– የሪዮ ኦሊምፒክ 296 ቀናት ይቀሩታል
ከዛሬ ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተነሥተን ስንቆጥር በብራዚል ዘንድሮ የሚካሄደው የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ሊጀመር 296 ቀናት ይቀሩታል፡፡ የዓለም ሁሉ ዓይንና ጆሮ ወደ ብራዚላዊቷ መዲና ሪዮ ዲጂኔሮም ይሆናል፡፡
የዓለም ቁጥር አንድ ቡና አምራች በሆነችው ብራዚል በሚካሄደው 31ኛው ኦሊምፒያድ የቡና መሠረት የሆነችው ኢትዮጵያ እንዳለፉት ኦሊምፒያዶች ሁሉ ተወዳዳሪ ሆና ለመገኘት ቅድመ ዝግጅት መጀመሩ ይታወቃል፡፡
እንደ ማሳያ ባለፈው ዓመት ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች፣ ለቴክኒክ ኃላፊዎችና ባለሙዎች እንዲሁም ለሐኪሞች በስፖርት ሜዲስን ሥልጠና መሰጠቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ሌላ በብስክሌት ሁለት ተወዳዳሪዎች ፍቅረኛሞቹ ፅጋቡ ገብረ ማርያምና ሐድነት አስመላሽ እንደሚካፈሉ ተረጋግጧል፡፡
አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ካቢኔ መመሥረትና ስፖርት ኮሚሽንን ከወጣቶች ጋር ቀላቅሎና የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር መሆኑን ተከትሎ አዲሱ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች ጋር በኦሊምፒክ ኮሚቴው ጽሕፈት ቤት ምክክር አድርገዋል፡፡
ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በድረ ገጹ እንዳመለከተው፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ጥቂት ወራት ለቀሩት የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ስለኦሊምፒክ ኮሚቴው አደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓት ገለጻ የተደረገላቸው ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ከኮሚቴው ጋር ተቀራርበው እንደሚሠሩ፣ የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅትና ተሳትፎ አስመልክቶ ሚኒስቴሩ በተደራጀ አግባብ ድጋፉን እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