ለሕግ ሙያና ለሕግ ሥርዓታችን የሚጨነቁ አንጋፋ ጠበቃ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የተወለደበትን ቀን በማስታወስ 50ኛ ዓመት እንደሞላው ነገሩኝ፡፡ ሕጉ ከአያቴ እስከ ልጄ ዘመን የቆየና የሚቆይ፣ ለሕግ ባለሙያዎችና ለፍርድ ቤት ቀዳሚ መሪ (መጽሐፍ ቅዱስ) እንደመሆኑ ዕለቱ ሊዘከር እንደሚገባ ተረዳሁኝ፡፡ ሕግ በደምሳሳው ከዓላማው አንፃር በሁለት ሊከፈል የሚችል ሲሆን፣ መብትና ግዴታን የሚዘረዝርና የሚያሳውቀው የሥረ ነገር ሕግ ወይም መሠረታዊ ሕግ (Substantive law)፣ ሁለተኛው ደግሞ መብትና ግዴታ በፍርድ ቤት የሚፈጸምበትን መንገድ የሚያበጅ፤ የሚያሳየው ደግሞ የሥነ ሥርዓት ሕግ በመባል ይታወቃል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕግ ዋና ዓላማው ሰዎች መብትና ግዴታቸውን ሲፈጽሙ የአፈጻጸሙን መንገድ፣ ሁኔታና ጊዜ ማመላከት ነው፡፡ የሥረ ነገር ሕግ የሰው ልጆችን መብቶችና ግዴታዎች የሚደነግግ ሰፊው የሕግ ክፍል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መስሎ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶች፣ ጥቅሞችና ግዴታዎች ወደ ተግባር ካልተተረጐሙ ወይም ተፈጻሚ እንዲሆኑ ካልተደረገ የመኖራቸው ጉዳይ ትርጉም የለሽ ይሆናል ማለት ነው፡፡ መብቶቹ ወደ ተግባር እንዲተረጐሙ የማድረግ ድርሻው የሥነ ሥርዓት ሕግ እንደመሆኑ መጠን የሥነ ሥርዓት ሕግ ከመደበኛው ሕግ ባላነሰ ጠቃሚ ነው፡፡ ለሕግ ሙያ ባዕድ ለሆኑ ሰዎች ነጥቡን በምሳሌ በአጭሩ ለማብራራት እንሞክር፡፡ ውል እንዴት ይመሠረታል? የተዋዋይ ወገኖች መብትና ግዴታ ምንድነው? የውል ግዴታ የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎችና መፍትሔዎቻቸው ምን ይመስላል? የሚሉትን ነጥቦች የሚዳስስልን የውል ሕግ ሲሆን፣ የሥነ ነገር ሕግ (መሠረታዊ ሕግ) አካል ነው፡፡ እንደ ውል ሕግ ሁሉ የቤተሰብ ሕግ፣ የውርስ ሕግ፣ የሽያጭ ሕግ፣ የንግድ ሕግ ወዘተ. በዚህ ምድብ ይወድቃሉ፡፡ ውል ተመሥርቶ አንዱ ተዋዋይ ወገን የውል ግዴታውን ባልተወጣ ጊዜ መብቱ የተነካበት ወገን በፍርድ ቤት መፍትሔ እንዴት ያገኛል (ክስ እንዴት ይጽፋል? የት ፍርድ ቤት መዝገብ ይከፍታል? ምን ዓይነት ማስረጃ መቼ ያቀርባል? በሙግት ሒደት ምን ይጠበቅበታል? ፍርድ ቤቶችስ ምን ሥርዓት ይፈጽማሉ?) የሚለውን መሠረታዊው ሕግ መልስ ስለማይሰጥ ጉዳዮቹ በሥነ ሥርዓት ሕግ የሚሸፈኑ ይሆናል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕግ ሊሆን የሚችል ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ ምልከታ የምናደርግበትና 50 ዓመቱን የሚንዘክርለት የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግን ይሆናል፡፡ አንድ ሰው በመሠረታዊው ሕግ ያለውን መብት ቢያውቅ በፍርድ ቤት መብቱን እንዴት ሊያስፈጽም እንደሚችል ግንዛቤ ከሌለው ዕውቀቱ ምን ይረባዋል? ከዚህ አንፃር የሥነ ሥርዓት ሕግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችንን ውልደትና ዕድገት፣ አወቃቀርና ይዘት በዚህ ጽሑፍ የምንመለከት ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንት በጽሑፉ ቀጣይ ክፍል ስለ ዓላማውና ጠቀሜታው፣ ስላልሸፈናቸውና ዘመን ስላለፈባቸው፣ ስለማይፈጸሙትና ለውጥ ስለሚፈልጉ ጉዳዮች ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
የሕጉ ውልደትና ዕድገት
አሁን የምንጠቀምበት የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ የወጣው መስከረም 28 ቀን 1958 ዓ.ም. ነው፡፡ የተወሰኑ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ከማለፋቸው ውጭ የሕጉ ዕድሜ 50 ዓመት ሞልቷል፡፡ ሕጉ በአምሳ ዓመቱም ዋንኛ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ምንጭ ነው፡፡ ሕጉ የወጣው በድንጋጌ ቁጥር 52/1958 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ በፓርላማው ፀድቋል፡፡ ሕጉ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከወጡት በመጽሐፍ መላክ ከተሰደሩት (Codified law) አንዱ ነው፡፡ ንጉሡ በጊዜው በኅብረተሰቡ ያሉ ሕጋዊ ግንኙነቶች ዋስትና እንዲያገኙና ከኮመን ሎው (ልማዳዊ ሕግ/ዳኛ ሠራሽ ሕግ) በተሻለ ተጨባጭና በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል በመሆኑ በኮድ መልክ መዘጋጀቱን መርጠዋል፡፡ ሕግጋቱ በአብዛኛው ከሌሎች አገሮች የተቀዱ ሲሆን፣ በጊዜው ተፈጻሚ የነበሩትን ልማዳዊና ባህላዊ ሕግጋት ለማካተት ጥረት ቢደረግም ቀድሞ ሕግጋቱን የማዘጋጀት ሥራ ባለመሠራቱ፣ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም ሥልጠናቸው የፈረንጆቹን ያህል ባለመሆኑ የማካተት ሥራው አመርቂ አልነበረም፡፡ ሕግጋቱ ሲቀረፁ ንጉሡ በሰጡት መመርያ መሠረት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የራስ አስተዳደር በምንም መልኩ እንዳይሸረሸር ከተለያዩ አገሮች ሕግጋት እንዲቀረፁና የአንድ አገር ሕግ ብቻ እንዳይቀዳ አዘዋል፡፡ አስተሳሰቡ የአንድ አገር ሞኖፖሊ ካለ ያው ቅኝ ግዛት ነው በሚል አለያም የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም በሚል መነሻ ይመስላል፡፡ ከተለያዩ አገሮች መውጣቱም የሕግ ሥርዓቱን ዘመናዊ ያደርጋል ተብሎ በጊዜው ታምኗል፡፡
የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓቱም ሲቀረፅ በተመሳሳይ መነሻ ሐሳብ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አለን ሴድለር በዝርዝር እንዳስቀመጡት ከታሪክ አንፃር የሥነ ሥርዓት ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ አነስተኛ የሆነ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር፡፡ በአውሮፓ አኅጉር የተደረገውን የለውጥ ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ የሕጓን ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ ዝግጅት በጀመረችበት ጊዜ አንድም የሥነ ሥርዓት ሕግ አልነበረም፡፡ ፕሮፌሰር አለን ሴድለር ለዘመናት በልማድ ያለጽሑፍ ሥራ ላይ ሲውሉ የነበሩት ልማዶች (በላልበል ወዘተ.) ሕግጋት ሊባሉ አይችሉም ከሚል አስተሳሰብ ይህንን ሳይሉ አልቀረም፡፡ በእርግጠኝነት በሁሉም የሚታወቁ፣ ስፋቱና ወሰኑ የተለየ፣ ግልጽና ዝርዝር ደንጋጌዎች ከሌሉ የሥነ ሥርዓት ሕግጋት ነበሩ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በ1934 ዓ.ም. ስለዳኝነት ሥራ አካሄድ የወጣውና የፍርድ ቤቶችን አመራር ሥርዓት ያቋቋመው አዋጅ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ሚኒስቴር (በዚያ ጊዜ መጠሪያው) በሚያፀድቀው መሠረት የሥነ ሥርዓት ደንቦችን እንዲያወጡ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ በ1936 ዓ.ም. ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእሱና በበታች ፍርድ ቤቶች የሚታዩት ጉዳዮች የሚቀርቡበትንና የሚካሄዱበትን ሥርዓት በተመለከተ ድንጋጌዎችን አውጥቶ ነበር፡፡ በተከታታዮቹ ዓመታት ተጨማሪ ደንቦችም ሊወጡ ችለው ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ደንቦች በአጠቃላይ ሲታዩ ሰፋ ባለና ዘርዘር ባለመንገድ ያልቀረቡና በርካታ የሥነ ሥርዓት ሕግን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ያላካተቱ ነበሩ፡፡ በተገቢው መንገድ ዘርዘርና ሰፋ ባለመንገድ የተዘጋጀ የሥነ ሥርዓት ሕግ አለመኖሩ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ያለውን የፍትሕ አሠራር ሊያዳክመው እንደቻለ በሁሉም ዘንድ ሊታመንበት በመቻሉም የሥነ ሥርዓት ሕግ የማርቀቅ ሥራ በድሮው የፍርድ ሚኒስቴር ውስጥ ተጀመረ፡፡
የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ እንደሌሎቹ ሕጎች በውጭ ባለሙያ ሳይሆን በፍርድ ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የሕግ አርቃቂ ክፍል በኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች መረቀቅ ጀመረ፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሥነ ሥርዓቱ ሕግ በብዙ ቦታዎች ያሉት ድንጋጌዎች በሥረ ነገር ሕጉ የተካተቱ ድንጋጌዎችንም የያዘ ቢሆንም አንዳንዶችን ግን ለውጥ በማድረግና በማስፋፋት እንዲያዝ ተደርጓል፡፡
አብዛኛዎቹ በሕጉ የተካተቱት ድንጋጌዎች አዳዲስ ሲሆኑ፣ የሌሎች አገሮች የሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ለምሳሌ በሕንድ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ የተመሠረቱ ነበሩ፡፡ ሆኖም የመገልበጡ ሁኔታ ግን በጥንቃቄ በመምረጥ ላይ ያተኮረ እንደነበር ፕሮፌሰር አለን ሴድለር ይገልጻሉ፡፡ እንደሳቸው ሐሳብ የውጭ አገርን ሕግ እንዳለ ገልብጦ ማቅረቡ አስፈላጊ ባለመሆኑ አዲሱ የሥነ ሥርዓት ሕግ በተለይ ኢትዮጵያዊ ይዘትና ባሕርይ እንዳለው ተደርጎ መወሰድ የሚችል ነው፡፡ ሕጉም የተረቀቀው የኢትዮጵያን የፍትሕ አስተዳደር ለማሻሻልና በሕግ ባለሙያዎችና በዳኞች በአግባቡ ተፈጻሚ የሚሆን ሕግ ለማውጣት ታስቦ ነው፡፡ የፕሮፌሰሩ ሐሳብ መነሻው ትክክል ቢሆንም ምንም ኢትዮጵያዊ የሆነ የዳበረ ልማድ ባልተካተተበት ሁኔታ ለሕጉ የኢትዮጵያዊነት ምስክር መስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡
የሕጉ አወቃቀርና ይዘት
ሕጉ ምጥን ያለና 483 ቁጥሮችን የያዘ ነው፡፡ ሕጉ በዘጠኝ መጽሐፎች፣ በምዕራፎችና በክፍሎች ተከፋፍሏል፡፡ የአፈጻጸም ሥርዓትን የሚመለከተው ምዕራፍ ደግሞ ንዑስ ክፍሎችም ይዟል፡፡ ነገር ግን በንዑስ ክፍል የመከፋፈሉ ሁኔታ የሚታየው በዚህ የአፈጻጸም ክፍሉ ብቻ ነው፡፡ ስለ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን፣ በከሳሽነትና በተከሳሽነት የሙግት ተካፋይ ስለመሆን፣ የፍትሐ ብሔር ክስን የሚመለከቱ ጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ በመጀመሪያ ደረጃ ስለሚታዩ መደበኛ ክርክሮች፣ ልዩ ሥነ ሥርዓት፣ ስለ ይግባኝ፣ ፍርድን መቃወምና ፍርድ እንዲሻሻል ወይም እንዲጣራ ስለማመልከት፣ ስለ ፍርድ አፈጻጸም፣ ስለወጪና ኪሣራ እንዲሁም ማጠቃለያ ድንጋጌዎች በሕጉ በቅደም ተከተል የተካተቱ ነጥቦች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር አለን ሴድለር የሕጉን አወቃቀር በተመለከተ ሁለት ወሳኝ አስተያየቶችን ‹‹Ethiopian Civil Procedure›› በሚለው ማብራሪያቸው ላይ አካትተዋል፡፡ የመጀመሪያው ሕጉ በስተመጨረሻ ያካተታቸውን ፎርሞች ይመለከታል፡፡ ሕጉ አቤቱታን፣ የመጥሪያ አሰጣጥን፣ ልዩ ልዩ ጉዳዮችንና የፍርድ አፈጻጸምን የሚመለከቱ አራት ፎርሞችን አካትቶ ይዟል፡፡ እነዚህ ፎርሞች የግዴታ ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረግ እንዳለባቸው ሕጉ በወጣ በሦስተኛው ዓመት ፕሮፌሰሩ በጻፉት ማብራሪያ ላይ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ የሕጉንም ይዘት በጥሞና ከተመለከትነው የፕሮፌሰሩ ሐሳብ ትክክል ስለመሆኑ እንረዳለን፡፡ ለአብነት ያህል አንቀጽ 80(2)፣ 94(3) ብንመለከት ሕጉ በግልጽ በተዘጋጁት ፎርሞች አቤቱታዎቹ እንዲቀርቡ ያዛል፡፡ ሁለተኛው ፕሮፌሰሩ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች ስለሚጨመሩበት ወይም ስለሚሻሻሉበት ሁኔታና ስለአተረጓጎሙ የገለጹት ነው፡፡ ማሻሻሉ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣን ሲሆን፣ አተረጓጎሙን በተመለከተ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ከመሠረታዊው ሕግ ጋር በአንድ ላይ ሊነበብ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ የተወሰኑ የፍትሐ ብሔር ሕግ ድንጋጌዎች በሥረ ነገሩ ሕግ ላይ በቀረቡት መሠረት መነበብ ይኖርባቸዋል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰር አለን ሴድለር ሁለቱን ሕግጋት ማጣጣም (አብሮ ማንበብ ቀድሞውኑ) አስቸጋሪ እንደሆነ ሦስት ምክንያቶችን በመስጠት ይገልጻሉ፡፡ የመጀመሪያው የሥነ ሥርዓት ሕጉና የፍትሐ ብሔር ሕጉ የተረቀቁት በተናጠል በተለያየ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው የፍትሐ ብሔር ሕግ ይዘትና ቅርፅ ‹‹የሲቪል ሕግ ሥርዓት›› የሚከተሉ አገሮችን ሞዴል ይዞ የቀረበ ሲሆን፣ የሥነ ሥርዓቱ ሕግ ግን ‹‹በልማዳዊ ሕግ ሥርዓት›› የሚተዳደሩ አገሮችን ሞዴል ይዞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሦስተኛው በሁለቱ ሕግጋት ያሉት የቃላት አጠቃቀም ልዩነት ነው፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ ያሉትን ሥነ ሥርዓት ነክ ጽንሰ ሐሳቦች በሥረ ነገሩ (በፍትሐ ብሔር) ሕግ ላይ በትክክል ከተጠቀመበት ቃላት ጋር ለማገናኘት መሞከር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰሩ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡ ይህን ያህል ስለሕጉ ውልደት፣ ዕድገት፣ አወቃቀርና ይዘት ለመታሰቢያ ካወሳን በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ በሕጉ ላይ የጸሐፊውንና የሕግ ባለሙያዎችን ትችት እናቀርባለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