– በጥጥ ላይ ያተኮረው ዓለም አቀፍ ጉባዔ እዚህ ይካሄዳል
በአገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሚጠቀሱት መካከል የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ወይም የስፌት አምራች ፋብሪካዎች ይገኙበታል፡፡ የእነዚህ ፋብሪካዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 130 መድረሱም ይነገራል፡፡ ይሁንና እነዚህን ተቋማት በጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከሚመግቡት መካከል ትልቁን ቦታ የሚይዘው የግብርናው ዘርፍ ሲሆን፣ በተለይ የጥጥ ምርት ገዘፍ ያለ ድርሻ አለው፡፡
በአገሪቱ በጥጥ አምራችነታቸው ከሚታወቁት አካባቢዎች መካከል አፋር፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለጥጥ ምርት የተመቹ ቢሆኑም የሚፈለገውን ያህል ምርት ለፋብሪካዎች ማቅረብ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ የምርት እጥረት ብቻም ሳይሆን የዋጋና የጥራት ጥያቄዎች በጥጥ አምራቾችና በጨርቃ ጨርቅ አምራቾች መካከል ያለው መፋጠጥ በተለይ ምርቱ ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ጎልቶ ሲወጣ እየታየ ብዙ ሲያነታርክ፣ በድርድር ዋጋ እንዲወሰን የተደረገበት ጊዜም የቅርብ ትዝታ ነው፡፡
ከጥቂት ቀናት በፊት የጥጥ ዋጋን በሚመለከት ከሪፖርተር የተጠየቁት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ምላሽ አላቸው፡፡ እንደ አቶ ስለሺ ማብራሪያ በአገሪቱ ያለው የጥጥ ምርትና የሚሸጥበት ዋጋ ከዓለም ገበያ አኳያ ሲታይ የተዛባና የማይዳኝ ሆኖ ያስቸገረ ነው፡፡ ‹‹ጥጥ ዓለም አቀፍ ሸቀጥ በመሆኑ በዓለም ገበያ የሚዳኝ ቢሆንም በእኛ አገር ያለው ግብይት ግን ዘመናዊ ስላልሆነ መዛባት አለ፡፡ ከውጭ የሚመጣው ጥጥ ሁሉንም ወጪውን ችሎ በኪሎ 39 ብር ሲሸጥ የአገር ውስጥ ጥጥ ግን በኪሎ 46 ብር እየተሸጠ ነው፤›› ያሉት አቶ ስለሺ፣ እርግጥ የማምረቻ ወጪው ከፍተኛ መሆን ብቻም ሳይሆን ዘርፉ የሚገባውን ድጋፍ ስለማያገኝ ዋጋው እንደሚንር አብራርተዋል፡፡
ዓምና በየካቲት ወር በተካሄደው የጥጥ አምራቾች፣ መዳመጫ ባለንብረቶችና ላኪዎች ማኅበር ዓመታዊ ጉባዔ ወቅትም የጥጥ ዋጋ አከራካሪ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የጥጥ ዋጋ 45 ብር እንደነበር ተነግሯል፡፡ ይሁንና የዓለም ዋጋ 35 ብር በመሆኑ የአገር ውስጥ የጥጥ መሸጫ ዋጋን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ሲቃወሙ እንደነበረም ይታወሳል፡፡ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ይህንኑ በመግለጽ ተቃውሟቸውን እንዳሰሙ አይዘነጋም፡፡ እርግጥ እንዲህ ያለው ጥያቄ ካቻምናም ተስተጋብቶ ነበር፡፡
ጥጥ አምራቾች በበኩላቸው ካቻምና የጥጥ ዋጋ ተወደደ ተብሎ በግድ ዋጋ እንዲቀንሱ መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ጥጥ በገፍ አምርተው የሚገዛ በማጣታቸው ምክንያት ግን ከጥጥ ምርት እየወጡ ስለመሆናቸውም ሲገልጹ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በአንፃሩ ዓምና በነበረው የጥጥ ምርት መጠን ላይ ከ50 ሺሕ ቶን በላይ እጥረት ማጋጠሙ የሚታወሰን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ይጠበቅ ከነበረውና ይለማል ከተባለው መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ 60 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ብቻ ሊገኝ እንደሚችል፣ ከዚህም ሊያንስ ወይም ሊጨምር እንደሚችል አቶ ስለሺ ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹የጥጥ ልማት ዘንድሮ ተደናቅፏል፡፡ በዝናብ መዘግየት ምክንያት የጥጥ ምርት ቀንሷል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ የተዘራው የጥጥ ሰብል በመምከኑና ማሳዎችም ወደሌላ ቶሎ ወደሚበቅል ምርት ፊታቸውን በማዞራቸው የጥጥ ምርት ዘንድሮ በእጅጉ እንደሚቀንስ አስታውቀዋል፡፡
ከአፋር፣ ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከደቡብ ክልልና ከሌሎች ጥጥ አምራች አካባቢዎች የተወከሉ ኩባንያዎች ከዚህ በፊት ባቀረቡት ቅሬታ መሠረት መንግሥት የጥጥ ምርትን ችላ ብሎታል፡፡ ከአፋር ክልል የመጡ ጥጥ አምራቾች፣ አዋሽን የሚገድበው አጥቶ እንዲሁ በባዶ ሜዳ እየፈሰሰ፣ የጥጥ ማሳቸው ውኃ በማጣት ምርት መታጎሉን ጠቅሰዋል፡፡ ከደቡብ ኦሞ ዞን የመጡ ባለሀብትም ከወይጦ ወንዝ ውጭ ሌላ የውኃ ምንጭ ማግኘት ስላልቻሉ 38 ሔክታር መሬት ላይ የዘሩት ጥጥ ምርት ሳይሰጥ ሙሉ በሙሉ መድረቁን በስብሰባው ወቅት ለተገኙት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሠ ኃይሌ ገልጸውላቸዋል፡፡ በመሆኑም የወይጦ ወንዝ ውኃ ሥርጭትና ክፍፍል መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
መንግሥት በ2007 በጀት ዓመት፣ 98 ሺሕ ሔክታር መሬት መልማቱን፣ ከዚህ በመነሳት 60 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ለፋብሪካዎች ሊቀርብ እንደሚችል የገለጹት፣ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባንቴ ካሴ ምኅረቱ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ባንቴ እንዳስታወቁት፣ ከ60 ሺሕ ቶን ውስጥ አሥር ሺሕ ያህሉ ለአገር ውስጥ ባህላዊ አልባሳት ምርት የሚውል በመሆኑ፣ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚቀርበው 50 ሺሕ ቶን ብቻ ሲሆን፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ግን 100 ሺሕ ቶን ጥጥ እንደሚፈልግ ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመሆኑም የአቅርቦት ክፍተቱን ለመሙላት ቀሪው 50 ሺሕ ቶን ጥጥ ከውጭ መምጣት እንዳለበት አስታውቀው ነበር፡፡ በጥጥ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ምርት እያቆሙ ነው ያሉት አቶ ባንቴ፣ እስካለፈው ዓመት የካቲት ወር ድረስ ከ3,500 ቶን በላይ ጥጥ ከውጭ መግባቱንም ገልጸው ነበር፡፡
ግሎባል አሊያንስ ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ (ጌይን) የተባለው የአሜሪካ ድርጅት በበኩሉ መንግሥት በጥጥ ዋጋ ላይ የጣለውን ቁጥጥር አጥብቆ እንደሚቀጥል ማስታወቁን ይህም በደላሎች አማካይነት የሚጨምረውን የጥጥ ዋጋ ለመከላከል ያደረገው እንደሆነ መግለጹን ይፋ ባደረገው ሪፖርት አካቷል፡፡ በማሳ ላይ የጥጥ ዋጋ በኪሎ ከ30 እስከ 38 ብር (ጌይን በኩንታል እንደሚሸጥ ያሰፈረው ስህተት እንደሆነ ይታሰባል) ሲሆን፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ግን ከ50 እስከ 60 ብር በማውጣት ለመግዛት በመገደዳቸው የዋጋ ቁጥጥር በጥጥ ምርት ላይ እንደሚደረግ መንግሥት መግለጹን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ጥጥ አምራቾች፣ የዓለም የጥጥ ዋጋ ቢቀንስም አገር ውስጥ የሚሸጡበትን ዋጋ ለመቀነስ እንደማይፈልጉ፣ ይህም ደግሞ ከማምረቻ ወጪ ከፍተኛነት በመነሳት እንደሆነ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በአንፃሩ መንግሥት የጥጥ መሸጫ ዋጋን በመተመን መንቀሳቀሱንም ሲተቹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የፋይናንስ አቅማቸው ደካማ ስለሆነ መንግሥት ከውጭ አምጥቶላቸው ቀስ ብለው መክፈል የሚችሉበት ላይ ትኩረት በማድረግ ሊሆን ይችላል ከውጭ በሚመጣው ላይ ያተኮሩት፤›› በማለት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከውጭ እንደገባ ስለሚፈልጉባቸው አዝማሚያዎች ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ከጥጥ አምራቹ ሲገዙ ወዲያውኑ ክፍያ እንዲፈጽሙ ስለሚጠየቁ ከፋይናንስ አኳያ እንደማይፈልጉት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን ችግር በመቅረፍ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል በማቅረብ ብቻም ሳይሆን ግብዓቶችን በብድር እያቀረበ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (የቀድሞው ጅንአድ) ጥጥን ጨምሮ ሌሎችም ግብዓቶችን ከውጭ በማስመጣት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጅት ለጨርቃ ጨርቅ አምራቾች በተለይ በሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት ሲጉላሉ ለነበሩት እፎይታ ማስገኘቱን አቶ ፋሲል ገልጸዋል፡፡
የጥጥ አምራቾች ማኅበር ባቀረበው ጽሑፍ መሠረት በአገሪቱ ከሦስት ሚሊዮን ሔክታር በላይ ለጥጥ ልማት ተስማሚ መሬት አለ፡፡ ይህ ሁሉ መሬት ባይለማም በተለይ ከአራት ዓመታት ወዲህ ግን የአገሪቱ የጥጥ ምርት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎችን ፍላጎት ማሟላት እንደተሳነው በጽሑፉ ተጠቁሟል፡፡ በስድስት ክልሎች ባለሀብቶችና አነስተኛ ገበሬዎች በጥጥ ልማት ላይ መሳተፋቸው ሲታወቅ፣ በዚህ ዓመት ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ ያፈልጋቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው የተዳመጠ የጥጥ መጠን 76 ሺሕ ቶን እንደሆነ የማኅበሩ ጽሑፍ ያመለክታል (መንግሥት 100 ሺሕ ማለቱን ልብ ይሏል)፡፡ ይህንን ያህል መጠን የጥጥ አምራቾች እንደማያቀርቡም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
‹‹መንግሥት የጥጥ ልማትን ዘንግቶታል››፣ ‹‹ባለቤት የለውም››፣ ‹‹የጥጥ ልማት በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው፤›› የሚሉትን ትችቶች ጨምሮ በህንድና ቻይና እንደሚደረገው ለጥጥ አምራቾች ድጎማ ይደረግ፣ ከውጭ የሚገባው ጥጥ የጥራት ደረጃ አገር ውስጥ ከሚመረተው በታች በመሆኑ፣ መንግሥት ለአገር ውስጥ ጥጥ ትኩረት ያድርግ የሚሉ ሐሳቦች ሲነሱ ከርመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ መንግሥት እንደ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ላሉት መስኮች የሰጠውን ትኩረት፣ ለጥጥ ልማትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ትኩረት እንዲሰጠው አምራቾች ሲጠይቁም ተደምጠዋል፡፡ አሁን በሚታየው አኳኋን የጥጥ ልማት አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሪቱ ውስጥ ይመረታል ተብሎ የሚጠበቀውን የጨርቃ ጨርቅ ምርት ማምረት እንደማይቻል ተነግሯል፡፡
ዓምና በግንቦት ወር ይፋ ያደረገው ሪፖርት በሚሰጠው ትንታኔ መሠረት ደግሞ የአገሪቱ የጥጥ ምርት እየቀጨጨ ከመጣባቸው ምክንያቶች መካከል ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች ወደ ስኳር ፋብሪካና ሸንኮራ አገዳ አምራችነት መቀየራቸው አንዱ ነው፡፡ በጌን ሪፖርት መሠረት እንደ ተንዳሆ ጥጥ እርሻ ያሉትንና በአገሪቱ ግዙፍ የነበሩትን ጥጥ አምራች ድርጅቶች ወደ ስኳር አምራችነት መለወጡ የጥጥ ልማት ላይ ትልቅ ጫና እንዳሳደረ ተመልክቷል፡፡ በዓለም ከአሥር ስኳር አምራች የዓለም አገሮች ተርታ ኢትዮጵያን የማሰለፍ ውጥን እንዳለው ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይሁንና በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክም በአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት አገሮች ዝርዝር ውስጥ አገሪቱን የማሰለፍ ህልም እንደተወጠነም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይገልጻል፡፡
መንግሥት በበኩሉ ለጥጥ አምራቾች ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከመከለል (እስካሁን የለማው ከሦስት ከመቶ አይበልጥም) ባሻገር፣ በጥጥ መስክ ምርምሮችን እየደገፈ እንደሚገኝ ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ በዘረመል ምሕንድስና የሚራባ የጥጥ ዝርያ ለማባዛትና ለአምራቾች ለማቅረብ ምርምር መጀመሩን፣ ይህም ወደ ተግባር እንዲተረጎም ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር የሚመራ የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት ከማቋቋም በተጨማሪ ለጥጥ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት አምቾችን ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ጋር በማቆራኘት ያለሙትን እንዲሸጡ በማድረግ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡ ለዚህ ዋቢ የሚያደርገውም በአገር ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የውጭ ፋብሪካዎች ከጥጥ አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ያደረጓቸውን ስምምነቶች ነው፡፡ ካቻምናና ዓምና በተደረገ ስምምነቶች መሠረት አይካ አዲስ፣ ኤልስ አዲስ፣ ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ከጥጥ አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የምርት አቅርቦት ስምምነት መፈራረማቸውም አይዘነጋም፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታደሠ ኃይሌ ይፋ እንዳደረጉት፣ መንግሥት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይጠብቃል፡፡ እርግጥ ባለፈው በጀት ዓመት ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ የታሰበው አንድ ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም ሊገኝ የቻለው ግን ከ100 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ መሆኑም ታውቋል፡፡ ይሁንና ከዚህ ዓመት ጀምሮ በአምስት ዓመት ውስጥ በየዓመቱ ከዘርፉ የሚጠበቀው የወጪ ንግድ ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንዲሆን መታቀዱን አቶ ስለሺ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ዋጋ የሚያወጣ ምርት እንደሚመረትም መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ‹‹ኤድ ባይ ትሬድ›› ከተባለው ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የአፍሪካ ጥጥ ምርትን የሚያስተዋውቀው ጉባዔ፣ የውጭ ተሳታፊዎችንና የአገር ውስጥ የጥጥና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾችን በማገናኘት ስለዘርፉ ዛሬ ጥቅምት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ላይ ለማወያየት ቀጠሮ ይዟል፡፡