‹‹ሰንደቅ ዓላማችን የሰው ዘር መገኛ፣ ራሱን ያላስደፈረ ሕዝብ መለያ የብዝኃነት መገለጫ ዓርማ ነው፡፡››
ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ለስምንተኛ ጊዜ በመላ አገሪቱ በተከበረበት ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝተው ካደረጉት ዲስኩር የተወሰደ፡፡ ‹‹በሕዝባዊ ተሳትፎ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ እየተጋች ያለች አገር ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል በዓሉ ሲከበር የአባት አርበኞች የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሰልፍ ትርዒት ሲያሳዩ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤትም ‹‹ምዕራፍ ብዙኃን›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ድራማ አቅርቧል፡፡ ረዥሙ ሰንደቅ ዓላማ እንደሆነ የተነገረለት ባለ 450 ሜትር ርዝመትና ሁለት ሜትር ከ10 ሣንቲም ቁመት ሰንደቅ ዓላማም በስታዲየሙ የመሮጫ መም ዙሪያ ተዘርግቶ ታይቷል፡፡