Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የግብር ምጣኔው እንደሚሻሻል እንደሚጠበቀው ሁሉ መንግሥትም አቅጣጫ ሰጥቶበታል››

አቶ በከር ሻሌ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

አቶ በከር ሻሌ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተናፈሰ የሚገኘውን የገቢ ግብር ማሻሻያና አጠቃላይ የአገሪቱ የግብር ሥርዓት በተመለከተ ዮሐንስ አንበርብር ከአቶ በከር ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ በጀት ዘመን የመጀመርያ ሩብ ዓመት በቅርቡ ተጠናቋል፡፡ አጠቃላይ የገቢ አሰባሰባችሁ ምን ይመስላል?

አቶ በከር፡- ያለፉት ሦስት ወራት የገቢ አፈጻጸማችንን በተመለከተ በሩብ ዓመት ውስጥ 35.2 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ ነበረን፡፡ አፈጻጸማችን 34.4 ቢሊዮን ነው፡፡ ይህም የዕቅዱ 97.5 በመቶ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ጥሩ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ ምክንያቱም በዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ነበርን፡፡ በዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ያጠፋነውን ጊዜ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ መቶ በመቶ ዕቅዳችንን መምታት ያስችለን ነበር፡፡ በአዋጅ እንድንሰበስብ የተጣለብን ኃላፊነት 142 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በየዓመቱ እንደምናደርገው ዕቅዳችንን ለጥጠን ወደ 146 ቢሊዮን ብር ከፍ አድርገነዋል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የተገኘው 97.4 በመቶ አፈጻጸምም ይህንኑ ዕቅድ እንደ ግብ የቆጠረ ነው፡፡ ቀጣዩ ሁለተኛ ሩብ ዓመት የአጠቃላይ ዕቅዱ 40 በመቶና ከዚያ በላይ የሚሰበሰብበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአገሪቱ የገቢ አሰባሰብ ምን ዓይነት መልክ ይኖረዋል? የአገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ከጠቅላላ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) አንፃር ሲመዘን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል የተለየ ያቀዳችሁትና ያደረጋችሁት ዝግጅት አለ?

አቶ በከር፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን አጠቃላይ የአገሪቱ ገቢ ከአጠቃላይ ጂዲፒው 18 በመቶ ይደርሳል ብለን አቅደናል፡፡ የአገር ውስጥ ታክስ ደግሞ ከጂዲፒው 17 በመቶ ይደርሳል ብለን አቅደናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢው ከጂዲፒው ያለው ጥምርታ 14 በመቶ ነው፡፡ አጠቃላይ ታክሱ ከጂዲፒው ያለው ጥምርታ ደግሞ 13 በመቶ ነው፡፡ የተቀመጠው ግብ ይኼ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ተቋማችን ብዙ የሚሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ዋናውና አንደኛው የታክስ አስተዳደር አቅም ግንባታ ማካሄድ ነው፡፡ የታክስ አስተዳደር አቅም ግንባታውን በክህሎት፣ በአደረጃጀትና በአሠራሮች ተለዋዋጭነቱን ጠብቀን መገንባት ይኖርብናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የመረጃ አጠቃቀምን የሚመለከት ነው፡፡ ለአንድ አገር ዘመናዊ የታክስ ሥርዓት የመረጃ አስተዳደር ሥርዓቱ ዋነኛ ነው፡፡ ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተነዋል፡፡ የጉምሩክ ዋጋ መተመኛ ሥርዓት የሆነውን “ASICUDA++” ወደ “ASICUDA World” ለመቀየር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአገር ውስጥ ገቢ የምንጠቀመው የመረጃ ሥርዓት “SIGTAS” ሲሆን፣ ይኼንንም የማሻሻል ሥራ አትኩረን እየሠራን ነው፡፡ ሌላኛው የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት የጀመርነውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የግብር ከፋዩን አመለካከት መቀየር ነው፡፡ የአገሪቱ ግብር ከፋዮች ለአገሪቱ ዕድገት አስተዋፅኦ ባደረጉ ቁጠር የዕድገቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከልብ አምነው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ የሚገባ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የግንዛቤ ሥራው በስፋት ሊሠራ የሚገባ ነው፡፡ ሌላው ሥራ የታክስ መሠረቱ ሰፋ ያለ እንዲሆን ማድረግም ይጠበቅናል፡፡ ይኼም ማለት ከኢኮኖሚው የሚገኘውን ገቢ ለመሰብሰብ ያልተፈተሹ የታክስ መሠረቶችን ወደ ታክስ መሠረቱ ማስገባት ሌላኛው ተግባራዊ የሚሆን ዕቅድ ነው፡፡  የኅብረተሰቡን ለታክስ ሕግ ተገዥነት ማሳደግ፣ ሕገወጥ ግብር ከፋዮችን ወደ መስመር መመለስ፣ እንዲሁም ሕገወጦችን በሕግ ማስቀጣት የሚቀጥሉት ተግባራት ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  አገሪቱ ላለፉት ከአሥር ዓመታት በላይ ባለ ሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መንግሥት እየሰበሰበ አይደለም የሚሉ ጥናቶች አሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

አቶ በሽር፡- አሁን ያነሳኸው ጥያቄ በመንግሥት በኩልም የተገመገመ ነው፡፡ የአገሪቱን ገቢ የማመንጨት አቅም ላለመጠቀማችን ምክንያቶቹ ቀደም ብዬ የገለጽኳቸው መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ናቸው፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ያመነጨውን ገቢ አሟጠን ሰብስበናል የሚል ዕምነት የለንም፡፡ የታክስ አስተዳደሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ መጥቷል፡፡ የታክስ አሰባሰባችንም እንዲሁ እያደገ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በ2002 ዓ.ም. ወደ ጂቲፒው ስንገባ የነበረው አጠቃላይ ገቢ 34 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ አሁን ወደ 133 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ተችሏል፡፡ ይኼ ትልቅ ዕድገት ነው፡፡ ወደ አራት እጥፍ ነው የተሰበሰበው፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚው ባደገ ልክ የታክስ ገቢ አቅሙን አሟጠን አልተጠቀምንበትም፡፡ በመሠረታዊነት ችግሮቹ ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው ናቸው፡፡ አንድ የታክስ አስተዳዳሩ የማስፈጸም አቅም ውስንነት ነው፡፡ ግብር መሰወር ባህል የሆነበት አገር ነው፡፡ ኪራይ ሰብባቢነትንና በአቋራጭ መበልፀግን ውስብስብ ሐሳቦችን መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት አሁን በቅርቡ ተቋማችን አንድ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይኖረዋል፡፡ ይህ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የአዲስ አበባን ቅርንጫፎች በባለቤትነት ኃላፊነት ወስዶ የሚመራ ነው፡፡ የፌዴራል አገር ውስጥ ታክስ በአንድ ዘርፍ በምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲመራ አድርገናል፡፡ የፌዴራሉ ቀድሞ ተደራጅቷል፡፡ ኮርፖሬት ታክስን የሚመለከት፣ እንዲሁም የክልሎችን አቅም የመገንባት አጠቃላይ የታክስ ፖሊሲዎችንና አሠራሮችን በማጥናት ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ አጠቃላይ አገራዊ የተቀናጀ የታክስ ፖሊሲ እንዲፈጠር የሚሠራ ነው፡፡

የአዲስ አበባውን በተመለከተ ያሉት ግብር ከፋዮች ብዛት ያላቸው ቢሆኑም አነስተኛ ግብር ከፍዮች ናቸው፡፡ ከገቢ አንፃር ዝቅተኛ ቢሆንም ከመልካም አስተዳደር፣ ከሕግ ተገዢነት አንፃር ትልቅ ችግር አለ፡፡ የመርካቶ የሕግ ተገዢነት ችግር አለ፡፡ እንደገና ከመስተዳድሩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ በባለቤትነት ይህንን የሚከታተል አደረጃጀት ይኖረናል፡፡ የገመገምናቸውን ችግሮች ከፈታንና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የወጠንናቸውን ማሳካት እንችላለን ብለን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢን በውክልና መሰብሰባችሁ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ አግባብ አለው ወይ? ከተማዋ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግሥት ቢሆንም ራሷን ችላ በቻርተር ተቋቁማለችና ግጭት የለውም ወይ? ይህ አሠራርስ እስከ መቼ ይቀጥላል?

አቶ በከር፡- በመጀመርያ በሁለትዮሽ ስምምነት ነው ወደዚህ የውክልና ሥራ የመጣነው፡፡ ማለትም በአዲስ አበባ አስተዳደርና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ነው ወደ ውክልና አሠራር የመጣነው፡፡ አዲስ አበባ በቻርተር የምትተዳደር ቢሆንም የፌዴራል አካል ናት፡፡ ውክልናውን ስንወስድ አቅም ገንብቶ አጠቃላይ የታክስ ሕግ ማስከበር ሥራዎችን እንዲሠራ ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለመረከብ ያስፈለገው የክልሎች የገቢ አሰባሰብም ሥርዓት እንዲያዝ ታስቦ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ያለው ገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ሲይዝ አጠቃላይ የአገሪቱ የገቢ ሥርዓት ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አለው፡፡ ወጪውን የአዲስ አበባ አስተዳደር ይሸፍናል፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራውንና ሥርዓት የማስያዝ ኃላፊነቱን የእኛ ተቋም በመሥራትና ገቢውን በመሰብሰብ ለከተማው የሚያስረክብበት አሠራር ነው ተግባራዊ ያደረግነው፡፡ ይህ አሠራር በ2003 ዓ.ም. ወደ እኛ ተቋም ሲመጣ የአዲስ አበባ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ብር የማይበልጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 17 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ትልቅ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ወደ 22 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ስለዚህ ውክልናው ውጤት ያመጣ ከመሆኑም ባሻገር የሕግ ስህተት የለውም፡፡ በውይይትና በመግባባት አንድ ላይ ስለምንሠራ፡፡ ወደፊት በባለሥልጣን ደረጃ አደረጃጀት ኖሮት ተጠሪነቱ ለከንቲባው የሚሆንበት አሠራር ይወጣል፡፡ ነገር ግን መቼ ነው ይህ አደረጃጀት የሚመጣው የሚለው ገና የተወሰነ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ገቢ ግብር ማሻሻያው እንምጣና በአጠቃላይ የገቢ ግብር ማሻሻያው ምን ይዞ ይመጣል?

አቶ በከር፡- የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያው እየተሠራ ነው ያለው፡፡ ለሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደ መሠረት የሚሆን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት እንደሚስብም እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ትልቅ ማሻሻያ ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ማሻሻያው እንዲሠራ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በባለቤትነት ከእኛ ተቋም ጋር በመሆን ጥናቱን የማከናወን ሥራ በ2007 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡ የመጀመርያ ረቂቆች ተጠናቀዋል፡፡ የተለዩ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ላይ መሠረታዊ አቅጣጫ ለመስጠት እየተሞከረ ነው፡፡ በአጠቃላይ ማሻሻያው ሁለት ተልዕኮ ይኖረዋል፡፡ አንደኛው ውስብስብ የሆኑ ችግር የያዙ አሠራሮችን ይፈታል፡፡ አንድ አዋጅ ከወጣ በኋላ ረዥም ጊዜ መቆየት ስላለበት የወደፊት ዓመታት ታሳቢዎችንም ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ በገቢው ላይ እንዲሁም በታክስ ሕግ ተገዥነት ላይ ያሉ ክፍተቶችንም የሚያጠባብቅ ነው፡፡ ጠበቅ ያለ የታክስ ሕግ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነትን የሚዋጋ ሕግ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊና አኅጉራዊ የገበያ ተወዳዳሪነታችንንም ታሳቢ የሚያደርግ ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ውስጥ ተወዳዳሪ እንድንሆንና አሁን የተያያዝነውን የኢኮኖሚ ሽግግር ማገዝ የሚችል የሕግ ሰነድ ይኖረናል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ጥናቶች የኢትዮጵያ የግብር ሥርዓት ሸማቹ አካባቢ ትኩረት በማድረጉ ከፍተኛ የግብርና ጫና በንግድ ማኅበረሰቡና የቅጥር ገቢ በሚያገኘው ማኅበረሰብ ላይ ይታያል የሚል ትችት ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ላይ በግልዎት ወይም በተቋም ደረጃ ያለዎት አስተያየት ምን ይመስላል?

