Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዳግም ያገረሸው የእስራኤልና የፍልስጤም ውዝግብ

ዳግም ያገረሸው የእስራኤልና የፍልስጤም ውዝግብ

ቀን:

በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል በቅርቡ ያገረሸው ብጥብጥ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በአንድ አካባቢ በሚኖሩት እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን መካከል ያለውን ታሪካዊ አለመግባባት ለመፍታት ከ23 ዓመታት በፊት የሰላም ስምምነት ወይም ‹‹ኦስሎ አኮርድ›› ቢፈረምም ለሕዝቡ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ሰሞኑን የተከሰተው በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለው አለመግባባትና ብጥብጥ፣ እ.ኤ.አ. ከ2014 የጋዛ ወይም በኢራቅና በሶሪያ ካለው ጦርነትና ግጭት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ በውስጡ ያመቀው ችግር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ብጥብጥ የሚያቀጣጥል ነው፡፡

23 ዓመታትን ያስቆጠረውና በእስራኤል የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሐቅ ራቢንና የፓለስታይን ሊብሬሽን ኦርጋናይዜሽን (ፒኤልኦ) መሪ በነበሩት ያሲር አራፋት የተፈረመው ስምምነት፣ በፒኤልኦ በኩል እስራኤል የምትባል አገር ስለመኖርዋ ዕውቅና የሰጠ፣ በእስራኤል በኩል ደግሞ ፒኤልኦ የፍልስጤማውያን ተወካይና ተጠሪ መሆኑን ያረጋገጠ ነበር፡፡ ስምምነቱ ፍልስጤማውያን ራስ ገዝ አስተዳደር እንደሚኖራቸውና ሕጋዊና የፖለቲካ መብት እንዳላቸው የሚያረጋግጥም ነበር፡፡ የኦስሎ አኮርድ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ሰላም ለማስፈን ታስቦ የተፈረመ ቢሆንም፣ ከ23 ዓመታት በኋላ በፍልስጤማውያን ወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት አጥቷል፡፡ የራስ ገዝ አስተዳደር ኖሯቸው በእስራኤል የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እየተረገጡና እየተገለሉ እንደሚኖሩ በመግለጽ ብሶታቸውን በብጥብጥ መግለጽ ጀምረዋል፡፡

የእስራኤል ፖሊሶችና ወታደሮች እንዲሁም አንዳንድ ሲቪሎች በፍልስጤማውያኑ ላይ ተነስተዋል፡፡ በዚህም እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን እየተገዳደሉ ነው፡፡ በሕዝቡ መካከል ፍርኃት ነግሷል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከመላክ ተቆጥበዋል፡፡ ሰዎች ከጥይት ባለፈም በሥለት አልያም በመስተዋት ቁራጭ ተወጋግተው መገዳደል ጀምረዋል፡፡

በእስራኤል የበላይነት የሚተዳደር የፍልስጤም ራስ ገዝ ሥርዓት ይብቃ በማለት ብሶታቸውን ለመግለጽ ጐዳና የወጡ፣ እንዲሁም በቤት ለቤት አሰሳ ብዙ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ በዌስት ባንክ፣ በምሥራቅ ኢየሩሳሌምና በጋዛ አንዳንድ ቦታዎች እየተቀጣጠለ ያለው ብጥብጥ እራኤልን ያጥለቀልቃታል ሲሉ፣ በእስራኤል የሚገኙ የፍልስጤማውያን መሪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ወር የተስተዋለውም ብጥብጡ መስፋቱና ዓይነቱን መቀየሩም ነው፡፡ ግለሰቦች ይገዳደላሉ፣ ሲቪሎች ፖሊሶችንና የፀጥታ ኃይሎችን ያጠቃሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ይሰማ የነበረው የእስራኤል ፖሊስ ፍልስጤማዊን ገደለ ወይም ፍልስጤማዊ እስራኤላዊን ገደለ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ መሳ ለመሳ ሆኗል፡፡ ሰዎች በሥለት ተወግተው ሲገደሉም ተስተውሏል፡፡ የፍልስጤማውያኑ በተለይም የወጣቶቹ ምሬት በእጃቸው እንደ ቀድሞው ድንጋይ ብቻ ሳይሆን ጩቤን አስጨብጦ መጥቷል፡፡ አንዳንድ ሲቪል እስራኤላውያንም ፍልስጤማውያንን በመግደል መሳተፍ ጀምረዋል፡፡

አልጄዚራ እንደዘገበው፣ ባለፈው ሰኞ አንድ ኤርትራዊ በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎችና እስራኤላውያን ተደብድቦ ተገድሏል፡፡ የተገደለው በ19 ዓመቱ የእስራኤል ወታደር ላይ ግድያ ፈጽሟል ተብሎ ተጠርጥሮ ቢሆንም፣ የ29 ዓመቱ ሀብቶም ዘሪሁን ከደሙ ንፁህ ነበር ተብሏል፡፡ እሑድ ምሽት በቤርሳቤህ በሚገኝ አውቶቡስ ማቆሚያ ሥፍራ አውቶቡስ እየጠበቀ ነበር የእስራኤል ፍልስጤማዊ የሆነ ግለሰብ መሣሪያና ጩቤ ይዞ አንድ የእስራኤል ወታደር በመግደል፣ አሥር ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው፡፡ በአካባቢው የነበረው ኤርትራዊ በደኅንነት ሠራተኛ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ሲወድቅ፣ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተደርበው ቀጥቅጠውታል፡፡ የደኅንነት አካላትም አብረዋል፡፡ ኤርትራዊው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ እውነተኛ የወታደሩ ገዳይ እሱ እንዳልነበረ በምርመራተረጋግጧል፡፡

በእስራኤል የዚህ ዓይነቱ ክስተት ተበራክቷል፡፡ ንፁኃን በማያውቁት እየተገደሉ ነው፡፡ እስራኤል ለሕዝቦቿ ደግሞ የሥጋት ምድር ሆናለች፡፡ ከዚህ ቀደም ለፀጥታ ኃይሎች የነበረው መብት ወደ ሕዝቡ ሰርፆ፣ ያጠቃናል ያሉትን መግደልና መደብደብ ጀምረዋል፡፡ ፍልስጤማውያንና እስራኤላውያን የአንድ ወንዝ ልጆች ቢሆኑም፣ ዓረብና እስራኤል የሚሉ ልዩነቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ጐልተው ታይተዋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በእስራኤል ዘረኝነት ነግሷል፣ የኤርትራዊው ግድያም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ይላል፡፡ በኤርትራዊው ሞት ከደኅንነት አካላት ውጪ ሲቪሎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ጉዳዩ ከመንግሥት አቋም ጋርም ይገናኛል ሲል ነው አምነስቲ መግለጫውን የሰጠው፡፡

በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት መቆጣጠር የእስራኤል ደኅንነት አካላት ኃላፊነት ቢሆንም ሲቪሎች እጃቸውን እያስገቡ ነው፡፡ በእስራኤል ከዘረኝነት ባለፈም የውጭ ዜጐችን የመፍራት ሁኔታ እየተንፀባረቀ ነው፡፡ ይህም አገሪቷን ለከፋ ብጥብጥ ይዳርጋታል ተብሏል፡፡

የኢየሩሳሌም ከንቲባ ኒሯ ባርካት፣ መሣሪያ ያላቸው እስራኤላውያን በሙሉ ራሳቸውን ከሥለትና ከመሣሪያ ጥቃት ለመከላከል ሁልጊዜም ታጥቀው እንዲዘዋወሩ መግለጻቸውን ተከትሎም፣ እስራኤላውያን ሲቪሎች በፍልስጤም ላይ ተነስተዋል፡፡ ፍልስጤሞችም እንዲሁ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1993 እስራኤል እንደ አገር ፍልስጤም እንደ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሆኑ ያስቻለው የኦስሎ ስምምነት በአንድ አገር የሚገኙትን ሁለት ሕዝቦች እኩል መዳኘት አልቻለም፡፡ ፍልስጤሞች የራስ ገዝ አስተዳደር ይኑራቸው እንጂ ደኅንነቱ፣ ወታደሩ ሁሉ የተያዘው በእስራኤላውያን ነው፡፡ ይህንን በተለይም ከስምምነቱ በኋላ የተወለዱ ፍልስጤማውያን ወጣቶች አይቀበሉትም፡፡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ወይም ፍልስጤማውያን እስራኤሎች በስምምነቱ ሁለተኛ ዜጋ ሆነው እንደተቆጠሩ ይናገራሉ፡፡ ፍልስጤሞች የሚፈልጉትን መሪ መምረጥ አይችሉም፡፡ በእስራኤል ባሉ ሕጐች ለመዳኘትም ልዩነት ይደረግባቸዋል፡፡ ወደ ዌስት ባንክና ጋዛ የሚገባም ሆነ የሚወጣ ፍልስጤማዊ የሚደረግበት ቁጥጥርም የጠነከረ ነው፡፡

ከኦስሎ ስምምነት በፊት የነበሩ ፍልስጤማውያን ስምምነቱን በየዋህነት ቢቀበሉትም፣ ለአሁኑ ትውልድ አልዋጥ ብሏል፡፡ እኩልነትን ሳይሆን የበታችነትን ያጐናፀፈ ስምምነት ሲሉም ያጣጥሉታል፡፡ በመሆኑም በብጥብጡ ሙሉ ለሙሉ እየተሳተፉ ያሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ብጥብጥም የሞቱት ከ23 ዓመት በታች ያሉ ፍልስጤማውያን ወጣቶች ናቸው፡፡

በአንድ አገር የሁለት መንግሥታት መፍትሔን ይዞ የመጣው የኦስሎ አኮርድ፣ በአሁኑ የፍልስጤም ትውልድ ተቀባይነት አጥቷል፡፡ ‹‹በደል ውስጥ ከርመናል›› የሚሉ ፍልስጤማውያን ወጣቶችም በብጥብጡ እንዲሳተፉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ፍልስጤማውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ብጥብጡ ተጋግሏል፡፡ ላለፉት ሦስት ሳምንታት በነበረው ብጥብጥ 41 ያህል ፍልስጤማውያንና ስምንት እስራኤላውያንም መሞታቸው ይነገራል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን፣ በእስራኤል በተነሳው ብጥብጥ እስራኤላውያን ምን ያህል እንደተጨነቁና በፍልስጤሞች ላይ እንደተነሱ፣ ከዚሁ ጐን ለጐንም ፍልስጤሞች የነበራቸው የሰላም ተስፋ በተለያዩ ጊዜያት እንደተኮላሸና በየጊዜው በእስራኤል በኩል በሚካሄዱ የሠፈራ ፕሮግራሞች እንደተበሳጩ ገልጸዋል፡፡ አሁን የተጀመረው ብጥብጥ ግን የሁለቱንም የሰላም ፍላጐት እንደማያሳካ፣ ይልቁንም ለከፋ ግጭት እንደሚዳርግና የመካከለኛው ምሥራቅን ወደ አዘቅት ሊከት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፈታኝ በሆነው በአሁኑ ጊዜ ብጥብጥን በቃ ልንለው ይገባል፤›› ብለዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...