Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ማስቀጠል እየከበደ መሄዱ አይቀርም

ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ማስቀጠል እየከበደ መሄዱ አይቀርም

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

የኢትዮጵያ ፈጣን ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ የብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የሲኤንቢሲ አፍሪካ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ ጁሊያንስ አምቦኮ እንደሚለው፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ስትታይ ከአፍሪካ ትንሳዔ ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ወሳኝ አገሮች አንዷ መሆን ችላለች፡፡

በአገር ውስጥ ካለው እውነታ አንጻር በዚህ አባባል ሙሉ ተስፋ የሚያሳድሩ ዜጎችም ትንሽ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እንደ አገር የተጀመሩት ሁሉም ዘርፎች (ኮንስትራክሽን፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ አገልግሎት…) ሁሉም መጠኑ (ዕድገቱ) ይለያይ እንጂ ወደፊት በመሄድ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ በእነዚህ መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ መምጣት ሰፋፊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ዜጎች ኑሯቸው እየተሻሻለ ሀብት ማፍራት ይዘዋል፡፡ እንደ አገር የዘላቂ መሠረተ ልማት የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ክምችትም እየታየ ነው፡፡ ይህን ዕድገት አስመልክቶ ቀደም ባለው ጊዜ እምብዛም ዕውቅና የማይሰጡት የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ብቻ ሳይሆኑ ምዕራባዊያን መመስከራቸው ትርጉሙ ሁለት ነው፡፡ አንደኛው ዕድገቱ እምብዛም አዋጭ አይደለም ሲባል በነበረው “በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ፖሊሲዎች” አማካይነት እየመጣ ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ዕድገቱ በራሱ የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጡ የሦስተኛ ወገንን ዕውቅና እያገኘ መሆኑን ያመላክታል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የአፍሪካ አማካሪ አንድሪያ ሪችተር ሁም የተመዘገበው ዕድገት ከፖሊሲው ትክክለኛነት የተነሳ መሆኑን ሲገልጹ፣ “በኢትዮጵያ ሁሉም ፖሊሲዎች በተገቢው ሁኔታ የሚሠራባቸው፣ እንደ ምዕተ ዓመት ግብና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ያሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በልዩ ትኩረት የሚፈጸሙ በመሆናቸው ድርጅታችን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመሥራት ሁሌም ቢሆን ዝግጁ ነው፤” ብለዋል፡፡

እነዚህን መልካም መንደርደሪያዎች የምናነሳው እንደ ዜጋ የአገራችን ዕድገት የሚያኮራን ብቻ ሳይሆን በተጨባጭም የሚጠቅመን ስለሆነ ነው፡፡ ልጆቻችንን እንደቀደመው ትውልድ ስለጦርነት፣ ድርቅና ረሃብ ወይም ውድቀትና ሽንፈት እየሰሙ ማደግ የለባቸውም፡፡ ዛሬም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ባይወገድም ድርቅ፣ ስደትና ውርደት መለያችን ሆነው በየአገሩ ያሉ ዜጎቻችን አንገት እንዲያስደፋም አንሻም፡፡ ስለሆነም በዕድገቱ ከመደሰት አልፈን አሻራችንንም ለማሳረፍ መኳተን ይኖርብናል፡፡ ግን ሥር ነቀል ለውጡን ለማረጋገጥ ጉድለቶችን ማየት ተገቢ ነው፡፡

የአፍሪካ አገሮች ፈጠራና ቴክኖሎጂን ካልያዙ አይፈጥኑም

ጀርመን የሚታተመውና በፖለቲካ፣ በባህልና በቢዝነስ ላይ የተለያዩ ትንተናዎችን የሚያቀርበው ታዋቂው “ዶችላንድ” መጽሔት ከወራት በፊት በአፍሪካ አገሮች የፈጠራና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ አንድ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፡፡ “The Lack of Africa Inovation & Technology Complementation” የሚል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ዛሬ አፍሪካ ያላት የሕዝብ ቁጥር ከአንድ ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይኼ ደግሞ ምንም እንኳን በ54 መንግሥታት ሥር ያለ ቢሆንም ከቻይናና ከህንድ ቀጥሎ የሚጠቀስ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ነው፡፡ ስለሆነም በዋጋ ዝቅተኛና ሊያመርት የሚችል ጉልበት፣ ሰፊ ገበያና አቅም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታና ዕድል በምርታማነት፣ በፈጠራና በቴክኖሎጂ መር አካሄድ በመምራት ወደ ሽግግር መውሰድ ካልተቻለ ደግሞ፣ የአፍሪካ አገሮች የተናጠል መጠነኛ ዕድገት ተጠናክሮ ሊቀጥል አይችልም ሲል ነው የገለጸው፡፡

እነቻይና፣ ህንድም ሆኑ ኮሪያና ታይዋንን የመሳሰሉ የፈጣን አዳጊ አገሮች ተምሳሌቶች ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት አንስቶ መንኮራኩር ስለማምጠቅ፣ አኅጉር ተሻጋሪ ሚሳይሎችን ስለመገንባትም ሆነ ኒክሌርን ከመጨበጥ በላይ ያስጨንቃቸው የነበረው ከሌላው ዓለም ኮርጀውም ሆነ አሻሽለው የምርታማነትን መሣሪያዎችን መጨበጥ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት፣ ኮምፒዩተራይዝድ የሆነ የአዲሱን ትውልድ ዕውቀትና ክህሎት መታጠቅ፣ የቀለም ትምህርትን ከተግባር ጋር በላቀ ሁኔታ አስተሳስሮ ከኋላ ቀር ግብርናና አኗኗር ተመንድጎ መውጣትና የመሳሰሉት ተግባራት ላይ አተኩረዋል፡፡ ወደ አፍሪካ ሁኔታ ስንመጣ ግን የተለየ ገጽታ ይስተዋላል፡፡ አሁንም በእርስ በርስ ጦርነት፣ በግብረ ሽብርና ሁከት የሚታመስ አገርና ሕዝብ አለ፡፡ አሁንም እጁን ለዕርዳታ በመዘርጋት የተሸከመው ሀብት ላይ ተቀምጦ የሚለምን ምንደኛ አገርና መንግሥት ያለባቸው ቀጣናዎች አሉ፡፡ አኅጉራዊ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ መቀናጀቱም ገና ለጋ የሚባል ብቻ ሳይሆን በፍጥነት የሚያድግ አይመስልም፡፡ ከሁሉም በላይ ቴክኖሎጂን ከማላመድና ፈጠራን ከማበረታታት ይልቅ የሌሎች ግኝቶችን ማንቆለጳጰስና መሸከም ይታያል ነው ተንታኞች የሚሉት፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከችግሩ ቀድማ እንድትወጣ ማሰብ የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ እርግጥ ዩኒቨርሲቲዎች ከጀመሩት 30/70 የማኅበራዊና ተፈጥሮ ሳይንስ ቀመር አንፃር በርካታ መሐንዲሶች፣ የላብራቶሪና የኢንዱስትሪ ሙያተኞች የሚፈጠሩበት ዕድል ተዘርግቷል፡፡ ግን ጥራቱና በተግባር ላይ የተመሠረተ ትምህርት መሰጠቱ ላይ ጥርጣሬ አለ፡፡ ተቋማቱ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር የኢንዱስትሪና የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚፈልገው የሠለጠነ የሰው ኃይልና መንግሥት ለምርምርና ለፈጠራ የሚሰጠው ትኩረት ሁሉ መፈተሽ አለበት፡፡ እንደ አገር የምርምር ማዕከላት በየዘርፉ የት አሉ? ምን ፈጠራና ግኝት አላቸው? የትኞቹ በመተግበራቸው ምን ዓይነት ውጤት መጣ? ብሎ ማጤንም ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ ግን ከዘልማዳዊ ዕድገት ያለፈ ፈጣን ሽግግር ማምጣት ያዳግታል፡፡   

ተስፋ የተጣለበት ግብርና በምን ተዓምር ይደግ?

ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው ሲባል የኖረው በብዙ መገለጫዎች ነው፡፡ ከ85 በመቶ በላይ ሕዝብ የሚተዳደርበት ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ምንጭና የጥቅል አገራዊ ምርቱ ምሰሶ ስለሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ፈጣንና ዘላቂ የአገር ዕድገትን ለማምጣት የግብርናው ዕድገት ወሳኝ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ባሳለፍናቸው አምስት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት ውስጥ ጥቅል የዋና ዋና የአገሪቱ ሰብሎች ምርት ከነበረበት 168 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 270 ሚሊዮን ኩንታል ዕድገት ማምጣቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል፡፡ ይህ ምርታማነት ለመምጣቱም የአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ፣ እንዲሁም የማዳበሪያ ተጠቃሚነት መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ ጥቁር አፈር ማጠንፈፍ፣ የመስኖም ሆነ የኩሬ ውኃ መጠቀምና አነስተኛ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን ሥራ ላይ ማዋል መቻሉም ያስገኘው ፋይዳ አለ፡፡ እንደ አገር በግብርናው መስክ ለተገኘው ተከታታይ ዕድገት የመንግሥት የዘርፉ መሪዎች፣ የግብርና ሙያተኞችና ራሱን አርሶ አደሩን የሚያስመሰግኑ ሥራዎች መሠራታቸውም አይካድም፡፡ በአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ በቤተሰብ ጉልበት የእርሻ እንክብካቤና የበጋ ሥራዎች ላይ ሚሊዮኖች በመሳተፋቸው በሔክታር የነበረው አማካይ ምርታማነት በብዙዎቹ አካባቢዎች ለውጥ ታይቶበታል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን አሁን በኩርማን መሬት ላይ የዓመት ቀለቡን እንኳን መሰብሰብ የማይችል አርሶ አደር አለ፡፡ ዛሬም ቢሆን ከ90 በመቶው በላይ አርሶ አደር እርሻውን የሚያርሰው በበሬና በኋላ ቀሩ አስተራረስ ዘዴ ነው፡፡ በአገሪቱ “ሚሊየነር አርሶ አደሮች” አሉ የመባሉን ያህል በአንዳንድ አካባቢዎች (ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ፣ አፋርና ወለጋ) ባሉት አካባቢዎች በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚያመርቱ የመስኖ ውኃ አጠቃቀምን ለጓሮ ቃሪያ እንኳን ማዋል ያልቻሉ የገጠር ነዋሪዎች ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ በአገሪቱ ያለውን ሰፊ መሬት ያህል ወደ ሜካናይዝድ እርሻ የተገባበት አለመሆኑ (የገቡት ጥቂት ኢንቨስተሮች ፍሬም በገበያው ላይ ያመጣው አንዳች ለውጥ አለመታየቱ ያሳስባል)፣ መንግሥት በቀዳሚው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTPI) የያዘው የመስኖና ውኃ አጠቃቀም ሰፊ መርሐ ግብር የታለመለትን ያህል አለመሳካቱም የዘርፉ ሥጋት ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ በያዝነው ዓመት ከአሥር ዓመታት በኋላ የተከሰተው የኤልኒኖ ክስተት የሆነው የድርቅ አደጋ እስካሁን የታየውን የምርታማነት መሻሻል ክፉኛ እንደሚያዳክመው እየተሰጋ ያለው፣ በዝናብ እጥረቱ ብቻ ሳይሆን ከወራት በኋላ ይከሰታል በተባለው ጎርፍ ምክንያት ነው፡፡

ታዲያ ግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ራሱ መንግሥት በ2012 ዓ.ም. መጨረሻ (የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ማብቂያ) ላይ የአገር ውስጥ የሰብል ምርቱን በእጥፍ አሳድጌ 580 ሚሊዮን ኩንታል አደርሳለሁ ማለት በምን መነሻ ይሆን? የሚሉ ድምፆች በርክተዋል፡፡ ሰሞኑን በግብርና ሚኒስቴር የዕቅድ ውይይት ወቅት ከራሱ ከተቋሙ ሙያተኞችም ሆነ “የሕዝብ ክንፍ” ከተባለው ተሳታፊ በአፅንኦት የተነሳው “በውስጥ መሬትና በውኃ አጠቃቀም የተለየ ነገር ሳይመጣ፣ የተፈጥሮ አደጋን በብቃት መከላከል ደረጃ ሳንደርስ እንዴት በእጥፍ ልናሳድግ እንችላለን?” የሚለው ጥያቄ በቂና የተፈታ መልስ አላገኘም፡፡ “አገሪቱ ካላት ሰፊ መሬት ውስጥ ከ3.5 እስከ አራት ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው በመስኖና በጠብታ መስኖ በማልማት የታቀደውን የምርታማነት ጣሪያ እንደርሳለን፤” ሲባል፣ በግል ባለሀብቱ? በመንግሥት? ወይስ አርሶ አደሩን በማደራጀት? የሚለው ጥያቄ ሊመለስ ይገባል፡፡  

የማዕድናትና የተፈጥሮ ሀብቶች ጉዳይ ከፍለጋ ቁዘማ ይውጣ

“ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ባለፀጋ፣ ያልተነካ ዕምቅ ሀብት ባለቤት” የምትባል እንደሆነች ተጠንቶም ሳይጠናም ለዘመናት ተነግሯል፡፡ በእርግጥ የተፈጥሮ ሀብት (እንደ ነዳጅ፣ ወርቅ፣ ድንጋይ ከሰል፣ አልማዝ…) የለንም ብለን እጅ አጣጥፈን እንዳንቀመጥ የሚያደርጉ ምልክቶች አሉ፡፡ አንደኛው በባህላዊ መንገድም ቢሆን ማዕድናትና ዕንቁ ጌጣጌቶችን የሚያመርቱ ዜጎች አሉ፡፡ እንደ ሚድሮክ የመሳሰሉትም ከፍተኛ የወርቅ ምርት በማምረት ቀላል የማይባል ሀብት እያገኙ ነው፡፡ ያም ሆኖ “አለ” የሚባለው ማዕድንና እንደ አገር ያገኘነው ጥቅም እዚህ ግባ የማይባልና ትርጉም አልባ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የአሜሪካ፣ የጀርመን የፈረንሣይና ጣሊያን አጥኚዎች፣ እንዲሁም በደርግ ጊዜ እንደ ሩሲያ፣ ቼኮዝሊቪኪያ፣ ቡልጋሪያና ምሥራቅ ጀርመን ያሉ አጥኚዎች፣ በኢሕአዴግ ጊዜም (ምንም እንኳን ቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው መስክ ባይሆንም) የቻይና፣ የሩሲያና የአሜሪካ የማዕድን ፈላጊዎች አንዳንዴም የኢንዶኔዢያና ማሌዥያ ጆኦሎጂስቶች ከኢትዮጵያውያን የመስኩ ምሁራን ጋር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እስካሁን ግን እምብዛም ኢኮኖሚውን በፈጣን የበረራ ጥርስ ውስጥ በማስገባት ወደተጨባጩ ዕመርታዊ ዕድገት የሚያመጣ ሀብት አልተገኘም፡፡

ኢሕአዴግ ማዕድናትና የተፈጥሮ ሀብትን አስመልክቶ በተለያዩ ሰነዶች እንዳረጋገጠው መጀመሪያ፣ “አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ስንገነባ” ቢመጣም ጠንቅ ይሆንብናል የሚል ነው፡፡ ይልቁንም የሰው ሀብት/ጉልበት፣ መሬትና ውኃን ተጠቅመን ካፒታል በመገንባት በሒደት በትንሽ የሌሎች ድጋፍ በራስ አቅም ልናመርተው እንችላለን የሚል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ የነዳጅ ምልክት የታየባቸውን የሶማሌ ክልል፣ የጋምቤላና የደቡብ ኦሞ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ፈላጊ እንኳን አደፋፍሮ ለማሳማራት እንዳስቻለ የሚናገሩ አሉ፡፡ በእርግጥ የተወሰኑ ሙከራዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የመንግሥት የእስካሁኑ ስትራቴጂ ትክክል ነው የሚሉ ሳይሆኑ ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር ሳይገነባ፣ የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና እኩልነት ማረጋገጥ ሳይጀመር ፌደራሊዝምን (ያውም ጠባብነቱ ጣሪያ በነካበት ሁኔታ) እያቀነቀኑ ይህን ሀብት አገኘሁ ማለት ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ሶማሊያን፣ ማዕከላዊ አፍሪካን… መሆንን ያስከትላል ይላሉ፡፡

አሁን ግን ቢያንስ ጊዜው የደረሰ ይመስላል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተነገረ ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ግኝት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘው ከፍተኛ ክምችት ያለው ጋዝ በጂቡቲ በኩል የመተላለፊያ መስመር ለማበጀት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ቢያንስ ለ50 ዓመታት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር (በአሁኑ ዋጋ) የሚያስገኝ ገቢ የሚያመጣ ነው፡፡ የጋዙ አምራችነት የሚፈጥረው ተሰሚነትና የኃይል ሚዛንም ቢሆን ሌላ ትኩረትንና ዓለም አቀፍ ተፈላጊነትን ያስገኛል፡፡ ይህ ግን ጅምር ብቻ ነው፡፡ ብዙ ገና ሥራ፣ ሰፊ ቁፈራ፣ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የመፍጠር ጣጣ አለበት፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ጉዳዩን በድርበቡ የማንሳት ፍርኃት ካለ ግን የኢኮኖሚው እመርታ መፈተኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት ከሌላቸው አገሮች አንፃር ከፍተኛ ዕድገት አስመዘገብን የሚለው መከራከሪያ ብዙ ስለማይወሰድ ማለት ነው፡፡

የመልካም አስተዳደር ችግሩ አለመቀረፍ ጣጣ አለው

የአስተዳደርና የሕግ የበላይነት መስተካከል ከፖለቲካና ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር ብቻ ማየት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ዋነኛው ግን ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ለአገራዊ ስሜትና ለባለቤትነት መንፈስ ያለው ፋይዳ ነው፡፡ ዜጎች በነፃነት ለመንቀሳቀስም ሆነ የእኔነት መተማመንን ለመፍጠር ታማኝና ፍትሐዊ የሆነ የመልካም አስተዳደር እንዲዘረጋላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በዘመድ፣ በዘር፣ በብሔር፣ በሃይማኖትም ሆነ በሀብት የሚፈጸምን መድልኦና በደል አይሹም፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሄዶች በጊዜ እየታረሙ ካልሄዱም እንዳለፈው ታሪካችን ሁሉ ወደማመፅና ፍትሕን የመፈለግ ቁጣ ሊገፋ እንደሚችል መዘናጋት ተላላነት ነው፡፡ ወይም የመጡበትን መንገድ መርሳት ነው፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የመልካም አስተዳደር እጦትንም ሆነ የሕግ የበላይነት መሸርሸርን በመርህ ደረጃ ይቃወመዋል፡፡ በተግባር ግን እየተቸገረ ይመስላል፡፡ ይህም ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ማነስ፣ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት መላላት ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲን ከልብ ለማስፈን ካለመፈለግ ይመነጫል፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ እንዴት ከኢኮኖሚው ዕድገት መቀጠል ጋር ይያያዛል የምትሉ የዋሆች ትኖራላችሁ ብዬ አላምንም፡፡ በፍትሕና በርትዕ አስተዳደር መኖር ያልተማመነ ባለሀብት ሀብቱን አያፈስም፡፡ ዳያስፖራውም ሆነ የውጭ ባለሀብትም ሀብትና ንብረቱን አያነቃንቅም፡፡ በአገር ውስጥም ቢሆን የእኔነት ስሜት እየጠፋ መንግሥት ሲገነባ ሌላው ማፍረሱ አይቀርም፡፡ ሌብነት፣ ክዳትና ወንጀል እየሰፋ ተስፋ ቆራጭነት እየሰፈነ ከሄደም ጭራሽ ወደኋላ መመለስና መንኮታኮትን ያስከትላል፡፡

ስለሆነም መንግሥት ደፍሮ ማስተካከል ያልቻለውን የመልካም አስተዳደር እጦት መዘዝ በጥንቃቄ አጤኖ ሊያርምና ሊያስተካክል የሚገባው ዛሬ ነው፡፡ በአጠቃላይም ለቀጣይ የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞ ቀላል እንደማይሆን ተገንዝቦ መረባረብ ይገባል፡፡  

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...