ልዩነት ጤናማ እስከሆነ ድረስ ለአንድ ኅብረተሰብ በጣም ተፈላጊ ሲሆን፣ በፖለቲከኞች መካከል ያለው ልዩነት ደግሞ ከብዙ አማራጮች ውስጥ የተሻለውን ለመያዝ ይጠቅማል፡፡ “ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር” የሚሉት ፈረንሣዮች በልዩነት ውስጥ አንድነት፣ በአንድነት ውስጥ ደግሞ ልዩነት መኖሩ ጠቃሚ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ለፖለቲካ ሥልጣን የሠለጠነ ፉክክር የሚካሄድበት ዋነኛው ሥርዓት የሆነው፣ ልዩነቶች በአግባቡ ተይዘው ሕዝብ የፈለገውን የሚመርጥበት በመሆኑ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን በአገራችን ብዙ ጊዜ ልዩነቶች በጠላትነት የመፈራረጅና የመጨካከን መገለጫ ሆነዋል፡፡
ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያለውን የአገሪቱን የፖለቲካ አካሄድ ለሚመረምር ልዩነቶችን ማቻቻል ወይም በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ባለመቻል ምክንያት፣ በርካታ ዜጎች ለሞት፣ ለስቃይና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በዘመነ ቀይ ሽብር የደረሰው ያ ሁሉ ጭፍጨፋና ማሰቃየት ልዩነትን በአግባቡ ካለመያዝ የመጣ ዕብደት የታከለበት ድርጊት ነበር፡፡ በዚህ ዘመንም የምንመለከተው ልዩነቶችን ይዞ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ከመነጋገር ይልቅ መወነጃጀል፣ ለብሔራዊ መግባባት የሚበጁ ሐሳቦችን ከማቅረብ ይልቅ መገፋፋት ተመርጠዋል፡፡ ራስን አነሳስቶ ግማሽ መንገድ በመጓዝ ከተፎካካሪ ጋር ለመነጋገር ከመሞከር ይልቅ፣ በሩንና መስኮቱን በመዘጋጋት አትድረስብኝ ማለት ቀላልና ተራ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለዴሞክራሲ ምለው እየተገዘቱ፣ ልዩነትን አክብረው በሚያነጋግሩዋቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዳገት ሲሆንባቸው ይታያሉ፡፡ ዴሞክራሲ ልዩነቶች በሠለጠነ መንገድ የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከሚገለጽባቸው ባህሪያት መካከል መንግሥት በነፃና በፍትሐዊ መንገድ የሚመረጥበት፣ የሕዝብ ተሳትፎ በምልዓት የሚታይበት፣ የሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበትና የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹ ዜጎችን ከመፈለጉም በላይ፣ ዜጎች በአመለካከታቸው ምክንያት ምንም ዓይነት አደጋ እንዳይደርስባቸው ይከላከላል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት በተንሸራሸሩ መጠን ልዩነቶች አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ዜጎችም የሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ ማንም ከሕግ በላይ አይሆንምና፡፡
ዴሞክራሲ ማለት ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ገበያ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች ያለምንም መሸማቀቅ ሐሳባቸውን በነፃነት ይገልጻሉ፡፡ የሚቀበለው ይቀበላል፣ የማይፈልገው ይተወዋል፡፡ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ግን ልዩነትን ለማስተናገድ ዝግጁ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች ናቸው የሞሉት፡፡ ብዙዎቹ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ከውዳሴ በስተቀር ትችት መስማት አይፈልጉም፡፡ ደጋፊዎቻቸውም ጭፍኖች ስለሆኑ የሌላውን ነፃነት ማክበር አይፈልጉም፡፡ ፅንፍ በረገጡ አቋሞቻቸው የተነሳ ከመሰዳደብና ከመወጋገዝ በስተቀር ልዩነቶቻቸውን እንኳ ለመደማመጥ ዝግጁ አይደሉም፡፡ የዴሞክራሲን ጽንሰ ሐሳብ በመቃረን ልዩነቶችን ይጨፈልቃሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ሲሉ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ በአባላቶቻቸው ውስጥ ለማስረፅ አለመቻላቸው ያስገርማል፡፡ የአንዱ ደጋፊ ሌላውን ‘ባንዳ’ ሲለው፣ ሌላኛው ደግሞ ‘ቅጥረኛ’ ይለዋል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው በዚህ በሠለጠነ የሰው ልጅ መብት ከምንም ነገር በላይ ልዩ ትኩረት ባገኘበት ዘመን፣ የፈለጉትን የፖለቲካ አቋም መያዝ በጠላትነት ማስፈረጁ ያንን አሳዛኝ የፖለቲካ ጠባሳችንን ያስታውሰናል፡፡ መለስተኛ ልዩነትን አቻችሎ በተባበረ መንፈስ አንድ ላይ መሥራት ይገባቸው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተራ በተራ የደርግ የግድያና የሥቃይ ሰለባ መሆናቸው አይረሳም፡፡ ሁሉም ከድርድር ይልቅ ኃይል በመሻታቸው አንድ ትውልድ መና ቀርቷል፡፡ ዛሬ ቢያንስ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ዕድሉ የተሻለ በሆነበት በርንም ልብንም መዝጋት ያሳፍራል፡፡ ልዩነት ካልተከበረ እንዴት ስለዴሞክራሲ ይወራል? ከመወጋገዝ ይልቅ ድርድር ይቅደም፡፡
የአገሪቱ ፖለቲከኞች ችግር በማኅበራዊ ድረ ገጾች ውስጥ ደግሞ ራሱን የቻለ አሳዛኝ ምሥል ይታይበታል፡፡ ማንነትን፣ ሃይማኖትን፣ የፖለቲካ አመለካከትንና የመሳሰሉትን በልዩነት ውስጥ መቀበል የተሳናቸው ወገኖች ያለምንም መሳቀቅ ክፉ ድርጊት እየፈጸሙ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት የጋራ ጉዳይ ላይ ሳይቀር ልዩነት መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ልዩነትን በፍፁም ማስተናገድ የማይፈልጉ ወገኖች የሰዎችን ማንነት ሳይቀር ይዘልፋሉ፡፡ ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ግለሰቦችን ሰብዕና ይዳፈራሉ፡፡ ውይይቶችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ዘርንና ዕምነትን መሠረት ያደረጉ አሳዛኝ ስድቦችን ያዥጎደጉዳሉ፡፡ ያስፈራራሉ፡፡ ይኼ ሁሉ የሚከናወነው በዴሞክራሲ ስም ነው፡፡ ሐሳቦች ላይ ከመንጠልጠል ይልቅ ሰዎችን ማዋረድ በጣም የተለመደ ሆኗል፡፡
ዴሞክራሲ የሚያብበው ዜጎች የፖለቲካ ተሳትፏቸው በመጨመሩና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በማስከበራቸው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲ በምን ዓይነት መርህና ሥነ ምግባር እንደሚመራ በመገንዘብ ጭምር ነው፡፡ በመጀመሪያ ሁሉም ዜጎች ሕግ ማክበር አለባቸው፡፡ ከአመፅና ከብጥብጥ ራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል፡፡ አንድ ሰው ወይም ድርጅት ሐሳቤ ተቃውሞ ገጥሞታል ብሎ ሁከት ማንሳት ወይም ተፎካካሪዎቹን ማንገላታት የዴሞክራትነት መገለጫ ሳይሆን አምባገነንነት ነው፡፡ ማንም ሰው የሌሎችን ሐሳብ ባይስማማበት እንኳ ሰብዓዊ መብታቸውንና ክብራቸውን መጠበቅ አለበት፡፡ ማንም ቢሆን በፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የማይስማማውን በሕገወጥነትና በሰይጣንነት መፈረጅ የለበትም፡፡ ዴሞክራሲ እንደዚህ አይልምና፡፡ ማንም በሰው በምርጫ ሥልጣን በያዘ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡ ነገር ግን የመንግሥትን የሕዝብ ውክልና ሊሽር አይቻልም፡፡ የዴሞክራሲ መርህ መገለጫ ባለመሆኑ፡፡
ግለሰቦችም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች የራሳቸውን አስተሳሰብ በነፃነት ሲገልጹ፣ የሌሎች ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ አለባቸው፡፡ የፈለገውን ያህል ቢመረንና ብንጠላው እንኳ የሌሎችን አስተያየት መስማት የግድ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የተለመደ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲያብብ የሚፈልጉ ሁሉ ይህንን በቅጡ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ዛሬ በሰላማዊ መንገድ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገሉም ሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ልዩነትን ያክብሩ፡፡ በሐሳብ መለያየት ማለት ሞት አይደለም፡፡ ይልቁንም ለሕዝብ አማራጭ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሰጥቶ የመቀበል መርህ ተግባራዊ የሚደረግበትና ሁሌም ድርድርን የሚያስቀድም ነው፡፡ የድርድርን በር እየከረቸሙ በየፊናህ ማለት አይቻልም፡፡ የዴሞክራሲ በር በተዘጋጋ መጠን ሕገወጥነት ይሰፍናል፡፡ አመፅ ይከተላል፡፡ በዴሞክራሲ አንድ ወገን ሁሌም የሚፈልገውን ሙሉ በሙሉ አያገኝም፡፡ የተለያዩ ዓላማዎችን የሚያራምዱም እንደ አጀንዳቸው ተፈላጊነት አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ሁሉም በየራሳቸው ፍላጎት ድልን ያጣጥማሉ፡፡ ስለዚህ ልዩነቶች የተለያዩ አስተሳሰቦች ማበቢያ እንጂ የጠብ መፈልፈያ መሆን የለባቸውም!