Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጀብድነት በፊልም

ጀብድነት በፊልም

ቀን:

ሙሉጌታ አማሩ መገርሳ (ደብሊው) የተወለደው መሳለሚያ አካባቢ ነው፡፡ በልጅነቱ በአቅራቢያው የሚገኙ ኮረብታዎችን መውጣት፣ ከፍ ካሉ ሥፍራዎች መዝለል ይወድ ነበር፡፡ ፏፏቴ ያለባቸው አካባቢዎች ላይም ይዋኛል፡፡

ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን ደፍሮ ማድረግ ያዝናናው እንደነበር ይናገራል፡፡  የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለም አክሮባት መሥራት፣ ወደግንብ መውጣትና መውረድ ያዘወትር ነበር፡፡ የአካል ብቃት ከሚጠይቁ መሰል ክንዋኔዎች ጎን ለጎን ወደ ፊልም የመግባት ሕልም ነበረውና፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ አጫጭር ፊልሞችን መቅረፅ ጀመረ፡፡

በፊልሞቹ የማርሻል አርትና ሌሎችም ስፖርታዊ ችሎታዎችን የሚጠይቁ ትዕይንቶች ያካትት ነበር፡፡ ትዕይንቶቹ በብዛት የሚሠሩት በስታንት፣ ማለትም አንድን ተዋናይ ወይም ተዋናይት ወክሎ ጀብድ በሚከውን ባለሙያ ነው፡፡ ሙሉጌታና  ጓደኞቹ እንደ ስታንት፣ እንደ ተዋናይም በመሆን መሥራትን ተያያዙት፡፡ ከዚያ በኋላም ስታንት የሚያስፈልጋቸው ፊልሞች (በብዛት አክሽን ፊልሞች) ላይ አሻራውን ማሳረፍ ጀመረ፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት ስታንት እስከሆነበት ‹‹ኒሻን›› ፊልም ድረስ በርካታ ፊልሞችን ሠርቷል፡፡ አይሞከሩም፣ አይደፈሩም የተባሉ ትዕይንቶችን ተወጥቷል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ያለ ጉዳት አይደለም፡፡ ከልጅነቱ አንስቶ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ልጅ ሳለ ‹‹በራሴ ላይ የማመጣውን ጉዳት ራሴ ማከም አለብኝ፤›› ብሎ ስለሚያምን እጁ ሲሰበር፣ ወይም እግሩን ወለም ሲለው ራሱን ያክማል፡፡ በፊልም ሥራው ይጠቅሙኛል ብሎ ያመነባቸውን ከአካል ብቃት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችም ወስዷል፡፡ ተዋንያንን የሚፈትኑ ትዕይንቶች ያካተቱ ፊልሞች በብዛት አለመሠራታቸው ያሳዝነው ስለነበር በሙያው ለውጥ ለማምጣት ዘርፉን እንደተቀላቀለ ይናገራል፡፡  ድፍረት የተሞላበት ትዕይንት የማይታይባቸው ፊልሞችን ‹‹የዋህ ፊልሞች›› ይላቸዋል፡፡

ፊልሞች ላይ የተለየ የአካል ብቃት ወይም ችሎታ የሚጠይቁ ትዕይንቶች ሲኖሩ፣ ተዋንያኑ መከወን ካልቻሉ በስታንቶች ይተካሉ፡፡ በተቀረው ዓለም አደገኛ የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን የሚፈጽሙ ስታንት ሳያስፈልጓቸው፣ ትዕይንቶችን የሚወጡ ተዋንያንም አሉ፡፡ የራሳቸውን ስታንት ከሚሠሩ ተዋንያን መካከል ጃኪ ቻን፣ ጄሰን ስታትሀም፣ አንጀሊና ጆሊና ዳንኤል ክሬግን መጥቀስ ይቻላል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2001 ‹‹ወርልድ ስታንት አዋርድስ›› በሚል የስታንቶች ውድድር ተጀምሯል፡፡ የመጀመርያውን የዕድሜ ዘመን ሽልማት ያገኘውም አርኖልድ ሸዋዚንገር ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሲኒማ ያን ያህል ጎልተው የወጡ አክሽን ፊልሞች ወይም ስታንት የሚያስፈልጋቸው ትዕይንቶች አሉ ለማለት ባያስደፍርም፣ ለሙያው ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ባገኟቸው ፊልሞች ከሞት ጋር ይፋጠጣሉ፡፡

‹‹አላዳንኩሽም›› ሙሉጌታ በስታንትነት ከሠራባቸው ፊቸር ፊልሞች የመጀመርያው ነው፡፡ ‹‹አሸንጌ›› ላይ የአንዲት ሴት አርበኛ ስታንት ሆኖ ይሠራል፡፡ አርበኛዋ ከጣልያን ካምፕ ጥይት ሰርቃ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ስትሰጥ ትያዛለች፡፡ የጣልያን ወታደሮችም በአሰቃቂ ሁኔታ ይደበድቧታል፡፡ እንደ ተዋናይቷ ሆኖ የሚደበደበው ሙሉጌታ ነው፡፡ መኪና ማጋጨት፣ መደባደብ፣ ከፎቅ መዝለል ከሚጠቅሳቸው ትዕይንቶች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ‹‹ስርየት›› ላይ  መስታወት ሰብሮ ከፎቅ የዘለለበትን ትዕይንት አይዘነጋውም፡፡ መድማት፣ መቆረጥ፣ መሰበርና ራስን መሳት የዘወትር ገጠመኞቹ ናቸው፡፡ ፈተናዎቹን ይወዳቸዋል፡፡ ሁሌም አዳዲስ ፈተናዎች በሚጋረጡበት ሁናቴ ራሱን ከመክተት ወደኋላ አይልም፡፡

አክሽን ፊልም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ እንደሚቀረው ይናገራል፡፡ አክሽን ፊልም ለማዘጋጀት የሚደፍሩ ባለሙያዎች ውስን ከመሆናቸው ባሻገር፣ ተመልካቹም ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው፡፡ ‹‹አክሽን ፊልም አሳማኝ መሆን አለበት፤ ተመልካቹ ደንግጦና ትዕይንቱን አምኖ የሚያየው ግብዓቱ የተሟላ ሲሆን ብቻ ነው፤›› የሚለው ሙሉጌታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ አክሽን ፊልሞች ይህን መስፈርት እንደማያሟሉ ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል አክሽን ፊልም የሚጠይቀውን ወጪ የሚደፍሩ ፕሮዲውሰሮች ጥቂት ናቸው፡፡  ፊልሞች ቢሠሩም ማርሻል አርትን ከማሳየት ያለፈ ሚና ሲኖራቸው አይስተዋልም፡፡  ጸሐፊዎች በስክሪፕታቸው ከባድ ትዕይንት አያካትቱም፤ ቢያካትቱም የሚሠራ ባለሙያ እንደሌለ ስለሚያስቡ ያወጧቸዋል፡፡ ‹‹አይቻልም ባይባልና ድፍረት የሚጠይቁ ትዕይንቶች ቢኖሩ ፊልሞቻችን እየገዘፉ ይሄዳሉ፤›› ይላል፡፡

አስቂኝ የፍቅር ፊልሞችና ድራማዎች መብዛታቸው ስታንቶችን ከገበያ እያስወጣቸው ይመስላል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የአክሽን ትዕይንት ያካተቱ ፊልሞች በሚሠሩበት ወቅት ስታንቶች የተሻለ ዕድል ነበራቸው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ስታንቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ያሉትም በሙያው ለመዝለቅ አይሹም፡፡ ሕይወታቸውንና አካላቸውን ለአደጋ በማጋለጥ የሚሠሩት ስታንቶች፣ በቂ ክፍያ አያገኙም፡፡ ለፊልም በሚያደርጉት አስተዋጽኦም ተገቢው ክብር አይሰጣቸውም፡፡ በዚህ ምክንያትም ሙሉጌታ ከዚህ በኋላ በስታንትነት ስለመሥራቱ እርግጠኛ አይደለም፡፡

ሐሳቡን የሚጋራው ሌላው ስታንት አስፋው በፍቃዱ ነው፡፡ እንደ ሙሉጌታ ሁሉ ከሙያው መውጣት እያሰበ ነው፡፡ ስታንቶች ለፊልም እንደሚያስፈልጉ የሚያውቁ  ጥቂት መሆናቸውን ይናገራል፡፡ አስፋው ወደ ሙያው የገባው ለአክሽን ፊልሞች በነበረው ፍቅር ተነሳስቶ ሲሆን፣ በቴኳንዶ፣ በጂምናስቲክና በስታንትነት ወደ 20 ዓመታት ገደማ ሠርቷል፡፡ የብሩስ ሊ፣ ጀት ሊና ጃኪ ቻንን ሥራዎች ከመከታተል አልፎ መሥራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሚሰማውን ደስታ ይገልጻል፡፡ ደስታው በጥርሱ መሸረፍ፣ በትከሻው መውለቅና ሌሎችም ጉዳቶች ዋጋ የመጣ መሆኑም አያሳዝነውም፡፡

‹‹የምሠራው እርካታ ቢሰጠኝም፤ ስታንትነት ተጠቃሚ አያደርግም፤›› ይላል፡፡ በ‹‹ኢካቦድ››፣ ‹‹ላንተ ስል አልሞትም››፣ ‹‹አፍሮኒዝም›› እና ሌሎችም ፊልሞች ሠርቷል፡፡ ‹‹ሔሮሽማ›› ላይ መሣሪያ አንግቦ ከተራራ በሚወርድበት ትዕይንት ያየው ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ ‹‹ደፋር ነኝ›› ቢልም ልጅ ከወለደ በኋላ ቆም ብሎ ማሰብ ጀምሯል፡፡

ስታንቱን ከአደጋ የሚጠባበቁ እንደ ገመድና ፍራሽ ያሉ ግብዓቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ መሥራት ያስቸግራል፡፡ የስታንቶችን ሥራ የሚያውቁ የፊልም ተመልካቾችም ጥቂት ናቸው፡፡ አንድ ስታንት ፊልም ሲሠራ ጉዳት ቢደርስበት ዞር ብሎ የሚያየው የለምም ይላል፡፡

ሰለሞን ገብሬ (ሶል ቢሊ) እንደ አብዛኞቹ ስታንቶች አክሽን ፊልም ላይ በሚያያቸው ተዋንያን ተማርኮ ነው ሙያውን የተቀላቀለው፡፡ አደጋ የሚያስከትሉበት ሁነቶችን እየፈጠረ ለማለፍ ይጣጣር ነበር፡፡ ሥልጠና ወስዶ በአካል ብቁ ከሆነ በኋላ አጫጭር ፊልሞች ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ የመጀመርያ ፊልሙ ‹‹ኢካቦድ›› ከፎቅ መዝለል፣ መደባደብና ሌሎችም ፈታኝ ትዕይንቶች የተካተቱበት ነበር፡፡

በመቀጠል ‹‹አልሞትም›› የተሰኘ አክሽን ፊልም ፕሮዲውስ አድርጓል፡፡ አክሽን ፊልም ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ፕሮዲውሰሮች አለመኖራቸውን ከሌሎቹ ባለሙያዎች ጋር ይስማማበታል፡፡ እሱም ስታንት ከመሆን በተጨማሪ ፕሮዲውስ ወደ ማድረግ የገባው ለዚሁ ነው፡፡ አክሽን ፊልሞችን ሲያዘጋጅ ከገጠሙት ፈተናዎች ውስጥ የገምጋሚዎች የተዛባ እሳቤና ሲኒማ ቤቶችን ይጠቅሳል፡፡

‹‹ሳይቦርግ›› የተሰኘውን የቫን ዳም ፊልም ጽንሰ ሐሳብ በመውሰድ ‹‹አዳኝ›› የሚል ፊልም አዘጋጅቷል፡፡ ሆኖም የመሣሪያና የስለት ድብድቦች ከፊልሙ መውጣት እንዳለባቸው እንደተገለጸለት ይናገራል፡፡ ሲኒማ ቤቶችም አክሽን ፊልም የማሳየት ፍላጎት የላቸውም፡፡ የፊልሙ ዝግጅት ቀላል እንዳልነበረ ሲያስረዳ፣ እሱ ተራራ ላይ የሚሰቀልበትን ትዕይንት ያነሳል፡፡ ስታንቶች የተጎዱበት አጋጣሚ ብዙ ስለነበረም ፊልሙን ለመጨረስ ዓመታት ወስዷል፡፡

ሰለሞን ከሙሉጌታና ከአስፋው በተለየ አሁን የአክሽን ፊልም የሚሻሻልበት ወቅት እንደሆነ ይናገራል፡፡ መሰል ፊልሞችን የመሥራት ፍላጎትና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ መግባታቸው የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ያምናል፡፡ ብዙ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አይሠሩም ብለው ወደኋላ የሚሉባቸውን ትዕይንቶች፣ ስታንቶች ወደ ፊልሙ ሲገቡ የማዘጋጀት ድፍረቱ አላቸው፣ አክሽን ፊልሞች በጥሩ ሁኔታ ከተሠሩ እንደሌላው ፊልም ተመልካች እንደሚያገኙም ይናገራል፡፡

ስታንት ሽመልስ ጌታቸው በበኩሉ፣ አክሽን ፊልሞች ማራኪ ታሪክ ካላቸው ተመልካች እንደሚያገኙ ይገልጻል፡፡ ሽመልስ ከልጅነቱ አንስቶ አክሮባትና ሰርከስ በመሥራት ያካበተው ችሎታ ስታንት መሆንን ቀላል አደረገለት፡፡ የመጀመሪያ ሥራው ‹‹አላዳንኩሽም›› ሲሆን፣ ‹‹ከነአን››፣ ‹‹ኦፕሬሽን አጋአዚ›› እና ሌሎችም ፊልሞቹ ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ የወጣው ‹‹የመሀን ምጥ›› ላይ የመኪና ግጭት ትዕይንት አለው፡፡ በሌሎች ፊልሞችም ብዙ ለአደጋ ያጋለጡትን ትዕይንቶች ቢሠራም፣ ‹‹እስካሁን የሚፈትነኝ ሥራ አላገኘሁም፤›› ይላል፡፡ የፊልም ባለሙያዎች ፈታኝ ትዕይንቶችን የሚወጡ ባለሙያዎች እንዳሉ ከግምት አስገብተው ቢጽፉ መልካም ነው ይላል፡፡

ሽመልስ ከተቀሩት የሙያ አጋሮቹ ጋር ሙያው እንደማያዋጣ ይስማሙበታል፡፡ የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ እንኳን ሳያዘጋጁ ስታንት ማሠራት የሚፈልጉ ባለሙያዎች መኖራቸው ለሙያተኞቹ የሚሰጠውን  አነስተኛ ቦታ አመላካች ነው ይላል፡፡ አክሽን ፊልም የሚሠሩ ባለሙያዎችንም ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ታሪካቸው ደካማ የሆኑ ፊልሞች መቅረባቸው፣ ተመልካቾች ሁሌም አክሽን ፊልሞች ተመሳሳይ እንደሆኑ አስቀድሞ በመገመት ከመመልከት እንዲቆጠቡ አስገድዷል፡፡

ስታንቶችን ታሳቢ ያደረጉ ፊልሞች መበራከት እንዳለባቸውና ሙያተኞቹም ለሥራቸው የሚገባቸው ክፍያና ክብር ማግኘት እንደሚገባቸው ሽመልስ ከሌሎቹ ስታንቶች ጋር ይስማማበታል፡፡ ተመልካቾች አክሽን ፊልሞችን  እንደ አንድ አማራጭ የሚወስዱበት ጊዜ እንደሚመጣም ተስፋ ያደርጋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...