Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርማዲጎን በለዛ መነጽር

  ማዲጎን በለዛ መነጽር

  ቀን:

  ለዛ ፕሮግራም ከሸገር 102.1 ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋር በመተባበር በዓመቱ ውስጥ ታትመው ለሕዝብ የቀረቡትን የሙዚቃ አልበሞችና ነጠላ ዜማዎች በሌላው ዓለም እንደሚደረገው የዓመቱ ምርጥ የተባሉትን ሥራዎችና አርቲስቶችን ሕዝቡ እንዲመርጥ በማድረግ ዕውቅና መስጠት ማወዳደርና መሸለም ከጀመረ እነሆ አምስት ዓመት ሞላው፡፡

  ለዚህ ሥራ መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ሲሆን፣ የለዛ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ብርሃኑ ድጋፌነህ ግን ከፍ ያለ ምስጋናና አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ ብርሃኑ ድጋፌን በአካል አላውቀውም፡፡ ነገር ግን ሸገር ኤፍኤም 102.1 ሥራውን ከጀመረ ከስምንት ዓመታት ወዲህ ለዛና ኮሌጅ ታይም በሚለው ዝግጅቱ፣ በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ ላድማጮቹ የሚያቀርበው የምሳ ሰዓት ሙዚቃ ዝግጅቶቹ የቤተሰቤን ያህል ተላምጀዋለሁ፡፡ ‹‹የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል፤›› እንዲሉ በተረጋጋና በሰከነ መንፈስ ለአድማጮች ከሚያቀርብላቸው መረጃዎች ባሻገር በኮሌጅ ታይም ዝግጅቱ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች (ላዲሶቹም ሆነ ለነባሮች) የሚጠቅምና በባለሙያዎች የተደገፈ የምክር አገልግሎት ስለሚያቀርብ፣ ተማሪዎቹን በመልካም ስብዕና ከመቅረፅ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡

  የተለያዩ ጋዜጠኞችና በልዩልዩ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የአየር ሰዓት በሬዲዮም ይሁን በቴሌቪዥን ሲይዙ ለመጀመርያዎቹ ጥቂት ወራት ጋም ብሎ ከነደደ በኋላ እንደመስቀል ደመራ ክስም ሲል በሚታይበት አኳኋን የብርሃኑ ዝግጅት ግን አንድ ዓይነት ቅርፁን ጠብቆ ሰከን ባለ መልኩ እስከዛሬ መዝለቁ ግለሰቡ ለሙያው ምን ያህል እንደተገዛና ምን ያህል ጽኑ እንደሆነ ያመለክታል፡፡

  ከዚህም አለፍ ብሎ የተሠሩትን የጥበብ ሥራዎች ለማበረታታትና ዕውቅና ለማሰጠት ላለፉት አምስት ዓመታት መማሰኑ ምን ያህል መስዕዋትነት ሊያስከፍለው እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ለአዳራሹ ዝግጅት፣ ለመድረክ ቅንብርና ለሌሎችም ዝግጅቶች ከሚያፈሰው ጉልበት በተጨማሪ አርቲስቶቹን ማሰባሰቡ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆን መገመት አያቅትም፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በ2004 ዓ.ም. በተካሄደው የዕውቅና መስጫ ሽልማት ፕሮግራም ላይ እንደ ቴዲ አፍሮ ዓይነቱ ተሸላሚ አርቲስት በቦታው አለመገኘቱ ነው፡፡ ተሸላሚ በመሆኑ አለመምጣቱ ታወቀ እንጂ ተጠርተው ያልመጡ አርቲስቶች እንደነበሩ መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ብርሃኑ ሰውን ክብር ለመስጠት (አንዳንዴ ክብሩንም ተነጥቆም ቢሆን) ላደረገው ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ታላቅ ክብር ይገባዋል፡፡

  ማዲንጎ አፈወርቅ በአገራችን በድምፃዊነት ከተካተቱት ዘፋኞች አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ ማዲንጎ በካሴትም (ሲዲ) በመድረክ ‹ሲዘፍን ላዳመጠው ሰው፣ የድምፁ አወጣጥ እንደ አንዳንድ ዘፋኞች ሳይለዋወጥ ቅርፁንና ውበቱን እንደጠበቀ መጫወት መቻሉ በልዩ ሁኔታ እንድናስቀምጠው ያደርገናል፡፡ ማዲንጎ በተፈጥሮ የታደለ ጥሩ ድምፃዊ ነው፡፡ የማዲንጎ ዘፈኖችን ሳዳምጥ በልዩ ሐሴትና ተመስጦ ነው፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ እንኳ ያቀረበልን የአልበም ገፀ በረከት ምን ዓይነት ድንቅ ነው? ማዲንጎ ከዚህ በፊት ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ቃለ መጠይቅ ከታች ተነስቶ እዚህ መድረሱን ሳይደብቅ ገልጿል፡፡ ለእሱ ያለኝ ክብርና አድናቆት ልዩ ነው፡፡ ልዩ አድናቆቴ ይድረሰው፡፡

  በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የለዛና የሸገር 102.1 ሬዲዮ የዓመቱ ምርጥ ሥራዎች የሽልማት ሥነ ሥርዓትን ተከትሎ ሰይፉ ፋንታሁን በሚያዘጋጀውና ቅዳሜ ምሽት መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀን በቀረበው የታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ላይ ስላቀረበው ቅሬታ ግን ውስጤ ያልተመቸውን ሐሳብ በማንፀባረቁ ሳልታዘበው አልቀረሁም፡፡ በመሠረቱ እንደዚህ ዓይነቱ የሽልማት ውድድሮች የሚካሄዱት አንዱን ላይ ሰቅሎ ሌላውን ድምጥማጡን ለማጥፋት ሳይሆን፣ ሰላማዊና አዝናኝ በሆነ መልኩ የተሰጠውን በፀጋ በመቀበል የእርስ በርስ ዕውቅናና መከባበርን ለማምጣት ነው፡፡ በማንኛውም ዓይነት የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በዕጩነት ቀረበ ማለት አሸነፈ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ለዕጩነት መቅረቡ ራሱ የሚፈጥረው ልዩ ስሜት ይኖረዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡

  አንድ ሰው የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት ያለበት እሸለማሁ ብሎ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ቢሸለሙም ለእነሱ ክብርና ዕውቅና እሰጣለሁ ብሎ መሆን አለበት፡፡ ብርሃኑ በሥነ ሥርዓት ላይ አርቲስቶቹ እንዲገኙ ለማድረግ ምን ያህል እንደለፋ ለማሳየት ማዲንጎ በሰይፉ ፕሮግራም ላይ የሰጠውን ቃል ማቅረቡ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ በእሱ አገላለጽ ከሆነ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሊገኝ የቻለው ትሸለማህ ስለተባለ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህ ማለት አትሸለምም ቢባል ኑሮ በሥነ ሥርዓቱ ላይ አይገኝም ነበር ማለት ነው፡፡

  እኔ እንደሚመስለኝ በአገራችን ያነጋገር ዘይቤ አንዱን ሰው ለውድድር ስታዘጋጀው ‹‹አልተቻልክም››፣ ‹‹እየመራህ ነው›› ማለት ተወዳዳሪውን አጉል ተስፋ መስጠት ሳይሆን ካነጋገር አንፃር የምንጠቀምበት ዘይቤ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ማዲንጎ እንደገለጸው (ብርሃኑም እንደዛ ብሎ ከሆነ) ማዲንጎ ብርሃኑ እየመራህ ነው አልተቻልክም ብሎ ስላለኝ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኘሁ እንጂ አልገኝም ነበር ብሎ ማለቱ ትክክለኛ አስተሳሰብ አይመስለኝም፡፡ መሸለም ብቻ ሳይሆን ቆሞ አጨብጭቦ ሌላውን ማሸለምም እኮ ክብር ነው፡፡ ከዚህ አልፎ በአዘጋጁ ላይ የሰነዘረው ትችት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ብርሃኑ እንደዛ ቢል እንኳ ድረ ገጹን የሚቆጣጠረው ሰው በሰይፉ ፕሮግራም ላይ በግልጽ ብርሃኑ እስከመጨረሻው ውድድር ሰዓት ማወቅ እንደማይችል ቃሉን ሲሰጥ ሰምተናል፡፡ ግምጥምና ዜማ ተቀብሎ ማንጎራጎር ክብር የሚያሰጥ እንደሆነ ሁሉ ለሰው ክብር ለማሰጠት መሮጥና ማመስገን ደግሞ የበለጠና ልዩ ክብር የሚያሰጥ ይመስለኛል፡፡ በሥራ ሒደት ላይ ጀማሪ እንደመሆኑ አንዳንድ እንከኖችን ቢስተዋሉ እንኳ ያንን ለማስተካከል ከሚደክመው ሰው ጎን መገኘት እንጂ ያንን ሁሉ የተደከመበትን ነገር በዜሮ ማባዛቱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡

  ማዲንጎ ማሸነፉን ብቻ ይዞ ለመግባት ማሰቡ ስህተት ሆኖ ሳለ፣ የሽልማት ሒደቱን በሚዲያ ማጠልሸቱ በሙያ አጋሮቹም ዘንድ ትዝብት ላይ የሚጥለው ይመስለኛል፡፡ ዘመናዊው ዓለም የሚጠይቀው በማንኛውም ዓይነት ፉክክር ውጤትን በፀጋ መቀበል፣ ሕዝብ የሰጠውን ውሳኔ ለዚያውም በድረ ገጹ የተሰጠን ድምፅ አልቀበልም ብሎ እምቧ ከረዩ ማለት ያለመሠልጠን ምልክት ይመስለኛል፡፡ በዚህም መሠረት ያ ለዓመታት አክብሬ ሳዳምጠው ለነበረው ያ በአዲስ ዓመት ገንዘቤን ሆጭ አድርጌ፣ በግዮን ሆቴል ላካሄደው የሙዚቃ ድግስ የሰጠሁት ያጨበጨብኩለት ማዲንጎ አፈወርቅ ቦታና ክብር ተናጋብኝ፡፡

  እውነት ለመናገር እኔ ይህን አስተያየት ስጽፍ ብርሃኑ ድጋፌነህንም ሆነ ማዲንጎ አፈወርቅን ከሥራቸው ውጭ በአካል አላውቃቸውም፡፡

  (ዳንኤል አያሌው፣ ከአዲስ አበባ)

   

   

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img