አቶ በከር፡- በመጀመርያ ደረጃ የገቢ ግብር አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ያለው ማለቴ ነው ኢ ፍትሐዊ ነው የሚል ድምዳሜ የለንም፡፡ ፍትሐዊ ግብር ነው በእኛ አገር ያለው፡፡ አሁንም ቢሆንም ከጊዜው ጋር የሚሄድ የግብር ሥርዓት ለመፍጠር ነው ማሻሻያ የምናደርገው፡፡ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት በአገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታና ዛሬ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆመን ነገ ወደምንሄድበት አቅጣጫ ይዞን ሊሄድ የሚችል መነሻ የገቢ ግብር ማሻሻያ ነው የሚኖረን እንጂ፣ የቀድሞው ኢ ፍትሐዊ ነው ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ግብር ከፋይ ካገኘው ገቢ በታክስ ምጣኔው እኩል ነው የሚከፍለው፡፡ ሁለተኛው የሚያገል ወይም ዜጎችን በልዩነት የሚያይ አይደለም፡፡ ነገር ግን አሁን ከደረስንበት አገራዊ ሁኔታ አንፃር የሚገቡ መሠረታዊ ለውጦች አሉ፡፡ በዋናነት ከኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከመልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ የንግድ ተወዳዳሪነትና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከመፍጠር አንፃር የሚካተቱ ማሻሻያዎች ይኖራሉ፡፡ ጠንካራ የታክስ ሕግ ከሌለን ልፍስፍስ አቋም ይዘን የምናስበው ደረጃ መድረስ አንችልም፡፡ ሌላው ከተቀጣሪ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን በተመለከተ ማለትም የደመወዝ ግብር ምጣኔው በዝቷል፣ እንዲሁም የታክስ መነሻ የሆነው 150 ብር ደመወዝ አንሷል የሚሉ ትችቶችና ጥያቄዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄውን ለመመለስ ጥናት እንዲካሄድ በመንግሥት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ ጥናቱ እየተካሄደ መሆኑን አብዛኛው ሰው አውቆታል፡፡

ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የደመወዝ ገቢ ግብር ማሻሻያ ምጣኔ የተባሉ ቁጥሮች ወጡ፡፡ እነዚህ መረጃዎች ግን በጭራሽ ትክክል አይደሉም፡፡ ጥናቱ ተጠናቆ የሚመለከተው አካል ውሳኔ ካሳረፈበት በኋላ ነው ይፋ መሆን የሚችለው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በራሳቸው ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ኅብረተሰቡን ሊያሳስቱት ይችላሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች ትክክል አይደሉም ለማለት ብቻ ሳይሆን ጥናቱ ገና አልተጠናቀቀም፡፡ ነገር ግን ማሻሻያው ከግምት የሚያስገባቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የግብር ምጣኔው ማሻሻያ እንደሚደረግበት እንደሚጠበቀው ሁሉ መንግሥትም አቅጣጫ የሰጠበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የገቢ ግብር ምጣኔ ከ150 ብር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛውን የከተማ ደሃ የሚጎዳ ነው፡፡ በተመሳሳይ የመጨረሻው 35 በመቶ የተጣለበት አምስት ሺሕ ብርና ከዚያ በላይ በአሁኑ ወቅት ትልቅ የሚባል ደመወዝ አይደለም፡፡ ይህንን ያገናዘበ ማሻሻያ ነው የሚደረገው ማለት ይቻላል?

አቶ በከር፡- የጥናቱ መነሻ እሱ ነው፡፡ ከታች ያለው ከግብር ነፃ ደመወዝ እንዲሁም የመጨረሻው የግብር ምጣኔ ላይ ነው ጥያቄ የሚነሳው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ሲባል የማክሮ ኢኮኖሚ መናጋትን እንዳያስከትል ከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የሚደረገው፡፡ ከታች ያለውን ከግብር ነፃ ደመወዝ ከ150 ብር ከፍ ለማድረግ ሲነካ፣ ከላይ ያለውንም ጭምር ስለሚነካ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጠቃላይ ሥርዓቱን በማያናጋና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሊታይ ይችላል፡፡ ይህ ነው የተቀመጠው አቅጣጫ እንጂ ከታች ይህንን ያህል ይደርሳል ከላይ ደግሞ እንዲህ ይሆናል የሚል አቅጣጫ ላይ አልተደረሰም፡፡ ገና በሒደት ላይ ነው ያለው፡፡ ግን አጠቃላይ መሻሻል እንዳለበትና በጥናት መመለስ እንደሚገባው ነው አቅጣጫ የተሰጠው፡፡ አቅጣጫውን መነሻ አድርጎ ኅብረተሰቡ የየራሱን ግምት እየወሰደ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- የገቢ ግብር ሲባል የደመወዝ ግብርን የተመለከተ ብቻ አይደለም፡፡ በንግድ ድርጅት የትርፍ ግብር የመሳሰሉት የገቢ ዓይነቶች ላይም የምጣኔ ለውጥ ሊኖር ይችላል?

አቶ በከር፡- ለዚህ ነው እኮ በጥናት መመለስ አለበት የሚባለው፡፡ ስለገቢ ግብር ስናወራ ስለደመወዝ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ግብር ከፋይ ይመለከታል፡፡ አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማያናጋ ብዬ ለመግለጽ የሞከርኩበት ምክንያት ማሻሻያው የሚመለከተው ሁሉንም የገቢ ግብር ዓይነቶች ነው፡፡ የግብር ጫና በዛበት በሚል ብቻ ሳይሆን፣ ማሻሻያው እየተሠራ ያለው ራሱን ከግብር ሥርዓቱ ሰውሮ የሚኖረውን ወደ ሥርዓቱ ለማምጣት ነው፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኛው ገቢውን መደበቅ አይችልም፡፡ ሌላው ዘርፍ ላይ ያለው ግን ገቢውን በትክክል አሳውቆ ግብር እየከፈለ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአግባቡ ከማይከፍለው ማኅበረሰብ የሚፈለገውን ገቢ መሰብሰብ መቻል አለብን፡፡ በሌላ በኩል በኑሮ ውድነቱና በሌሎችም የተነሳ ጫና ያለበትን አካባቢን አጥንቶ መልስ መስጠት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካለው የኑሮ ውድነትና የታክስ ጫና አንፃር ይህ ጥናት ቀድሞ መከናወን አልነበረበትም? በአጠቃላይ በእርስዎ አስተያየት አልዘገየም?

አቶ በከር፡- አልዘገየም የሚባለው አንፃራዊ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በተደጋጋሚ ጊዜ ቀደም ብሎ ቀርቧል፡፡ ጥያቄውን መንግሥት ሰከን ብሎ መመልከት ነበረበት፡፡ በማኅበራዊው፣ በፖለቲካው እንዲሁም በኢኮኖሚ ገጽታዎቹ መታየት ነበረበት ጥያቄው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ መንግሥት አሁን ጥያቄውን በጥናት ለመመለስ የወሰነበት ሰዓት ወቅቱን የጠበቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መቼ ተግባራዊ ይሆናል ለሚለው በዚህ ዓመት ወደ ተግባር ይገባል የሚል ግምት አለን፡፡ ከተለጠጠ በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ ላይ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በማሻሻያው ምክንያት በመንግሥት ገቢ ላይ ቅናሽ ሊታይ ይችላል የሚል ሥጋት የለም ወይ? ወይስ ይህንን ለማካካስ የሚካተቱ ሌሎች የግብር ዓይነቶች አሉ

አቶ በከር፡- የግብር አዋጁ ሲሻሻል ገቢውን ትርጉም ባለው ደረጃ እንዳይጎዳ ታሳቢ ይደረጋል፡፡ ገቢውን የሚጎዳ ከሆነማ የገቢ ግብር አዋጁ ማሻሻያ አይቀረፅም፡፡ እነዚህ የምጣኔ ማሻሻያዎች ምን ተፅዕኖ ይኖራቸዋል የሚለው በጥናት የሚመለሰው ለዚህ ነው፡፡ በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የለበትም፡፡ የደመወዝ ወይም የሌላውም የገቢ ግብር ሊቀንስ ይችላል፡፡ ነገር ግን በሌላ በኩል ወደ ታክስ ሥርዓቱ ውስጥ የሚቀላቀል አዲስ የገቢ ግብር ሊኖር ይችላል፡፡ በእያንዳንዱ ግለሰብ ተቀጥሮ የሚሠራ ቁጥሩ የትየለሌ ነው፡፡ ይህ ግብሩን በሥርዓቱ አይከፍልም፡፡ ይህ ሁሉ ወደ ታክስ ሥርዓት ውስጥ ሲገባ ጉድለቱን ሊሞላ ይችላል፡፡ ቀደም ብለው ወደ ሥራ የገቡ አነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የተሰጣቸውን የታክስ እፎይታ ጨርሰው ሲገቡ ጉድለቱን ይሞሉታል፡፡ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ግን በምንም ዓይነት አንከልስም፡፡ ማሻሻያው የገቢ ግብር መጠኑን ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት ነው የተያዘው፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት የግብር ሥርዓት ከተማው አካባቢ በተለይም ሸማቹ ላይ ላለፉት ዓመታት ትኩረት ሰጥቷል ይባላል፡፡ በዚህ የተነሳ የአገሪቱ የታክስ መሠረት ጠባብ ነው፡፡ በመሆኑም ግብር የማያውቀው ሰፊ ሕዝብ በኢትዮጵያ አለ፡፡ ለአብነት ያህልም የአገሪቱ ኢኮኖሚን የሚመራው የግብርና ዘርፍ የመንግሥት ግብር አያውቀውም የሚል አመለካከት አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መደበኛ ያልሆነ (ኢንፎርማል) የንግድ ዘርፍ በከተማ አካባቢ አለ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ በከር፡- የአገሪቱ ኢኮኖሚ የገቢ የማመንጨት አቅም በውጭ አማካሪ እየተሠራ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ኢንፎርማል የንግድ ዘርፍ የሚባሉት ወደ ግብር ሥርዓቱ አለመግባታቸውን አስመልክቶ የሚቀርበው ትችት ተገቢ ነው፡፡ ኢንፎርማል የንግድ ዘርፍ የሚባሉት የንግድ ቦታ በማጣት ተባራሪ ንግድ የሚያከናውኑ፣ በጎዳና ላይ ሊሆን ይችላል አልያም በየኮርነሩ አነስተኛ ከለላዎችን አድርገው የሚሠሩ ናቸው፡፡ በደረታቸው፣ በጭንቅላታቸው ላይ አድርገው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ልውውጥ የሚያደርጉ አሉ፡፡ እነዚህ ናቸው ወደ ግብር ሥርዓቱ ያልገቡ ኢንፎርማል ዘርፍ የምንላቸው፡፡ ሌሎችም አሉ ቋሚ የንግድ ቦታ የሌላቸው፡፡ የንግድ ፈቃድ ሳያወጡ፣ ወይም የግብር መለያ ቁጥር ሳይኖራቸው የሚሠሩ፡፡ እነዚህ ወደ ግብር ሥርዓቱ መግባት አለባቸው፡፡

ይህንን ለማስተካከል ከከተሞች የንግድ ቢሮዎች ጋር በመተባበር ማስተካከል ይገባል፡፡ ይህ በከተሞች ውስጥ ከፍተኛ አብዮት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ የሚሠሩበት ቦታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ሥራ ከከተማ አስተዳደር ጋር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከግብርና ጋር በተያያዘ ያነሳኸውን በተመለከተ በእኛ መንግሥት ግምገማ ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው፡፡ አብዛኛውን አርሶ አደር ይዞ ነው ያለው፡፡ ከ80 በመቶ በላይ የአገራችንን ሕዝቦች ይዞ ያለ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ነገር ግን ከግብርና አንድ አርሶ አደር የሚያገኘው ገቢ ትንሽ ነውና የግብር ጫና ለመፍጠር እንደ አቅጣጫ የተያዘ ነገር የለም፡፡ አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም የሚከተለው የታክስ ሥርዓት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የክልሎች የታክስ ሥልጣን ነው፡፡ የገቢ ግብር አዋጁ አርሶ አደሩን ይነካል የሚል መነሻ የለውም፡፡ የታሰበ ነገርም የለም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች