Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኩርፊያና ፈገግታ ሲደበላለቁስ?

ሰላም! ሰላም! “ስቴፈን ሐውኪንግ ሐበሻ ሳይሆን አይቀርም” አለኝ በቀደም አንድ ወዳጄ። የዓለም ወሬ ለመስማት በእጁ ሬዲዮ ይዞ፣ ዓይኑን ቴሌቪዢን ላይ ሰክቶ ቢውል ቢያድር የማይሰለቸው ታውቃላችሁ? እስኪ አሁን የመንደር፣ የአገር፣ የባንዲራ ፖለቲካና ነገር አጠገቡ እያለ ሰው በራሱ ላይ ተጨማሪ ሕመም ይናፍቃል? እያደር ብሷላ ዓለም እብደቷ! እንዲያውም የባሻዬ ልጅ፣ “ዓለማችን የተጠናወታት የካንሰር በሽታ፣ ከሰው ልጆች የሚለየው ሳይጨርሳት የሚጨርሰን መሆኑ ብቻ ነው፤” ብሎኛል። ማለት መቼ ይታክተውና እሱ። እና ያን ወዳጄን ትኩር ብዬ እያየሁት፣ “ማነው ደግሞ ስቴፈን ሐውኪንግ?” አልኩት። ለራሴ እንኳን የፈረንጆቹ የጎረቤቶቼ ስም እየጠፋብኝ ተቸግሬያለሁ እኮ። ወድጄም መሰላችሁ? አብሬው አፈር የፈጨሁትና ውኃ የተራጨሁት ምን ቫይረስ እንደሚገባበት አላውቅም፣ “ሐበሻ ብለህ አትጥራኝ” እያለኝ ነዋ! “ኢትዮጵያዊነትን እዛው ብቻህን ተሸከመው፤” ያለኝም አለ። “ኧረ ምን ጉድ ነው?” ብዬ ሳልወድግ በግድ መሰል አገኘሁ ስል ደግሞ “ቢዚ ነን” ይሉኛል።

“ምን ተገኘ?” ካልኩ ደላላነቴ አላስችል ብሎኝ፣ ቢዝነስ ነገር ከሆነ ራሴን ልሸጥ (‘አንበርብር አንተ እኮ ደላላ አትመስልም። ዘንድሮ  ቢዝነስ ማለት ራስን መሸጥ ነው’ ሲለኝ የኖረ ወዳጄ በሙስና ቅሌት አሁን ሸቤ ነው። ግን ‘የታሰሩትን ጠይቁ!’ አልተባለም?) ስጠይቃቸው፣ “የተሰቀለ ባንዲራ አውርደን የወረደ ባንዲራ እየሰቀልን ነው፤” ይሉኛል። እኔ የማንም አይገርመኝም። ብቻ የተቀደደ ካልሲያቸውን ሳይቀይሩ ባንዲራ የመቀያየር ፋሽን ውስጥ የገቡ ሰዎች ናቸው የሚያስገርሙኝ። እንዳይገባን እንጂ እንዲገባን ስለማንታገስ አይመስላችሁም? አልተግባባንም መሰለኝ። እሺ እሱን ተውትና ሐበሻው ራሱ ሐበሻነት ሰለቸኝ እያለ፣ የሰው ሰው ሐበሻ ሊሆን ነው መሰል ያለኝ ወዳጄ ሐውኪንግ ስመ ጥር፣ ‘ጂኒየስ’፣ የሥነ ህዋ ተመራማሪ ‘ሳይንቲስት’ እንደሆነ አብራራልኝ። ሐበሻነትን የለጠፈበት በ‘ጂኒየስነቱ’ መስሎኝ ጮቤ ረገጥኩ። በስንቱ ነገር መሰላችሁ ሳናጣራ ስንዘል የተሰበርነው!

ኩራት ተሰማኝ ብያችኋለሁ። “ይገርምሃል እኛ ኢትዮጵያውያን እንዳሁኑ ጀግንነትና ስመ ጥርነታችን ለመጠጥ ማስታወቂያ በግብዓትነት ከማገልገሉ በፊት…”  እያልኩ ስቀጥል፣ “ኧረ በእሱ አይደለም ሐበሻ ነው ያልኩህ፤” ብሎ አቋረጠኝ። አቤት! ሰው ዕድሜ ልኩን ባልተያዘ ነገር እያበጠ ቱስስስስ ሲል ይኖራል? ቀላል አሟሸሸኝ እንዴ? “አንበርብር ሰውዬው እኮ ከአልበርት አንስታይን ቀጥሎ አለ የተባለ ‘ኩላሊት’ ያለው ሰው ነው። ሰሞኑን ታዲያ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ አላህ፣ እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም። አረጋግጫለሁ አይል መሰለህ?” ሲለኝ ተወዛገብኩ። “እና ይኼ ምኑ ነው ሐበሻ?” ብለው፣ “እህ! ‘የለም’ ሞልቶ የተረፈው እኛ አገር ነው ብዬ እኮ ነው። ፈረንጅ በባህሪው ‘አልቋል’፣ ‘የለም’፣ ‘ሊሆን አይችልም’፣ ወዘተ ቃላት መጠቀም እንደማይወድ ሌላው ቢቀር ስራህ ሳያሳይህ አልቀረም። በተቃራኒው ደግሞ አየህ የእኛ ኑሮ የተመሠረተው በ‘የለም’ ነው። መብራት የለም። ውኃ የለም። ፍትሕ የለም። ሰው የለም። ዴሞክራሲ…” እያለ ሊቀጥል ሲል ማቋረጥ ነበረብኝ። “በቃ! በቃ!” . . .  ‘ድው!’  እንደ አፈ ጉባዔ መዶሻ ነረትኩበት። ኦ፣ ለካ ገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ፓርላማውን በመቆጣጠሩ ከአጀንዳ እያፈነገጠና በጥያቄ እያፋጠጠ ንግግሩ የሚቋረጥበት ተቃዋሚ የለንም። ‘የለም’ አልኩ እንዴ እኔም? በሉ! በሉ! የለሁበትም!

 ግድ የለም ነገም ሌላ ቀን ብለን እንለፈውና ወዳጄ በእንቶ ፈንቶ ጊዜን የፈጀብኝ ስለመሰለኝ ቀጥል አልኩ። እንኳንም ጪስ ማውጫ አልኖረን። ቢኖረን ኖሮ ግን አስባችሁታል? አየር በመበከል በኢንዱስትሪ ብዛት የትና የት ከደረሱት አገሮች በላይ አየር በመበከል ካሳ ከፋዮቹ ዛሬ እኛ ነበርን። ሳይደግስ አይጣላ እሱ! ታዲያ በመንገዴ ባሻዬን ሳገኛቸው አላስችል ብሎኝ የዓለማችን ቁንጮው ሳይንቲስት ያለውን ስነግራቸው፣ “ሁሉም እየተነፈሱ ፈጣሪን መገዳደር አመላቸው ነው። ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ሆኖ ይኼን አባባሉን ከደገመው መጥተህ እንድትነግረኝ አደራ፤” አሉኝ። ወይ ተስፋ አይሆኑን ወይ ተስፋ አይሰጡን? ተስፋ መንጠቅ ብቻ ሥራቸው ነው ልበል አንዳንድ አወቅን ባዮች? የምር!

ያው ታዲያ ተፍ ተፍ እንዳለ ነው። “ሕይወታችን በምን ይመሰላል? ቢባል አንዱ “በገብረ ጉንዳን” ብሎ መለሰ አሉ። “የትኛው ግብራችን ነው አንተ ካልጠፋ ነገር ከጉንዳን ያመሳሰለን?” ሲባል፣ “ሠልፋችን” ብሎ አረፈው። የትራንስፖርት ችግር ያማረረው መሆን አለበት መቼም። “ቲሽ! በባቡር አይሄድም?” ብዬ ነበር እኔም እንደ እናንተ። “ዘመኑ እኮ የ‘ኮምፒቲሽን’ ነው የ‘ፒቲሽን’ ማሰባሰቢያ አይደለም፤” አለኝ ሌላው፡፡ “እንዴት?” ብዬ ሳልጨርስ (በዚህ ሰብዕናዬን በዚህ እንዴቴን የሚያስቀማ ዘመን ላይ ልውደቅ?’ አያስብልም እሺ አሁን?) “አታየውም እንዴ ፍጥነቱን። እንኳን እኛ ኤሊም በአቅሟ ለዘመናት የተጫናት ድንጋይ እንዲቀልላት ከሆነም እንዲነሳላት የት ሄጄ ልለምን በምትልበት የጥንቸሎች ዘመን፣ የባቡራችን ፍጥነት ፊርማ ለማሰባሰብ ካልሆነ ‘ቻፓ’ ለመሰብሰብ መቼ ይሆናል?” አይሉኝ መሰላችሁ። ለነገሩ ባቡሩ አሁን መገስገስ ጀምሯል እኮ፡፡ እኔ ደግሞ ለተንኮሌ “የምን ፊርማ?” ብዬ ነገር መጠምዘዝ። “የብሶት” መቀጠል እነሱ። “ማነው የባሰው?” እኔ። “የባሰው!” እነሱ። “እንዲያ ስንባባል አለብኝ ጭልምልም” አለች ስትዘፍን ውላ ብታድር የማትሰለቸዋ።

ውሎ ማደር ቀርቶ በቅጽበት ዕይታ አንቅረን የምንተፋው ነገር በዝቷላ እኮ ዘንድሮ። ለማንኛውም እንደኔ እንደኔ “አልበር እንዳሞራ ሰው አርጎ ፈጥሮኝ…” ማለቱን ትተን ከባቡሩ ራስ ወረድ ብንል ጥሩ ነው። ‘በአንድ ራስ ሁለት ምላስ’ ያስተዛዝባል። በዚያ፣ ‘ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን፣ ንፋሱ ዕድገታችን እያላችሁ አስደፈጠጣችሁን’ ብለን ሳንጨርስ በዚህ፣ ጉረኛዋን ጥንቸል ትሁቷ ኤሊ በሩጫ ውድድር ቀድማት መግባቷ ሲተረትለት እንዳላደገ ትውልድ ‘ተኝታችሁ አስተኛችሁን’ ማለት ‘ፌር’ አይደለም። ደግሞስ እንነጋገር ከተባለ ዝግታ ነው ፍጥነት እየጨረሰን ያለው? ባህልና ወጉን ያሳሳው? ሰውን በወጣበት በየመንገዱ ያስቀረው? አብዮቱንስ ‘የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ’ ያስባለው? ዝግመት ነው ፍጥነት? የእናንተ ነገር እኮ አይታመንም። ተከታታይ ፊልምና ድራማ ሰቅዞ ይዟችሁ ‘የለም! አብዮቱን ተወው አላለቀም’ ትሉ ይሆናል እኮ። ‘ይኼኔ ነው መሸሽ’ አሉ ብልጦች!

ኋላማ ሁለት ‘ሲኖትራክ’ ላሻሽጥ የምሆነውን አላውቅም። መቼ ዕለት ነው የባሻዬ ልጅ ድድ ማስጫዎቹ ከመንደራዊነት ወደ ‘ዲጂታል’ ማኅበረሰባዊ ድረ ገጽነት የተለወጡለት የፌስቡክ ትውልድ፣ የሚለጥፋቸውን ፎቶዎች ሲያሳየኝ ነበር። ይኼው ‘ሲኖትራክ’ የተባለ ጦሰኛ ከባድ መኪና የኋሊት ተገልብጦና ፊቱን ወደ ሰማይ ቀስሮ፣ “አውሮፕላን መግጨት አማረኝ” ተብሎ ተጽፎበት አየሁና ሳቅ ሳቅ አለኝ። ልብ አድርጉልኝ። ሳቅ ሳቅ አለኝ እንጂ አልሳቅኩም። “ግዑዝ አፍ የለውም ብሎ የሰው ልጅ በገዛ ራሱ ጥፋት ታዛዡን አዛዥ፣ አገልጋዩን ገናዥ የሚያደርግበት ሥልቱ ሳቅ ሳቅ ያስብላል እንጂ ያስቃል?” ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ፣ “ወደፊት ሕግና ሕግ አስከባሪውን አላፍር አልፈራ ላለው ‘ሲኖትራክ’ መፍትሔ ሆኖ መገኘቱ አይቀርም ብዬ አስባለሁ፤” አለኝ። ‘እኛማ ተናንቀን ምድር ጠቦናል’ ነው እኮ ነገሩ። እኔነት አልገራ ሲል ታዲያ ምን ይሁን?

ባሻዬ መቼ ዕለት ነው አንድ ምሳሌ አጫወቱኝ። ሰውዬው ኑሮ አሰልቺና ድግግሞሽ ሆነበት። የዕለት ተዕለት ውጣ ውረዱን ለመርሳት አውጠነጠነ። ወደ አንድ መምህር ሄደና፣ “በዚህ ሁኔታ መቀጠል አልችልም። የዓለም ነገር ሞላ ሲሉት ይጎላል፣ ጎደለ ሲሉት ይሞላል። ከዚህ ወዲያ ከሚታየው ነገር ባሻገር ወደማይታየው ዓለም ገብቼ በአዕምሮ ነቅቼ ለመኖር ቆርጫለሁና ይምሩኝ፤” ይላቸዋል። “መልካም! አሁን በመንገድ ስትመጣ ምን አይተሃል? አዕምሮህ ውስጥ የሚመላለሰው ምንድነው?” አሉት። “በመንገድ አንድ አህያ አይቻለሁ። በአዕምሮዬም ያለው እሱ ነው፤” አላቸው። “በል ተቀመጥና መጀመሪያ አህያውን ከሐሳብህ አውጥተህ ጣል፤” ይሉታል። ታገለ አልቻለምም። ኋላም ወደ መምህሩ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ! አቃተኝ፤” ቢላቸው፣ “በመንገድ ላይ ያየኸውን የትም የማታውቀውን ያንተ ያልሆነውን አህያ ከሐሳብህ ማውጣት ካቃተህ፣ ታዲያ አንተ እንዴት ነው እኔነትህን አውጥተህ መጣል የምትችለው?” አሉት ይባላል። አደራ ደግሞ አንበርብር ብሎን ነው ብላችሁ ነገር ዓለሙን ረስታችሁ ልማት በማደናቀፍ እንዳታሳሙኝ!

በሉ እንሰነባበት። እንደ ነገርኳችሁ ‘ሲኖዎቹ’ በቀላሉም ባይሆን ተሻሻጡልኝ። የድለላዬንም ተቀበልኩ። ዋዛ ገንዘብ አላገኘሁም። ወደ ቤቴ ሱክ ሱክ እያልኩ መጓዝ ስጀምር ድንገት በአንድ ሕንፃ መስታወት ውስጥ ራሴን ታዘብኩት። ልብስ ቀይሬ አላውቅም። ካፖርቴንም የመተካካት ፖሊሲው ሲያልፍ አልነካውም። ምናምን መስያለሁ። ‘እስከ መቼ ነው እየሠራሁ እንደማይሠራ ሳያምርብኝ፣ ሳለብስ፣ ሳልዘንጥ፣ መኪና ሳልነዳ፣ ቪላ ሳልሠራ፣ እንደ ሰው ‘ቦትል’ ሳላወርድ፣ በውስኪ ሳልራጭ የምገፋው?’ ብዬ አስቤ ከፋኝ። ከማን አንሼ ስሜት ናጠኝ። ይኼኔ በድንገት ስልኬ ጠራ። ባሻዬ ናቸው። የማንጠግቦሽ ቡና አጣጭ፣ በሠፈሩ የተከበሩና የተፈቀሩ ወይዘሮ ማረፋቸውን ባሻዬ አረዱኝ። ስከንፍ ወደ ባሻዬ። ስደርስ፣ “እንጃ ለማንጠግቦሽ እንዴት ብለን እንደምናረዳት አላውቅም፤” አሉኝ። “ምን አገኛቸው ይባላል? ደህና አልነበሩ እንዴ ትናንት?” ስላቸው ባሻዬ “ደህናማ ነበሩ። የሙዝ ልጣጭ ነው አሉ አንሸራቷቸው ወድቀው በዚያው የቀሩት፤” ሲሉኝ ክው። የአንዱ ጥጋብ የአንዱ መውደቂያ የሆነበት ዓለም እንደ አዲስ አስደነገጠኝ።

ከጥቂት ሰዓታት በፊት ሰው መሆኔ ሳይሆን በፋሽን፣ በአበላልና በአጠጣጥ ከሰው ማነሴ ሲያበሳጨኝ የነበርኩት ሰውዬ፣ የታቆረ ውኃ ውስጥ ተነክራ እንደ ወጣች ድመት ቀልቤ ተገፈፈ። ኋላም ብዙ ሰማሁ። ገሚሱ፣ “እንጀራ በልተው ከመጥገብ አልፈው ፍራፍሬ መመገብ የጀመሩት ጎረቤቶቻችን እነማን ይሆኑ?” ሲል ሌላው ደግሞ፣ “ኪሎ ሙዝ ስንት ገባ ይሆን እናንተ?” ሲባባል አንዱ፣ “ሙዙን የበላው የሠፈር ሰው አይደለም አልፎ ሂያጅ ባለመኪና ልጦ ጥሎት ነው፤” አለ፡፡ “አይተሃል?” ሲባል “አይቻለሁ!” ብሎ ሲምል ሲገዘት ብዙ ብዙ አየሁ፣ ሰማሁ። ብዙ ብዙ ነገር ተገነዘብኩ፡፡ ዳሩ አለሁ ሲሉ መቀጨት ቅርባችን ሆነና ሰው ከመሆናችን በፊት በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ለእሽቅድምድም ስንናጭ ትንታ አቅም ገዝታ፣ የሙዝ ልጣጭም ሰበብ ሆና ያዘዘበት ና ተብሎ ይህቺን ዓለም ሳይወድ በግዱ ይሰናበታታል። ይኼን እየሰማ ይኼንን እያየ ቋሚ እንባን አብሶ ዳግም ይራመዳል፣ ዳግም ይነሳሳል፣ ይፎካከርማል። ያለ ወጪ ቀሪ ሒሳብ እያሰላ፣ ሞት ሁሉን እኩል ያደርጋል። ‘ሳቅ ሳቅ ቢለንም እንባ ይጋርደናል’ ያለው ማን ነበር? ኩርፊያና ፈገግታ ተደባልቀውበት እኮ ነው፡፡ መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት