Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋል

  በመንግሥቱ መስፍን

ውድ የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጆች እንዴት ከረማችሁ? ባለፈው ሳምንት እሑድ ዕትማችሁ በአስተያየት ዓምድ፣ አቶ ገመቹ ዘለዓለም ዱሬ የተባሉ ጸሐፊ የአገራችንን ፌዴራሊዝም ሥርዓት ከዓለም አቻ ሥርዓቶች ጋር አነፃጽረው በተለይ ድክመቶቹን ለመንቀስ ሞክረዋል፡፡ በተለይ ከጋራ አስተዳደር፣ ከኢኮኖሚያዊና ከማኅበራዊ ፍትሕ እንቅፋቶች፣ ከፌዴራሊዝምና ከዴሞክራሲ አኳያ የመሰላቸውን ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

እኔም እንደ አንድ ዜጋ በጉዳዩ ላይ ሐሳቤን ስሰነዝር የኢትዮጵያ የፌዴሬሊዝም ድክመትን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬውንም በማውሳት ነው፡፡ በእርግጥ በአሜሪካ የኮንፌዴሬሽን ሥርዓት እጥረቶችን በማሻሻልና አዲስ መልክ ይዞ እንዲመጣ በማድረግ፣ ለመጀመርያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1789 ሥራ ላይ በዋለው ሕገ መንግሥት ዘመናዊ ፌዴራሊዝም ተመሥርቷል፡፡ ከዚያም በኋላ በስዊዝ እ.ኤ.አ. በ1848፣ በህንድ በ1949፣ በናይጄሪያ በ1960 የፌዴሬሊዝም መንግሥት ምሥረታ አንፃር የእኛ የ20 ዓመታት ጉዞ በዕድሜ ለጋ የሚባል ነው፡፡

በእኛ ፌዴራሊዝም የሚታዩ በጎ ምልክቶች

በሕገ መንግሥቱ የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአናሳውንም ሆነ የብዙኃኑን ሕዝብ ውክልና ይይዛል፡፡ የአገሪቱ መንግሥትን ውስን በጀት በፍትሐዊ ሥሌትና ቀመር ለክልሎችም ያከፋፍላል፡፡ ይህ ተቋም ለምሳሌ በጀርመን ፌዴራሊዝም ውስጥ ያለ ሲሆን፣ ውክልናው የስድስት ትልልቅ ብሔሮች ብቻ ነው፡፡ በእኛ አገር ግን ከአንድ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ላላቸው ብዙዎቹ ብሔረሰቦች ውክልና ይፈቅዳል፡፡

በአሜሪካ እንደ ግልግል ፍርድ ቤት ከፍተኛውን የሕገ መንግሥት ትርጓሜና ሥልጣን የያዘው አካል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ በጀርመን ዓይነቶቹ አገሮች ደግሞ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ምክር ቤት አለ፡፡ በኢትዮጵያ ይህን ትልቅ ኃላፊነት የሚሸከመው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚባለው ተቋም ነው፡፡ ይሁንና ተቋሙ በፖለቲካ ስብጥሩ፣ በመፈጸም አቅሙና ግብዓትን በመሰሉ መገለጫዎች መጠናከር ከቻለ የተሻለ ውጤት የማምጣት ዕቅድል ይኖረዋል፡፡

የፌዴራሊዝም መንግሥታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ በመተግበሩ ያለጥርጥር በብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ተጠቃሚነት ላይ ቀላል የማይባል መሻሻል መጥቷል፡፡ ትናንት ምንነታቸው የማይታወቁ ሕዝቦች ታሪካቸው፣ ቋንቋቸውም ሆነ ኪነ ጥበባቸው መተዋወቅ ይዟል፡፡ በልማቱ መስክም በመሠረተ ልማትና በማኅበራዊ ዕድገት የላቀ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ የተዛባ ግንዛቤ የመያዝና ሕዝብን ከአገዛዝ ጋር አጣምሮ በጥላቻ መነጽር የማየት ዝንባሌ ቢከሰትም፣ የሕዝብ ለሕዝብ መስተጋብር ለመፍጠር እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን ያሉ በዓላት መብዛታቸውም ይታያል፡፡

የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገለልና ልዩነትን በማስወገድ ረገድ የፌዴራል ሥርዓቱ ያበረከተው አስተዋጽኦም እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ልማት ባሻገር ለእነዚህ ማኅበረሰቦች አወንታዊ ዕርምጃዎች (Affirmative Actions) መወሰዱም ይታወቃል፡፡ ይኼም በፖለቲካ ውክልና፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቅበላ፣ በሲቪል ሰርቪስ ቅጥርና በሌሎችም ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህ ሒደት በአግባቡ ካልተፈጸመ ግን አወንታዊ ዕርምጃዎች ላይ ጥገኝነት ሊፈጥር ይችላል፡፡ ድጋፍና ዕገዛን እንደ ዘላቂ መብት የመውሰድ እንቅፋትንም በመንገድ ላይ ይገትራል፡፡

አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባንዲራ፣ አንድ ታሪክና አንድ ብሔራዊ ማንነት ማዕቀፍ ውስጥ በጅምላ ተቆልፎበት እንደኖረ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የላላ ቢመስልም፣ በእኩልነትና በጋራ ቤትነት መንፈስ ሲታይ የአሁኑ የፌዴራል ሥርዓት የተሻለ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም በጠባብነትም ሆነ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ከልክ በላይ በመለጠጥ፣ ከዴሞክራሲያዊ አንድነት ይልቅ መለያየትና መራራቅ የሚቀነቀንበት ሁኔታ ልጓም ያስፈልገዋል፡፡ አንዳንዱ የፌዴራል መንግሥቱን የሥራ ቋንቋ፣ የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማም ሆነ አገራዊ ምልክቶችን ለመቀበል ሲንገፈገፍ እየታየ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መታረም አለበት፡፡

በእኛ ፌዴራሊዝም የሚታዩ ችግሮች

  1. ፌዴራሊዝምና ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት››

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የፌዴራል መንግሥታዊ አደረጃጀት ካዋቀረበት ጊዜ አንስቶ በየክልሉ የታዩ የልማት ለውጦች አሉ፡፡ የልማትና የሰላም ግኝቱ ብቻ ሳይሆን፣ የዴሞክራሲውም ሆነ የሕዝብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነቱ ሲመዘን በምንም መለኪያ ከአሐዳዊው ሥርዓት የተሻለ ነው፡፡ ይሁንና ኢሕአዴግንም ሆነ መንግሥቱን እያስፈራው የመጣው ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የተባለው የሙስናና የአቋራጭ መበልፀጊያ ፈተና ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሥጋት አሁን ባለችው ኢትዮጵያ መሠረታዊና አሳሳቢ ችግር እንዳይሆን፣ መንግሥትም ቀን ከሌት በጉዳዩ ላይ መነጋገር መጀመሩ እየተሰማ ነው፡፡

‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› (Rent Seeking) የሚለው ሐረግ በእኛ አገር መነገር ከጀመረ ከ15 ዓመታት ያነሰ ዕድሜ ቢያስቆጥርም፣ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ምርምር ውስጥ ግን የነበረና ያለ ነው፡፡ በተለይ የኖቪል ሽልማት አሸናፊው ኢኮኖሚስት ጆሴፍ ስቲግሊትዝ ‹‹The Price of Inequality›› በተሰኘው መጸሐፋቸው ጉዳዩን አፍታተው ገልጸውታል፡፡ ‹‹የሥልጣን ማማውን የተቆናጠጡ ግለሰቦች የፖለቲካ ኢኮኖሚውን ጨዋታ ሕግጋት ለእነሱ እንዲመቻቸው አድርገው የሚቀርፁበት፣ ከሕዝቡ ዘንድም የማይገባቸውን ነገር ባልታሰበ መንገድ የሚያገኙበት፣ ብሎም ሀብትን ያላንዳች ድካምና ውጣ ውረድ የሚያሰባስቡበት ሥርዓት ነው፤›› ይለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም እምብዛም ከዚህ የተለየ ብያኔ አይደለም ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚሰጠው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ፌዴራሊዝም ነውና ምን አገናኘው ታዲያ  ለምትሉ አንባቢያን፣ አንዳንድ መከራከሪያዎችን ለማንሳት እወዳለሁ፡፡

እስካሁን ባለው የሕዝብ አስተያየትና ጥቆማ በብዙዎቹ ክልሎች በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የሚገኙ አንዳንዶች ‹‹ቱባ›› ባለሀብቶች መሆን የቻሉት፣ በኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ ነው፡፡ ማንኛውም ተሿሚ እንደየትኛውም መንግሥት ሠራተኛ በደመወዙ ቢኖር የዕለት ጉርስ፣ የልጆች ትምህርትና የቤት ኪራይን ሸፍኖ የሚተርፈው እዚህ ግባ የሚባል ንብረት አይኖረውም፡፡

ዛሬ ዛሬ እየታየ እንዳለው ግን ባለ ግዙፍ ሕንፃዎች፣ የትልልቅ ድርጅት ባለቤቶችና ኢንደስትሪያሊስት መሆን የቻሉ ባለሥልጣናት በየአካባቢው ተፈጥረዋል፡፡ ትናንት በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ ተቋማት ውስጥ ደመወዝተኛ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ባለሀብት እንዴት መሆን ቻሉ?  ምንጩስ ምንድነው?  አሁንም በሥልጣንና በኃላፊነት ላይ ሆነው የሕዝብን ጥቅምና የአገርን እሴት እየጠራረጉ ወደ ግል ካዝናቸው የሚያስገቡ ኃይሎች የሉምን? መባል አለበት፡፡ በተለይ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ከአገር ወደ ውጭ የሚወጣ ገንዘብ ሚስጥሩ ምንድነው? ማለት የዋህነት አይደለም፡፡

በድምሩ በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ በየድርሻቸው ላይ መወሰን የሚችሉ ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና መንግሥታዊ ተቋማት በዝተዋል፡፡ በወረዳና በቀበሌ ሳይቀር በሚሊዮን የሚቆጠር የመንግሥት በጀት ይመደባል፡፡ ለግዥ፣ ለሽያጭና መሰል ሥራዎችም ይውላል፡፡ በየክልሉ እንደ አሸን እየፈሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳን  በመቶ የሚሊዮኖች የሚቆጠር የግንባታና የአስተዳደር በጀት እያገኙ ነው፡፡ የብዙዎቹ የፋይናንስ አስተዳደር ለምዝበራ የተጋለጠ ቢሆንም፡፡ ታዲያ ይህን ለጋ ያልተማከለ የሀብት ክፍፍል በጥብቅ ዲሲፕሊን፣ በጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ በሕግና በሥርዓት መምራት ካልተቻ ፈተና ሆኖ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ሒደቱን መመርመርና ሕመምን ማከም የነገ ሥራ ሊሆን አይገባም፡፡

  1. ፌዴራሊዝም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ሊላበስ ይገባል

በዚህች አገር ታሪክ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በጭላንጭል ደረጃ እንኳን፡፡ ይኼ ደግሞ በብዙዎቹ ኅብረ ብሔራዊነት ባለባቸው አገሮችም የሚስተዋል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በብዙ ቦታ የማንነት ብዝኃነት ያቀፈ መንግሥት ከመሠረት ይልቅ፣ ልዩነትን ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ ታይቷል፡፡ ከዚህ እውነታ ተነጥሎ የማይታየው የአንድ ቡድንን የበላይነት (Hegemonic Control) አየሩን መሙላቱ እንደማይቀር ከላይ ለመጠቃቀስ ተሞክሯል፡፡

በአሁኒቷ ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ለዘመናት በአሐዳዊ አስተሳሰብ የኖረ ማኅበረሰብ መብቱንና ተሳትፎውን እያራመደ መምጣቱ ይታያል፡፡ ይሁንና በሕዝቡ ውስጥም ሆነ መሬት ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሚመጣ ኅብረ ብሔራዊ ውህደት (Multi Cultural Integration) መገንባት ካልተቻለ ውጤቱ አመርቂ ሊሆን አይችልም፡፡

ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚታየው በብሔሮች መካከል የመናናቅ፣ የመዘላለፍና የጥላቻ ፖለቲካ መንዛት የሚሹ ፅንፈኛ ወገኖች አሉ፡፡ በቀደሙት ሥርዓቶችም ሆነ አሁን በሥልጣን ላይ የነበሩና ያሉ መሪዎችን ወይም ቡድኖችን ከወጡበት ማኅበረሰብ ጋር በመጨፍለቅ፣ ሕዝብን እንደ ሕዝብ መውቀስና መርገምም ይታያል፡፡

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው አሁንም በርካታ ቋንቋዎች፣ ከዘጠኝ የማያንሱ የክልል ባንዲራዎች፣ የተለያዩ ባህሎችና ወጎች ቢኖሩንም አንድ የጋራና የሥራ ቋንቋ አለ (ያውም በታሪክ አጋጣሚ የዳበረና የተሻለ ሊያግባባም ሆነ የጋራ የመሆን ዕድል ያለው)፡፡ ለዘመናት የምንኮራበት የአንድ ሰንደቅ ዓላማ ባለቤቶችም ነን፡፡ በታሪክ ድርሳናት ላይ ልዩነቶች እንዳሉ ቢታወቅም የሺሕ ዓመታት ታሪክ ባለቤቶች ነን፡፡ የእምነትና የሃይማኖት፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦናችንም ውህደታችንን ለማጥበቅና ለማጠናከር የሚያስችለን ነው፡፡ ይሁንና ወደ ጠንካራ አንድነትና ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት በኩል የጎላ ድክመት ይስተዋላል፡፡

መንግሥት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እንገነባለን ሲል ክልል ከክልል ወይም ዞን ከክልል የሚያገናኝ መንገድ በመሥራት ነው፡፡ ትልቅ ፋብሪካ ወይም ግድብ በመገንባት፣ ባቡር በመዘርጋት አድርጎ የሚወስድ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የጠነከረ ውህደት (መጋባት፣ መዋለድና አብሮ መኖር…) ካልተፈጠረ የጋራ ቤት ሊኖር አይችልም፡፡ የጋራና የውል የምንለው ዓርማ፣ ሀብትም ሆነ ሌላ ነገር ከጠፋም ሁሉም የሚያስበው ስለመንደሩ ኮረብታዎችና ተፈጥሮ ነው፡፡

ለዚህም ነው የፌዴራል መንግሥቱ መዋቅር፣ የመከላከያ ሠራዊቱ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲው፣ ወዘተ የጋራ ተዋጽኦና የሁሉም የበላይነት ስሜት ሊፈጥር ይገባል የሚባለው፡፡ እንደ ጠባብነትና ትምህክተኝነት ያሉ የአገር ነቀርሳዎችን ጠንክሮ መፋለምም ወሳኝ መሆኑ ተደጋግሞ የሚገለጸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለከፈን በዘር ላይ የተመሠረተ ጋብቻም ሆነ መዋለድ ጥርጣሬ ውስጥ ከመግባት ወጥተን፣ በኢትዮጵያዊና አልፎም አፍሪካዊ ስሜት በኩራት መዋሀድ ይኖርብናል የምንለው፡፡

በድምሩ ፌዴራሊዝምን ከነአሰስ ገሰሱ እንቀበል ሲባል ጎርፉ ይዟቸው የሚያመጣቸውን የአገር አረሞችና በታታኝ አስተሳሰቦችን በመጠበቅ፣ በኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመኖር መዘጋጀት ይገባናል፡፡ ካለፈው የተሳሳተ ታሪካችን በመማር የተሻለ ሥራ መሥራትም ይጠበቅብናል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን እያበበ የመጣው ፌዴራላዊ ሥርዓት ማደግና መጠናከር ያለበት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በጥንካሬ ሚናችንን መወጣት አለብን፡፡ በኢኮኖሚ ለመበልፀግ ስንተጋ፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መንገሥና በማንነታችን እየኮራን አዲስ የሠለጠነና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ በማነፅ ሊሆን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles