Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእጀኞችን ያፈራው ሠዓሊ ወርቁ ማሞ

እጀኞችን ያፈራው ሠዓሊ ወርቁ ማሞ

ቀን:

‹‹… አሁን በምን እጅ ተብሎ ቢናቅም፣ ፀንቶ ታሪክ ሠራ

እጅ የሌለው ወርቁ እጀኞች አፈራ››

ስለሠዓሊ ወርቁ ማሞ ከተሰነቁ ስንኞች አንዱ ነው፡፡ ሠዓሊው ልጅ ሳሉ የተቀበረ ቦንብ እጃቸው ላይ ፈንድቶ ነበር ሁለት እጆቻቸውን ያጡት፡፡ ለዓመታት በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ሥነ ጥበብ አስተምረዋል፡፡ አሁንም የሥነ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸውን ወጣቶችን ከማስተማር አልቦዘኑም፡፡ በሥራዎቻቸው ጎልተው ከሚንፀባረቁ መካከል እናትነትና ተፈጥሮ ይጠቀሳሉ፡፡  

የ81 ዓመቱ ሠዓሊና መምህር ወርቁ ሥነ ጥበብን በማስተማር አምስት አሠርታት አስቆጥረዋል፡፡ አያሌ የሥነ ጥበብ ልሂቃንን ስለማፍራታቸው እንዲሁም በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ተጠቃሽ ስለሆኑ ሥራዎቻቸው ለመዘከር፣ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የምስጋና መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ በዝግጅቱ ዛሬ አንጋፋ የሆኑ የቀድሞው የሠዓሊው ተማሪዎች፣ ወጣት ሠዓልያን እንዲሁም የሙያ አጋሮቻቸው  ስለ ሠዓሊው ተናግረዋል፡፡

ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ከአንጋፋዎቹ አንዱ ሲሆን፣ ሠዓሊውን የገለጸው ‹‹ወርቁ በጥበብ ዓለም ውስጥ በጀግንነት የተፈጠረ አንድና ብቸኛ ሰው ነው፤›› በማለት ነበር፡፡ ሠዓሊው በሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት (የአሁኑ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት) ካስተማሯቸው መካከል አንዱ ነው፡፡

በ1965 ዓ.ም. የአራተኛ ዓመት ተማሪ ስለሠዓሊ ወርቁ መምህራቸው እንደሆኑ ሲያውቅ የተሰማውን ያስታውሳል፡፡ ወርቁ ሁለት እጆቻቸውን በቦምብ ቢያጡም፣ ቡሩሽን ከሸራ ከማዋሀድ ወደ ኋላ አላሉምና፣ ቡሩሻቸውን በክርኖቻቸው መካከል ይዘው እሸቱና የክፍሉ ተማሪዎች ይመለከታሉ፡፡ በዚያ ቅፅበት ደስታና ድንጋጤ ተሰምቷቸው ነበር፡፡ ‹‹በአንድ በኩል እንዴት ነው የሚያስተምረን? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብን ነበር፤ ዝናውን ሰምተን ስለነበረ መምህራችን በመሆኑም ደስታ ተሰምቶን ነበር፤›› በማለት ያስታውሳል፡፡

ከትውስታዎቹ መካከል ሠዓሊው ለማስተማር የሚጠቀሙባቸውን ልዩ መንገዶች ያነሳል፡፡ ዛሬ ላይ እሱም ለማስተማር ከሚጠቀምባቸው መንገዶች ውስጥ የወርቁ ዘዬዎች እንደሚገኙበትም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹የመምህርነት አሻራው እስከዛሬ ድረስ ይታያል፤ ንፍገት የሌለው መምህር ነው፤›› ብሏል፡፡

ሠዓሊ ወርቁ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ትምህርታቸውን በሩሲያ ከተከታተሉ በኋላ ነበር፡፡ ሠዓሊ እሸቱም ለትምህርት ወደ ሩሲያ ባቀናበት ወቅት፣ ወርቁ በተማሩበት ተቋም ወደር ከማይገኝላቸው ተማሪዎች አንዱ እንደነበሩ መስማቱን አክሏል፡፡ በሌላ በኩል ለሠዓሊው የምስጋና መርሐ ግብሮች ከማሰናዳት ጎን ለጎን፣ ሥራዎቻቸው በሙዚየም መቀመጥ እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኰንን በበኩሉ፣ ‹‹ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልዕክት ዘወር ባለ አማርኛ መግለጹን አልረሳውም፤›› በማለት መምህሩን ያስታውሳል፡፡ ተማሪዎች ማስተካከል የሚገባቸውን እንዲያርሙ ለማድረግ፣ የሚጠቀሙበትን ልዩ መንገድ ከገጠመኞቹ ጋር አካፍሏል፡፡

ተያይዞ የተነሳው ሠዓሊው ሕይወታቸውን ተመርኩዘው ተማሪዎቻቸውን መቅረፃቸው ነው፡፡ ተማሪዎች እንዲሆኑ የሚነግሯቸውን ዓይነት ሰው ሆነው መገኘታቸውን ‹‹የሚመክረውን የሚኖር ሰው ነው፤›› ሲል ገልጿል፡፡ የሠዓሊውን ሥራዎች ሙዚየም ከማስገባት በተጨማሪ ስለ ሠዓሊው የሕይወት ተሞክሮ የሚያትት መጽሐፍ ቢዘጋጅ መልካም እንደሚሆን ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ‹‹እጆቹ ስለሌሉ አይደለም ጎበዝ ሠዓሊ ነው የሚባለው፤ እጅ ካላቸው በበለጠ ሠርቶ ስላሳየ ነው፤›› በማለት ሠዓሊው ያላቸውን ችሎታ ገልጿል፡፡

መርሐ ግብሩን ያዘጋጁት ሠዓሊው አሁን የሚያስተምሩበት አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ማሠልጠኛ ተቋም ከኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ጋር በመተባበር ነው፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሠዓሊ ሥዩም አያሌው፣ ‹‹መምህራችንና አንጋፋው ሠዓሊ ወርቁ፣ ለ50 ዓመታት በማስተማር ላበረከተው አስተዋጽኦ ለማመስገን ስለተሰናዳው ዝግጅት ለትምህር ቤቱ ምስጋና አቀርባለሁ፤›› ነበር ያለው፡፡

 የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ከበደ በበኩሏ፣ ሠዓሊው በአስቸጋሪ የጤና ሁኔታ ላይ ቢሆኑ እንኳን ከማስተማር ወደኋላ እንደማይሉ ተናግራለች፡፡ ‹‹ትውልድን በመልካም ሰብዕና በመቅረፅ ለዓመታት ያለማቋረጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የምስጋና ምሽት በማዘጋጀታችን ክብር ይሰማናል፤›› ስትልም አክላለች፡፡

ብዙዎችን በሥራዎቻቸው ማነሳሳት የቻሉትን እኚህ ሠዓሊ፣ በአንድ ወቅት ገጣሚ ታገል ሰይፉ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡፡

እጆቹን ቢያጣ እጅ አበቀለ

እልል በይ ጥበብ፣ ጉድ በል ተማሪ

እጁን ሲቀጥል እንደ ፈጣሪ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...