Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዲቪው ትርታ

የዲቪው ትርታ

ቀን:

ቀደም ባሉት ዓመታት ዲቪ ሲደርሳቸው ቤትና ሌላ ንብረታቸውን ሸጠው በስኬት የተሞላ የአሜሪካ ሕይወታቸውን አልመው የተጓዙ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ቤተሰብ ቤትና ንብረትን ጠቅልሎ አሜሪካ ገባ የሚለውን ማድመጥ የተለመደና ምንም ዓይነት ጥያቄ የማይነሳበት ነገርም ነበር፡፡ ምክንያቱም የዲቪ ሎተሪ በተጀመረበት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በስፋት የነበረው አመለካከት ለመማርም ይታሰብ ለመሥራት በአሜሪካ ነገሮች የተመቻቹ ናቸው፤ ለዚህም የትኛውንም ዓይነት ዋጋ መክፈል ተገቢ ነው የሚል ዓይነት ነበር፡፡

ስለዚህም አሜሪካ ለመሄድ ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሎተሪው ለወጣለት ሰው ከፍተኛ ብር በመስጠት በጋብቻ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ልጆች እንዲሁም የቤተሰበ አባል ሆነው የተጓዙ በርካቶች ናቸው፡፡

ለዲቪ ተጋብተው አሜሪካ ላይ ጋብቻቸውን ያጸኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ ላይ በተመሠረተ የሐሰት ጋብቻ አሜሪካ ገብተው ወደ እውነተኛ የትዳር ሕይወታቸው መመለስ የቸገራቸውም እንዲሁ አሉ፡፡ ዲቪ በዚያ ጊዜ የሐሰት ትዳር ለመመሥረት፣ ለዓመታት በፍቅር የኖሩበትን ትዳር ለማፍረስ፣ ስለፍቅር የገቡትን ቃል ለማጠፍ፣ ለብዙ ብር ብድር አመኔታ ለማግኘት የይለፍ ካርድ ያህልም ነበር በዚያ ጊዜ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ኢንተርኔት ቤቶት ተዘዋውረን ለመመልከት እንደሞከርነው ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር ዲቪ የመሙላት ነገር ዛሬ ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል፡፡ የዲቪ ሎተሪ መጀመር ይፋ ከሆነበት እለት ጀምሮ ኢንተርኔት ቤቶች የተለያዩ ማስታወቂያዎችን በባነር በማሠራት ጭምር ደጃፋቸው ላይ ሰቅለው የዲቪ ማስሞላት ቢዝነሳቸውን ለማጧጧፍ ይዘጋጁ ነበር፡፡

ዲቪ በሚሞላበት ወቅት ኢንተርኔት ቤቶች በግርግር ይሞሉ፤ ዲቪ ለመሙላት ሠልፍ ሁሉ ነበር፡፡ ያ ግርግር ዛሬ አይታይም፡፡ ምናልባት ሰዎች ኢንተርኔት ቢሯቸው፤ ቤታቸው በመኖሩ ነው ሊባል ቢችል እንኳ የአገሪቱ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ የሚገኝ ኢንተርኔት ቤት ባለቤት ነው፡፡ በቤቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሑፍ በመተየብ፣ ለተማሪዎች እንዲሁም አካባቢው ላይ በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጉዳይ ለማስፈጸም ለሚሄዱ ሰዎች የፎቶ ኮፒ አገልግሎት በመስጠት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ዲቪ ማስሞላት አዋጭ ቢዝነስ እንደበር በማስታወስ ‹‹በአንድ ወር ውስጥ እስከ ሃያ ሺሕ ብር ይሠራ ነበር፡፡ እኛም ሲጀመር በርና መስኮት ላይ ማስታወቂያዎችን እንለጥፍ ነበር›› ይላል፡፡

ዘንድሮ ግን ዲቪ ማስሞላቱን እንደተወው አምናም እንዳልሠራ ገለጸልን፡፡ ለምን? ለሚለው ጥያቄአችን መልሱ ‹‹ብዙ የሚጠይቅ ሰው የለም በቀን አንድ ሰው ቢጠይቅ ነው፡፡ ለአሥርና ለስምንት ብር ብዬ አሥር አሥራ አምስት ደቂቃ ከማጠፋ ሳልቸገር ፎቶ ኮፒዬን ብሠራ ያዋጣኛል ብዬ ነው›› የሚል ነበር፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የዲቪ ማስሞላቱን ሥራ እየተውት መሆኑን ገልጾልናል፡፡

በአቅራቢያው ስድስት ኪሎ ከሚገኝ አንድ ሌላ ኢንተርኔት ቤት ያገኘናት ሠራተኛ እንደገለጸችልን ሥራው እስከዚህም ባይሆን የዲቪ ፎርም ያስሞላሉ፡፡ ለአንድ ሰው የዲቪ ፎርም ማስሞላት አሥር ብር፤ ጥንዶች ሲሆኑ ደግሞ ለእያንዳንዳቸው አሥራ አምስት ብር ያስከፍላሉ፡፡

ስድስት ወይም ሰባት ጊዜ ያህል ዲቪ መሙላቷን የምትናገረው ወ/ሮ ወሰን አድማሱ የአሥር ዓመት ልጅ አላት፡፡ ቤት ሠርተው ጥሩ የሚባል ኑሮ የሚኖሩ ቢሆንም ወደ አሜሪካ የመሄድ ፍላጎት ስላላቸው ልጃቸው አንድ ዓመት ሳይሞላው ጀምሮ (ከተጋቡ ጀምሮ ማለት ነው) ዲቪ እንደሚሞሉ ገልጻልናለች፡፡

እሷ እንደምትለው ሁልጊዜም የዲቪ ሎተሪ መጀመሩ እንደተሰማ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ነው የሚሞሉት፡፡ እሷም ባለቤቷም ለጉዳዩ ትኩረት ስለሚሰጡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ከመሙላት ተዘናግተው አያውቁም፡፡ አሜሪካን አገር የሚገኝ ትልቅ ወንድሟም ሳይጀመር ጀምሮ ስለሚያሳስባቸው ዲቪ እሷና ባለቤቷ የሚረሱት ነገር አይደለም፡፡

እንዳነጋገርነው የኢንተርኔት ቤት ባለቤት አምና እሷና ባለቤቷም ዲቪ አልሞሉም፡፡ ዘንድሮ ደግሞ መጀመሩንም አለማወቃቸውን ገልጻልናለች፡፡ ቤት ከመሥራታቸው በፊት ለዓመታት የኖሩት ተከራይተው ነበር፡፡ ቤት ሲቀይሩም ሆነ ሌሎች ውሳኔዎችን ሲወስኑ ውሳኔዎቻቸው ‹‹ዲቪ ከደረሰን›› የሚለውን ታሳቢ ያደረጉ እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ግን በዲቪ ተስፋ በመቁረጣቸው ከከተማ ወጣ ብሎ የጀመሩት መኖሪያ ቤታቸውን አፋጥነው በመጨረስ መግባታቸውን ትናገራለች፡፡ ዘንድሮም ዲቪ የመሙላት ፍላጎት የላቸውም፡፡ እሷም ባለቤቷም ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ልጃቸው ከፍ ሲል ለትምህርት እንዲሄድ ግን ይፈልጋሉ፡፡  

ዛሬም አሜሪካ የመሄድ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም በተደጋጋሚ ሞልተው ስላልተሳካላቸው ተስፋ ቆርጠው ዲቪ መሙላት እንዳቆሙ ብዙዎች ነግረውናል፡፡ ከተጀመረ ጀምሮ ዲቪ እየሞሉ እንደሆነ ነገር ግን ዛሬም ድረስ ተስፋ ሳይቆርጡ የዘንድሮውን ሁሉ እነደሞሉ የገለጹልን አሉ፡፡ በማብቂያው ዕለት ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ኢንተርኔት ቤት ዲቪ ለመሙላት ተገኝቶ በነበረው ወረፋ ምክንያት ሞልቶ ከጨረሰ በኋላ ፎርሙ ተልኮ ሳያልቅ ሰዓቱ ሞልቶ ካመለጠው ዕድል ውጭ ዲቪ ከተጀመረ ጀምሮ ዘሎት እንደማያውቅ የገለጸልን አንድ በግል ድርጅት ውስጥ የሚሠራ አካውንታትን ነው፡፡

በሰላሳዎቹ መጨረሻ የሚገኝ ነው፡፡ አዲስ ከሚባሉት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ መምህር ነው፡፡ ‹‹ዲቪ በፖስታ መላክ አቁሞ በኢንተርኔት ከሆነ ጀምሮ ሞልቻለሁ፡፡ እስካሁን አምስት ጊዜ የሞላሁኝ ይመስለኛል፤›› ይላል፡፡ የተሻለ ነገር ፍለጋን ታሳቢ በማድረግ ዲቪ እንደሚሞላና ሕይወቱ የሚሄደው በጣም በዝግታ በመሆኑ ወደ ውጭ መሄድ እንዳለበት ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዲቪ ዓይነተኛ አማራጭ ነው ለሱ፡፡ ብዙዎች ዲቪ ሲሞሉ ይደርሰኛል የሚል ተስፋ ስለሚሰንቁ ከተወሰነ መሙላት በኋላ ተስፋ ቆርጠው የሚያቆሙ ቢሆንም እሱ እንደዚህ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹የልብ ዝግጅቴ ሊደርሰኝ ላይደርሰኝ ይችላል የሚል ነው›› የኔ ድርሻ መሞከር ብቻ ነው ይደርሰኛል ብዬ አልጠባበቅም›› በማለት ይገልጻል፡፡

የዘንድሮውን ዲቨ ሎተሪ ፎርም የሞላው በተጀመረ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ እሱ የሚከታተል ቢሆንም ባለቤቱም ወደ አሜሪካ የመሄድ ከፍተኛ ጉጉት ስላላት ታስታውሰዋለች፡፡ እሱ እንደሚለው በተወሰነ መልኩ እሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ ቢል እንኳ ለልጆቹ (የሦስት ልጆች አባት ነው) የተሻለ ነገን ለመፍጠር ዲቪ መሙላቱ ትክክል እንደሆነ ይገልጻል፡፡

የሰው ኃይል ፍልሰት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ትልቅ ችግር ነው፡፡ በእውቀቱ በብቃቱ አገሩን ያገለግላል የሚባለው ወጣቱ መሰደድ ችግር መሆኑም በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ እንደሌሎች ወጣቶች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ዲቪ ይሞላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮችን በመጥቀስ ሁሌም ወደ አሜሪካ መሄድ መፈለጉ ምናልባትም በአዕምሮው ጥያቄ ያስነሳበት እንደሁ ጠየቅነው መምህሩን በአዕምሮው የሚፈጠረውን ሙግት የሚያስታርቀው አገሩን ጥሎ ዕድሜ ዘመኑን አሜሪካ መኖር ሳይሆን ህልሙ ወደ አገሩ በመመለስ እንደሚያገለግል ለራሱ በመንገር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሕይወቴ ሲቀየር ተመልሼ ለአገሬ በመሥራት እካሳለሁኝ፡፡ የማስተምራቸው ተማሪዎች ዲቪ ሲሞሉ ቢያጋጥመኝ ለምን ትሄዳላችሁ አልልም፡፡ ምክንያቱም አገር ሁሉ እየሄደ ነው ተመልሳችሁ አገራችሁን ጥቀሙ ብቻ ነው የምለው፤›› ይላል፡፡

ብዙዎች የተሻለ ነገር ፍለጋ ከአገር ሲወጡ አንድ ቀን እንደሚመለሱና ለአገራቸው እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡ የሚስተዋለው እውነት ግን በተለያዩ ምክንያቶች መመለስን ማሰብ እንኳ ሲቸገሩና እንመለስበታለን ያሉት አንድ ቀንም የማይመጣ አንድ ቀን ሆኖ ሲቀር ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ኤምባሲ የወጣ መግለጫ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ. ከ2003 እስከ 2011 ድረስ ባለው ጊዜ በየዓመቱ በዲቪ ሎተሪ ወደ አሜሪካ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት ሺሕ በላይ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2012 ላይ እድሉን አግኝተው የሄዱት 1,264 ሰዎች ናቸው፡፡ በ2013 ደግሞ ቁጥሩ 2,335 ሲሆን በ2014 ደግሞ 2,493 ሆኖኗል፡፡  

የዘንድሮው ዲቪ (DV 2016) የተጀመረው መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚቆይ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...