Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በጓጉንቸር የተቆለፉ ልቦች

ሰላም! ሰላም! ዋንጫ ባያስበላም አለ ገጣሚው። ለነገሩ ምን ዋንጫ አለ? የሚበላ ማለቴ ነው። ቢኖርም ቅሉ የሚያስበላ ሲኖር እኮ ነው። አንጀት ጠብ የሚል ነገር እስክንበላ አደራ አባባሌን ጠበቅ እያደረጋችሁ አንብቡልኝ። ማጥበቅና ማላላት ያለቦታቸው እየገቡ የምንስተው በዝቷል። እውነት እውነት እላችኋለሁ! ኦ፣ ለካ እውነትም የበላንበትን ወጭት መስበር እንደለመድነው ሰባብረን አቀጭጨናታል። ‘እውነት ምንድነው?’ ስትሉኝ ሰማሁ? ነግሬያለሁ! መፈልፈል (ይህም ይጥበቅ) እንጂ መፈላሰፍ ክልክል ነው! ድሮስ ተከላካይ ከመከልከል ሌላ ምን ያውቃል? በሉኛ!

ግን እንግዲያው በእውነት ካልማልን በምን እየማልን ልንገፋው ነው? ካልማልን ደግሞ መተማመን አልፈጠረብንም። ካልተጠራጠርን ደግሞ የሚረግጠን ብዛቱ። ‹‹በመረገጥ ብዛት ሶል እናስንቃለን፤›› ሲለኝ የነበረው ማን ነበር? ‹‹ወይ ዕድሌ! ደግሞ ብዬ ብዬ በነበር ልብሰልሰል?›› አሉ ባሻዬ። ‘እንዳላበጠረች ማንገዋለል አቃታት’ ማለት ይኼኔ ነው። ቀን ሲጥል አትሉም? አይ የእኔ ነገር። መቼም አንድ ነገር ከያዝኩ አለቅም። ባለፍኩ ባገደምኩበት ሥፍራ ሁሉ ይህችን ተረት ደጋግሞ መተረት ሙያ አድርጌያት ነበር። ዕድሜ ለአዲሱ ደንግጦ ለሚያስደነግጠው ትውልድ አንድ ትንሽ ልጅ ነው ያስተወኝ። ‹‹ማንገዋለል ምንድነው?›› አለኝ። በቀላሉ እንዲገባው ሥዕላዊ ምሳሌ መስጠቴ ነው በእኔ ቤት።

‹‹ለምሳሌ ጤፍ አለ። ከእህሉ ጋር የተደባለው ቆሻሻ አብሮ እንዳይቦካና ተጋግሮ እንዳይበላ በሰፌድ እየተሰፈረ እ? .  .  . ገብቶሃል? . . . እንዲህ አድርገህ ስታዞረው  . . .›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹ሰፌድ ምንድነው?›› ብሎ አቋረጠኝ። ደግሞ ለማቋረጥ! እንኳን ልጅዬው አባቱስ አያቱንስ ማን አህሏቸው? አይደል እንዴ? ‘ኧረ እንኳንም ጤፍ ምንድነው?’ አላለኝ እያልኩ ከልቤ አመሰገንኩት። ልቤ መምታት ስለመቀጠሉ ግን ከምኔ ማመስገን እንዳለብኝ አላወቅኩም። ጥቂት አውጠነጠንኩ። ስለሰፌድ ማብራራት ብጀምር ስንደዶና አክርማ ተራቸውን መጠየቃቸው የማይቀር መሆኑ ገባኝ። እውነትም ይኼ ትውልድ ያለ ሥዕላዊ መግለጫዎች መማር የከበደው ነው በሚለው ጥርጥር የለኝም። ይልቅ የተጠራጠርኩት ሸምግሎም ‘ዴሞክራሲ ምንድነው?’ ማለት አለማለቱን ነበር። ‘ማ?’  . . .  አዲሱ ትውልድ ነዋ! አሮጌውማ አሮጌ ነው!

የልብ የልባችንን እንጫወት ካልን ዘንድ (ጌቶች እንዳይቆጡ ጨዋታው ሁሉ የገና መሆን አለበት እንዴ? እህ . . .  ምን እኔን ታዩኛላችሁ?) የተፈታውን እያሰርን ያሰርነውን እየፈታን መጫወት ደስ ይላል። ማን ነው እሱ ‹‹ሲታሰር ወደኔ ሲፈታ ወደሱ›› የሚል ሙዚቃ የተጫወተው? መመላለሱን አላውቅበት ስንል እኮ ነው በልዩነት ከማመን አልፈን ካልተጨፈላለቅን እያልን የምንሸራተተው። ሸርተቴ የሚጫወት ብላቴና ማየት እንዴት እንደናፈቀኝ እግረ መንገዴን ስነግራችሁ ቅር እንዳይላችሁ። ልጅነቴን ስናፍቅ ማን አለኝ ያለ እናንተ? የምናነጋግረው ሰው መስሎኝ ያጣነው። የሕዝብ ቁጥር መጨመር የሚያሳስበኝ እኮ ለዚህ ነው። በተባዛን ቁጥር የሚናገረን እንጂ የሚያነጋግረን ሰው ይመነምናል። በጥናት ያልተደገፈ ወሬ አታውራን ትሉኝ ይሆናል። ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ ወሬ በጥናት መደገፍ የተጀመረው? እንኳን ወሬ እኛስ ብንሆን በጭፍን እንደግፋለን በሥልት እንገፋለን እንጂ ተደግፈን እናውቃለን እንዴ? የተፈታውን ማሰር፣ የታሰረውን መፍታት ብዬ የጠበቀውን ማጥበቅ የላላውን ማላላት ላይ ስገባ አሁን ገና ታወቀኝ እናንተ። የአፈጻጸም ችግር በሚለው ልታለፍ? ምነው? ንስሐም እኮ የግምገማ አካል ነው!

እናላችሁ ጠላልፎ ያሰረን ነገር መዓት ነው። ሰንሰለት ይሁን ገመድ እዚያው እናንተ አጣርታችሁ ድረሱበት። እኔ የማውቀው ‘ሥውር’ መሆኑን ብቻ ነው። መቼ ዕለት ከባሻዬ ልጅ ጋር ስለዚሁ ሥውር ትብታብና እስር ስናወራ (ትብታብ ማለት ምን ማለት ነው?’ እንዳትሉኝና ከደላላነት ወደ መዝገበ ቃላትነት እንዳልቀየር) ምሳሌዋን ያስተዋለበት መጽሐፍ ርዕስ ጠፋውና ለማስታወስ እየሞከረ የሚከተለውን አጫወተኝ። ኑሮ ራሱን እያስረሳው ርዕስ ጠፋህ ተብሎ መውቀስ ግፍ ነውና ተውት። እንዲያው እኮ! እና ምን አለኝ፣ ‹‹በአንድ መንደር ውስጥ በልብስ አጣቢነት የሚተዳደር ሰው ነበር። የአካባቢውን ነዋሪዎች የቆሸሸ ልብስ ይቀበልና በአህዮቹ ጭኖ ወንዝ ይወርዳል። አጥቦ አድርቆ ሲያበቃ ለየባለቤቶቹ ይመልሳል። ‘ላውንደሪ በስሎው ሞሽን’ በለው፤›› ሲል ሳቅን።

ቀጠለ፣ ‹‹እናም አንድ ቀን ሰው ተሰባሪ ነውና በጠና ታሞ ከአልጋው መነሳት አቃተው። ልጁን ጠርቶ ‘በል ዛሬ እኔን ተክተህ ያልታጠቡ ልብሶች አሉና አህዮቹን ጭነህ ወንዝ ውረድ’ አለው። ልጁም እንደታዘዘው አህዮቹን ጭኖ ቅደሙ ሲላቸው ሊነቃነቁ ነው? እግራቸው በችንካር እንደተቸነከረ ከረገጡበት አልነቅል አሉት። ቢታገል አልሆነም። አባቱ ዘንድ ሄደና የሆነውን ሲያስረዳው ‘ውይ! ረስቼው ሳልነግርህ። እግራቸውን አስሬዋለሁ’ አለው። ልጅዬው ግራ ተጋብቶ ‘ምንም ገመድ የሚባል አላየሁም’ ሲለው፣ ‘ይኼውልህ ማታ ማታ ወደ ማደሪያቸው አስገብቼ እግሮቻቸውን ተራ በተራ በእጄ ዳሰስ ዳሰስ አደርገዋለሁ። እንደታሰሩ ያስባሉ። ጠዋትም እንደዚያው ሳደርግ እንደፈታሁዋቸው ያምናሉ። እንዲያ አሠልጥኛቸዋለሁና አሁን ሄደህ እግሮቻቸውን ስትዳስሰው እስራታቸውን እንደተፈታላቸው ያምናሉ’ አለው። ልጁም አባቱ እንዳለው አደረገና ወደ አጠባው ሄደ። በላ ይፍቱኝ በል፤›› ብሎ ቀላለደ።

ወዲያው ግን የመጽሐፉን አርዕስት ለማስታወስ ትግሉን ሲቀጥል ሳየው ትከሻውን ቸብ እያደረግኩ፣ ‹‹በቃ እርሳው ፈትቼሃለሁ!›› ብዬ አሾፍኩበት። የምር ግን ከምሳሌው ብዙ ተማርኩ። ብዙ ነገር አያያዝኩበት። ባልተያዘና ባልተጨበጠ ነገር እውነት መስለውና ገሃድ መስለው የተበተቡንን ገመዶች በጣጥሼ መጣል አሰኘኝ። ግዳይ መጣል እንደለመደ አዳኝ ሸልል ሸልል አለኝ። ምን ዋጋ አለው ገመዱ አሁንም አልታየኝ እንዳለ ነው። እስኪ ካያችሁት ጥሩኝና ተባብረን እንበጣጥሰው። እስከዚያው ‘መሃረቤን ያያችሁን’፣ ‘እስራቴን ያያችሁ’ በሚለው ተክተው ልጆቻችን ሲጫወቱ እንዲያድጉ መረባረብ አለብን። እኛም መሃረብ እነሱም መሃረብ ስንፈልግ ከኖርንማ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ መሠለፍ ብቻውን ምን ዋጋ አለው? . . .  እ?  . . . ፍታት ላይ ናችሁ መሰል ዝም አላችሁ?

በቀደም ዕለት ምን እንደሆነ ላጫውታችሁ። ሁለት ዶዘር ሳላስበው አሻሽጨ ኪሴ አብጧል። መቼም ሲያመጣው አንዴ ነው። ሲሸኘውም ያው ነው ለነገሩ። እና ምን የመሰለ ባለሦስት ፎቅ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ቻይናዎች እንከራየዋለን ብለውኝ ውል እስኪፈራረሙልኝ እንቆራጠጣለሁ። ቤቱ 80 ሺሕ ብር መከራየቱ ነው። ‹‹እነዚህ ቻይናዎች ግን አልምተውልንም ተከራይተውንም እንዴት ነው የሚሆነው?›› የሚሉት ባሻዬ አዕምሮዬ ውስጥ ዥዋዥዌ ይጫወታሉ። የቤት ንብረቱ የኪራይ ዋጋ መናር ባሻዬ ቢገርማቸው አይደንቅም። በእሳቸው ዕድሜ እንኳን ገንዘብ ቁጥር መቼ ሺሕ ቤት ገብቶ ዓይተው ያውቃሉ ብዬ ነዋ። ይልቅ ለእኛ ለእኛ (የግርምት ጭቃ አቡክቶ የለሰነን መሆናችንን መቼም መጠርጠር ያለብን አይመስለኝም) ይድነቀን። በመቶ ብር መክሰስ መብላት ስላቃተን ንብረት የሌለን ሰውነታችንን ማከራየት መጀመራችን ብቻ ሊገርመን ሳይገባ ታዲያ።

አዎ! አንድ ወዳጄ አዘውትሮ የሚቀልዳት ቀልድ አለች። ‹‹አየር መንገዳችን መቼ ይሆን በመቶ ብር በረራ የሚጀምረው?›› እያለ ያፌዛል። እንዲህ የባጥ የቆጡን ስቧጥጥ ድንገት የመንደሩ ውሪዎች የቡድን ጨዋታ ቀልቤን ሳበው። በሦስት ተከፍለው ድንጋይ መወራወር ነው የሚጫወቱት። አላፊ አግዳሚው ይራገማል። እኔም የበኩሌን ከመቆጣቴ በፊት ሴራቸውን ማጥናት ጀመርኩ። አንደኛው ምድብ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ምድብ ነው። ሁለተኛው የፑቲን ሩሲያ። ሦስተኛው ያው ሰላም የራቃት እስራኤል። ስስቱን ምድብ እስካጠና ሦስት ባልጩት ድንጋይ በጆሮ ግንዴ በኩል አልፏል። ‘የጎዳና ላይ ነውጥ አነሳሾች’ ብዬ ልጠቁማቸው አስቤ ሕፃናት መሆናቸው ትዝ ቢለኝ ‹‹አትተውም!›› ስላቸው ‹‹ወልደህ ቅጣ! ምን አገባህ በሰፈራችን?!›› እያሉ ሦስቱ አንድ ሆኑብኝ። ወይ አርማጌዲዮን! ላይ ስንጠብቀው ታች? ጉድ ነው ዘንድሮ!

በሉ እንሰነባበት። ቻይናዎቹ ከቤቱ ባለቤቶች ጋር ውል እንደቋጠሩልኝ አጣድፌ የድለላዬን ተቀበልኩ። ፈገግታ እንደጀማመረኝ ሲያይ (እንጃ ማን እንደሆነ) የ40/60 ወርኃዊ ክፍያ፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የካርድ፣ ተቃጥሎ ያልቀየርኩት አምፖል፣ የገላ ሳሙና፣ የልብስ ሳሙና፣ ኦሞ፣ አጃክስ፣ ማንጠግቦሽ ሳትገዛልኝ እንዳትመጣ ብላ ያስጠነቀቀችኝ መድኃኒት . . . ምን አለፋችሁ ከአነስተኛና ጥቃቅን እስከ መካከለኛና ከፍተኛ ወጪዎቼን አንጋግቶ አስታወሰኝ። በቆምኩበት አጥወለወለኝ። ከሥጋዬ አልፎ ተርፎ አጥንቴ ሲሸራረፍ ይታወቀኛል። ቀኑ ጭልም ሲልብኝ ራሴን ለማዝናናት ‘የዓይን ብርሃናችን መስመር እንኳንም ከኤልፓ አልተቀጠለ’ ለማለት ሞከርኩ። ሙከራዬ እየከሸፉብን ካለፉ ሙከራዎቻችን ጋር አብሮ ተደመረ፣ ከሸፈ። ውጥረቴን ለማርገብ ወደ ባሻዬ ልጅ ደወልኩና አዘውትረን ወደምንገናኝባት ግሮሰሪያችን አመራሁ። ሳገኘው ነገርኩት። ‹‹ሞክሮኝ የማያውቀውን ዛሬ መሀል አውራ ጎዳና ላይ አዞረኝ፤›› ስለው ደንግጦ፣ ‹‹ደምህን መለካት አለብህ፤›› ብሎ ሰቀዘኝ። ብርጭቆ ማጋጨቱ ወደሌላ ቀን ተዛውሮ እየበረርን መለስተኛ ክሊኒክ ዘው። ስለካ ‹‹‘ኖርማል’ ነው!›› ተባልኩ። ‘ኖርማል’ በአማርኛ ምንድነው? አላልኩም። አማርኛ መስሎኝ ‘ኖርማል?’ የልብ ምቴ ግን አንዴ እንደሚፈጥን አንዴ እንደሚዘገይ ተነገረኝ። ‹‹ደግሞ እሱም ላይ ቆጣሪ ተክዬ 15 በመቶ ላስቆርጥ?›› ስለው የባሻዬ ልጅ ነገር አዙሮ የጅብና የውሻን ተረት አስታወሰኝ።

አያ ጅቦ እሜት አህይትን ስለገበያ ዋጋ መጨመርና መቀነስ ሲጠይቃት ስትነግረው ቆይታ፣ ‹‹ለመሆኑ እኔ እንደምዘለው ትዘያለሽ?›› ይላታል። ‹‹ደግሞ ከአንተ ልነስ?›› ትለዋለች። ወደ አፋፍ ጠጋ ብሎ የአቅሙን ዘለለና፣ ‹‹በይ ነይ እስኪ አንቺም እዚህ ጋ ዘለሽ አሳይኝ፤›› አላት። ‘ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ’ ሆነና ስትዘል የአፋፍ አፈር ከድቷት ትወድቃለች። ጅብ ሆዬ ዘሎ ከተሸነቆረችበት ሰርጥ ገብቶ እየቦተረፈ ሲያጣጥማት ውሻ ጎምዥቶ ሲያስተውለው አየው። ‹‹ና በል እየመተርክ አብላኝ፤›› ይለውና ተማምነው ያጎርሰው ጀመረ። አውቆ ጠብደል ጠብደል ጉርሻ እያጎረሰው አኝኮ እስኪውጥ ፊቱን ዘወር ሲያደርግ ልቡን አንስቶ ዋጥ። ዞር ቢል ልብ የለም። ‹‹የታለ ልቧ?›› ሲለው ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ልብ ቢኖራትማ መቼ እዚህ ታገኛት ነበር?›› አለው ይባላል። አይዟችሁ በተረት አሳብቤ አፌን በዳቦ ለማስላስ አይደለም። ‘የኑሮ ጫና በዛ ብዬ ራሴን አልጥልም፣ የባሰ አለና ልቤን እጠብቃለሁ’ ለማለት ነው። ዳሩ ግን ስንቶቹ ልባቸውን በጓጉንቸር በቆለፉበት ዘመን እንዲህና እንዲያ ካልተባባልን አስቸጋሪ ነው፡፡ በጓጉንቸር የተቆለፉ ልቦች በዝተዋልና፡፡ መልካም ሰንበት!       

   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት