Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ራስን የመመገብና የድርቅ ፈተናዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ‹‹በምግብ ራሳችንን ችለናል›› ያለበትና ያወጀበት ዓመት ሳይገባደድ ነበር ድርቅ ከበር ማንኳኳት የጀመረው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ ግን መንግሥት አገሪቱ በምግብ ራሷን እንዳለች ማወጁ ይታወሳል፡፡ ይህ በሆነ በወራት ልዩነት ግን ድርቅ መጣ፡፡ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎችም ለምግብ ዕርዳታ ተጋለጡ፡፡ በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች እንስሳት መሞታቸው ታውቋል፡፡ መጠኑና ብዛቱን መንግሥት ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል፡፡

የድርቁ ስፋትና ጥልቀት ከውጭ ዕርዳታ መጥፋት ጋር ተዳምሮ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ ለድርቁ ተጋላጮች 596 ሚሊዮን ዶላር ወይም 12 ቢሊዮን ብር ያህል እንደሚያስፈልግ ይፋ ተደርጓል፡፡ መንግሥት አራት ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን አሳውቋል፡፡ ወደፊትም እንደድርቁ ስፋትና አሳሳቢነት የሚደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ድርቁ ባየለባቸው አካባቢዎች ባደረጓቸው ስብሰባዎች ወቅት አስታውቀዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለሚመራው ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ጸሐፊ የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ፣ ከለጋሽ አገሮች ይህ ነው የሚባል ድጋፍ ባለመገኘቱና ‹‹መንግሥት ለዜጎቹ ቅድሚያ መስጠት ስላለበትም›› አራት ቢሊዮን ብር ድርቅ ለመታቸው አካባቢዎች ማዋሉን ይፋ ያደረጉት በሳምንቱ መጀመሪያ ነበር፡፡ ስለድርቁ ማብራሪያ ለመስጠት፣ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች፣ የውጭ ዲፕሎማቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ማለትም በካቶሊክ ሪሊፍ ሶሳይቲ ሥር የሚታቀፉትን ቢሯቸው በመጥራት አነጋግረዋል፡፡ ስለድርቁ ስፋትና አሳሳቢነት፣ ስለሚያስፈልገው የድጋፍ መጠንም አሳውቀዋቸዋል፡፡

ዝናብ ጠባቂው የእርሻና የማሳ ሥራ፣ እርጥበት አዘል በሆኑ የግጦሽ መሬቶች ላይ የተንጠለጠለው የአርብቶ አደሩ ሕልውና በበልግና በመኸር ዝናብ መዘግየት፣ መቀነስና መዛባት የተነሳ የዕለት ዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ጨምሮ ስምንት ሚሊዮን አደረሰ፡፡ የድርቁ መነሻም ኤል ኒኖ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ የዚህ የተፈጥሮ አደጋ ክስተት እንግዳ ባይሆንም በሌሎች አገሮች የጎርፍ መጥለቅለቅና የአውሎ ነፋስ አደጋዎችን ሲያስከትል፣ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ መሆኑ በተነገረለት መጠን ኢትዮጵያን የድርቅ ሰለባ አድርጓል፡፡ በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠር ገበሬና ቤተሰቡ፣ ልጆቹና ቀዬው ለዕርዳታ እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡

ይሁንና መንግሥት የድርቁ አደጋ ከቁጥጥሬ ውጭ አይደለም ማለቱም ተሰምቷል፡፡ እርግጥ ለጋሾች መንግሥት ከወትሮው በተለየ መንገድ ሁለት ያልተመዱ ነገሮችን ስለማድረጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዱ ያለወትሮው ለድርቁ ተጋላጮች የሰጠው የድጋፍ ምላሽ ነው፡፡ መንግሥት ሰፊና ፈጣን ምላሽ  መስጠቱን ከገለጹ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ሴቭ ዘ ችልድረን አንዱ ነው፡፡  በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ለደረሰው ድርቅ መንግሥት የሰጠው ምላሽ ብቻም ሳይሆን መረጃዎችን ግልጽ እያወጣ ማሳወቁ በለጋሾች ዘንድ አስመስግኖታል፡፡

 በሰው ሕይወት ላይ አደጋ እያንዣበበ ለመሆኑ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ካደረጓቸው ንግግሮች መረዳት ይቻላል፡፡ ሰዎች በድርቁ ሳቢያ በረሃብ እንዳይጎዱና እንዳይሞቱ መንግሥታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ጉዳዮችን የሚስተባብረው ቡድን  ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት የተከሰው ድርቅ ለአስከፊ የምግብ እጥረትና ለተመጣጠን ምግብ እጦት ያጋለጣቸው ሕፃናት ቁጥር ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ድርቅም የከፋ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙትን አገሮች ቀውስ ውስጥ በመከትት ለከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ዳርጓቸው የነበረው ድርቅ በሶማሊያ አስከፊ ሞት አስከትሎ እንደነበር፣ ሕፃናትን ለቅንጨራና ለመመናመን አድርሶ ሲገድላቸውም ታይቷል፡፡  በኢትዮጵያ የምግብ እጥረቱ አስከፊ አደጋ የጋረጠባቸው ሕፃናት ቁጥር 43 ሺሕ ደርሷል፡፡

