[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]
- ዊኬንድ እንዴት ነበር ክቡር ሚኒስትር?
- ዊኬንድ አስደሳችም አሳዛኝም ነበር፡፡
- ምን ተገኘ?
- ያው የኳስ ጉዳይ ነዋ፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር የኳስ ነገር አይሆንልዎትም አይደል?
- ነግሬህ የለ፤ ሱሴ ነው እኮ፡፡
- ምነው ሌላ ሱስ ቢኖርዎት?
- ሌላ የምን ሱስ?
- የሥራ ነዋ፡፡
- ምን አልክ አንተ?
- ኧረ ስቀልድ ነው ክቡር ሚኒስትር፣ ከኳስ ሌላ ያለዎት ሱስ ሥራ አይደል እንዴ?
- ከኳሱ በላይ ነው እንዲያውም የሥራ ሱሴ፡፡
- ምን ጥያቄ አለው?
- እህሳ?
- እንዲያው እንደ እርስዎ ዓይነት አንድ ሰው ቢኖረን እኮ አለቀልን በቃ፡፡
- አለቀልን በቃ ስትል?
- ማለቴ በቃ ቀን ተሌት በሥራ አለቅን ማለቴ ነው፡፡
- እኔ ደግሞ መሥሪያ ቤቱ አለቀለት ያልክ መስሎኝ ነበር፡፡
- ያው ነው፡፡
- ምን አልክ?
- አይ ያው እኛ በሥራ ካለቅን መሥሪያ ቤታችንም ያልቅለታል ብዬ ነው፡፡
- ዛሬ ምነው አሽሙር አበዛህሳ?
- እና አስደሳቹ ነገር ምን ነበር?
- ብሔራዊ ቡድናችን ለቀጣዩ ዙር አለፈ፡፡
- ተሸነፍን አይደል እንዴ?
- የሴቶቹን ነው የምልህ፡፡
- ያሳዘነዎት የወንዶቹ ነው ማለት ነው?
- እንዴታ?
- ያው በስፖርት እኮ መሸነፍና ማሸነፍ ያለ ነው፡፡
- አሁን ሽንፈትን የምንቀበልበት ጊዜ አይደለም፡፡
- እንዴት?
- ልክ እንደ ዕድገታችን ለስፖርቱም ትኩረት ስለሰጠነው እኮ ነው ራሱን የቻለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋምነው፡፡
- አዎ ይገባኛል፤ ግን ይኼ ያለ ነገር ነው፡፡
- በጣም ያስገረመኝ ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?
- ለምንድን ነው?
- ባለፈው በአንዴ ሁለት አገር አሸንፈው አሁን እንዴት ብዬ ነዋ?
- መቼ ነው በአንዴ ሁለት አገር ያሸነፉት?
- ሳኦቶሜ ኢንድ ፕሪንስፔን ነዋ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እነሱ እኮ ሁለት አገሮች አይደሉም፡፡
- ኤንድ እያለ እንዴት ሁለት አይደሉም ትለኛለህ?
- አንድ አገር ነው፡፡
- የት ነው ለመሆኑ የሚገኘው?
- እንዴ የአፍሪካ ኅብረት አባልም ናት እኮ፣ ምዕራብ አፍሪካ ያለች አገር ናት፡፡
- እንዴት አላውቃትም ታዲያ?
- ለነገሩ ትንሽ አገር ናት፡፡
- ታዲያ አነስተኛና ጥቃቅን አገሮችን እያደራጁ አገር ያደርጋሉ፣ እኔ ምን ላድርግ?
- ለነገሩ እንኳን እኔ ሆንኩ?
- ለምኑ?
- ሌላ ሰው ይኼን ቢሰማ ጥሩ አልነበረም፡፡
- ምን ያመጣል?
- ይሳለቅብዎታል፡፡
[አንድ ከውጭ የመጣች ዘመዳቸው ልትጠይቃቸው ቢሯቸው መጣች]
- አገርሽን እንዴት አገኘሻት?
- ብዙ ነገር ተቀይሯል፤ በጣም ደስ ይላል፡፡
- ይኼ ገና ጅማሮ ነው፤ ከዚህም ባለፈ ትደነቂያለሽ፡፡
- በጣም ብዙ ሕንፃዎች እየተሠሩ ነው፡፡
- አገራችን እየተመነደገች ነው ስልሽ?
- አንድ ነገር ግን መልመድ አልቻልኩም፡፡
- ምኑን ነው ያለመድሽው?
- አየሩ በጣም ከባድ ነው፡፡
- አዲስ አበባ እኮ ነፋሻማ ነች፡፡
- በፊትማ እንደዚያ ነበረች፤ አሁን ግን ሙቀቱ ከባድ ነው፡፡
- ምን እናድርግ ታዲያ?
- ዛፎች መትከል ነዋ፡፡
- ዛፍ እኮ የዕድገት መለኪያ አይሆንም፡፡
- እንዴ ዕድገት በምንድን ነው የሚለካው?
- በሕንፃ ብዛት ነዋ፡፡
- ለዚህ ነው የፎቅ ጫካ የበዛው?
- ዋናው እሱ ነው፡፡
- ለማንኛውም እስቲ ሻይ ደጅ እንጠጣ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከዘመዳቸው ጋር ሻይ ለመጠጣት ከቢሮ ወጡ]
- ሻይ የት መጠጣት ትፈልጊያለሽ?
- ፓርክ ያለበት ቦታ እንሂዳ፡፡
- ፓርክ ያለው አንዱ ለቡ ነው፤ ሌላው ደግሞ ዱከም ነው፡፡
- ሩቅ ናቸው ማለት ነው?
- አዎን በጣም ሩቅ ናቸው፤ ከከተማ ወጣ ያሉ ናቸው፡፡
- ለምንድነው ከከተማ የወጡት?
- እንዴ ኢንዱስትሪ ከተማ ውስጥ ምን ያደርጋል? ወጣ ማለት አለበት፡፡
- የምን ኢንዱስትሪ ነው?
- የኢንዱስትሪ ፓርክ ነዋ፡፡
- የለም የለም፤ እኔ ያልኩት እኮ የመናፈሻ ፓርክ ነው፡፡
- የምን የመናፈሻ ፓርክ አመጣሽ?
- ውጭ እኮ መናፈሻ ፓርኮች በየቦታው ነው ያሉት፤ አይተው አያውቁም እንዴ?
- ኧረ እኛ ውጭ ስንሄድ የሚያስጐበኙን እኮ የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡
- ታዲያ ወጣቶች የት ይዝናናሉ?
- አሁን ጊዜው የመዝናኛ አይደለም፡፡
- እና ፓርክ እዚህ አካባቢ የለም እያሉኝ ነው?
- ፓርክ ምን ይጠቅማል?
- እንዴ ወጣቶች በሉ፣ አዛውንቶች አረፍ የሚሉበት መናፈሻ በመሆኑ አዕምሮን በሚገባ ያድሳል፡፡
- ይኼውልሽ ወጣቶች መታደስ ያለባቸው በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡
- ባስኬት ቦል መጫወቻ ቦታም የለም፡፡
- እሱ ጨዋታ የኒዮ ሊብራሊስቶች ነው፡፡
- እሺ የእግር ኳስ ሜዳስ የለም?
- እሱም ቢሆን የእነሱ ጨዋታ ነው፡፡
- እሺ የእኛ ጨዋታ ምንድን ነው?
- ሩጫ ነዋ፡፡
- እሺ የሩጫ ሜዳ የት ነው ያለው?
- እነ ኃይሌ መቼ ሜዳ ላይ ሮጡ? ተራራ ለተራራ ተሯሩጠው ነው እኮ ስኬታማ የሆኑት፡፡
- በኢንተርኔት የምሰማው እውነት ነው ማለት ነው?
- ምንድን ነው የሰማሽው?
- በየሰፈሩ እንደ አሸን የፈላው ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ነው፡፡
- መዘንጋት የሌለብሽ ጫት ኤክስፖርት የሚደረግ ምርት መሆኑን ነው፡፡
- ምን እያሉኝ ነው?
- ኤክስፖርት ስለሚደረግ እዚህ የሚቅመው የለም፡፡
- ወጣቱን ሌላ ዜግነት ሰጣችሁት እንዴ? ለማንኛውም ግን አስቡበት፡፡
- ምኑን?
- ወጣቱ ላይ ኢንቨስት ማድረጉን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ኧረ የዚያን ልጅ ነገር እያሳሰበኝ ነው፡፡
- የቱ ልጅ?
- ባለፈው ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀው ዘመዴ ነዋ፡፡
- ምንድን ነው ያሳሰበሽ?
- እስካሁን ሥራ አላገኘም፡፡
- በምንድን ነበር የተመረቀው?
- ሶሺዮሎጂ መሰለኝ፡፡
- እሱ ትምህርት አሁንም አለ ማለት ነው?
- ለምን አይኖርም?
- ማለቴ ልማታዊ ነው ወይስ …
- በል በል ይኼን ዲስኩርህን እዚያው፡፡
- እሺ ምን ተሻለ?
- የሆነ ቦታ ወሽቀዋ፡፡
- የት ላስገባው እባክሽ?
- አንዱ ወዳጅህ ጋ ነዋ፡፡
- በቃ መላ እፈልግለታለሁ፡፡
- መላ ሳይሆን ሥራ ነው የሚፈልገው ልጁ፡፡
- ተይው ለእኔ አልኩሽ እኮ፡፡
- በአስቸኳይ ይሁን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሀብት ጋ ደወሉ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ እባክህ?
- ሰላም ነኝ፤ ተጠፋፋን አይደል?
- በጣም እንጂ ጠፍተሃል፡፡
- ምን ሥራ እኮ አላላውስ ብሎኝ ነው?
- አውቃለሁ፤ ዕድገት ያለ ሥራ አይመጣም፡፡
- ለዚያ ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ፈልጌህ ነበር፡፡
- ምን ልታዘዝ?
- አንድ የግል ጉዳይ ነበረችኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ማድረግ የምችለው ነገር ከሆነ ችግር የለም፡፡
- ኧረ በጣም ማድረግ የምትችለው ነገር ነው፡፡
- ምንድን ነው?
- አንድ ዘመዴ ነበር፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ተመርቆ ሥራ እየፈለገ ነው፡፡
- ኢንጂነሪንግ ነው ያጠናው?
- አይደለም፤ ሶሺዮሎጂ ነው ያጠናው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ያለኝ ኤንጂኦ አይደለም፡፡
- እሱ መቼ ጠፋኝ?
- ማለቴ እኔ ኮንስትራክሽን ላይ ስላለሁ ኢንጂነሮች ብቻ ነው የምቀጥረው፡፡
- የምን ቢሮክራሲ ማብዛት ነው?
- አያስቁኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ብዬ ነው ያሳቅኩህ?
- አይ ቢሮክራሲ ሲሉ እኔ ጋ ነው ወይስ እርስዎ ጋ ቢሮክራሲ ያለው ብዬ ነው፡፡
- ይኼው ቅጠር ስትባል አንተ እኮ ነህ ቢሮክራሲ እያበዛህ ያለኸው፡፡
- ብችልማ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
- እንዴት አትችልም?
- የልጁ ፊልድ ከምሠራው ሥራ ጋር አይገናኝማ፡፡
- ለመሆኑ ባለፈው ያወጣነውን ጨረታ ተሳትፈሃል አይደል?
- ይኼው ውጤቱን እየተጠባበቅን አይደል እንዴ?
- እንደዚያ ሆኖ ነው ሰው አልቀጥርልህም የምትለኝ?
- እጅ ጥምዘዛ ጀመሩ እንዴ?
- አይ እንዲያው ገርመኸኝ ነው፡፡
- ንስሃ የገባችሁ መስሎኝ ነበር እኮ?
- የምን ንስሃ?
- በጉባዔያችሁ ላይ ስትምሉ ስትገዘቱ አልነበር እንዴ?
- ምን ብለን?
- ብልሹ አሠራርን አስወግደን መልካም አስተዳደርን እናሰፍናለን እያላችሁ፡፡
- እንዳንተ ዓይነት ኪራይ ሰብሳቢ እያለ እንዴት እናስወግደው ታዲያ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ይኼው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡትን አልቀጥርም እያልክ አይደል እንዴ?
- ስለማያስፈልገኝ ነዋ፡፡
- ጨረታውም አያስፈልግህም ማለት ነው፡፡
- ወዴት ወዴት ነው?
- አዲስ አሠራር ጀምረናል፡፡
- የምን አሠራር?
- ሥራ በአዲስ መልክ ጀምረናል አልኩህ፡፡
- እርስዎ እንኳን በአዲስ መልክ የጀመሩት ሥራ አይመስለኝም፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው?
- ሙስና!