Wednesday, October 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊዝቅ የተደረገ ሰውነት

  ዝቅ የተደረገ ሰውነት

  ቀን:

  ዓርብ የገበያ ቀናቸው በመሆኑ ማልደው በመነሳት ያዘጋጇቸውን ልዩ ልዩ የሸክላ ውጤቶች ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ የእንጀራ ምጣድ፣ ማሰሮ፣ ሸክላ ድስት፣ ጀበናና የአበባ ማስቀመጫ አዘጋጅተዋል፡፡ የሚቀረው ተጨማሪ ውበት የሚሰጠውን ዘይት መቀባት ነበር፡፡ አንዷ ሸክላ ሠሪ ዘይቱን የምትቀባበት የረባ ቡርሽ አልነበራትም፡፡ እንደ አማራጭ ስትጠቀምበት የነበረው ስስ ፌስታልም አገልግሎቱን በመጨረሱ ጥላ በእጇ መቀባቱን ተያይዛዋለች፡፡ ድክ ድክ የሚል ሕፃን እራቁቱን ቆሟል ከጎኗ፡፡ በጥድፊያ ላይ በመሆኗ በዙሪያዋ ለሚካሄዱ ነገሮች ትኩረት አልነበራትም፡፡

   በእነ ወ/ሮ አሚቾ ማርቆስ ጊቢ ውስጥ ሁለት አባዎራዎች ይገኛሉ፡፡ ጊቢው ጠባብ ነው፡፡ አንደኛው አባወራ አቶ ብርሃኑ ታኬሳ 25 ዓመቱ ነው፡፡ ትዳር የያዘው ገና ልጅነቱን ሳይጨርስ በ14 ዓመቱ ነበር፡፡ ስምንት ልጆች አፍርቷል፡፡ ላይ በላይ የተወለዱት ሕፃናት የተጎሳቆሉ ናቸው፡፡

  ትንሿ ጎጆ ከአቅሟ በላይ ታጭቃለች፡፡ ከአንደኛው ጥግ አንድ ጥጃ ታስሮ ይታያል፡፡ ሌላኛው ጥግ ደግሞ ማብሰያ ነው፡፡ ቁርስ ለማብሰል የተለኮሰው እሳት አልጠፋም፡፡ ቤቱ በጭስ ታፍኗል፡፡

  በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ሕይወታቸው ግን ከሌሎቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የተለየ መልክ አለው፡፡ የሚኖሩት ከሌላው ኅብረተብ ተነጥለው ነው፡፡ ወደ ቤታቸው ለመድረስ ረዥም የእግር መንገድ መጓዝ፣ የመቃብር ሥፍራ እንዲሁም ደን ማቋረጥ ግድ ይላል፡፡ በዚህ አካባቢ ከመሰሎቻቸው ጋር ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የተገለሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥንብ ይበላሉ፣ ይሸታሉ፣ ርኩስ ናቸው በሚል ‹‹ፉጋ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

  ፉጋ የሚል አንቋሻሽ ስያሜ የተሰጣቸው ሸክላ ሠሪዎች በሌሎቹ የአካባቢው ተወላጆች ዘንድ ከሰው በታች ተደርገው ይታያሉ፡፡ በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ፉጋዎች በከምባታ አካባቢ በመጀመርያ ከሠፈሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ናቸው፡፡  ቁጥራቸው በአሁን ወቅት ከ32 እስከ 35 ሺሕ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ በአንድ ቦታ ሰብሰብ ብለው ሲኖሩ አልፎ አልፎ ተበታትነው ሲኖሩ ይታያል፡፡ ነገር ግን የሚኖሩበት የተወሰነ ቦታ የላቸውም፡፡ ብዙ ጊዜም በጫካ ውስጥ አልያም ከሌሎች መሬት ተጠግተው ይኖራሉ፡፡ ከሚኖሩበት ቦታ ድንገት የመፈናቀል ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው፡፡        በሸክላ ሥራ የሚታወቁት ፉጋዎች ሸክላ የሚሠሩበትን አፈር ለማግኘትም ይቸገራሉ፡፡

  በአካባቢው የሚገኘው ሌላ የኅብረተሰብ ክፍል ዎማኖ ይባላል፡፡ ዎሞኖዎች ለፉጋዎች ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይከፍሉ የተለያዩ ሥራዎችን ያሠሯቸዋል፡፡ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ አሜን ብለው ካልተቀበሉ ከሚኖሩበት ይፈናቀላሉ፡፡ ስለዚህም የሚታዘዙትን የጉልበት ሥራ ለመሥራት ይገደዳሉ፡፡

  ትዕዛዝ ለፉጋዎች ከመቀበል ባለፈ ከዎማኖዎች ጋር ምንም ዓይነት ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠር የማይታሰብ ነው፡፡ ድንገት መንገድ ላይ ቢገናኙ እንኳን ፉጋው ከርቀት የዎማኖዎችን ክብር በሚያጎላ መልኩ እየሰገደ ሰላምታ ማቅረብ ግዴታው ነው፡፡ በሠርግ፣ በለቅሶና በሌሎችም ማኅበራዊ ጉዳዮች ከዎማኖዎች ጋር እኩል መቀመጥ አይቻልም፡፡ በረንዳ ላይ ከአንደኛው ጥግ ይቀመጣሉ፡፡ የሚመገቡትም ከዎማኖዎች የሚተርፈውን ነው፡፡ ሌላው በሚጠጣበት ዕቃ እንዲጠጡም አይፈቀድላቸውም፡፡ በመሆኑም ውኃም ይሁን ሌላ ነገር በቅጠል እንዲጠጡ ይገደዳሉ፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ወጥተው ለመሸመት ቢሹ ሻጩ ከእጃቸው ገንዘብ መቀበል ስለማይፈልግ ይቸገራል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀምም አይችሉም፡፡ አንገታቸው ላይ ጣል ከሚያደርጉት የበግ ቆዳ ውጪ አልባስ መጠቀምም አይፈቀድላቸውም፡፡

  ዛሬ ላይ ይፈጸምባቸው የነበሩ ግፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ በተለይም በከምባታ ጠንባሮና አላባ ማኅበረሰብ ውስጥ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚንቀሳቀሰው ኬኤምጂ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከ15 ዓመታት በፊት በአካባቢው በጀመረው እንቅስቃሴ ለውጦች እንዲመዘገቡ ጥረት አድርጓል፡፡ ዛሬ ላይ ፉጋ ብሎ መጥራት በሕግ ያስከስሳል፡፡ በምትኩም እጀ ወርቅ ተብለው እንዲጠሩ ተደርጓል፡፡ ከሰው መቀላቀል ችለዋል፡፡ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት እንዲልኩም ተፈቅዶላቸዋል፡፡

  ምንም እንኳ ለውጥ ቢኖርም መገለልና መድሎው ዛሬም አለ፡፡ በአንድ አምልኮ ሥፍራ ማምለክ ቢችሉም አብሯቸው ለመቀመጥ ፈቃደኛ የሚሆን የለም፡፡ በዚህ ረገድ አቶ ብርሃኑ የገጠመውን እንዲህ ያስታወሳል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ተጠቃቅሰው ከአጠገባችን ይነሳሉ፡፡ አልፎ አልፎም ክፉ የሚናገሩን አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የአምልኮ ቦታችንን ቀየርን፤›› ይላሉ፡፡ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ቢልኩም ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡

  ከዎማኖዎች ጋር በትዳር መጣመር ከባድ ቢሆንም ኬኤምጂ ባደረገው ቅስቀሳ የተወሰኑ ሰዎች ይህን እንዲደፍሩ ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ጥንዶቹ ከፍተኛ ችግር ሲገጥማቸው ይስተዋላል፡፡ አጋጣሚው ፉጋዎች እንደማንኛውም ሰው መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት ቢሆንም ከዚያኛው ወገን የሚፈጠረው ጫና በሕይወት እስከመፈላለግ ይደርሳል፡፡

  በዚህ ረገድ በቅርቡ ጋብቻ ፈጽመው ልጅ ያፈሩት የወ/ሮ ገነት ሊሬና አቶ ግርማ ዘለቀ ሕይወት ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ስለተፈጠረው ሁኔታ ከዎማኖ በኩል የሆኑት የገነት ቤተሰቦች እንደሰሙ ‹‹አዋረድሽን›› በሚል ደብድበዋታል፡፡ አብራው እንዳትሆን አስጠንቅቀዋታል፡፡ ግንኙነታቸው እንዳልተቋረጠ የሰሙት ወላጆቿ ቢዝቱባትም በትዳር ከመጣመር አላገዷቸውም ነበር፡፡

  ከቤተሰቦቿ ተደብቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ድብብቆሹ አላዘለቃቸውም፡፡ ቤተሰቦቿ እውነቱን ደረሱበት፡፡ ‹‹በነፍስ ሲፈልጉኝ በየገጠሩ እየተደበቅን ነበር የምንኖረው፤›› የሚለው አቶ ግርማ ሁኔታው አሳሳቢ ስለነበር ውድቅት ላይ አካባቢውን ለቅቀው ሆሳዕና እንደገቡ ይናገራል፡፡ ከአካባቢው ከተሰወሩ በኋላ ያሉበትን የሚያውቅ አልነበረም፡፡ የቀን ሥራ እየሠሩ ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ ልጅም ወልደዋል፡፡ ዱራሜ የተገኙት ባለፈው ሳምንት ኬኤምጂ ባዘጋጀው የእኩልነት መድረክ ላይ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ነበር፡፡

  በተለያዩ አገሮች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ እንዲሁም በመደብና በመሳሰሉት አንዱ የኅብረተሰብ ክፍል ሌላውን ሲያገል ቆይቷል፡፡ ይህ የተለያዩ አገሮች እውነታ እንደሆነ ሁሉ በኢትዮጵያም ፉጋን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መገለል የታሪክ እውነት ነው፡፡ በገጠር አካባቢ ብቻም ሳይሆን አዲስ አበባ ላይ ጭምር ከዶርዜ፣ ቀጨኔ አካባቢ ከሚኖሩ ሸክላ ሠሪዎች (ብዙዎች አጠራር ቀጨኔዎች) ጋር ጋብቻ መመሥረት ችግር የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ዛሬም ነገሮች ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል ለማለት የማያስደፍሩ ነገሮች አሉ፡፡

  በደቡብ ክልል በዳውሮና በቦንጋ አካባቢ የሚገኘው ‹‹መንጃ›› የተባለው የኅብረተሰብ ክፍልም ተመሳሳይ መገለል ይደርስበታል፡፡ መንጃዎች እንደ ፉጋዎች ሁሉ ከሌላው ማኅበረሰብ ተነጥለው በጫካ ዙሪያ ይኖራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም አድነው የሚመገቡ ሲሆን፣ ከሌላው የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ የተገፉ መሆናቸውን የምትናገረው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነችው ወይዘሪት ማጂ ኃይለማርያም ነች፡፡ በመንጃ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ጥናት ያደረገች ሲሆን፣ ፒኤችዲዋን በመሥራት ላይ ትገኛለች፡፡

  ጥናታዊ ጽሑፉን የሠራችው እ.ኤ.አ. በ2009 ሲሆን ጥናቷ መንጃዎች የሚደርስባቸውን መገፋት ያሳያል፡፡ ጥናቱን በሠራችበት ወቅት በዳውሮ አካባቢ ቁጥራቸው 11,000 የሚሆኑ መንጃዎች ነበሩ፡፡ የሚኖሩት ከኅብረተሰቡ ተነጥለው ከተራራ ጫፍ ላይ ወይም ከገደል ሥር ነው፡፡ የሞተ ከብት፣ ጦጣና ጃርት አድነው ይመገባሉ፡፡ መጥፎ ጠረን አላቸው፣ እንዲሁም እርኩስ መንፈስ አላቸው ተብሎ ስለሚታሰብ በማንኛውም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ አይካተቱም፡፡

  ‹‹ውኃ ጠምቷቸው ቢጠይቁ የሚሰጣቸው በሰባራ ብርጭቆ ወይም በቅጠል ነው፡፡ ይህም እነሱ የነኩት ዕቃ ስለሚጣል ቢጥሉም እንዳይቆጫቸው ነው፤›› የምትለው ወይዘሪት ማጂ በአጋጣሚ ከቤት ቢገቡ ቤቱ እንደረከሰ ይቆጠርና ርኩስ መንፈስን ለማጥፋት በሚል ሃይማኖታዊ ዕድሳት እንደሚደረግ ገልጻለች፡፡

  ከከተማ ርቀው ስለሚኖሩ ጤና፣ ትምህርና ሌሎችም የመሠረተ ልማት አውታሮች አይደርሳቸውም፡፡ በዚህም በማንኛውም የጋራ ጥቅም የሚወክላቸው እንዳይኖር ሆኗል፡፡ ይህም በድህነት እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡ መሰል የኅብረተሰብ ክፍሎች በደቡብ አካባቢ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ በሰሜኑ አካባቢ በተለይም በአማራ ክልል በፈላሻ ማኅበረሰብ ላይም ጎልቶ ይስተዋላል፡፡

  በጣና ሐይቅ ዙሪያ የሠፈሩት ፈላሻዎች የዘር ግንዳቸው ከወደ እሥራኤል መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህም ቤተ እስራኤላውያን ይባላሉ፡፡

  ዲና ፍሪማን የተባለችው ጸሐፊ በመጻሕፏ እንደገለጸችው ጥሩ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበረው በዘመነ መሳፍንት ወቅት ከሥርወ መንግሥቱ ጋር በነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የአገዛዝ ሥርዓቱ ሲዳከም የእነሱም ዕጣ ተመሳሳይ ሆነ፡፡ በወቅቱ ሥልጣን የያዘው ንጉሥ ይዞታቸውን በማስለቀቅ በጣና ዙሪያ እንዲሠፍሩ አስገደዳቸው፡፡ እንደ ዜጋ አይቆጠሩም፡፡ የራሳቸው የሆነ የሚያርሱትም መሬት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም የተለያዩ የዕጅ ሥራዎች ሠርተው በመሸጥ ኑሮን ይገፉ ጀመረ፡፡ ወንዶቹ አንጥረኛ፣ ቆዳ አልፊ ሲሆኑ ሴቶቹ ደግሞ ሸክላ ይሠራሉ፡፡ ከእጅ ሥራቸው ጎን ለጎንም ሌሎች ሊሠሯቸው የማይፈቅዱትን በሕግ የተፈረደባቸውን የወንጀለኞችን አካል እንዲቆርጡ፣ የቆዳ በሽታ እንዲያክሙ ይገደዱ ነበር፡፡ ቡዳ ናቸው በሚልም ሌላው ኅብረተሰብ ያገላቸው ጀመር፡፡ ሌሊት ሌሊትም ከሰውነት ወደ ጅብነት ተቀይረው ሬሳ ከመቃብር አውጥተው ይበላሉ ስለሚባል ይደርስባቸው የነበረው የሥነ ልቦና ጫና ከባድ ነበር፡፡

  ጉማሬ አድነው ይበላሉ በሚል የሚገለሉት የወይጦ ማኅበረሰቦችም የሚኖሩበት የራሳቸው የሆነ ቦታ ያልነበራቸው ናቸው፡፡ እንደፈላሻዎቹ ሁሉ በአማራ ክልል ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ኑሮን ለማሸነፍ ይጥራሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ከሌላው የአካባቢው ማኅበረሰብ መሬት በመከራየት ያርሳሉ፡፡

  በኦሮሚያ አካባቢም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ይታወቃል፡፡ ዋታ በኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ የሚኖሩት ራቅ ባለ አካባቢ ከተራራ በስተጀርባ ነበር፡፡ ሙት ይበላሉ፣ ሃይማኖት የላቸውም በሚል ኅብረተሰቡ ያገልላቸው ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ከሰው ተቀላቅለው ቢኖሩም ዛሬም የመገለሉ ሁኔታ አለ፡፡ በተለይም በትዳር መጣመር ዛሬም ችግር እንደሆነ የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ኢዛና አምደወርቅ ብዙ ጊዜ በዝቅተኛ መደብ የሚጠቃለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሬት እንደማይኖራቸው ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሚኖሩበት የተወሰነ ቦታ ማግኘትም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህም የተለያዩ የእጅ ሥራዎች መሥራት ይጀምራሉ፡፡ የአኗኗር ደረጃቸውም ዝቅተኛ ስለሚሆን በአመጋገብና በአለባበስ ከሌላው ይለያሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሌላው ኅብረተሰብ እንደተለየ ፍጡር ሁሉ ይፈርጃቸዋል፡፡ በዚህም የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ሆኗል፡፡

  ሁኔታው ከዓመታት በፊት አስከፊ ገጽታ ቢኖረውም ዛሬ ላይ መሻሻሎች አሉ፡፡ ‹‹በተለይም በድሮ ጊዜ መሬት ላራሹ ሲባል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትንሽም ቢሆን መሬት ማግኘት ችለዋል፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች ተቀላቅለው መኖር የጀመሩ ቢሆንም መገለሉ አሁንም እንዳለ አልሸሸጉም፡፡

  ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ይታያል፡፡ ይበልጥ ለውጥ ለማስመዝገብ ግን ‹‹በሚገለሉት ማኅበረሰቦች ላይ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ እንዲያርጉ መሠራት አለበት፡፡ የመገለላቸው ምክንያት የሆኑ ድርጊቶችንም ማስቀረት ወሳኝ ነው፤›› ሲሉ የችግሩ መፍትሔ ነው ያሉትን ተናግረዋል፡፡

   

    

         

    

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img