በነሐሴ ወር ሁለተኛው ሳምንት ይፋ ተደርጎ የነበረው የተረጂዎች ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ነበር፡፡ ነገር ግን በክረምቱ ዝናብ መዛባትና መቀነስ ምክንያት ቁጥሩ ወዲያውኑ እያሻቀበ መጣና ወደ 7.2 ሚሊዮን ጥቂት ቆይቶም ወደ 7.4 ሚሊዮን አሻቅቦ በአሁኑ ወቅት 8.2 ሚሊዮን መድረሱን አቶ ምትኩ ይፋ አድርገዋል፡፡ እርግጥ ከዚህ ውስጥ 4.4 ሚሊዮኑ ከዚህ ቀደም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ዕርዳታ ሲያገኙ የነበሩትን የሚወክል ቁጥር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በጠቅላላው ለኢትዮጵያ የድርቅ ሰላባዎች ያስፈልጋል ከተባለው 12 ቢሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን 258 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከለጋሾች ቢገኝም ጥቅም ላይ በመዋሉ የምግብ፣ የተጨማሪ ምግብ አቅርቦት፣ የግብርና ዘርፍ ላይ ለሕልውና የሚያስፈልጉ ምግብ ነክ አቅርቦቶች ከፍተኛ እጥረት መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቸኳይ የሕፃናት ትምህርት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ለሰብዓዊ ድጋፎች በአስቸኳይ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን 237 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ዩኒሴፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለልማት ከተያዘው በጀት ወደ አስቸኳይ ዕርዳታ መንግሥት መዋል እንዳለበት ዩኒሴፍ ማሳሰቡም ተዘግቧል፡፡ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ለጋሾችና ዲፕሎማቶች መንግሥት ለልማት ከመደበው ገንዘብ ወደ ዕርዳታ ፈንድ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የቀደሙት የድርቅ ክስተቶች ማኀደር

በዓለም ላይ የተመዘገቡ የድርቅና የረሃብ ክስተቶች ከተመዘገቡ ዓበይት የታሪክ ክስተቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ድርቅና የረሃብ ብሎም የቸነፈር ታሪክ የሚቀዳው ከ16ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ እንደሆነ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ በአፄ ምንሊክ ዘመን ደግሞ ክፉ ቀን የሚል ሥያሜ ያተረፈው የረሃብ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ የያዘ ነው፡፡ ሰው፣ ከብቱ፣ ሕፃናትና አዛውንቱ ያለቁበት ይህ መነሻው ከህንድ በመጡ ከብቶች ሳቢያ አብሮ በገባው አባሰንጋ በሽታ ከብቶች በማለቃቸው መሬት የሚታረስበት ጠፍቶ እንደነበር የዘገቡ የታሪክ ጸሐፍትም አልታጡም፡፡

በንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን የደረሰው የረሃብ እልቂት ግን አገሪቱን በዓለም መድረክ ስሟን በቸነፈር ያስጠራና ዛሬም ድረስ መታወቂያዋ ያደረገ ነበር፡፡ በተለይ በ1977 ዓ.ም. በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ አንድ ሚሊዮን ያህል ሰዎች ማለቃቸውን በማስታወስ የሚገልጹ መረጃዎች ሲጠቀሱ፣ ለአገሪቱ የረሃብ ተጎጂዎች በዓለም የናኙ ዘፋኞች ለዕርዳታ ዘፈን ያወጡበት፣ እንደነ ቦኖና ጌልዶፍ ያሉትም ዕርዳታ አሰባስበው ወደዚህ ያመጡበት ዘመን ሆኖ ተመዘገበ፡፡ በወቅቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለደረባ ሆነው ሲሠሩ የነበሩትና ከሁለት ዓመት በፊት ራሚሮ አርማንዶ ዲ ኦሊቬራ ሎፔዝ ዳ ሲልቫን ሪፖርተር አነጋግሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ረዳት ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ ሪፖተር ስለ 77ቱ ድርቅ በጠየቃቸው ወቅት ይህንን ብለው ነበር፡፡

‹‹በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ባላስታውስ ይሻለኛል፡፡ ለምን ትጠይቀኛለህ? ስለነበረው ሁኔታ ማወቅ ፈልገህ ከሆነ በተለያዩ መንገዶች ሪከርድ ተደርጓል፤ ከዚያ ማግኘት ትችላለህ፡፡ ለማንኛውም በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ለተፈጠው ድርቅና ረሃብ ዋነኛ መንስዔው በኢትዮጵያና በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የወቅቱ መንግሥት ይከተል የነበረው ፖሊሲ ችግሩን የበለጠ አባብሶታል፡፡ የተፈጠረውን ቀውስ በእንጭጩ ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ ችግሩን ለመደበቅ የማይቻልበት ደረጃ እስኪደርስ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ዝምታን መርጧል፤›› ያሉት ዳ ሲልቫ፣ መንግሥት ብቻም ሳይሆን የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ሆነ ሌሎች ለጋሽ ተቋማት የተከሰተውን ድርቅና ረሃብ ለመመከት አቅም እንዳልነበራቸው ገልጸዋል፡፡

በምግብ እህል ራስን ስለመቻል ከሚነገረውና ከተነገረው

‹‹ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በምግብ ራሷን የቻለች አገር ትሆናለች ብለው ያስባሉ ወይ? የሪፖርተር ቀጣዩ ጥያቄ ነበር፡፡ በምላሻቸው ‹‹በትክክል፡፡ አለበለዚያ እዚህ አታገኘኝም ነበር፡፡ ለውጥ መፍጠር የሚችል እምቅ አቅም፣ ፍላጐት፣ ራዕይና ስትራቴጂ መኖሩን ስትገነዘብ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፡፡ እነዚህን አስፈላጊ ነገሮች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ መመልከት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን የምትችል አገር ለመሆን የሚያስችል አቅም አላት፤›› በማለት አገሪቱ በምግብ ራሷን መቻሏ እንደማያጠራጥራቸው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተደጋጋሚ ፓርላማ ቀርበው ካሰሙት ንግግር፣ ከዚህ በተጨማሪ በድል በዓል ወቅት በስታዲየም ባደረጉት ንግግርም ጭምር ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን መቻሏን ገልጸዋል፡፡ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው በፓርላማ ተገኝው አገሪቱ በምግብ እህል ራሷን መቻሏን አስታውቀዋል፡፡ ዴኤታዎቻቸው ባገኟቸው አጋጣሚዎች ይህንኑ አስተጋብተዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የአገሪቱ አጠቃላይ ዋና ዋና የሰብል ምርት ሽፋን 270 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱን ግብርና ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት ዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ አለ ተብሎ ቢታሰብ፣ አንድ ሰው በአማካይ 25 ኪሎ ግራም በወር ማግኘት ችሎ ነበር ማለት ነው፡፡  ይህ በመሆኑም በአገሪቱ ግብርና ዘርፍ ራስን መመገብ ተችሏል ቢባልም ከውጭ ስንዴ ገዝቶ ማስገባት አልቀረም፡፡ ለድርቁ ጉዳተኞች እስካሁን የተገዛውን ጭምሮ አንድ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ በዚህ ዓመት ለመግዛት ዓለም አቀፍ ጨረታ መውጣቱ ተሰምቷል፡፡

ይሁንና ከዳር ዳር አጀንዳ ሆኖ የሰነበተው የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግብርና ዘርፍ ያሰበውን ከማሳካት ወዲህ ማዶ ያደረ እንደሆነ አስፍሯል፡፡ የዕቅዱ የመጨረሻ ረቂቅ ሰነድ እንደሚያትተው፣ በግብርና ዘርፍ በዕቅዱ የተቀመጡትን ግቦች አብዛኞቹን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ለአብነትም በ2002 ዓ.ም. በመጠባበቂያ ምግብ ክምችት በኩል በወቅቱ ከነበረው 0.41 ሚሊዮን ቶን በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ሦስት ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይታሰብ ነበር፡፡ ይህ ግን የሚደረስበት ግብ አልሆነም ብሎታል፡፡

 ከዚህ በተጨማሪም የዋጋ ንረት በማረጋጋት፣ የወጪ ንግድን በማጠናከር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማስፋትና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በመጠንና በጥራት ማቅረብ የመሳሰሉትን ዕቅዶች ሊያሳካ አልቻለም ተብሎ ተገምግሟል፡፡ አንዳንድ እንደ ስንዴ ያሉ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ዋጋ ማረጋጋት ግድ ሆኖ ተገኝቷል ያለው ረቂቅ ሰነዱ፣ በጠቅላላው በማክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ትልቁን የዋጋ ማረጋጋትም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ግኝነቱ የተሰጠውን የበላይነት ድርሻ ያልተወጣ ብሎታል፡፡

በሌላ በኩል በዓለም የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት በኩል ይፋ የተደረገው የዘንድሮው የዓለም የረሃብ ተቋሚ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ለረሃብ ተጋላጭነታቸው አሳሳቢ በሚባለው ቀለበት ውስጥ እንደሚወድቅ ይፋ አድርጓል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ የረሃብ ተጋላጭነትን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ ብትችልም፣ ከ117 የዓለም አገሮች ውስጥ በአሳሳቢና በአስፈሪ የረሃብ ቀለበት ውስጥ ከሚጠቀሱ 52 አገሮች ውስጥ መገኘቷ ግድ ሆኗል፡፡ የአሁኑ ድርቅም እስከ መጪው ጥር ወር ዕርዳታ የሚሰፈርላቸው ሰዎችን ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሆነው እንደሚቀጥሉ አሳይቷል፡፡ እስከዚያው ድረስ መንግሥት ያስፈልጋል የተባለውን 12 ቢሊዮን ብር ስለማሟላቱ መተማመኛ ባይሰጥም፣ ከለጋሾች የተፈለገው ዕርዳታ ባይገኝ በራሱ እንደሚወጣው ግን ቃሉን ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች