Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አክሰስ ሪል ስቴት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ደንበኞች ሥጋት ውስጥ ገብተዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአክስስ ሪል ስቴት ኩባንያ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደ አገር ከተመለሱ በኋላ አንዳች መፍትሔ ያመጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ኩባንያው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለመጀመሩ ሥጋት እንደፈጠረባቸው ቤት ገዢዎች ገለጹ፡፡

አቶ ኤርሚያስ መንግሥት የሕግ ከለላ ሰጥቶአቸው ከተመለሱ ስምንት ወራት ቢቆጠሩም፣ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ ባለመታየቱ ተስፋቸው በድጋሚ እየጨለመ መምጣቱን የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዢዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስ የአክሰስ ሪል ስቴት ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ለተቋቋመው በከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ለሚመራው ዓብይ ኮሚቴ ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን የዓብይ ኮሚቴው አባላት በተለያዩ የፓርቲና መንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ተጠምደው፣ ላለፉት አራት ወራት መሰብሰብ ባለመቻላቸው በዕቅዱ ላይ እስካሁን ውይይትም ሆነ ውሳኔ አልተላለፈም፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደጠቆሙት፣ ዓብይ ኮሚቴው ተሰብስቦ ውሳኔ ባለማሳለፉ አሁን በቦታው ላይ የሚገኙ አንዳንድ የቦርድ አባላትና የቤት ገዥዎች ተወካይ ነን የሚሉ ግለሰቦች በአክሰስ ሪል ስቴት ውስጥ ውዝግብ በማስነሳት ችግር እየተፈጠረ መሆኑ እንዳሳሰባቸው የቤት ደንበኞች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት፣ ዓብይ ኮሚቴው ውሳኔ ያልሰጠበት የዕቅድ ሰነድ እንደሚተነትነው አቶ ኤርሚያስ ከሦስት ኩባንያዎች ጋር ሲያካሂዱ የቆዩትን ድርድር አገባደዋል፡፡

የመጀመሪያው በአያት፣ በሲኤምሲ፣ በኒያላ ሞተርስ፣ በለቡና በመገናኛ አካባቢ ሰንራይዝ ሳይቶች የግንባታ ሥራዎችን በፍጥነት መጀመር ነው፡፡ በተለይ በመገናኛ ሰንራይዝ ያለው ግንባታ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ሊጀመር እንደሚችልና የሚገነባውም ግንባታ ወደ 19 ፎቅ ለማሳደግ መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ይኼንን ለማከናወን የሕንፃዎች ዲዛይን የተሠራ ሲሆን፣ ይህን ግንባታ ለማካሄደ ከቻይናው ሂቢል ፒንግ ሪል ስቴት ኩባንያ ጋር ሽርክና ለመፈጸም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን የአቶ ኤርሚያስ ዕቅድ ሰነድ እንደሚያስረዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ የቻይናው ሂቢል ፒንግ 60 ሚሊዮን ዶላር ለማቅረብ መወሰኑንና ገንዘብም ለቅረብ እንደሚቻልም ማስረጃ ማቅረቡን ምንጮች ጠቁመው፣ ይኼ ግንባታ ከተካሄደ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ቤት ገዢዎች እንደሚውል ማሳወቁን አስረድተዋል፡፡ 320 ቤቶች ያሉት የኒያላ ሞተርስ ሳይት ከአራት ወራት ግንባታው መጀመር የነበረበት ቢሆንም በችግር ፈጣሪዎች ምክንያት እስካሁን አልተጀመረም ተብሏል፡፡

ሌላኛው የአቶ ኤርሚያስ ዋነኛ አጋር እንደሆነ የተነገረለት የቻይናው ሲሲኢሲሲ ኩባንያ ነው፡፡ ይኼ ኩባንያ በሁለም ሳይቶች የቤቶች ግንባታ ለማካሄድ ማቀዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ በባቡር መስመርና በኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ የተሰማራ የቻይና ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡

ይኼ ኩባንያ የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርን ከፍተኛ አክሲዮን ለመግዛትና የሁሉንም የአክሰስ ሪል ስቴት ፕሮጀክቶች ለመገንባት ፍላጎት ማሳየቱን ለዓብይ ኮሚቴው በቅርቡ የቀረበ የዕቅድ ሰነድ ላይ መገለጹን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሲሲኢሲሲ የአክሰስ ሪል ስቴት ማኔጅመንት የሚረከብ መሆኑንም ሰነዱ ማብራራቱን ምንጮች ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ለአክሰስ ሪል ስቴት ግንባታዎች አስፈላጊ የሆኑ የገንዘብ አቅርቦትና የግንባታ አቅም የተገኘ መሆኑን፣ የአፈር ፍተሻና የሕንፃ ዳግም ዲዛይን ሥራ እንዲሠራ ኢቲጂ ተመርጧል፡፡ ኢቲጂ ይኼንን ሥራ በብድር ለመሥራት የተሰማማ መሆኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አክስስ በአብዛኛው የነበሩበት የቦታ ጉዳዮችና የፍርድ ቤት ክርክር በጥሩ ሁኔታ በመወጣት ላይ መሆኑን ለዓብይ ኮሚቴው የቀረበው ሰነድ እንደሚያመለክት፣ ነገር ግን አቶ ኤርሚያስ እነዚህን ችግሮት ለመፍታት ጥረት ቢያደርጉም፣ በተለይ በቦርድ ውስጥ ባሉ የተወሰኑ አባላት ችግር እየገጠማቸው መሆኑን፣ የቤት ደንበኞች የሆኑት እነዚህ ምንጮች መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሥራ አመራር ቦርዱ አቶ ኤርሚያስን ከቦርድ ሰብሰቢነት እንዳነሳቸውና የሥራ አመራር ቦርዱ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው አምስት ለሁለት በሆነ ድምፅ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም አቶ ኤርሚያስ የተነሱበት ቃለ ጉባዔ፣ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት አልተረጋገጠም ተብሏል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ቃለ ጉባዔውን እስካልተረጋገጠ ድረስ የቦርዱ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ መሆናቸው  ለዓብይ ኮሚቴው ተተንትኗል፡፡

 ነገር ግን አቶ ኤርሚያስ ከቦርድ እንደተነሱ ተደርጎ መነገሩ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር የሚያደርጉት ድርድር ላይ እንከን የሚፈጥር በመሆኑ፣ ዓብይ ኮሚቴው ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ የቤት ደንበኞችን ፍላጎት እንዲያሟላ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ቤት ገዢዎች በአሁኑ ወቅት የአክሰስ ሪል ስቴት ቦርድ ምን እየሠራ ነው? የቴክኒክ ኮሚቴውስ? የዓቢይ ኮሚቴው አባላት ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የአገር ጉዳዮች በመጠመዳቸው ምክንያት የአክሰስ ሪል ስቴት ጉዳይ ስለተዘነጋ፣ አሁን አዲሱ መንግሥት ከተመሠረተ ወዲህ ምን እየሠሩ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ ከውጭ ከመጡ በኋላ ተረጋግቶ የነበረው አክሰስ ሪል ስቴት አሁን ሥጋት እያንዣበበት ስለሆነ፣ አቶ ኤርሚያስ በየደረጃው ያቀረቡት ዕቅድና የሥራ አፈጻጸም በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ፣ ዓብይ ኮሚቴው በመንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ የቤት ገዢዎች ጠይቀዋል፡፡ በአክሰስ ሪል ስቴት ውስጥ ሥራ እያደናቀፉ ያሉና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ ሰዎችም በሕግ እንዲባሉ ዓቢይ ኮሚቴውን ተማፅነዋል፡፡

የዓብይ ኮሚቴ አባላት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር፣ የፍትሕ ሚኒስትር፣ የንግድ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴውም ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ ተወካዮች ናቸው፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ የንግድ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኑረዲን መሐመድ ናቸው፡፡ ዓብይ ኮሚቴው በቅርቡ ተሰብስቦ ውሳኔ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአክሰስ ሪል ስቴት ወቅታዊ ሁኔታና በቦርድ አባላትና የገዢዎች ወኪል ነን በሚሉ ግለሰቦች እየተፈጸመ ስላለው ጉዳይ አቶ ኤርሚያስ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች