Friday, February 23, 2024

ኤርትራ የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት ተማፀነች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩት የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢጋድ አገሮች የጋራ ጠላት በሆነችው ኤርትራ ላይ የጠነከረ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ አድርገው ነበር፡፡

በዚሁ በሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ጉዳይ ላይ በጠራው መደበኛ ያልሆነ የውይይት መድረክ ላይ ኢጋድን ወክለው የተገኙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከዚህ ቀደም በኤርትራ ላይ የተጣለው ፖለቲካዊ ማዕቀብ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆንና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦች በኤርትራ መንግሥት ላይ መጣል እንዳለባቸው አሳስበው ነበር፡፡

ካነሷቸው የኢኮኖሚ ማዕቀቦች መካከል የኤርትራ መንግሥት በውጭ ከሚገኙ ዜጎች ገቢ ላይ የሚሰበስበው ሁለት በመቶ ቀረጥ ወደ ኤርትራ እንዳይተላለፍ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በኤርትራ የማዕድን ሀብት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም ማለት የውጭ ኩባንያዎች በኤርትራ የማዕድን ዘርፍ እንዳይሳተፉ፣ እንዲሁም ግዢ እንዳይፈጽሙ የሚጠይቅ ነው፡፡

ኤርትራ በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም. ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ፣ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ግፊትና ጫና ማዕቀብ እንዳይጥልና አካሄዱን ቆም ብሎ እንዲያስብ ጠይቃ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ራሱ የፀጥታው ምክር ቤት ያቋቋመው የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን፣ ኤርትራ በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ በወታደራዊ ሥልጠና፣ እንዲሁም በመሣሪያ እንደምትደግፍ አረጋገጠ፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ያቀረበውን የማዕቀብ ሰነድ በመደገፍ ተግባራዊ እንዲሆን ከወተወቱ የምክር ቤቱ አባል አገሮች መካከል አሜሪካ በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡

በመሆኑም የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2009 በኤርትራ መንግሥት ላይ ከጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማለትም የፖለቲካ መሪዎችና ወታደራዊ አመራሮች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ፣ እንዲሁም በእነዚህ አመራሮች ላይ ከጉዞ ማዕቀብ ውጪ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በዲሴምበር 2011 ላይ ጥሏል፡፡

ይህ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ግፊት በኢጋድ በኩል የቀረበ ሲሆን፣ በተለይ አገሪቱ ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘው ገቢ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም ለማወክ እየተጠቀመችበት በመሆኑ ማዕቀብ እንዲያርፍበት ተጠይቆ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ከሚያገኙት ገቢ ሁለት በመቶ በመቀነስ ወደ አገር ቤት የሚልኩት እንዳይተላለፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ማዕቀቡ ከተጣለ ከአራት ዓመታት በኋላ ኤርትራ በኢኮኖሚ ማዕቀቡ የተዳከመች ትመስላለች፡፡ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት በጠራው መደበኛ ያልሆነ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት፣ በተመድ የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ግርማ አስመሮም ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፡፡

በውጭ ከሚኖሩ ኤርትራውያን ዓመታዊ ገቢ ሁለት በመቶ ተሰብስቦ የሚውለው በጦርነት ለተሰው ዜጎች ቤተሰቦችና የጦር ጉዳተኞችን ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ግርማ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን በዓመት የሚልኩት 11 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ አጠቃላይ የኤርትራ መንግሥት የሚያወጣው ግን ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት ሊገነዘበው የሚገባው ኤርትራ ከማዕድን የምታገኘውን ገቢ በፍፁም ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ውጪ (ማለትም ለእኩይ ዓላማ) አውላ እንደማታውቅ፣ አምባሳደር ግርማ ለምክር ቤቱ የማዕቀብ ኮሚቴ አሳውቀዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ዓመታዊ በጀት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን የሚያገኘው ከማዕድን ዘርፍ መሆኑን በመጥቀስ፣ የማዕቀቡ መነሳት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አወንታዊ ተፅዕኖ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

‹‹ማንኛውም የዓለማችን አገርና ሕዝብ ወደኋላ ሊተው አይገባም›› የሚለውን ተመድ በቅርቡ ያፀደቀውን ድኅረ 2015 የልማት ግቦች ያስታወሱት አምባሳደር ግርማ፣ በኤርትራ ላይ በተጣለው ፍትሐዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ምክንያት የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በኤርትራ ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ በተመድ ከተያዘው የድህነት ቅነሳ አጀንዳ ውጪ በመሆኑ፣ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ ማዕቀብ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር ግርማ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ምክንያት የሆኑት ኤርትራ በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ የሽብር ቡድን ትረዳ ነበር መባሉ፣ እንደሁም በኤርትራና በጂቡቲ መካከል በተነሳው የድንበር ግጭት ሰበቦች መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ ኤርትራ አልሸባብን እንደምትረዳ ቀደም ባለው የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ሪፖርት ማረጋገጥ አለመቻሉን ቡድኑ ራሱ መጥቀሱን እንዲሁም በቅርቡ ባደረገው ምርመራም ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማግኘቱን ራሱ መግለጹን ለፀጥታው ምክር ቤት የማዕቀብ ኮሚቴ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው የማዕቀቡ ምክንያት በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተነሳው የድንበር ውዝግብ በጭራሽ ከአካባቢውም ሆነ ከዓለም ፀጥታ መደፍረስ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ የሰጡት ምክንያትም የግጭቱ መጠን ይህንን ያህል የሚያሳስብ ባለመሆኑ፣ ሁለተኛ ደግሞ ራሱ የፀጥታው ምክር ቤት ባፀደቀው መሠረት የኳታሩ ኤሚር የማግባባት ሥራውን እያከናወኑ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኳታር 200 ወታደሮች በአካባቢው መሰማራታቸውን በማውሳት፣ የማዕቀቡ ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት ትርጉም የሌላቸው መሆናቸውን ተከራክረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፀጥታው ምክር ቤት ያቋቋመው የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ገለልተኝነትን ተችተዋል፡፡

የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ሐሰተኛ የፈጠራ መረጃዎችን በመጠቀም ሪፖርቱን እንደሚያጠናክር፣ ለዚህም እንደማሳያነት መረጃዎችን ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ እንደሚቀበል አምባሳደር ግርማ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ከእነዚህ ከኤርትራ ጋር ግጭት ካላቸው ኢትዮጵያና ጂቡቲ እንዴት እውነተኛ መረጃ ይጠብቃል?›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

አጣሪ ቡድኑ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ለፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ይግባኝ ብትልም፣ ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉን አምባሳደሩ ለኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ለምሳሌ ኤርትራ በየመን ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር ያላትን ግንኙነት መገምገም እንደሚፈልግ፣ ከዚህ በማለፍ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላልተፈታው የድንበር ውዝግብና በኤርትራ አጠቃላይ ውስጣዊ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ሥልጣኑ እየገባ ነው ሲሉ አምባሳደሩ ይከሳሉ፡፡

የኤርትራና የኢትዮጵያ ጉዳይ የተወራሪና የወራሪ ጉዳይ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር እንደምትገደድ እየገለጸች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በማስረጃነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. ጁላይ 7  ቀን 2015 ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወታደራዊ ዕርምጃ በኤርትራ ላይ ልትወስድ ትችላለች›› ማለታቸውን በማስታወስ፣ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን የኢትዮጵያን ዛቻ በቸልታ ማለፍ ሳይሆን ሊያወግዘው ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሰጡት ምክንያትም በአንድ አገር ላይ ወታደራዊ ኃይል የመጠቀም ወይም ለመጠቀም መዛት የተመድ ቻርተርን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ እንደሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን የሚጠቀም ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዝምታ የተመረጠ ይመስላል፡፡

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ኃያላን አገሮች ተመድ ያቋቋመው የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ሪፖርት ላይ የተዓማኒነት ጥያቄ እያነሱ በመሆኑና በዚህ ጥያቄ ውስጥ ግፊት ለማድረግ መሞከር፣ አጠቃላይ ችግሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ ብቻ መስሎ እንዲታይ ያደርጋል ከሚል ሥጋት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑት ሩሲያና ፓኪስታን ሪፖርቱ ሚዛናዊ አይደለም ማለታቸውና ጣሊያንና ኖርዌይን የመሳሰሉ አገሮች ደግሞ ጥርጣሬ እንዳላቸው መግለጻቸውን ባለሙያዎቹ ይጠቅሳሉ፡፡

ኢትዮጵያ ማዕቀቡ በኤርትራ ላይ በቆየባቸው ያለፉት አራት ዓመታት በኤርትራ ላይ የፈለገችውን ተፅዕኖ እንደፈጠረችና የበላይነቷንም እንዳሳየች የሚገልጹት ተንታኞቹ፣ ከዚህ በላይ ግፊት ማድረግም ፖለቲካዊ ስህተት መፈጸም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ባለሙያዎቹ ይህንን ይበሉ እንጂ ተመድ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ወይ የሚለው ከሁለት ወራት በኋላ ይታወቃል ተብሎ ተገምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -