ኢትዮጵያ የዘመነ አዲስን ሦስተኛ ሚሌኒየም በ2001 ዓ.ም. ለመቀበል በዋዜማው በ2000 ዓ.ም. ላይ አዲስ ክብረ በዓል ማክበር የጀመረችው የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ነበር፡፡
በዓሉ ሕጋዊ መሠረት ይዞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወጣ አዋጅ ቁጥር 654/2001 አንቀጽ 4 ላይ በየዓመቱ የመስከረም ሁለተኛው ሰኞ እንዲከበር በደነገገው መሠረት፣ ለስድስት ዓመታት በወርኃ መስከረም (አንዳንዶቹ ሦስተኛው ሰኞ ላይ ቢከበሩም) ተከብሯል፡፡
ነገር ግን በሰንደቅ ዓላማ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2፣ ንኡስ አንቀጽ 4፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሚል ርእስ ሥር ‹‹ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን (ከዚህ በኋላ ‘ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን’ እየተባለ የሚጠራ) በየዓመቱ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሰኞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡›› ባለው መሠረት፣ አምና የጥቅምት የመጀመሪያ ሰኞ የዋለው ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ስለነበረ በዓሉ በአግባቡ ተከብሯል፡፡
ዘንድሮ በዓሉ የጥቅምት የመጀመሪያ ሰኞ በዋለበት ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. መከበር ሲገባው፣ በሁለተኛው ሰኞ ጥቅምት 8 ቀን እንዲከበር የተደረገው ለምንድን ነው?