Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሆይ!

  የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሆይ!

  ቀን:

  የሽመና ባህልና የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ጉዳይ እንዴት ያቻችሉታል?

    በስንታየሁ ኪዳኔ ከኤስንስ የሥልጠናና የምርምር ማዕከል

  እንደ ዛሬ  በፋብሪካ እየተመረተ አማራጭ ከመገኘቱ በፊት በአገራችን ዋነኛ ወይም ብቸኛ ልብስ ሸማ ነበር፡፡ ሸማ ለኢትዮጵያውያኖች ገመና መሸፈኛ ልብስ ብቻ ሳይሆን የመገበያያ ገንዘብና ለመንግሥታት እንደግብር የሚከፈል ጠቃሚ ባህላዊ እሴት ነበር፡፡  አሁንም ሸማን የዘወትር ልብስ አድርገን ባንጠቀምበትም መጤው አለባበስ ስልችት ሲለን ወይም ደግሞ እንደ አገራችን ወግና ማዕረግ ደምቀን ተውበን እንልበስ ካልን ያለን ዋነኛ ወይም ብቸኛ አማራጭ ያው የሽመና ውጤት ነው፡፡ ይኸ ብቻ ሳይሆን እንደድሮው ገንዘብ አድርገን ግብር ባንከፍለውም ወይም ደግሞ ዕቃን በዕቃ ባንለዋወጥበትም የሸማን ልብስ እንደምልክት ቋንቋ በመጠቀም ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያለንን የግልም ሆነ የጋራ ሀሳብ እንለዋወጥበታለን:: ከዚህ በተጨማሪ የሸማ ልብስ የአገርኛውን ከዓለም አቀፉ ባህል አጣምረን የምንገልጽበት፣ የኢትዮጵያዊነት መለዮአችን፣ ኢትዮጵያን ብለው ለሚመጡ ቱሪስቶች ሁሉ በኩራት ይዘንላቸው የምንቀርበው ገፀ-በረከት፣ ማንኛውንም ሀገረ-ሰብ ሁነትና ዝግጅቶችን የምናደምቅበት፣ አንድ ሙዚቃ ፊልም ስዕልና ሌሎችም ዓይነት የጥበብ ሥራዎችን አገርኛ ይዘት አንዲኖራቸው ለማድረግ የሚረዳ ግብዓት፣ ከኢኮኖሚ አንፃርም ድንበር የለሽ የሙያ ትስስርን መፍጠር የቻለ የምርት ሒደት ያለው የባህል ኢንዱስትሪ ውጤት ነው፡፡ 

  የሽመና ኢንዱስትሪ የሚሰጠው ጥቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም  ‹‹ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ›› እንደሚባለው በየዘመኑ በቁስል ላይ ቁስል የሚጨምር ቀስት ሲወረወርበት እንጂ የፈውስ ሕክምና ሲደረግለት አይታይም፡፡ ለምሳሌ በባለሙያዎች ላይ ይደርስ የነበረው ጥላቻና ውግዘት ከዘርፉ ባለፈ አገሪቱን በአጠቃላይ ኪሳራ ውስጥ እየጨመራት እንደሆነ የተረዱት አፄ ምኒልክ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት በሚል እሳቤ ጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም. አውጀውት የነበረው አዋጅ ‹‹ዝክረ-ነገር›› በተባለው መጽሐፍ ላይ በዚህ መልኩ ተጽፎ ይገኛል፡፡  

  ሠራተኛን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ብረት ቢሠራ ጠይብ፤ ሸማ ቢሠራ ሸማኔ፤ ቢጽፍ ጠንቋይ፤….እያላችሁ በየሥራው ሁሉ ትሰድባላችሁ፡፡ ልጁ፣ ምናምን ሥራ የማያውቀው ሁሉ ብልኁን እየተሳደበ አስቸገረ፡፡ …..ባለሙያ አሳጥታችሁ አገሬን ባዶ ልታደርጉትና ልታጠፉት ነው፡፡ እንግዲህ ግን እንዲህ ብሎ የተሳደበ እኔን የሰደበ ነው፡፡ …አንድ ዓመት ይታሠራል፡፡

  ነገር ግን ሙያተኞች ብዙ እንዳይጓዙ ያደረገ የአጥንት ውስጥ አሩር፣  በጊዜ ሒደት ታክሞ ሙሉ ለሙሉ ሳያገግም በኃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ደግሞ ሌላ የቀስት አሩር ከወደ አውሮፓ ተወረወረ፡፡ እንደሚታወቀው በአፍሪካ እየተስፋፋ የመጣው ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ምርቶችን የመጠቀም አባዜ የአገር ውስጥ ምርትን በተለይም ደግሞ የሽመና ኢንዱስትሪውን ከሚገባው በላይ ከገበያ ውጪ አድርጎት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እነገብረ ሕይወት ባይከዳኝን የመሰሉ የአገራችን ቀደምት የኢኮኖሚ ሊቆች እንዲሁም ሜሲንግ፣ ካርትሴን፣ ቃሲርና ሌሎችም የምዕራቡ ዓለም የባህል ተመራማሪዎች ዘርፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደብዛው ይጠፋል እያሉ አሟርተውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ሸማ ሠሪው በነፃ የቤተሰብ ጉልበት እየተደጎመና ያለችውን ትንሽ የገበያ ምንጭ እያንጫለቀ በሞትና በሕይወት መካከል ይገኝ የነበረውን የሽመና ሙያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እያስታመመ በሕይወት አቆይቷል፡፡

  አሁን ደግሞ የሸማ ገበያው ደርቶ ከምንጭነት ወደ ባህርነት እየተንቦረቀቀ ባለበት ወቅት ‹‹ልጁ ሲገኝ ማዘያው አይገኝ›› እንደሚባለው ተተኪ የሸማ ሠሪዎች እጥረትን የተላበሰ ሌላ የሞት ጥላ በሸማ ሥራ ኢንዱስትሪው ላይ እያንዣበበበት ይገኛል፡፡ ይህ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ለማረጋገጥ በሸማ ሠሪዎች መንደር የግማሽ ቀን ቅኝትና ቃለ-መጠይቅ ማድረግ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የተተኪ ባለሙያ እጥረት የብዙ ዘመናት ግድፈቶች ጥርቅም ውጤት ቢሆንም ለአለፉት አሠርት ዓመታት በዘርፉ የሕፃናት ተሳትፎ እንዳይኖር ለማድረግ እየተደረገ ያለው ዘመቻ  ትልቁ የችግር መንስኤ እንደሆነ አምነን መቀበል ያለብን እውነታ ነው፡፡

  እንደሚታወቀው የሸማ ሥራ ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የሚካሄድበት ዘርፍ ነው በሚል ድምዳሜ ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ዜጋ በሸማ የማምረት ሒደት ውስጥ እንዳይሳተፍና በማምረቻ ቦታ ፈጽሞ ድርሽ እንዳይል በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ላለፉት አሠርት ዓመታት የሸማ ሥራ ልክ እንደቢራ የዕድሜ ገደብ ተበጅቶለት  ‹‹ለትምህርትህ እንቅፋት ነው!›› ሐራም ነው በሚል አንድምታ ‹‹የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ ይቁም!›› ለሚሉና ሌሎችም የሕፃናት መብት መጣስን ለሚቃወሙ የከተማችን የመንገድ ዳር ማስታወቂያዎች ሁሉ ማድመቂያ ተድርጎ ሲወሰድ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  በቅርቡ  ማለትም ከነሐሴ 26 እሰከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአምስት ቀን በኦሮሚያ የባህል ማዕከል በተዘጋጀው ‹‹አዲስ ገጽታ›› የተባለ የሸማ ሥራ ኤግዚቢሽን ላይ በተደረገ የፓናል ውይይት ከቀረቡት ሦስት የመወያያ ጽሑፎች ውስጥ አንደኛው ‹‹የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን፣ በዋናነትም ልጆች በሸማ ሥራ ላይ አንዳይሳተፉ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚሰብክ መልዕክት ነበረው፡፡

  ክቡር ሚኒስቴር ሆይ! ታዳጊዎች በሽመና የምርት ሒደት ውስጥ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ይህ ሁሉ ዘመቻ ከመካሄድ በፊት የሚከተሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች  በአግባቡ ተፈትሸዋል ብለው ያምናሉ?

  1. ከነሐሴ 26 እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአምስት ቀን በኦሮሚያ የባህል ማዕከል በተዘጋጀው ‹‹አዲስ ገጽታ›› የተባለ የሸማ ሥራ ኤግዚቢሽን ላይ የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ የሸማ ሥራ የባህል ቅብብሎሽ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን    ሙያውን ለነገው አገር ተረካቢ ተደራሽ እንዲሆን ተግተን ካልሠራን ቅብብሎሹን  እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል? ወይስ ቅብብሎሹ አሁን ባለው ትውልድ ያከትማል? 

  2. ባህል በዕድሜ ይገደባል? ባህል በዕድሜ የሚገደብ ከሆነ በሰርከስ፣ በሙዚቃ፣ በትወናና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች ሕፃናት ያለገደብ ክህሎታቸውን አንዲያሳድጉ ጥረት የሚደረገው ለምንድነው? በሸማ  የምርት  ሒደት ውስጥ ምንም ዓይነት የልጆች ተሳትፎ እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጉ በዘርፉ ላይ የነበረውን የረጅም ጊዜ ንቀት አዘል ጥላቻ የበለጠ አጠናክሮ ለቀጣይ ትውልድ ማውረስ አይሆንብንም ወይ?

  3. በሽመናም ሆነ በሌሎች ዕደ ጥበብ  ዘርፎች ዕውቀት በአጥጋቢ ሁኔታ የሚተላለፈው በአጭር ጊዜ የትምህርት ቤት ቆይታ ሳይሆን ከወላጅ ወደ ልጅ ለረጅም ጊዜ አብሮ በመሥራት ሒደት ውስጥ አንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን እውነታ አይደለም አሁን በሥራ ላይ ያሉ ሸማ ሠሪዎች ይቅርና የሽመና ትምህርት በመስጠት ላይ ያሉ ዘመን አመጣሽ ድርጅቶችም ቢሆን የማይክዱት ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዋነኛ  የዕውቀት ማስተላለፊያ ድልድይ ‹‹በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ›› ስም በኃይል ከተሰበረና ልጆች በልምድና በክህሎት ተኮትኩተው ካላደጉ የተተኪ ሸማ ሠሪዎች የዕውቀት ምንጭ ከወዴት ሊሆን ነው?

  4. ዘመን አመጣሹን ሳይሆን ‹‹ለቀማ›› የሚባለውን እውነተኛውን የአገራችንን የሽመና ሙያ ጠንቅቆ ለማወቅ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ለጋነትንም እንደሚጠይቅ ጥናታዊ መረጃ አላችሁ? ለምሳሌ አሁን ያሉት ‹‹ጥበብ ሸማ›› ሠሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል ሙያውን የጀመሩት በለጋነት ዕድሜአቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዕድሜአቸው ገፍቶ፣ እጃቸው ጎልድፎ፣ ወገባቸው ደርቆ፣ ነገር ግን ሙያውን ለማወቅ ትልቅ ፍላጎት ሰንቀው የገቡ ብዙ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የዲግሪ ተመራቂዎች እንዲሁም ሌሎች ወገኖች ሙያውን ለማወቅ ብዙ ጥረው ግረው ሳይሳካለቸው መቅረቱን የሚያትቱ ብዙ ታሪኮችን ከወደ ሽሮ ሜዳ ማግኘት ይቻላል፡፡

  5. የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ሁላችንም ልንቃወመው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የሥራ ሰዓቱን የመገደብ ችግር ከሌለ በስተቀር የሽመና ሥራ በተፈጥሮው የጉልበት ሥራ ሳይሆን ልክ እንደ ኳስ፣ ሰርከስና ዳንኪራ ክህሎት የተሞላበት የሰውነት አንቅስቃሴን ከፈጠራ ጋር የሚጠይቅ የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ ምናልባት የሽመና ሥራ ሕፃናት በቀለም ትምህርታቸው ብዙ እንዳይጓዙ ማነቆ ይሆናል ከተባለ፣ የምርጫ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከእነዚህ ከጠቀስኳቸው ሙያዎች ውስጥ የትኛውንም ቢሆን   የቀለም ትምህርት ላይ ጫና ሳይፈጥሩ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ ሁሉም በቀለም ትምህርት ላይ ጫና እንደሚፈጥሩ ለመረዳት ስንት በዲግሪ የተመረቁ ፕሮፌሽናል ኳስ ተጨዋቾች አሉን? ስንት በዲግሪ የተመረቁ ታዋቂ ዳንኪረኞች አሉን? ስንት በዲግሪ የተመረቁ አትሌቶች አሉን? ስንት በዲግሪ የተመረቁ ሞዴልና ፋሽን ዲዛይነሮች አሉን? ብሎ መጠየቁ በቂ ነው፡፡ ደግሞስ መንግሥት መሠረታዊ የቀለም ትምህርት ለሁሉም ዜጋ ለማዳረስ እንጂ ሁሉንም ዜጋ በዲግሪ ለማስመረቅ ዕቅድ አለው? ቢታቀድስ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ልጆች የሽመናን ሙያ ከቀለም ትምህርታቸው ጋር አመጣጥነው እንዴት ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚችሉ ማስተማሩና ዘመቻ ማካሄድ ሲቻል፣ የሽመና ሙያ ‹‹ለትምህርትህ እንቅፋት ነው!›› ድርሽ እንዳትል ብሎ ማወጁ ለምን አስፈለገ?

  በመጨረሻም የሕፃናት በሸማ የምርት ሒደት ውስጥ መሳተፍ በኢትዮጵያ ብቻ የሚታይ ክስተት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በሽመና ሙያ አስተዳደር የተሻለ አፈጻጸም አላቸው የሚባሉት ሁለት አገሮች ጋናና ህንድ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ችግር መፍትሔ የሰጡት ሕፃናት የማካካሻ የቀለም ትምህርት ጊዜ እንዲኖራቸው በማድረግ፣  በምርት ሒደት ውስጥ የሚሳተፉበትን ሰዓት በማሳጠር፣ በሸማ ምርት ፈጽሞ አይድረሱ ከተባለ ደግሞ የሽመና ሀሁ የሚያስተምሩ የኔታዎችን ወይም ጡረታ የወጡ ሸማ ሠሪዎችን (Master Weaver) በየሠፈሩ በማጠናከርና ሌሎች ዕርምጃዎችን በመወሰድ እንጂ ልጆች በእጅ ሙያ ተኮትኩተው የማደግ መብታቸውን ሙሉ ለሙሉ በመንጠቅ አልነበረም፡፡ እነዚህና መሰል ተግዳሮቶች ከወዲሁ መፍትሔ ካላገኙ   ወደፊት የሽመና ባለሙያ አያስፈልገንም፣ ቢያስፈልገንም በሕፃናት ላይ ትኩረት ሰጥተው ከሚሠሩት አገሮች ከጋናና ህንድ በውድ ዋጋ ባለሙያ እናስመጣለን! ብሎ ከማወጅ አይተናነስም፡፡

  ስለዚህ በጥናት የተደገፈና ሁሉንም ያማክል ዳኝነት ከሚኒስቴሩ መሰጠት አለበት የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ይህ ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፡፡ አቶ ስንታየሁ ኪዳኔ የኤስንስ የሥልጠናና የምርምር ማዕከል ባልደረባ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...