Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መሟገትስ ከራስ ጋር!

እነሆ ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። እግርን የሆድ ነገር እያደከመው የሆድ ነገር ያስጉዘዋል። መንገዱ ላይ በርትተው በሙላት ከታተሙ ዳናዎች ይልቅ ዝለው ቀለማቸው የፈዘዙ ይበዛሉ። አቧራና ፀሐይ  የሚያበሳጫቸው ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የጭቅጭቅ ጦራቸውን ይሰብቃሉ። ለተቺና ለአቃቂር አውጪ አብዝተው የሚያፏጩና የሚያጨበጭቡ ይበዛሉ። ከሆታ ትርምሱ መሀል ታክሲያችን ውስጥ ከተሰየምነው ጥቂት ተሳፋሪዎች አንዱ፣ “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል አሉ እውነት ነው! ባልበላ አንጀታችን የምንቸልስበት አንሶ ጭራሽ ከነገር ብናፀዳውማ አንድ ቀንም አናድር፤” ይላል ጎልማሳው ተሳፋሪ። “ህም ያዳማጭ ያለህ እያልን ጆሮ የሚሰጠን ሰው እናስሳለን አንተ ከነገር በፀዳ ሆድ መቸለስ እንዳትጀምር ትፈራለህ? ኧረ እንዴት ያለ ዘመን ላይ ነን እናንተ። ግራ አሳይቶ ቀኝ፣ ቀኝ አሳይቶ ግራ ላይ የሚመታን በዛ እኮ፤” አለ ከጎኑ የተቀመጠው ወዳጁ የአትክልት ነጋዴ።

“ቻለው ዘመኑ የመቻቻል ነው፤” አለች ደግሞ ጋቢና ብቻዋን የተሰየመች ወጣት። “ታዲያ ምን እናድርግ በአንዱ ችግር ላይ ሌላ ችግር ሳይረገዝ እየተወለደብን፣ ቀኑ በውይይትና  በጥቆማ ምንም ሥራ ሳንሠራ እያለቀብን እኮ ነው፤” አለ ጎልማሳው ወደ ወዳጁ ዞሮ። ታክሲያችን ቀስ በቀስ እየሞላች ነው። ወግ አሳዳጁና ነገር አነፍናፊውም እንደዚያው ጆሮው እየተከፈተ ነው። ካሰበበት ለመድረስ የትራንስፖርት ችግር መላ ቅጡን ያጠፋበት ነዋሪ እግረ መንገዱን የኑሮውን እንቆቅልሽ ማብላላት የሰርክ ግዳጁ የሆነበት ይመስላል። እያንዳንዱ እንደ ማንነቱ የሚቀዝፈው የሐሳብ ማዕበል ላይ ተሰፍሮም ቢሆን የሚለው አያጣም፡፡ ወያላው ታክሲያችን መሙላቷን ሲያረጋግጥ ሳበው ብሎ ዘጋ። ‘ተው ሳበው ሳበው ሳበው መሸብኝ፣ የጆቢራ ራት ግብር አለብኝ’ እንዳለው አዝማሪ ለዕለት ጉዳዩ ያልቸኮለ የለም። መቼ ቸኩለንስ ሆነልን?

መንቀሳቀስ ጀምረናል። የሾፌሩ አነዳድ ከመነሻችን አወዛጋቢ ሆኗል። “ምነው ወዳጄ ገና ሳንጀምረው ተናገሩ እያሉ አናግረው እንደሚያደናግሩን ሰዎች ታሳቅቀን ያዝክ? ምን አጠፋን?” አለው ከወጣቷ አጠገብ ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪ። “ገና በቅርብ ነው ትንሽ መኪና መያዝ የጀመርኩት የከባድ መኪና ሾፌር ነበርኩ። አይዞን ቀስ በቀስ አስተካክላለሁ እ? እንኳን ይኼን ገዢው ፓርቲያችን ስንቴ ነገር ሲያበላሽ የማርያም መንገድ እየሰጠን አይደል እንዴ የኖርነው?” አለው። የሾፌሩ መልስ አሰጣጥ ወጣቱ ተሳፋሪ ‘ፖለቲካና ኮረንቲ’ በሩቁ ባይ ከሆነ ከዚህ በላይ አይቀጥልም ይመስላል። ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ሆነና አረፈው። “እኔን የሚገርመኝ ግን ሌላ ነው። ከቀላል ወደ ከባድ መሄድ አንድ ነገር ነው። ከከባዱ ወደ ቀላሉ መውረድ ግን እንዴት ነው የሚከብደው? በመስዋዕትነት ለዴሞክራሲ ከታገሉ ወዲያ ሁሉ በእጅ ሁሉ በደጅ ሲሆን፣ እንደገና ወደ ኋላ?” ቢል ወጣቱ ተሳፋሪ ሾፌራችን ባልሰማ ወደ ወያላው ዞሮ፣ “እስኪ ከበለጬህ አካፍለኝ በደሌን ልርሳበት፤” አለው። ተሳፋሪዎች ፈገግ አሉ።

ልጁ ሊያነሳ የሞከረው ጨዋታ ተቀባይ አጣ ሲባል መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ ተሳፋሪዎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የምትመስል ወጣት፣ “ይመስለናል እንጂ ተቀምጦ እንደ ማውራት ሁሉም እንደሚቀል፣ ቦታው ላይ ብንሆን እንዴት በከበደን፤” አለች በግጥም። ወዲያው አንድ ዕለት አጠገቤ ተቀምጦ፣ “መቼም ዘንድሮ በአጋጣሚም ይሆን በአገጣጣሚ ገጣሚው በዝቷል፤” ያለኝ ተሳፋሪ ትዝ አለኝ። እሱን ሳስብ አጠገቤ ተቀምጣ የነበረች ወይዘሮ፣ “ሰማህ ወይ ‘ኮብልስቶን’ ማንጠፍ ተረሳና ግጥም ተራውን አዲስ የሥራ መስክ ተብሎ ታወጀ እንዴ? ገጠምኩኝ ብሎ በሰላላ ሐሳቡ እየሰለለ እኛንም ስለሉ የሚለን በየሄድንበት አላስቀምጠን አለ እኮ! እንዴት ነው ነገሩ?” ብትለኝ ያ ያስታወስኩት ተሳፋሪ የላካት መስሎኝ ክው አልኩ። እንዲህ ውስጥ ለውስጥ መናበብ እየቻልን ግን ጥያቄያችን ብዙ መልሳችን ዝምታ የሆነው ለምን ይሆን ግን?

ታክሲያችን መብራት ይዟት ቆመች። ከታክሲያችን አጠገብ ውኃ የመሰለች ዘመናዊ አውቶሞቢል የሚያሽከረክር ጎልማሳ በሞባይል ስልክ ያወራል። ወያላው መስኮቱን ስለከፈተው የሚያወራውን ጥርት ብሎ ይሰማል። “ስማ ዛሬ የት ነው የምንቆርጠው? የትላንትናው ሥጋ ቤት አልተመቸኝም፤” ይላል። “እስኪ ማን ነህ መስኮቱን ዝጋው! እዚህ አገር በቃ መብላትም መፆምም አይቻልም?” አለች ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ አጠገብ ነጠላ የለበሰች አክፋይ መሳይ። “እንዴት ይቻላል? ክፍልፋዩ ከበዛ እኮ ቆየ። ለዚያም አይመስልሽም ፉክክሩ አላስቀምጥ ያለው?” አለቻት ተማሪዋ። “የምን ፉክክር?” ቀልቧን ስባት ኑሮ ለጨዋታዋ ጓጉታ ስትጠይቃት አጠገቤ የተቀመጠችው ወይዘሮ ጣልቃ ገባች።

“የሁሉም ነገር! ኑሯችንም የሞት የሽረት የሆነው ለዚህ እኮ ነው። እከሌ አንድ መኪና ገዛ፣ እኔ ሁለት መኪና ካልገዛሁ፣ እከሌ ኮንዶሚኒየም ቤት ገዛ፣ እኔ ፎቅ ቤት ካልሠራሁ፣ እከሌ አገባ እኔም ካላገባሁ። በቃ! ፉክክር። ሌላው እንዳይገርምሽ ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ብዙ ገንዘብ በሚከፈልበት ትምህርት ቤት የሚፎካከሩ ሰዎች ሆነናል እኮ። ስለዚህ ‘የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል’ ሆኖ፣ ራሱን ሆኖና መስሎ የሚኖር ሰው በባትሪ ፈልጎ ማግኘት በሙስና ያልጎደለ ካዝና ያለው መንግሥት መሥሪያ ቤት ፈልጎ እንደ ማግኘት ሆኗል፡፡ ከመፎካከር መመካከሩ ሳይሻለን አይቀርም፤” አለቻት። ይኼኔ ደግሞ ከአትክልት ነጋዴው አጠገብ የተቀመጠው ጎልማሳ የበኩሉን፣ “ብቻ አምላክ ፀሎታችንን ሰምቶ እንዲመልስልን ከአፋችን በላይ ልባችንን ማፆም መልመድ ነው ዋናው። ከወንድሙ ተጣልቶ ካልገደልኩ እያለ መሣሪያውን ይዞ ሲወጣ ሚስቱ ‘እሺ ባይሆን ባዶ ሆድህን አትሂድ እህል ቅመስ’ ብትለው፣ ‘ምን አልኩሽ ፆም መሆኑን ረሳሽው?’ እንዳለው ገበሬ እንዳንሆን ከስሜት ይልቅ ዕውቀት ያብዛልን። እምነታችን ሕይወት እንዲኖረው እሱ ይርዳን!” ብሎ ሳይጨርስ ወዳጁ አትክልት ነጋዴ ቀበል አድርጎ፣ “አቦ የሰው ገበያ አትዝጋ!” አለው። ታክሲያችን በሳቅ ሁካታ ተነቃነቀች።         ወያላችን ሒሳብ ተቀብሎ ሳይጨርስ ሦስተኛው መቀመጫ ላይ የነበሩ እንስቶች ‘ወራጅ’ ብለው ወረዱ። ወዲያው አንዲት ጠና ያለች ሴትና ወጣት ልጅ ገብተው ተሳፈሩ። ጉዟችን ቀጠለ። ሴቲቱና ወጣቱ ከደጅ የጀመሩትን ጨዋታ እያፋፋሙት ነው። “እና እንዴት ነህ? እኔም ሳልጠይቅህ ይኼውልህ ጠፋሁ። አይሞላ የዛሬ ጊዜ፤” ትለዋለች። “አይ አክስቴ እኔ ነበርኩ መጠየቅ የነበረብኝ እንጂ፤” ብሎ ሒሳብ ሊከፍል ሲል ትንሽ ተጨቃጭቀው የዘረጋውን ብር አጥፎ ኪሱ ከተተው። “እንዴት ነው ታዲያ እስካሁን አልመጣችም?” አለች አክስትየው ለአፍታ ዝም ብላ ቆይታ። “ማን?” አለ ወጣቱ ስላልገባው። “ልጅት ናታ! ለብቻ ኑሮ እስከ መቼ ነው? ጥሩ ሥራ ይዘሃል። ይኼው ብቻህን ስንት ዓመት ባዶ አልጋ እያሞቅክ ትኖራለህ? ሁሉንም ነገር ልመድ። ብቻ መኝታ ግን አልመክርህም፤” ስትለው የሰማው ወያላ፣ “እኔ የምለው አክስቶች በሙሉ የአርሰናል ደጋፊዎች ናቸው እንዴ? ያገኙትን ሁሉ ካላገባህ እያሉ ለማግባባት ሲደክሙ የሚውሉት?” ብሎ አጉተመተመ። የሰማነው በሙሉ በሳቅ ትንታ እኔን እኔን ተባባልን። ወጣቱ አክስቱን ዓይኗን ማየት አፍሮ፣ “መቼ ጠላሁ ብለሽ ነው! ግን ያው ሁሉም በጊዜው ነው የሚሆነው። ጊዜን መጠበቅ ነው ብዬ አለሁ፤” አላት። ጎልማሳው፣ “እውነት ነው ጊዜን መቅደም ቢቻልማ ዓባይን በአንድ ቀን ገድበን፣ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ አሠልፈን፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን አስፍተን፣ ሙሰኛውን ጠራርገን፣ ፕሬሱን በነፃነት ኑር ብለን እፎይ አንልም ነበር? ጊዜ ጠላት ሆነብን እንጂ ሥራማ ነበረን። ግድ የለም ችግራችን ሁሉ በሒደት ይቀረፋሉ ብለን ተስፋ ስናደርግ ቀናው ይገጥመናል፤” ብሎ ቁጭቱን ወደ ሌሎቻችን አስተላለፈብን። መቼም ደህና ነገር የሚያስተላልፍባችሁ ሰው የለም ዘንድሮ!   

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጎልማሳውና አትክል ነጋዴው ማታ በመጠጥ ስላጠፉት ገንዘብና ስለሠሩት ሥራ የግላቸውን ጨዋታ እየተጫወቱ ይሳሳቃሉ። “ጉድ ነው አንዳንዱ ሰው በቀን የማታ ታሪኩና ጨዋታው ትዝ ይለዋል። አሁን በዚህ ኑሮ እንኳን የማታ አስተዳደርህ የቅድሙ አረማመድህ ይታወስሃል?” የምትለኝ አጠገቤ ያለችው ወይዘሮ ናት። ይኼን ስትል አክፋይዋ ወጣት ብትሰማት ደግሞ “አልጋ፣ ጠፍቶ እንጂ አሁኑኑ ተኝቶ መታከም ያለበት የአዕምሮ ሕመምተኛ ብዛት በአገራችን 1.8 ሚሊዮን ነው መባሉን አልሰማችሁም?” ብላ ጮኸች። አንዳንዶች እንደ መደንገጥ ብለው ዞረው አዩዋት። “እውነቴን ነው አልጋ ጠቦን እንጂ ቆመን ስንጓዝ ብርቱ እየመሰልንና  ልብስ ስንት ጉዳችንን እየሸፈነልን እንጂ የታመምነው እኮ እልፍ ነን ጎበዝ!” አለች። “ታዲያስ! አለ ስንል የለም እያሉን፣ መጣ ስንለው ሄደ እያሉን፣ አለቀ ያልነው ገና ተጀመረ እየተባለ በመብራት፣ በትራንስፖርት፣ በመልካም አስተዳድር፣ በሥራ እጦት፣ በዚያ ላይ የኑሮው ውድነት ተጨምሮ፣ ቆመን መሄዳችን እኮ ተዓምር ነው!” ብሎ ከአክስቱ ጋር የተቀመጠው ወጣት ተናገረ። ታክሲያችን ለመቆም ቦታ እየያዘች ነው። ወያላው “መጨረሻ” ሲለን አጠገቤ ተቀምጣ የነበረችው ወይዘሮ፣ “አልጋው ጥቂት ታማሚው ብዙ!” ብላኝ ወደምትሄድበት ተጣደፈች። እስካሁን ድረስ ዝም ብለው የነበሩ አዛውንት ወደ በሩ እያመሩ፣ “ጎበዝ ኧረ በባንዲራው? ምንድነው እንዲህ መንጨርጨር? እስካሁን እኮ ችግራችሁን ብቻ ነው የምትለፈልፉት፡፡ ‘እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት ከማለት ይልቅ፣ አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ?’ የሚሉት ቧልት ደስ አይልም፡፡ ‘ሰው የሚያጭደው የዘራውን ነው’ ሲባል አልሰማችሁም? አዎን! የሚታጨደው የተዘራው ብቻ ስለሆነ ትልቁ ነገር ራስን መሞገት ነው፡፡ ከራስ ጋር ሙግት ይገጠም…” እያሉ ሲሰናበቱን እኛም ወደ ጉዳያችን አዘገምን፡፡ መልካም ጉዞ!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት