡

  በወቅቱ በአሥራዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አባ መጫ፣ አቶ ሺበሺ ገብረየስ በተባሉ አሳዳጊያቸው መሪነት የማስተዳደሩን ኃላፊነት ተቀበሉ፡፡ ይሁን እንጂ ልጅነት ያጠቃቸው ስለነበር በማስተዳደር ሥራው ብዙም ቤተሰቡን አላስደሰቱም፡፡ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር አገር መጎብኝት ተቀዳሚ ተግባራቸው ሆነ፡፡ ‹‹ልጅ ስለነበርኩ የተጣለብኝ ኃላፊነት አላሳሰበኝም፡፡ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አገር መጎብኝት ያስደስተኛል፡፡ ስለዚህም የተለያዩ ከተሞችን እጎበኝ ጀመር፡፡ በኢትዮጵያ ያልጎበኘሁት አካባቢ የለም፤›› ይላሉ፡፡

  ከቦታ ቦታ መዘዋወርን ቅድሚያ የሰጠው የልጅነት አዕምሮአቸው አንዳንድ ኃላፊነታቸውን አዘንግቷቸው ኖራል፡፡ ወላጅ አባታቸው በሕይወት ሳሉ በአባቢው ከሚገኙ ባላባት ለገዙት ሃያ ጋሻ መሬት፣ ቡና፣ ማር ቅቤና ሌሎችም ምርቶች ለባላባቱ ይገብሩም ነበር፡፡ ነገር ግን ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ኃላፊነቱን የተቀበሉት አባመጫ ሳይገብሩ ቆዩ፡፡

  በአንድ ወቅት የዘነጉትን ኃላፊነት ለመወጣት ከሰውየው ቤት ደረሱ፡፡ ጉዳዩ ከባድ ስለነበር መሬቱን ሊነጠቁ ሆነ፡፡ ጉዳዩ ያሳሰባቸው አባ መጫም አርፈው አልተቀመጡም፡፡ ክስ ለመመስረት አዲስ አበባ መጡ፡፡ ቅብጥብጡ የልጅ አዕምሯቸው ግን የትኩረት አቅጣጫውን ቀየረ፡፡ ይመላለሱበት የነበረው አውሮፕላን ‹‹ለምን በአካባቢዬ አይመጣም፡፡ ማረፊያ ሜዳም እንደሆነ ሰፊው የኪሎሌ ሜዳ አለ፤›› በሚል ሐሳብ ተሳቡ፡፡ አውሮፕላን ለመግዛትም ወሰኑ፡፡

  ጉዳዩን አዲስ አበባ ለሚገኙ ወዳጃቸው አማከሩ፡፡ የማቀርባቸው ወዳጅ ነበሩኝ፡፡ አውሮፕላን መግዛት እንደምፈልግ ነገርኳቸው፡፡ አይሆንም በማለት ጥቂት አንገራገሩ፡፡ በኋላ ግን አሳመንኳቸውና ጉዳዩን ለሌላ ሰው አማክረው ጥሩ ተስፋ አግኝቼ ነበር፤›› በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡

  ‹‹ገንዘቡን አምጣ አውሮፕላኑንም ይመጣል›› በመባላቸው ገንዘቡን ለማምጣትም ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመለሱ፡፡ ወዲያውም በወቅቱ የመገበያያ ገንዘብ የነበረውን ማርትሬዛ በስልቻ አስይዘው አሽከሮቻቸውን አስከትለው አውሮፕላን ለመግዛት አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡

  አውሮፕላኑን እንደሚያጋዟቸው ቃል የገቡላቸው ግለሰብ በቃላቸው አልተገኙም፡፡ ‹‹ገንዘቡን ከየት አመጣኸው ሲሉ አፋጠጡኝ፡፡ ተቀበሉኝም፡፡ የደበቅኩት እንዳለም እንድሰጣቸው ጠየቁኝ፡፡ በመጨረሻም እስር ቤት ሊያስገቡኝ ፈለጉ›› ያሉት አባ መጫ፣ ገንዘባቸው ቢነጠቅም ከወላጅ አባታቸው በውለታ የተሳሰሩ ግለሰብ ጉዳዩን  ሸምግለው እስር ቤት ከመግባት እንዳዳኗቸው ይናገራሉ፡፡

  በሁኔታው የተደናገጡት አባ መጫም ወደቀዬአቸው በመመለስ ግብርናውን አጠናክረው ይሠሩ ጀመር፡፡ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብም ቻሉ፡፡ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ፍላጎታቸውንም በአውሮላን ባይሆንም በመኪና አሳኩት፡፡ በቋጠሩት ጥቂት ማርትሬዛ፣ ላንድሮቨር መኪና ገዙ፡፡ ቤተሰብ መሥርተውም ሰባት ልጆች አፍርተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አራቱ በአሜሪካ፣ ሁለቱ በአዲስ አበባ ሲኖሩ ወንድ ልጃቸው ደግሞ አብሯቸው ይኖራል፡፡

  በደርግ ዘመን አብዛኛው ቤት ንብረታቸው ተወርሷል፡፡ የቀራቸውን ጥቂት የቡና መሬት ያርሳሉ፡፡ ኑሮ እንደበፊቱም ባይሆንም የሚቸግራቸው የለም፡፡ ኑሮ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

  ሌላው በበደሌ ከተማ ያገኘነው የ29 ዓመቱ ፍሥሐ በየነ ነው፡፡ ተወልዶ ያደገው በደሌ ነው፡፡ እንደ አባ መጫ የባለፀጋ ልጅ አልነበረም፡፡ እዚህ ግባ የሚባል ገቢም የለውም፡፡ ነገር ግን እንደ እሳቸው ሁሉ አውሮፕላን እንዲኖረው ይመኛል፡፡

  በከተማው የአውሮፕላን ማረፊያ ቢኖርም አገልግሎት ስለማይሰጥ አውሮፕላን ምን እንደሚመስል በቅርበት የሚመለከትበት አጋጣሚ አልነበረውም፡፡ ስለአውሮፕላን በልጅነቱ የሚያውቀው ጥቂት ነበር፡፡ ‹‹ሕፃን ሆኜ ወላጆቼ ቡና ላይ ስለ አውሮፕላን ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ ብዙ ጊዜም የአውሮፕላን ነፋስ ሰው ይበላል ሲሉ በጣም ያስፈራኝ ነበር፤›› የሚለው ወጣቱ፣ አውሮፕላን በቅርበት ለማየት ይመኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አውሮፕላንን በቅርበት የሚመለከትበት ዕድል ወደ ቀዬው መጣ፡፡

   ብዙዎቹ የከተማው ነዋሪዎችም አውሮፕላኑን ለማየት በአጀብ ከቦታው ደረሱ፡፡ ፍሥሐ አውሮፕላን እንዴት ሰው እንደሚበላ ለማየት ከቦታው ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን የጠበቀው ነገር ሳይከሰት ቀረ፡፡ አውሮፕላኑም ተነስቶ በረረ፡፡ ‹‹ማመን አቃተኝ፡፡ ይህን የሚያክል ነገር እንዴት በረረ ብዬም ተገረምኩ›› የሚለው ወጣቱ፣ አጋጣሚው እንዲመራመር እንዳስገደደውም ይናገራል፡፡ አውሮፕላን የመሥራት ፍላጎት ያደረበትም ያኔ ነበር፡፡

  የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሕልሙን ለማሳካት እርምጃውን አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ የተለያዩ መጽሔቶችና ሌሎችም ስለ አውሮፕላን አሠራር መረጃ የሚሰጡ ጽሑፎችን ማንበብና አንዳንድ የአውሮፕላን የውስጥ አካሎችን መሥራት ጀመረ፡፡ በ1997 ዓ.ም. በበደሌ ዳበና ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጀነራል ሜካኒክ ትምህርት የተማረው ፍሥሐ፣ ትምህርቱ በጥቂቱም ቢሆን ረድቶት እንደነበር ይናገራል፡፡

  ከአቅም ማነስ ባሻገር ትልቅ የቦታ ችግር ነበረበት፡፡ አውሮፕላኑን ይሠራ የነበረው በአንዲት አነስተኛ ክፍል ነው፡፡ አስፈላጊው ግብዓቶችን ማግኘት ይከብደዋል፡፡  አነስተኛ መርጃ ማሽኖች እንኳን አልነበሩትም፡፡ ‹‹የብየዳና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች አገኝ የነበረው ሰፈር ውስጥ አገልግሎቱን ከሚሰጡ ሰዎች በክፍያ ነው፡፡ ብረቶችን የማጣምመውም እህቶቼ እንዲቀመጡበት በማድረግ ነበር፤›› ሲል እየሳቀ ነበር፡፡

  ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ከወንድሙ በጋራ የሚሠራው የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ሥራ ጥቂት ገንዘብ እንዲይዝ አስቻለው፡፡ የተወሰኑ ግብዓቶችንም አሟላ፡፡ ትንሽም ቢሆን ሥራውን አቀለለለት፡፡ በዚህ መልኩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን አቁሞ ትኩረቱን በአውሮፕላን ሥራው ላይ አደረገ፡፡

  ምንም እንኳን አውሮፕላን ለመሥራት አልሙኒየም መጠቀም ቢኖርበትም፣ ካለው የዋጋ ውድነትና የተደራሽነት ችግር አንፃር በተገቢው መጠን ሊጠቀም አልቻለም፡፡ ‹‹ሠርቼ ለመጨረስ አንግል አይረን፣ ጋልቫናይዝድ ሺት ሜታልና ሌሎች ቀላል ብረቶች መጠቀም ነበረብኝ፤›› በማለት ውስን አቅሙ አማራጮችን እንዲጠቀም እንዳስገደደው ይናገራል፡፡

  ተገቢውን ግብዓት መጠቀም ባለመቻሉ ያሰበውን ያህል መሥራት ባይችልም፣ አራት ሜትር ርዝማኔ ያላት፣ ወደ ጎን ከክንፍ እስከ ክንፍ አምስት ሜትር ከሃያ የምትሰፋ የ34 ፈረስ ጉልበት ያላት አንድ ሰው የምትጭን አውሮፕላን ሠራ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ባደረገው ሙከራም እስከ 500 ሜትር ድረስ መንደርደር እንደቻለች ይናገራል፡፡ ማሻሻያዎችን በማድረግም በሥራ ላይ ሊያውላት ፍላጎት አለው፡፡ ሙከራው ፍሬ ያፈራ ዘንድ ሙያዊ ሥልጠና እንደሚያሻውና መንግሥትም ይህንን ተመልክቶ እንዲረዳው እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡  

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...