Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት አራት አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች እንዲቋቋሙ መመርያ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ መንግሥት ውሳኔ ከሰጠባቸው ስድስት ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ፣ ሌሎች አራት ኮርፖሬሽኖች እንዲደራጁ አቅጣጫ መሰጠቱን ምንጮች ገለጹ፡፡

የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ የዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን፣ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ማዕድንና ጋዝ ምርቶች አቅርቦት ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ የማዕድን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንዲቋቋሙ በመወሰኑ ኮርፖሬሽኖቹ ራሳቸውን እያደራጁ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ይዞ ኮርፖሬሽን ሆኖ የሚደራጀው የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ በቀጥታ ተጠሪነቱ ለማን እንደሆነ እስካሁን ውሳኔ አልተሰጠም፡፡ ከላይ ከተዘረዘሩት መካከል አራቱ ኮርፖሬሽኖች፣ ተጠሪነታቸው በቀጥታ አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ይሆናል፡፡

ከእነዚህ ስድስት ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ በቀጣዮቹ ወራት በአዲስ መልክ እንዲቋቋሙ መንግሥት አቅጣጫ የሰጠባቸው የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ኮርፖሬሽን፣ የምግብ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የባዮፊውል ኮርፖሬሽንና የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን መሆናቸው ታውቋል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ፣ የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ድርጅት ያለበት ዕዳ ተሰርዞ እንደ አዲስ ኮርፖሬሽን ሆኖ እንደሚቋቋም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል ከሚያከናውነው ሥራ በተጨማሪ፣ ለመስኮትና በር የሚሆኑ የፒቪሲና አሳንሰር (ሊፍት) ምርቶችን እንዲያካትት በስብሰባው ላይ ተገኝተው ለነበሩ የተገጣጣሚ የሕንፃ አካላት ድርጅት ኃላፊዎች አቶ መኩሪያ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

ባለፈው ሰሞን በሸራተን አዲስ በተካሄደ ስብሰባ ላይም አቶ መኩሪያ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመሬት ልማት ላይ የሚሠራ የመሬት አቅርቦት ኮርፖሬሽን እንደሚቋቋም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የመሬት አቅርቦት ኮርፖሬሽን የሚያከናውናቸው ተግባራት ለጊዜው ግልጽ መሆን አልቻሉም፡፡ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎችም የመሬት ኮርፖሬሽን ምን ሊሠራ እንደሚችል ግልጽ እንዳልሆነላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ተጠባቂ የባዮፊውል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት ሰባት ዓመታት ከተፈጥሮ ነዳጅ ጥገኝነት በከፊልም ቢሆን ለመላቀቅ ለባዮፊውል ልማት ትኩረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በሚያካሂዳቸው የስኳር ፋብሪካዎች በርካታ መጠን ያለው ኢታኖል ማምረት ጀምሯል፡፡ ነገር ግን ለግል ኩባንያዎች ለጃትሮፋና ጉሎ ተከል የሚሆን ሰፋፊ መሬት ቢቀርብም፣ ኩባንያዎቹ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ይህንን ዘርፍ በሚገባ እንዲመራና የባዮፊውል ኮርፖሬሽን እንዲቋቋም መንግሥት መመርያ መስጠቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ይህ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ የመተካት ሚና ተሰጥቶታል፡፡

በሌላ በኩል የምግብ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህ ኮርፖሬሽን ዘይትን የመሳሰሉ ስትራቴጂካዊ የምግብ ምርቶች ላይ በሰፊው ይሰማራል ተብሏል፡፡ እነዚህ ኮርፖሬሽኖች ተጠሪነታቸው አዲስ ለተቋቋመው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ከእነዚህ አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች በተጨማሪ ቀደም ሲል የተቋቋሙት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽንን በቀጥታ ያስተዳድራል፡፡ ከነዚህ ውጪ ያሉትን ብረታ ብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርክ ኮርፖሬሽንና አዲስ የተቋቋመው የኤሌክትሪክ ኮሬፖሬሽን የኮርፖሬት ገቨርናንስና ፋይናንስ ጤንነታቸውን እንዲከታተል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች