Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅትን ወቀሰ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅትን ወቀሰ

ቀን:

– የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለማስተላለፍ እንቅፋት ሆኗል አለ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዳይከናወኑ፣ ዋነኛ እንቅፋት ሆኗል የተባለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ ወቀሳ ቀረበበት፡፡

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማኔጅመንትን ሲያስተዳድር የቆየው የህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን፣ ችግሩን ለመቅረፍ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

አቶ መኩሪያ ይህንን የተናገሩት ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ከመከፈሉ በፊት ሲንከባለል የመጣ ችግር ነበር፡፡ በተለይም ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ተከፍሎ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን የህንዱ ኩባንያ ከያዘው በኋላም ችግሩ ከመፈታት ይልቅ የበለጠ ተወሳስቧል፡፡

በአዲስ አበባ አስተዳደርና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መካከል የተፈጠረው ችግር ምክንያት ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታም ሆነ፣ ግንባታው ከተከናወነ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያለመኖሩ ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ እንኳ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 35 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ዕጣ ቢያወጣም፣ መኖሪያ ቤቶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊገባላቸው ባለመቻሉ ለተጠቃሚዎቹ ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ በቅርቡ ለነዋሪዎች ይተላለፉ የተባሉት 40 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ከ90 በመቶ በላይ ግንባታቸው ቢጠናቀቅም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊቀርብ ባለመቻሉ ብቻ ዕጣ ማውጣት አልተቻለም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም በግምገማው ወቅት እንደተናገሩት፣ 35 ሺሕ ቤቶችን ዕጣ በማውጣትና ባለማውጣት ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለበት በተካሄደ ውይይት ላይ፣ ድርጅቱ ዕጣው እንዲወጣ መተማመኛ ሰጥቷል፡፡ “ነገር ግን እስካሁን ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመቅረቡ ቤቱቹን ለዕድለኞች ማስተላለፍ አልቻልንም፤” ሲሉ አቶ ጌታቸው ድርጅቱን ወቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ከ90 በመቶ በላይ የተጠናቀቁትን 40 ሺሕ ቤቶች ዕጣ ለማውጣት ተቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ እየቀረበ ያለው ወቀሳ ሁለት መነሻ ምክንያቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ በሚካሄድበት ወቅት የኤሌክትሪክ ምሰሶና ትራንስፎርመር አለማቅረብ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞችና ዋነኛ የግንባታ ተዋናዮች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈው ለገነቧቸው ቤቶች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችሉ ግንባታዎችን በወቅቱ አለማካሄድና እንዲሁም ኃይል አለማቅረብ የሚሉት ችግሮች ናቸው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅት ለኃይል ግንባታ የሚሆኑ መሣሪያዎችና የኤሌክትሪክ ኃይል በበቂ ሁኔታ እንዳለውና እንደሌለውም በውል እንደማይታወቅ ባደረጓቸው የሥራ ግንኙነቶች መረዳት እንዳልቻሉ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ባለሥልጣናት በግምገማው ወቅት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የመሬት ዝግጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ወልደ ገብርኤል እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጀት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለበት ለማለት ያስቸግራል፡፡ ወ/ሮ ሃይማኖት ምክንያታቸውን ሲያድረዱ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ድርጅት በከተማው ውስጥ ሕገወጥ ግንባታ ላካሄዱ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል ያስገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ የጨረቃ ቤቶች በ2003 ዓ.ም. እንዲፈርሱ በተደረገበት ወቅት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልም ተቋርጦባቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕገወጦቹ ጨረቃ ቤቶቹን መልሰው የገነቡ በመሆናቸው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ገብቶላቸዋል በማለት ወ/ሮ ሃይማኖት ተናግረዋል፡፡

“በሕጋዊ መንገድ ግንባታ ላካሄዱ ግለሰቦችና ለኮንዶሚኒየም ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገባት አለመቻል ድርጅቱ የማኔጅመንት ችግር እንዳለበት የሚያሳይ ነው፤” ሲሉ ወ/ሮ ሃይማኖት ተችተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የህንዱ ኩባንያ የማኔጅመንት ጊዜውን አጠናቆ የተሰናበተ ሲሆን፣ በምትኩ በአቶ ጎሳዬ መንግሥቴ የሚመራ አዲስ ማኔጅመንት ተሰይሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ ችግሩን አምነዋል፡፡ አቶ ጎሳዬ እንዳስረዱት፣ የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኔትወርክ እንደገና መታየት አለበት፡፡ ከኔትወርኩ በተጨማሪም የአዳዲስ የማስተላለፊያና የማሰራጫ ጣቢያዎች ግንባታ መካሄድ አለበት፡፡ “የተነሱት ነጥቦችን ወስደን እናስተካክላለን” በማለት የተናገሩት አቶ ጎሳዬ፣ ‹‹የማኔጅመንት ችግሩን በመፍታት ከአስተዳደሩ ጋር እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛውን ዙር የቤቶች ዕጣ ያወጣው በሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ዕድለኞቹ ቤታቸውን መረከብ ሳይችሉ ሰባት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ ይህም ለተለያዩ ችግሮች እንደዳረጋቸው እየተናገሩ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...