Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹አበበ›› እንጂ መቸ ሞተ

‹‹አበበ›› እንጂ መቸ ሞተ

ቀን:

ጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ስለአበበ ቢቂላ

በቅጽበት ፀንሶ ሞቱን

ድፍን ዓለም ደፍቶ አንገቱን

በልቡ ቀርፆት ጸሎቱን

በሕሊናው ነድፎት ስሙን

በገጹ ጽላት ታሪኩን …

‹‹አዕዋፍን በደመና ጀግናን በምድር ያስደነቀ

ማራቶን ጮራው ጠለቀ

በራሪው ኮከብ ወደቀ!

በቃ ጀግናው ተከተተ

ይኸው የማይሞት ሰው ሞተ!››

ብለን አንበል እባካችሁ፣ ‹‹አበበ›› ተስፋ ነውና

ተስፋ አይቀበርምና፤

የጐበዝ ነባቢት ነፍሱ

ያ የሕይወት ሕልም ዳሱ

የጀግኖች ክብረ ሞገሱ

የጐበዝ ነባቢት-ነፍሱ

የሰው መዝርቱእ አርአያ፤ የማይታጠፍ መንፈሱ

በጥረት የታጠፈለት፤ የምድር አጽናፍና አድማሱ፤

የየብስ የአየሩ ነበልባል

የማራቶን ዕፁብ-አይጣል፤

የምድር ዓለሙ ገሞራ

አገሩን በክብር ያስጠራ

ሳተናው እግረ ጆቢራ

ሎጋ ቢቂላ ዋቅጅራ፤

የጐበዛዝ ንጥረ ወዙ

የተስፋ ብርሃን መቅረዙ፤

ስሙን ላገር ስም ሰይሞ፤ የምሥራች ያስደወለ

ስንቱን ስንቱን ልበ ሙሉ፤ ከአድማስ አድማስ ያስከተለ፤

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ

ያረጋት የኦሊምፒክ ዓርማ፤

በወገኖቹ ልቡና፤ ቀና ኩራት ያሳደረ

እንደፍላፃ በአክናፉ፤ ያየርን ስርጥ የሰበረ

የፍሥሐን ዓዋጅ ለዓለም፤ በአቅመ ወዙ ያስነገረ፤

ባገር ፍቅር ልቡን ሞልቶ፤ ላቡን ነጥቦ የዋተተ

የዓለምን ጀግና በአድናቆት፤ በቅን ቅናት ያስሸፈተ

አልሞተም እንበል እባካችሁ! አበበ እንጂ መቸ ሞተ

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ጥቅምት 17 ቀን 1966 ዓ.ም.)

****************************

 

ጥቅምት 11 ቀን – የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል 51ኛ ዓመት

‹‹አበበ ቢቂላ በጳጉሜን 1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፤ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11.2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡››

ከ51 ዓመት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ የጻፈው ነው፡፡ 

ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. (ኦክቶበር 21 ቀን 1964)  ነበር፤ ቦታው ጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ በተለይ 15 አትሌቶች የኦሊምፒኩን የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኘት ቋምጠዋል፤ ለመፎካከር አፍጥጠዋል፡፡ የሮሙ ባለወርቅ አበበ ቢቂላ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ማድረጉና ሳያገግምም ከውድድር ሥፍራ መድረሱም የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ካልሲ አጥልቆ፣ ጫማውን ለተጫማው አበበ ውድድሩ አስቸጋሪ አልሆነበትም፡፡ እስከ መጀመሪያዎቹ 10 ኪሎ ሜትር የአውስትራሊያው ሮን ክለርክ ቢፎካከረውም ጥሎት በመሔድ ያለአንዳች የቅርብ ተቀናቃኝ በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰኮንድ በድል አድራጊነት ፈጸመ፡፡ ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም ባሸናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰኮንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን በ1 ደቂቃ 43 ካልዒት (ሰከንድ)፣ 8 ሣልሲት (ማይክሮ ሰከንድ) የሰበረበት ነው፡ 

‹‹እንደ በረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ 

ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡ 

አበበ በቶኪዮ ማራቶን ከመወዳደሩ 36 ቀናት በፊት ረቡዕ መስከረም 6 ቀን 1957 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና አድርጎ ስለነበር እንኳን ሊያሸንፍ ውድድሩን ይፈጽማል ብሎ ያሰበ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ 70,000 የሚሆነው የቶኪዮ ስታዲየም ተመልካች ማን ያሸንፍ ይሆን? እያለ ውድድሩን በጉጉት ሲጠባበቅ ማሸነፍን ምሱ ያደረገው ሸንቃጣው አበበ የ30 ደቂቃ የሰውነት ማሟሟቂያ አድርጎ ከመናፈሻ እንደወጣ አትሌት እየተዝናና ከስታዲየሙ ሲደርስ ተመልካቹ ዓይኑን ማመን አቅቶት ነበር፤ ከዚያም ውድድሩን አጠናቆ ወዲያውኑ እንደ ጠዋት የ5 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጅምናስቲክ መሥራት ሲጀምር ተመልካቹ መጀመሪያ ፈገግ አለ፡፡ ከዚያም በመገረም ዘግየት ብሎ አድናቆቱን በከፍተኛ ጭብጨባ ገለጸለት፤ ይላል ገድሉን የዘገበው የባሕር ማዶ መጽሔት፡፡ 

ዴቪድ ዋልቺንስኪ በኦሊምፒክ ድርሳኑ (The Complete History of Olympics 2004 Edition) እንደጻፈው፣ አበበ አካሉን ሲያፍታታ ላየው ‹‹አዝናለሁ፣ ማራቶን አጭር ሆኖብኛል›› ያለ አስመስሎበታል፡፡ እንዲያውም ለጋዜጠኞች በዚያን ጊዜ በሰጠው ምላሽ ለሌላ 10 ኪሎ ሜትር የሚያስሮጠኝ ኃይል አለኝ ነበር ያላቸው፡፡ 

በሜዳሊያ ሽልማት ሥነ ሥርዓቱም አንድ ያልተጠበቀ፣ ከዚያም በፊትም ያልታየ ሌላ አስደናቂ ነገር ተከሰተ፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም እንዲሁም ከቶኪዮ በኋላ ማሞ ወልዴ በሜክሲኮ (1961 ዓ.ም.) ማራቶንን ሲያሸንፉ የተዘመረላቸው 

‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ፣ 

ባምላክሽ ኃይል በንጉሥሽ›› የሚለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የጃፓን ባለሥልጣኖችም ሆኑ የሙዚቃ ባንዱ አያውቁትም ነበር፡፡ እናም ዘየዱ፤ የማርሽ ባንዱ አጋጣሚውን ተጠቀመ፡፡ የጃፓንን ሕዝብ መዝሙር ለኢትዮጵያ ድል ማብሰሪያ አደረገው፤ ሕዝቡም ፈነደቀ፡፡ 17 ቁጥር መለያን ያጠለቀው አበበም በጃፓን ሕዝብ ልቡና ውስጥ ታተመ፡፡ ነፍስኄር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከአራት አሠርታት በፊት እንዳሉት፣ ‹‹…አበበ በድጋሚ በማሸነፉ በጃፓን ሕዝብ ለዘለዓለም የማይረሳ ትዝታ ትቷል፡፡ ዛሬም በጃፓን እንደጣዖት ይመለከቱታል፡፡ ማራቶን በጃፓን ውስጥ እንዲህ ተወዳጅ ሊሆን የቻለው ከአበበ ቢቂላ ድል በኋላ ነው፡፡ አሁንም ይኸው መንፈስ ቀጥሏል፡፡›› 

አበበ ቢቂላ  በቀድሞ አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ በደብረብርሃን አውራጃ፣ ደነባ፣ ልዩ ስሙ ጃቶ ከሚባለው ቀበሌ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም. ተወልዶ ከ42 ዓመት በፊት ጥቅምት 15 ቀን 1966 ዓ.ም. ሐሙሱ ጧት ልክ ለሦስት ሩብ ጉዳይ ላይ በ41 ዓመቱ ማረፉ ይታወሳል፡፡ የኦሊምፒክ በኩር አበበ ቢቂላ ዜና ዕረፍት የሰማው ባለቅኔውና ጸሐፌ ተውኔቱ ጸጋዬ ገብረ መድኅንም እንጉርጉሮውን ‹‹‘አበበ’ እንጂ መቸ ሞተ›› በሚል ርእስ ጥቅምት 17 ቀን 1966 ዓ.ም. በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ከትቦት ነበር፡፡

(ሔኖክ መደብር)

****************************

‹‹ቡና ቡናዎች››

‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና

የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና

የዕድገታችን ገንቢ ቡና ቡና

አውታር ነው ቡናችን ቡና ቡና››

ከ1970ዎቹ ጀምሮ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ማለዳም ሆነ ምሽት ላይ የቡና ዋጋ መግለጫ በጥሩነህ ማሞ ከመቅረቡ በፊትና እየቀረበ ሳለ የሚደመጠው ዜማ፣ በ1970 ዓ.ም. በጅማ ከተማ ቦሳ 4 ቀበሌ የተቋቋመው ታዳጊ የኪነት ቡድን ኅብረ ዝማሬ ነበር፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት መሥራቹና አሠልጣኙ አቶ ታረቀኝ ወንድሙ ናቸው፡፡ ፎቶግራፋቸው የተገኘው ከጅማ ቲዩብ ድረ ገጽ ነው፡፡

****************************

እስራኤላዊና ፍልስጤማዊን በአንድ ገበታ

በእስራኤሎችና፣ በፍልስጤሞች መካከል የሚፈጠር ግጭት አዲስ ባይሆንም፣ ሰሞኑን የተከሰተው ግጭት አዲስ መልክ ይዞ መጥቷል፡፡ እስራኤሎችና ፍልስጤሞች በአንድ አካባቢ የሚኖሩ፣ የሚማሩና የሚሠሩ እንዲሁም ጎረቤታሞችና ጓደኛሞች ቢሆኑም፣ እርስ በርስ መተማመናቸው ተሸርሽሯል፡፡ ግጭቱ ከተጀመረ ከሦስት ሳምንት ወዲህም በአንዳንድ ቦታዎችም ሲቪሎች አንዱ አንዱን መግደላቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ ያሳሰበው የሂዩመስ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ኮሊ ዛፍሪር፣ እስራኤላዊና ፍልስጤማዊ በአንድ ገበታ ከተቀመጡ፣ በአንድ ምግብ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርግ አሳውቋል፡፡ ሃፍንግተን ፖስት በዛፍሪር የፌስቡክ ድረ ገጽ በዕብራይስጥ የተፃፈውን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የሬስቶራንቱ ጣፋጭ ምግቦች ላይ የተደረገው የ50 በመቶ ቅናሽ፣ ጀርባ የተሰጣጡትን እስራኤሎችና ፍልስጤሞች አብረው እንዲመጡና እንዲመገቡ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሰላም ለማምጣት አንዱ መንገድ ነው፡፡

መረጃውን ያገኙ አረቦችና አይሁዶች የሂዩመስ ሬስቶራንትን ማጨናነቅ ጀምረዋል፡፡ ጓደኛሞች የሆኑትም አብረው እየመጡ መመገብ ጀምረዋል፡፡ ብዙዎች ደግሞ የሬስቶራንቱን ባለቤት ሐሳቡን የሚደግፍ መሆናቸውን ሬስቶራንቱ ድረስ በመሄድ እየገለፁ ነው፡፡

ዛፍሪር፣ “ብዙ ዓረብ እንግዶች ነበሩን፡፡ ሆኖም ብጥብጡ ሲከሰት ደስታ አልተሰማኝም፡፡  በምግብ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ ያደረግሁት ከሰዎች ፊት ደስታን አገኛለሁ ብዬ ነው፡፡ እስራኤላዊና ፍልስጤማዊ ምግብ ለመመገብ አብረው መምጣት ጀምረዋል” ማለቱን ደግሞ ኤንቢሲ ዘግቧል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...