Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳሊኒ የግንባታ ውል ሳይፈራረም በአዲሱ ጊቤ አራት የኃይል ፕሮጀክት ቁፋሮ መጀመሩ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታዎችን በማካሄድ የሚታወቀው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የግንባታ ውል ሳይፈራረም በጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሲቪል ምህንድስና ሥራ መጀመሩን ምንጮች ገለጹ፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አራትን በሚመለከት ሐምሌ 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ሰነድ (MOU) ተፈራርሟል፡፡ ነገር ግን የመግባቢያ ሰነድ የአዋጭነትና የዲዛይን ጥናቶችን እንዲያካሂድ እንጂ ግንባታ የሚያስጀምረው አይደለም፡፡

ነገር ግን ከሥፍራው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የአፈር ቆረጣ ሥራዎችን በማካሄድ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎችን እያካሄደ ነው፡፡

የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ኮሜርሻል መምርያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ብርሃኔ ለሪፖርተር እንደገለጹት ግን፣ ድርጅታቸው እየሠራ የሚገኘው ወደ ሳይቱ የሚወስደውን መንገድ እንጂ የሲቪል ምህንድስና ሥራዎችን አይደለም፡፡ ምንጮች በአቶ ሰለሞን አስተያየት አይስማሙም፡፡

ከሳሊኒ በተጨማሪ በጊቤ አራት ፕሮጀክት ላይ ጥናት እንዲያካሂዱ አምስት የቻይና ኩባንያዎች በደብዳቤ ተጠይቀዋል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ እነዚህ ኩባንያዎች የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ አዝማሚያ ሥራው እንደተሰጠው የሚያስመስለው በመሆኑ፣ እነሱ የሚያከናውኑት ጥናት ባዶ ልፋት እንዳይሆንባቸው ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ያገኛል የሚል እምነት መኖሩን የሚያመለክቱት ምንጮች፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዜ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በጊቤ አራት ፕሮጀክት ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረዋል ይላሉ፡፡

በዚህ ውይይት ሳሊኒ ለዚህ ፕሮጀክት ፋይናንስ እንደሚያገኝ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መተማመኛ መስጠታቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በዚህ ምክንያት ሳሊኒ ወደ ግንባታ ለመግባት እንደተደፋፈረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አንድ፣ ጊቤ ሁለት፣ ጊቤ ሦስትና ጣና በለስ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክቶችን ያካሄደ ግዙፍ ተቋም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምልክት በሆነው ዓባይ ወንዝ ላይ የሚካሄደውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በመሆን እየገነባ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሳሊኒ የገነባው ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ሰሞኑን ለሙከራ 70 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን፣ ሳሊኒ ቀጣይ ማረፊያውን ጊቤ አራት ላይ ማድረጉ ነው የሚነገረው፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፣ ለጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከውጭ አበዳሪዎች ይጠበቅ የነበረው ፋይናንስ በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ውትወታ ምክንያት ባለመገኘቱ፣ ሳሊኒ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት የጊቤ ሦስትን ሲቪል ምህንድስና ለማከናወን ተገዷል፡፡

ጊቤ አራት በደቡብ ክልል በቱርካና ሐይቅ አቅራቢያ የሚገነባ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት እውን ከሆነ ኢትዮጵያ 1,450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ጊቤ አምስት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ከተካሄደ የማመንጨት አቅሙ 600 ሜጋ ዋት እንደሚሆን የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጥናት ያመለክታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት ሊገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች