ቢጫ ጡልጥሌ (Yellow Wagtail – Motacilla Flava) ቢጫና ወይራ አረንጓዴ ቀለም ያላቸው ሸንቃጣ ትናንሽ ወፎች፡፡ ጭንቅላታቸው አመዳማ ሲሆን፣ ክንፋቸውና ጅራታቸው አልፎ አልፎ ጠቆር ያለ ምልክት ያለው ወይራ አረንጓዴ ነው፡፡ የታችኛው አካላቸው ሙሉ በሙሉ ደማቅ ቢጫ ነው፡፡
በክረምት ወቅት ከሰሜን አውሮፓ የሚመጡ ዘላን ወፎች ሲሆኑ፣ በውኃ አካባቢ በሚገኙ አጭር ሳር ባላቸው ሜዳቸዎች ላይ ጭራቸውን አልፎ አልፎ ወደላይ እየቀሰሩ ሲራመዱ ይታያሉ፡፡
********
የኢትዮጵያ ወንጭፌ
የኢትዮጵያ ወንጭፌ (Ethiopian Swallow – Hirundu Aethiopica) ከላይ የሚያብለጨልጭ ጥቁር ሰማያዊ ከታች ነጣ ያለ ሽሮ ቀለም ያላቸው ትናንሽ ወፎች፡፡ በግንባራቸውና በጉሮሮአቸው ላይ አልፎ አልፎ ቀላ ያለ ቡኒ ምልክት ያላቸው ሲሆን፣ በደረታቸው ላይ ደግሞ ትንሽ ጥቁር እራፊ ይገኛል፡፡ ጭራቸው ረዘም ያለና የተከፈለ ነው፡፡ ቀን ቀን በሜዳና በዛፍም አካባቢዎች ሲውሉ ማደሪያቸው ግን በገደል ውስጥ ነው፡፡
- ከበደ ታደሰ ‹‹የኢትዮጵያ መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ወፎች የኪስ መጽሐፍ›› (2000)