Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትመንግሥት ሰማሁ ሲል ሰማሁ ልበል?!

መንግሥት ሰማሁ ሲል ሰማሁ ልበል?!

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

የዛሬ 84 ዓመት የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት በታወጀበት ጊዜ፣ በይፋ ንግግርና ዲስኩር፣ “ዘንድሮ በኢትዮጵያ የተፈጸመው ሐሳብና የተወጠነው ዕቅድ በዓለም ላይ በየትም መቼም ተደርጎ የማይታወቅ ነው፤” ተባለ፡፡ “የመንግሥት መሠረት የመትከልና የሕግ ምሰሶ የማቆም ሥራ ተሠራ፤” ተብሎ ብሥራቱ ታወጀ፡፡

እንዲህ ያለችዋ የመንግሥት መሠረት የተተከለባት የሕግ ምሰሶ የቆመባት አገር እነሆ ከእንግዲህ ወዲያ ከዱሮው ከራሷ ትዳርና አስተዳደር ብቻ ሳይሆን፣ ከሌላው ዓለም እንዴት የተለየች እንደሆነች በንፅፅርና በምሳሌ ተነገረ፡፡

የመንግሥት መሠረት ባልተተከለበትና የሕግ ምሰሶ ባልቆመበት አገር፣ “ንጉሡ ባለሙሉ ሥልጣን ሆኖ፣ በአገሩ ምንም የተለየ ልማድ ወይም ደንብ ሳይኖርበት፣ እብሪቱ ብቻ በየቀኑ የመራውን ሐሳብ፣ እንደፈቀደው እንደ ባህሪው ድንገተኛ መለዋወጥ እየለዋወጠ ያደርጋል፣ ያለፍርድ ይቀጣል፣ ይገድላል፣ ይሰቅላል፤” ተባለ፡፡ ከዚህ የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ጀምሮ ሲቆጠር የኢትዮጵያ የአሁኑ ሕገ መንግሥት አራተኛ ነው፡፡

በአገራችን ታሪክ ውስጥ ከኤርትራ መመለስ ወዲህ የፀደቁት ሕገ መንግሥቶች መብትን በመደርደርና በመሰደር፣ እንዲሁም ሕጋዊ ሥርዓቶችን በወረቀት ላይ ከመዘርጋት አኳያ ብዙ የሚነቀፍ ነገር አልነበረባቸውም፡፡ ሕገ መንግሥቶች ሁሉ በተግባር ያልዋሉት አጻጻፋቸው ስለማያምርና የሚረዳቸው ሰው በመጥፋቱ ወይም ከውስጣቸው የጎደለ ነገር ስለነበር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዘመን ሰፍኖ የቆየው አፈናና ጭቆና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ነፃነትንና እኩልነትን ትግል ከመጫር ጎን ለጎን፣ ሁሉም ቀርቶብን በሕግና በሥርዓት በተዳደርኩ ማለት ድረስ የተንገሸገሸ ሕዝብ ጥላቻ አትርፎ ኖሯል፡፡

ዛሬም ቢሆን በሕግ አምላክ ማለትን የመሰለ የሕዝብ ጩኸት ሲበዛ በርክቷል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንትናው እንደ አምናና ካች አምና ከውሉ የተላለፈውን ሰው ሁሉ፣ (ከሰው ሰው ሳይለዩ ትንሽ ነው ትልቅ ነው ሳይሉ) አላፊ አድርጎ፣ ፈርዶ፣ አስገዳጅነት ላለው ኃይል አሳልፎ ለቅጣትም ሆነ ለሌላ ግዳጅ የሚሰጥ፣ የሚሠራና ጤነኛ አሠራር የለንም፡፡ ከሕጋዊው መንገድ ይበልጥ ሕገወጡን መንገድና ዘዴ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ ፖለቲካና ባህል እጅግ ለምቷል፡፡ ከመክሰስ መከሰስ ተመርጧል፡፡ በፍትሕና በሕግ ሥርዓቱ ላይ እምነት ጠፍቷል፡፡

በሕግ አስፈጻሚውና አስከባሪው በኩል ሕገወጥነትን ለመግታት የሚወሰደው ዕርምጃና አካሄድ የመንግሥት የሥልጣን አካላቱንና የባለሥልጣኖቻቸውን፣ እንዲሁም የሠራተኞቻቸውን የራሳቸውን የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ የሚያስገምትና የሚያሳጣ ለሕግ የመገዛትን ስሜት የሚያጎሽ ሆኗል፡፡

ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣልና የሚነሳበትን የሚታወጅና የሚሻርበትን የሥልጣን አካላትንና የባለሥልጣናትን ተግባር የሚከለክልና የሚገታ፣ የሚቆጣጠርና የሚቀጣ ሥርዓት ገና ሥር አልሰደደም፣ የሕዝብ ዋስትና አልሆነም፡፡ ይህንን የገዥዎች ተግባር በፅናት የሚዋጋ፣ ማንም ግለሰብና ባለሥልጣን የሚፈጽመውን ሕገወጥነትና አጥፊነት ከሥልጣን ሲወርድ ብቻ ሳይሆን፣ (ለዚያውም የጊዜው ፖለቲካ ፊት ነስቶት ከሥልጣን ሲወርድ) ሥልጣን ላይ እያለም መጠየቅ አለበት የሚል፣ ሳይጠየቁ መኖር መቻል ይብቃ ብሎ ድምፁን የሚያሰማ፣ ችግሩ እንዳይከሰት ጠባቂ፣ ችግሩ ሲከሰትም አጋላጭና ተፈራጅ የሆነ ሲቪል ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ገና አልተከሰተም፡፡

እንዲያውም ኢትዮጵያ ውስጥ በየጊዜው የሚወጡ ክሶችና ስሞታዎች ሁሉ ከሚያነሱት አንዱ ጉዳይ መካከል ይኼው በማኅበር የመደራጀት ሕግና መብት ጉዳይ ነው፡፡

ነባራዊ አስገዳጅነት የሌለበት፣ የቢሻን ውሳኔ የሰፈነበት፣ ለሕጋዊነት ወግ እንኳን መጨነቅ ቀርቶ ተቃራኒው ባህል ሆኖ የተቋቋመበት አንዱ መስክ ራሱ ሕግ የማውጣት አሠራሩ ነው፡፡ የሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ ሕግ የሚያከብር፣ ለሕግ የሚገብር፣ ሕግ ያለው ስለመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ የሚወራረድ ዕዳ የሚገባ የለም፡፡ የሕዝብን የመታመን ክብር አልተጎናፀፈም፡፡

ይህ ጉዳይ በተለያዬ ጊዜያት ተነስቷል፡፡ በዚህ ጸሐፊ አቅም ራሱ ሳምንት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሕግ የማውጣት ሥልጣን የሚመለከት ነበር፡፡

የዚህን ጉዳይ ሌላ መልክና ይዘት ዛሬ ይዤ የመጣሁት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው የራሱን ማለትም የምክር ቤቱን የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ “መርምሮ” ማፅደቁ፣ እንዲሁም መርምሮ ባፀደቀው የአሠራር ደንቡ እንደገና አዲስ ያቋቋመው አሠራሩ ይህንኑ የአገር የሕግ ማውጣት ችግር ደግሞ ደጋግሞ ስለሚያስተጋባ ነው፡፡ አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያው ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ የተካሄደው መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ የተሻሻለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ረቂቅ ደንብ መርምሮ ያፀደቀውም በዚያኑ ዕለት ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት ሕግ አውጪው አካል ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ከፍተኛ የሥልጣን አካል እሱው ነው፡፡ ለፌዴራል መንግሥቱ በተሰጠው የሥልጣን ክልል ውስጥ ሕጎችን የማውጣት ሥልጣን የእሱው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱን የሚመሩ አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ ይመርጣል፡፡ ለምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያዋቅራል (55/10)፡፡ እንዲሁም ምክር ቤቱ ስለአሠራሩና ስለሕግ አወጣጡ ሒደት ደንቦችን ያወጣል (59/2) የሚሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኖች አሉት፡፡

በተለመደ፣ በተቋቋመና ዛሬ በእያንዳንዱ አዋጅ በሚመሰከር አሠራር (መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. የፀደቀውን የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር አዋጅ ጭምር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸው አዋጆች መግቢያ “… በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55(1) መሠረት የሚከተለውን ታውጇል” ይላል፡፡ የተጠቀሰውና በእያንዳንዱ አዋጅ መግቢያ የሚጠቀሰው 55(1) የሚለው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ሕጎችን ያወጣል፤” ነው፡፡

ምክር ቤቱ አዲሱን የተሻሻለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ያወጣው ግን (አወጣሁት ያለው ግን) ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን አንቀጽ 55(19) እና አንቀጽ 59(2) ጠቅሶ ነው፡፡ አፈ ጉባዔዎቹን የመምረጥና የምክር ቤቱን ኮሚቴዎች የማዋቀርና ስለአሠራሩና ስለሕግ አወጣጡ ደንብ የማውጣት ሥልጣኑን ማለት ነው፡፡ የተሻሻለውና በአዲስ የተተካው የምክር ቤቱ ደንብ የወጣው በአንቀጽ 59(2) መሠረት ብቻ ነበር፡፡

ምክር ቤቱ ያወጣው የሕግ ዓይነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 59(2) አጠራር መሠረት ደንብ (በእንግሊዝኛ “Rules and Procedures)” ስለተባለየወጣውን ደንብ ፋይዳ እንዳይቀንስብንና እንዳያጣጥልብን መስጋት አለብን፡፡ ምክር ቤቱ በዚህ ደንብ ለምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልጉ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ማዋቀሩ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንቦችን መወሰኑ እውነት ነው፡፡ የአገር የሕግ አወጣጥ ሥርዓት የተዘረጋውም አሠራሩ የተወሰነውም በዚህ ደንብ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የደንቡ ፋይዳ ምክር ቤቱ “በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለፌዴራል መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ሕጎችን ያወጣል፤” ከሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ጋር ተዛምዶ መመርመር አለበት፡፡

ከመስከረም 24 ቀን 20008 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራውን የጀመረው ምክር ቤት አምስተኛው ምክር ቤት ነው፡፡ በየወቅቱ የተሰየሙት ምክር ቤቶች ሁሉ ይገለገሉበት የነበረው የአሠራር ሕግ ግን ሁሌም በዚህ ስያሜ (ደንብ) የሚጠራ አልነበረም፡፡ ከጥቅምት 15 ቀን 1988 ዓ.ም. ጀምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ወጥቶ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ በዚያው በ1988 ዓ.ም. መለስተኛ ማሻሻያ ተደርጎበት ሲሠራ የኖረው ይህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ሕግ (አዋጅ) የተሻረውና በሌላ አዲስ አዋጅ ሙሉ በሙሉ የተተካው በሚያዝያ 1994 ዓ.ም. ነው፡፡ የአዲሱና የ1994 ዓ.ም. አዋጅ ስያሜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የኮሚቴዎች አደረጃጀትና አሠራር አዋጅ ቁጥር 271/94 ነበር፡፡

ይህንን አዋጅ የተካው የተሻሻለው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 470/1997 ነበር፡፡ በ97 ምርጫ ወቅት ነፍስ አውቆ ለነበረና ለተከታተለ ይህ ሕግ ከአወዛጋቢ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አቶ መለስ ዜናዊ ታኅሳስ 4 ቀን 1998 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፣ “ተቃዋሚ ድርጅቶችና ሌሎች አንዳንድ ወገኖች በዴሞክራሲያዊ ሒደታችን ላይ በጉድለትነት ካስቀመጣቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ የተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ…” ነበር፡፡

ይህ ጉዳይ ከምርጫ ቦርድ አሠራርና የማስፈጸም ብቃት፣ እንዲሁም ከሚዲያው ሁኔታ ጋር በወቅቱ አፋጣኝ የድርድር የምክክርና የማሻሻል ዘመቻ ይደረግባቸው ዘንድ ራሳቸውን አጀንዳ አድርገው ካቀረቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ ይህን የ1997 ዓ.ም. የተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር አዋጅ “በዴሞክራሲያችን ላይ በጉድለትነት” እንዲጠቀስ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ራሱ የፀደቀበት ጊዜና ያፀደቀው ምክር ቤት ነው፡፡ 1997 ዓ.ም.ን ጨርሶ የሚሰናበተው ምክር ቤት እዚያው ዓመት ላይ ከ1998 ዓ.ም. መስከረም ጀምሮ ሥራ ለሚጀምረው አዲስ ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር አዋጅ አፅድቆ የሚሄድበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይዘቱም ይፈተሽ ከተባለ የሕግ ማውጣቱን ሥራ የቀደመው ጥድፊያ ከሚመራውና ከሚያመላክተው በላይ በጣም አወዛጋቢና ሲበዛ የሚሸት ነገር ነበረው፡፡

በዚህም ምክንያት የ1999 ዓ.ም. የፓርላማን ዘመን መስከረም ላይ በከፈቱት በወቅቱ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት  በወቅቱ እንደተባለው፣ “በሕዝብ ተመርጠው የፓርላማ አባላት በሆኑ ፓርቲዎች መካከል በውይይትና በድርድር የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ” ፀደቀ፡፡ ስለዚህም ከመስከረም 26 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው አዋጅ ቁጥር 470/1997 ቀርቶ ከመስከረም 26 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው ደንብ ቁጥር 3/1998 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ሆነ፡፡

መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ያፀደቀው የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ይህንኑ የ1998 ዓ.ም. ደንብ የሚሽርና የሚተካ ነው፡፡  

የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ሕግ አዋጅ መሆኑ ቀርቶ “ደንብ” የሆነው በዚህ ድኀረ 97 (ምርጫ) ግርግር ውዝግብና ድምብርብሮሽ ውስጥ ነው፡፡

አዋጅ ወይስ ደንብ የሚለውን ጥያቄ የምናነሳው በተለይም የሕግ አውጪው (አዋጅ ተባለ ደንብ) ያው የተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ እየታወቀ ጥያቄውን ማንሳት የምንገደደው የቁንጫ ሌጦ እናውጣ፣ ፀጉር እንሰንጥቅ ብለን አይደለም፡፡ ሕግ ማውጣት የራሱን የተወካዮች ምክር ቤትን ሥራ ከሚፈታተኑት ምክንያቶች መካከል አንዱ በመሆኑ ነው፡፡

አጭርና የሚያስደንቅ እንዲሁም የሚያስደነግጥ ምሳሌ እናቅርብ፡፡ እንደሚታወቀውና እንደሚጠበቀው የተሻሻለው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 470/1997 የወጣው፣ በዚህ አዋጅ የተሻረው የ1994 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የኮሚቴዎች አደረጃጀትና አሠራር አዋጅም የታተመው በነጋሪት ጋዜጣ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1988 ሥራ ላይ በመዋሉ አዋጅ ቁጥር 470/97ን የሻረው ሌላ አዋጅ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ በነጋሪት ጋዜጣ መውጣት ግዳጃቸው ነው፡፡ ይህን ግድ የሚያደርገው “የሕዝብ የማወቅ መብት” ብቻ አይደለም፡፡ የሕግ ህልውና የሚያገኙት በነጋሪት ጋዜጣ ሲወጡ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በሌላ አቻ ደንብ የተሻረው ደንብ ቁጥር 3/1998 ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ በሚለው በአንቀጽ 193 ድንጋጌው “ይህ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የፀና ይሆናል፤” ይላል፡፡ ዕውን ይኼ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቷል ወይ? የታተመበት ኅትመት ራሱ “ይህ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ መስከረም 26 ቀን 1999 ዓ.ም ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ” ይላል፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ ባለው አሠራርና ሕግ፣ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የሚፈርሙትን ሰዎች አሳምረን እናውቃቸዋለን፡፡ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ አዲስ በፀደቀው የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ (ረቂቅ) አንቀጽ 59 መሠረት የፀደቀ ሕግ ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ለፊርማ እንደሚቀርብ ፕሬዚዳንቱ ሕጉን በ15 ቀናት ውስጥ መፈረም እንዳለበት፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ካልፈረመ ሕጉ በአፈ ጉባዔው ስምና ፊርማ ወጥቶ በሥራ ላይ እንደሚውል አዲስ ነገር ደንግጓል፡፡ የ1999 ዓ.ም. የምክር ቤቴ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ሕግ በአፈ ጉባዔው የተፈረመው በዚህ ዓይነት ምክንያት አይደለም፡፡

በነጋሪት ጋዜጣ የሚታተም ሕግ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ አሠራር የነጋሪት ጋዜጣው ዓመትና ቁጥር ይሰጠዋል፡፡ በመጽሐፍ መልክ ለየብቻቸውና ለየቅል የማይወጡ ሕጎችም ተከታታይ የገጽ ቁጥር የሚሰጣቸው መሆኑ አሁንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ደንቡ የነጋሪት ጋዜጣ አልወጣም ብለን አረጋገጥን ማለት የሕጉ ተፈጻሚነት አልጀመረም ማለት ነው፡፡ የሕግ አወጣጥ ሥርዓታችን ለምን ይህን ያህል “በትንሽ ነገር” ሲነካ የእምቧይ ካብ ይሆናል? ይህ “በነፃ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን” የተነሳን ሰዎች ጥያቄና ደንታ ነው፡፡

አዲሱ ደንብስ በነጋሪት ጋዜጣ ይወጣል? በነጋሪት ጋዜጣ የማይወጣ ሕግስ ሕግ ይባላል? ለሕጋዊነት ወግ እንኳን ያለመጨነቃችንን ባህል እየኮተኮትንና እያለማንስ በሕግ አምላክ ማለት እንችላለን? ይህ ውሳኔ መመርያ ለሚባሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ዕርምጃዎች” ሁሉ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የአጀንዳ “ሰነድ” በቅርብ ለሚያውቁና ጠጋ ብለው ለሚመለከቱ አንድ ረቂቅ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምክር ቤቱ የሚቀርብ ሲሆን፣ በአጀንዳው ሥር ያሉ በተራ ቁጥር የተዘረዘሩ ጉዳዮች እንዴት እንደሚጻፉ በደንብ ያውቃሉ፡፡ የተሻሻለውን የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ መርምሮ ለሚመለከተው ኮሚቴ ለዝርዝር ዕይታ መምራት ይላል ብለው ይጠብቃሉ፡፡ እንዲህ ግን አልተደረገም፡፡ መስከረም 27 ቀን 2008 የተሰየመው ፓርላማ ቀጥታ መርምሮ ሕጉን አፀደቀ፡፡ አሁን ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ መከረ ይባላል?

ገና መስከረም 24 ሥራቸውን የጀመሩ ተመራጮች (የተመራጮች ስንት በመቶ ሙሉ በሙሉ አዲስ ናቸው? ምን ያህል ነባር እንደሆኑ እንኳን የነገረን መንግሥትም ፕሬስም የለም) እንዴት ይህን ጉዳይ በአንድ ቀን ጀንበር ወሰኑ ይባላሉ?

የሕግ አወጣጥ ችግራችን ግን ከዚህ የባሰ የሰፋና የከፋ ችግር አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የአመራሩ ሚናና ቦታ ከፍ ያለ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማለትም መስተዳድሩ የኢትዮጵያ (ኢፌዲሪ) ከፍተኛ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ አካል ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕግ በማውጣት ሒደትና አሠራር ውስጥ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ሕግ አውጭ ግን አይደለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ የሚባል የሕግ ዓይነት የማውጣት ሥልጣኑ የተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው የውክልና ሥልጣን መሠረትና በእሱ ላይ ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ በተግባር የሚሠራው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ይህንን በተለይም “የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ስለማደራጀት” ከሥልጣኑ አንፃር ባለፈው ሳምንት አሳይተናል፡፡

ዛሬ በዚህ ጉዳይ መመለስ ያስፈለገው መንግሥት ይህንን ችግር ሰማሁ ሲል የሰማሁ ስለመሰለኝ ነው፡፡ በአንድ ቀን ውስጥ በፀደቀው በተነጋገርንበት የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ውስጥ ከተካተቱት አዳዲስ ጉዳዮች መካከል፣ “ደንብና መመርያ ስለማውጣት” የተባለው ይህንን ተስፋና ጥርጣሬ ይቀሰቅሳል፡፡ በአዲሱ ሕግ እንደተወሰነው ከሆነ፣

  • ምክር ቤቱ ሕግ ሲያወጣ በሚያወጣው ሕግ የማስፈጸሚያ ደንብና መመርያ በውክልና እንዲወጣ ሥልጣን ሊሰጥ እንደሚችል፣
  • ደንብና መመርያ እንዲወጣ በሕግ ምክር ቤቱ የውክልና ሥልጣን በግልጽ ካልሰጠ በስተቀር ማንኛውም አካል ደንብ ወይም መመርያ ማውጣት እንደማይችል፣
  • ምክር ቤቱ በሚያወጣው ሕግ በውክልና ደንብና መመርያ እንዲወጣ ሥልጣን ሲሰጥ ደንቡና መመርያውን የሚያወጡ አካላትን በግልጽ ማመልከት እንዳለበት፣
  • ማንኛውም የሚወጣ ደንብ የአዋጁን ወሰን የጠበቀና የተጣጣመ መሆን እንደሚገባው (ይህ ለሚወጣው መመሪያም ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት)፣
  • ምክር ቤቱ በሚያወጣው ሕግ ላይ ደንብና መመርያ እንዲወጡ ሲወስን የተጠቀሰው ደንብና መመርያ ሕጉ በሥራ ላይ በዋለ በሦስት ወራት ውስጥ መውጣት እንደሚገባው፣
  • ማንኛውም መመርያ ለማንኛውም ሰው ተደራሽ መሆን እንዳለበት፣ ተደራሽነቱንም የሚመለከተው ተቋም የበላይ ኃላፊ የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት መሆኑን፣ የመመርያዎችን ተደራሽነት ኃላፊነት ያልተወጣ ተቋም የበላይ ኃላፊ ተጠያቂነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

ከከፋውና ከወደቅንበት የመጨረሻ የአዘቅትና የዝቅታ ደረጃ እንነሳ፡፡ “በሕጋችን መሠረት ይኼ ክልክል ነው አይፈቀድም” በሚባልበትና ሕጋችሁንና መመርያችሁን (በገዛ ወጭም) ስጡን ሲባል ሚስጥር ነው በሚባልበት አገር ይህን “ማወጅ” በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ የችግሩን መኖር መረዳት ነው፡፡ ሲነግሩት የመስማት ምልክት ነው፡፡ መንግሥት የሾማቸውንና መልምሎ ሥራ ላይ ያስቀመጣቸውን የገዛ ራሱን ሰዎች ወግና ባህል የሚፈታተን “አዲስ” ተግባር ነው፡፡

በአገራችን በተንሰራፋው የሕግ አወጣጥና አፈጻጸም ድቅድቅ ጨለማ ላይ ብርሃን ለማወጅ፣ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አቋም ውስጥ የሕግ ዓይነቶችን ዝርዝርና ቅደም ተከተል (ደረጃ) በግልጽ አጥርቶ መደንገግ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ለምሳሌ “ደንብ” የሚባል የሕግ ዓይነት የግዳችንን እናውቃለን፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ራሱ “ደንብ” የሚባል የሕግ ዓይነት እነሆ ሲያወጣ ዓይተናል፡፡ በሚገርምና በሚደንቅ ሁኔታ ደግሞ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዋጅ ቁጥር 858/2006 እንደተደነገገው (ምክር ቤቱ በራሱ ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንደተመለከተው)፣ አዋጁን ያወጣው ምክር ቤት ለራሱ ለተወካዮች ምክር ቤት “ደንብ” የማውጣት ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች አስተዳደር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት ይመራል፡፡ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም የተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ደንባችን ሊያወጣ ይችላል ተብሎ የተደነገገው በዚሁ አዋጅ ነው፡፡    

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ “ደንብ” የማውጣት ሥልጣን የተሰጠበት ሌላው ምሳሌ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማቋቋሚያ ሕግ ነው፡፡ ራሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም አስፈላጊ የሆኑ ደንቦችን ሊያወጣ ይችላል ሲል የውክልና ሥልጣን ይሰጣል፡፡

እዚህ ዓይነት ድንብርብሮሽ ውስጥ የገባነው እንደነ ኦዲተር ጄኔራልና ምርጫ ቦርድ ያሉ ነፃ ተቋማት በፓርቲ ተቀጥላነት ውስጥ ወይም ማንኛውም ዓይነት ወገንተኝነትና ተዛነፍ ውስጥ የማይወድቁበትን ሁኔታ ማልማት ተገቢ ነው፡፡ ግድም ነው፡፡ “ሲባል እየሰማን” ነው፡፡

“ውሳኔ” የሚባል ነገርም ሕግ በማውጣት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተግባር ውስጥ በተጠቀሰው ደንብ ጭምር ተካትቶ እናያለን፡፡ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሠራዊት የዘመተው፣ የአዲስ አበባ መስተዳደር ድኅረ ምርጫ 97 በጊዜያዊ አስተዳደር ሥር እንዲሆን የተወሰነው (ከሌሎች መካከል)፣ በእንዲህ ዓይነት የምክር ቤቱ ፈቃድ በተገለጸበት የ“ሕግ” ዓይነት ነው፡፡ እነዚህ ቅደም ተከተላቸው፣ ስያሜያቸው፣ የበላይና የበታችነታቸው በግልጽና በሕግ መወሰን አለበት፡፡ የሕግ ማስከበር ሀሁ አንዱ ይኸው ነው፡፡ መታተምም ይፋ መሆንም የሕጎቻችን አንዱ ባህርይ መሆን አለበት፡፡

አዲሱ “ደንብ” ካካተታቸው ድንጋጌዎች መካከል ‹‹ምክር ቤቱ በሚያወጣው ሕግ ላይ ደንብና መመርያ እንዲወጣ ሲወሰን የተጠቀሰው ደንብና መመርያ ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መውጣት አለበት፤” ይላል፡፡ በነሐሴ 2001 ዓ.ም. የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ የሽብርተኝነት ተጎጂዎች ፈንድ ይቋቋማል ይላል፡፡ ይህም ፈንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት ይቋቋም ዘንድ ያስገድዳል፡፡ እንዲህ ያለ ደንብ አለን?

የ“መመርያ” ሕግነት የሚገርምና ሌላው ቢቀር ከአዲስ አበባ አስተዳደር አሉታዊ ልምድና ተሞክሮ ተምሮ እንዲወጣ አለመደረጉ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2001 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ ላይ ስለመመርያ ሲናገር፣ መመርያዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ሲወጡ የነበሩ፣ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ፣ የተበታተኑ፣ በሚመለከታቸው አካላት ሳይፀድቁ ሥራ ላይ እንዲውሉ የተደረጉና ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለማስፈን አመቺ ያልሆኑ ይላቸዋል፡፡ አስተዳደሩ በዚያው ወቅት ስለመመርያ ሲነግረን የከተማው ባለጉዳይ መብቱና ግዴታው የተመሠረተበት ብሎ የሚጠቅሰውና የሚማጠንበት መመርያ ከመስተዳድሩ እጅ ይጠፋና ባለጉዳዮች ራሳቸው ይዘውልን እንዲመጡ መጠየቅ መድረሱን ያህል ሥርዓት መወላለቁን አገር መበላሸቱን ያረዳናል፡፡

ዛሬ ይህን ሁሉ ችግር አስወግደን ሥርዓት ዘርግተን የቀድሞውን ስቃያችንን ሁሉ ከነመመርያዎቹ ሙዚየም ከተን፣ በዕረፍት ጊዜያችን በገዛ ራሳችን ላይ የምንስቅበት ጊዜ መሆን ነበረበት፡፡

ችግሩን እፈታለሁ ብሎ ‹‹ደንቡ›› ውስጥ ባካተተው ድንጋጌዎች የተመካው የተወካዮች ምክር ቤት ራሱ ከልጅ ልጅ (ከመሥሪያ ቤት መሥሪያ ቤት) የሚለይ አሠራር አለው፡፡ ለምሳሌ የሲቪል አቪዬሽን አዋጅ እንደተለመደው ለሚኒስትሮች ምክር ቤትና ለባለሥልጣኑ አዋጁን ‹‹በሚገባ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ›› ደንቦችን፣ ሥርዓቶችንና ደረጃዎችን የያዙ መመርያዎችን የማውጣት ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ከሌሎች መመርያዎች የማውጣት ሥልጣን ለየት የሚያደርገው የመመርያዎች አወጣጥና ኅትመትን የሚመለከት ተጨማሪ ዝርዝር ድንጋጌ መኖሩ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሲቪል አየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪን የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን፣ የሚመለከታቸውንም ሰዎች ማማከር፣ የሚያወጣቸውን መመርያዎች የማሳተም ኃላፊነት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህን በሌሎች መመርያ የማውጣት ሥልጣን መፍቀጃ ውስጥ በጭራሽ አናይም፡፡

ዕውን መንግሥት ችግሩ ተሰምቶት ከሆነ በእሱ በኩል ትልቁ ተግባር ለዚህ የተፈጠምኩ ነኝ ብሎ ማረጋገጫ መስጠቱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለውን ጉዳይ ለባለሙያና ለሕዝብ እንቅስቃሴ ይስጠው፡፡ በተለያየ ደረጃና ዓይነት የተዋቀሩ ባለሙያዎች የሕግ አወጣጥ ሥርዓቶችን ያጠኑት ይውቀጡት፡፡ ችግሩንና መፍትሔውን አቅርበው ሕዝብ ይነጋገርበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...