Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእስራኤሉ ኩባንያ ይዟቸው የነበሩ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ለሌሎች ኮንትራክተሮች ተሰጡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የአንዱ ፕሮጀክት ቀሪ ሥራ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል

ትድሃር የተባለው የእስራኤል ኮንስትራክሽን ኩባንያ ይዟቸው የነበሩና የተስተጓጎሉ የአራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ቀሪ ሥራዎች ለሌሎች ተቋራጮች ተላልፈው ተሰጡ፡፡

በታክስ ማጭበርበር ምክንያት የትድሃር ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜናሽ ሌቪ ከታሰሩ በኋላም ሆነ ቀደም ብሎ ሥራቸው ተስተጓጉሏል የተባሉትን የአራቱን የመንገድ ፕሮጀክቶች ቀሪ ሥራ ለማጠናቀቅ አዲስ የኮንትራት ውል የተፈራረሙት፣ አይኤፍኤች የተባለው የቻይና ኩባንያና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣኑ የራስ ኃይል ናቸው፡፡

ከአራቱ ፕሮጀክቶች ሦስቱን የባለሥልጣኑ የራስ ኃይል የሥራ ሒደት በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍለው በአንድ ፕሮጀክት ሥር የነበሩትን፣ ቀሪውን የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ የቻይናው አይኤፍኤች ኩባንያ በድርድር እንዲሠራው ተሰጥቶታል፡፡

አይኤፍኤች የተረከበው ፕሮጀክት ከምሥራቅ-ምዕራብ የቀላል ባቡር መስመር የመንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ከውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ልማት ሚኒስቴር-ለም ሆቴል-መገናኛ-ማዕድን ሚኒስቴር ድረስ ያለውን የተቋረጠ የመንገድ ሥራ መሆኑን፣ ሐሙስ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ስምምነቱ ሲፈረም ተገልጿል፡፡

የቻይናው ኩባንያ ከማዕድን ሚኒስቴር-ለም ሆቴል ድረስ ላለው ትድሃር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ላላጠናቀቀው ቀሪ ሥራ 272.6 ሚሊዮን ብር፣ ከለም ሆቴል-ውኃ ልማት-ካፒታል ሆቴል ድረስ ላለው ቀሪ ሥራ ደግሞ በ242.9 ሚሊዮን ብር ለመሥራት ተስማምቶ ኮንትራት ውል ፈርሟል፡፡ በድምሩ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁት የቀድሞ የትድሃር ቀሪ ሥራዎችን አጠናቆ ለማስረከብ ሰባት ወራት ተሰጥተውታል፡፡

ትድሃር ፕሮጀክቶቹን ሊነጠቅ የቻለው ሥራውን በአግባቡ ሊያከናውን ባለመቻሉ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በሐምሌ 2007 ዓ.ም. አማካሪ መሐንዲሱ ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሠረት የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ በአማካሪ መሐንዲሱ ኮር ኢንጂነሪንግ ያቀረበውን ፕሮፖዛል የተመለከቱት ባለሥልጣኑና የባለሥልጣኑ ቦርድ፣ ትድሃር መታገዱ አግባብ መሆኑን በማመናቸው የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ኮንትራት መቋረጥ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሥጋት ፈጥሮ የነበረው ፕሮጀክቶቹ ከዚህ በኋላ እንዴት ይከናወናሉ የሚለው ጉዳይ ነበር ያሉት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ የትድሃርን ቀሪ ሥራዎች ለሌሎች ኮንትራክተሮች አጫርቶ መስጠት  ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሦስቱ ፕሮጀክቶች በራስ ኃይል እንዲከናወኑ የባሥልጣኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሊወስን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ለቻይናው ኩባንያ የተሰጠውም ፕሮጀክት ያለጨረታ በድርድር እንዲሆን የተደረገውም በምክንያት ነው ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ የቻይናው ኩባንያ ትድሃር ሲያከናውነው ከነበረው ፕሮጀክት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሥራ ሲሠራ የቆየ በመሆኑ፣ የባለሥልጣኑ የሥራ አመራር ቦርድ ወደ ሌላ ጨረታ ከመግባት ይልቅ እሱን መደራደር ይሻላል ብሎ በመወሰኑ ነው፡፡

አይኤፍኤች ይህንን ቀሪ ሥራ ሊወስድ እንደሚችል ቢጠየቅ ተብሎ የሥራ አመራር ቦርዱ በሰጠው መመርያ መሠረት፣ ኩባንያው የቀረበለትን ጥያቄ በመመርመርና በመደራደር ሥራውን ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

ይህ ውሳኔ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ኢንጂነር ፍቃዱ፣ በተደረገው ድርድር ከዋጋም አኳያ ብዙ ለውጥ የሌለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አይኤፍኤች ትድሃር ወስዷቸው የነበሩትን ፕሮጀክቶች ለማከናወን ተጫርቶ ሁለተኛ ወጥቶ የነበረ፣ቀድሞም አቅርቦት የነበረው ዋጋ ከትድሃር ጋር ተቀራራቢ ስለነበረ በዚያ ዋጋ እንዲሠራ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡

አይኤፍኤች የትድሃር ቀሪ ሥራዎችን እንዲያከናውን የተደረገበት ሌላው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ፣ የግንባታ ሥራው አሁን ከተጨመረለት ፕሮጀክት ጋር ተከታታይነት ያለው በመሆኑና በዋነኛነት በተመሳሳይ ፕሮጀክት ላይ ባሳየው ከፍተኛ አፈጻጸም ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የራስ ኃይል እያንዳንዳቸው 2.8 ኪሎ ሜትር የሆኑትን ከአቡነ ጴጥሮስ-ፓስተርና ከፓስተር-ዊንጌት ፕሮጀክቶች ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ እንዲሁም ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ ዊንጌት ባለው ፕሮጀክት ውስጥ የቴሌኮም ፒቪሲና ማንሆል ቀሪ ሥራዎች ያከናውናል፡፡ በራስ ኃይል የሚከናወነው ሌላው ፕሮጀክት ደግሞ ከስድስት ኪሎ-ፈረንሳይ ኬላ-ጉራራ የመንገድ ፕሮጀክት ቀሪ የመንገድና የቴሌ መስመር ዝርጋታ ናቸው፡፡ በባለሥልጣኑ የራስ ኃይል የሚከናወኑ ሥራዎች በስድስት ወራት እንደሚጠናቀቁ እንደሚጠበቅ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በራስ ኃይል የሚሠሩት መንገዶች የግንባታ ወጪ አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ተሰልቶ የሚሠራ ነው፡፡ የሚያስጨምር ከሆነም ከትድሃር ከዚያ ፐርፎርማንስ ቦንድ ላይ ተቀናሽ እየሆነ ለግንባታው ይውላል ተብሏል፡፡ 

ከስድስት ኪሎ-ፈረንሳይ ኬላ-ጉራራ ዋናው መንገድ የተሠራ ቢሆንም፣ ከፈረንሳይ ወደ ቤላ የሚሄደው ተገንጣይ መንገድ ጅምር ላይ ነው፡፡ ይህም የሕዝብ ጥያቄ ማስነሳቱን ኢንጂነር ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡           

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም በሚድሮክ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲገነባ የቆየውና በ2006 ዓ.ም. በተፈለገው ፍጥነት ባለመከናወኑ የተነጠቀው የጉርድ ሾላ መንገድ ፕሮጀክት ለእንይ ኮንስትራክሽን ተሰጥቷል፡፡ ሚድሮክ ይህንን የመንገድ ፕሮጀክት የተነጠቀው በ2006 በጀት ዓመት ቢሆንም፣ በ2007 በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ በራስ ኃይል ግንባታውን ሲያከናውን ቆይቶ ነበር፡፡

በጉርድ ሾላ የመንገድ ፕሮጀክት ተሻጋሪ ድልድይና 30 ሜትር ርዝመት ያለው የመቃረቢያ መንገድ ለመገንባትም የሚያስችል ነው፡፡ ይህ የኮንትራት ውል ከእንይ ኮንስትራክሽን ጋር ተፈርሟል፡፡ እንይ ይህንን ሥራ ለማከናወን የተዋዋለው 171.2 ሚሊዮን ብር ዝቅተኛ የጨረታ ዋጋ በማቅረብ አሸናፊ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ የግንባታ ሥራው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡ በዚህ ጨረታ አይኤፍኤች ተጫርቶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ሀይዌይ ኢንጂነርስ የግንባታ ቁጥጥርና የማማከር ሥራ ያከናውናል፡፡

ከእነዚህ ኮንትራት ስምምነቶች በተጨማሪ ለአሥራ አንድ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የ28.09 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የኮብልስቶን ንጣፍ የመንገድ ሥራ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ መንደር የመንገድ መሠረተ ልማት ለማካሄድ ያስችላል የተባለው የኮብልስቶን መንገድ 6.05 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው፡፡ አሥራ አንድ ቦታ ተከፋፍሎ የተሰጠው የኮብልስቶን መንገድ ግንባታ በአንድ ኪሎ ሜትር ከ4.6 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያስወጣል ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ ከሥራ ተቋራጮቹ ጋር ውል የተፈጸመው 6.05 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ሥራን በአሥር ሜትር ስፋት ለማካሄድ የሚያስችል ነው፡፡ ግንባታው የውኃ መውረጃ መስመር ሥራን ጨምሮ መንገዱን እስከ ሰብ ቤዝ ማዘጋጀት ይሆናል፡፡ ይህም የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት አቅምን ለማሳደግ ተብሎ የተከፈተ የሥራ ዕድል መሆኑን፣ ከዚህ በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ሲሠሩ የነበሩ ኢንተርፕራይዞች ባለሥልጣኑ በሚያደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ ተቋራጭነት ሊያድጉ መቻላቸውን የባለሥልጣኑ መግለጫ ያመለክታል፡፡ ግንባታውም በሦስት ወራት የሚጠናቀቅ ነው ተብሏል፡፡ በዕለቱ ስምምነት ከፈረሙት 11 አነስተኛ ተቋማት ውስጥ ሁለቱ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ አልነበሩም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች