Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ተመልካች ሲያጨበጭብልኝ ደመወዜን የተቀበልኩ ያህል ይሰማኛል›› አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

‹‹ተመልካች ሲያጨበጭብልኝ ደመወዜን የተቀበልኩ ያህል ይሰማኛል›› አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም

ቀን:

ፍቃዱ ተክለማርያም ግርማ ሞገሱን የሚያጐላውን ካባ ደርቦ፣ ሹሩባውን አዘናፍሎ መድረክ ላይ ሲንጐራደድ የደስታ፣ የሐዘንና የንዴት ስሜቶች የተፈራረቁባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን ዳግም በቴአትር ቤቱ ተወስኖ እንደመጣ፣ ንጉሡም በፍቃዱ መላ ሰውነት እንደሰረጹ ያህል ተሰምቷቸው እነደነበር አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ የጀመረውን ንግሥና በኤዲፕስ ንጉሥ፣ በንጉሥ አርማህም ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ 60ኛ ዓመቱን፣ ለዓመታት በነገሠበት በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ያከበረው ፍቃዱ፣ በቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድራማ፣ በትረካ፣ በፊልምና የማስታወቂያ ሥራዎችም አሻራውን አሳርፏል፡፡ ‹‹የበቀል ጥርሶች›› እና ‹‹የሊቁ ሞት›› ከሬዲዮ፣ ‹‹ባለ ጉዳይ›› እና ‹‹ገመና›› ከቴሌቪዥን ሥራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› እና ‹‹ሳቤላ›› በትረካ ሕይወት ከዘራባቸው መጻሕፍት ጥቂቱ ሲሆኑ፣ በፊልሙ ‹‹ጉዲፈቻ›› እና ‹‹ቀይ ስህተት›› ይነሳሉ፡፡ ምሕረተሥላሴ መኰንን ፍቃዱ ተክለማርያምን አነጋግራዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትህን ትከታተል በነበረበት ወቅት ወደ ሙዚቃ እንዲሁም ቴአትር ታዘነብል ነበር፤ እስኪ በወቅቱ ስለነበረው ሕይወትህ አጫውተን፡-

ፍቃዱ፡- ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ጨዋታ እወድ ነበር፡፡ አስተማሪዎቼም የሚነበቡ ነገሮችን እንዳነብ ያደርጉ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የዚህ ሙያ ዝንባሌ ያደረብኝ፡፡ የወላጆች ቀን ሲከበር፣ በመንፈሳዊ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሲተወኑ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነበርኩ፡፡ በወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ)ም ለዛሬው የትወና አቅጣጫዬ መሠረት ከሆኑ አንዱ ነበር፡፡ ልጅነቴ በጣም ቆንጆ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣት ሳለህ አብዛኛውን ጊዜ የምታሳልፈው ፊልም በመመልከት ነበር እሱን ጊዜስ እንዴት ታስታውሰዋለህ? አሁንስ?

ፍቃዱ፡- ሲኒማ እመለከት ነበር፡፡ መጽሐፍም አነብ ነበር፡፡ በወጣትነት ጊዜዬ ሱስ ውስጥ የሚከትም እንኳን ቢሆን ሞክሬአለሁ፡፡ ግን በሱ መንገድ ሕይወቴን አልመራሁም፡፡ ፊልም እመለከታለሁ፡፡ ቆንጆ ፊልም አይቼ ስጨርስ ቆንጆ የነፍስ ምግብ በልቼ የረካሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ ለሙያዬም ስል እመለከታለሁ፡፡ አሁን ግን ጊዜም ስለሌለ ቁጭ ብዬ አንድ ፊልም ጨርሼ አላውቅም፡፡ ወደፊት አረፍ ስል እንደቀድሞ አያለሁ፡፡ መጽሐፍም አነባለሁ፡፡ እጄ ላይ አንድ ልቦለድ አይታጣም፡፡ ደክሞኝ እንኳን አንድ ገጽ ሳላነብ አልቀርም፡፡ አሁንም የእኛን አገር ጥሩ መጻሕፍት እያነበብኩ ነው፡፡ ያለነዚህ ሕይወት ትርጉም ያጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በወጣትነትህ ትሩፋት ገብረየስን እየተከተልክ እሷ በአንድ ድራማ ላይ ወክላ የምትጫወታትን ገጸ ባህሪ አባባል ‹‹ግደይ ግደይ አለኝ››ን እየደጋገምክ ስትናገር ምን ተፈጠረ? ዛሬ ላለህበት ደረጃስ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

ፍቃዱ፡- ከማንጎራጎሩና ከቀልዱ ወደ ትወናው ስመጣ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሳስብ ነው ትሩፋትን ያገኘኋት፡፡ የተሰማኝን ደስታ መግለጽ አልችልም፡፡ ለኔ ብላ እዛ አካባቢ የመጣች ነበር የመሰለኝ፡፡ ‹‹ግደይ ግደይ አለኝ››ን ከኋላዋ ማለት ጀመርኩ፡፡ ጓደኞቼና መንገደኞች እንደ ጉድ ያዩኛል፡፡ እሷ ከንክኗት ዞር ብላ ‹‹ማንን ነው ግደል ግደል የሚልህ›› አለች፡፡ የምታግዢኝ ካለ የተውኔት ፍላጐቱ አለኝ አልኳት፡፡ ጓደኞቼም አላስቀምጥ ብሎናል አሏት፡፡ አገር ፍቅር እንዳገኛት ቀጠረችኝ፡፡ አለፈልኝ ብዬ ሁለት ጓደኞቼን ይዤ ስሄድ የማደንቃቸው ትልልቆቹ ቆመዋል፡፡ እዚ መሀል ነው እንዴ የምገባው ብዬ እግሬ ተሳሰረ፡፡ ተስፋዬ አበበን አስተዋወቀችኝ፡፡ በኋላም ማክሰኞና ሐሙስ መመላለስ ጀመርኩ፡፡ የጎላ ተሳትፎ ባይኖረኝም በሁሉም እሳተፍ ነበር፡፡ አንድ የሬድዮ ድራማ ላይ ማጅራት መቺ ሆኜ ለሠራሁት ጣብያው 11 ብር ከ80 ሳንቲም ከፍሎኛል፡፡ ቴአትር አጅበን ህብረ ዝማሬ እንጫወት ነበር፡፡ እዛ ውስጥ የምድር ጦር ኦርኬስትራ አባልና ከቴሌም የመጡ ነበሩበት፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነና ችሎታችንን ማየት ፈለገ፡፡ ያኔ ተራ አባል ነበርኩ፡፡ በሕይወታችሁ የገጠማችሁና ስሜታችሁን የነካ ነገር ጻፉና መድረክ ላይ አቅርቡ ይለን ነበርና ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ጎበዙ ጓደኛዬ ሱራፌል ጋሻው አሁን በሕይወት የለም፤ የአቤ ጎበኛን ግጥም አቀረበ፡፡ እኔ ደግሞ የሼክስፒሩን፣ የጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህንን ትርጉም ‹‹መሆን ወይም አለመሆን…›› አቀረብኩ፡፡ ጋሽ ተስፋዬ ተደነቀና እዛው ‹‹ዕቃው›› ለሚል ቴአትር አጨን፡፡ በወቅቱ መንግሥት የማይፈልገውና ሳንሱር ሲደረግ የማያልፍ ስለነበረ ቴአትሩ ብዙም አልታየም፡፡ አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ መጥቶ ቴአትር ቤቱን በአዲስ መንገድ ሊመሠረት ሲል ደግሞ፣ ፋንቱ ማንዶዬና ሌሎችም ጎበዝ ልጆች አሉ ብለው ነገሩት፡፡ ማመልከቻም አስገባሁ፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሀዋርያትን፣ ቴዎድሮስ ሆነው የተጫወቱት ሰው ከአቶ ተፈሪ ጋር አብረው እየጠየቁኝ ነበር፡፡ የምጠየቀውን በትክክል የመለስኩ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን በአስተያየታቸው የወደዱኝ አልመሰለኝም፡፡ በኋላ እንደሰማሁት፣ ይኼን ልጅ እንዴት አዩት ሲባሉ ‹‹ሒ ኢዝ ኖት ዲሲፒሊንድ›› ብለው ነበር፡፡ አቶ ተፈሪ አይምሰሎት ይኼ ልጅ ጥሩ ተዋናይ ሊወጣው ይችላል አሏቸው፡፡ በእሳቸው ምዛኔ ቢሆን ወድቄ ነበር፡፡ እኚህ ሰው ከአመለከትኩ ከዓመታት በኋላ በ1976 ዓ.ም. ቴዎድሮስን ስጫወት አዩ፡፡ መንገድ ላይ ሁሌ ስንገናኝ ‹‹እንዴት ዓይነት አንበሳ ነሽ? መድረክ ላይ እንዴት ነው የሚያደርግሽ? ከዚ ሰውነት እንዴት ነው ያ ድምፅ የሚወጣው?›› ይሉኝ ነበር፡፡ ከዛ የአብዬ መንግሥቱ ለማ ‹‹ባለካባና ባለዳባ›› ላይ እንድንሳተፍ አደረጉ፡፡ እኔና ሱራፌል ከታላላቆቹ ከተስፋዬና ተፈሪ ጋር ለመሥራት በመብቃታችን ዕድለኞች ነበርን፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ባለካባና ባለዳባ›› ላይ የነበረህ ተሞክሮ ለመጀመርያ ጊዜ የመሪ ተዋናይነት ሚና ካገኘህበት የ‹‹እሳት ሲነድ›› ሲነፃፀር ምን ይመስላል?

ፍቃዱ፡- ጋሽ አባተ መኩሪያ የአያልነህ ሙላት አብዮታዊ ቴአትር የሆነውን ‹‹እሳት ሲነድን›› ለመሥራት ሰዎች ይመለምል ነበር፡፡ ቢሮ አካባቢ የሚንጎራደድ ሰው የመሪ ተዋናይ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ አባተ አንዳንድ ነገር እንድናቀርብ ሲጠይቅ በልቤ ‹‹አሁን ጊዜው ደርሷል›› አልኩ፡፡ እሱ ብዙ ሰው ላይ ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡ የዘፈን ግጥም ሲያቀርቡ ሰልችቶት ሲጋራውን ያጨስ ነበር፡፡ እኔ ወጣሁና ‹‹መሆን ወይም አለመሆን፤ እዚሁ ላይ ነው ችግሩ፤ የዕድል የፈተና አለንጋ ሲወናጨፍ ወስፈንጥሩ…›› እያልኩ ቀጠልኩ፡፡ ማነው ደሞ ይኼ ብሎ ትኩረቱን ሰጠኝ፡፡ የሚንጎራደደውን ሰው በል እስክሪፕቱን ስጠው አለው፡፡ ገፀ ባህሪው እምቢበል ይባል ነበር ‹‹እምቢበል አንተ ነህ!›› አለኝ፡፡ የመጀመርያው የመሪ ተዋናይ ሚና በዚህ ዓይነት አገኘሁ፡፡ እጅግ በጣም ድንቅ ነበር፡፡ መድረክ ላይ ገንዘብ፣ ሀብል ሰዓት እሸለም ነበር፡፡ ሴቶች ደግሞ ገንዘብ አስመስለው አድራሻ ይሰጣሉ፡፡ ያኔ ወጣትና አፍሮ ነበርኩ፡፡ ወጣትም ብሆን ሰው እደጋበዘኝ አልሄድም፡፡ እግዚአብሔርም ባይጠብቀኝ ዛሬ እዚህ አልገኝም ነበር፡፡ ዝና በወጣትነት ሲመጣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዛ በኋላ አብዮቱን የሚያንፀባርቁ የጋሽ ፀጋዬን ሥራዎች ወደመሥራቱ መጣሁ፡፡ ‹‹ኦቴሎ›› በጣም በሰው የተወደደ ነበር፡፡ ኦቴሎ ላይ የአበበ ባልቻ ባለሟል ነበርኩ፡፡ ቴዎድሮስ ሲመጣ የኔ ባለሟል አበበ ባልቻ ሆነ፡፡ በጣም ስለምንግባባ ያጠናነው እንኳን ቢጠፋን እርስ በራሳችን መድረክ ላይ እንጠባበቅ ነበር፡፡ ‹‹ጋሞ›› የተሰኘ የጋሽ ፀጋዬ ቴአትር ሠራንና ከአሥር ጊዜ በላይ ቅድመ ምርመራ ተደርጎበት፣ ከአንድ ጊዜ በላይ ሳይታይ ቀረ፡፡ በትወና ትክክለኛ አቅጣጫ እንድይዝ እንደ አባትም እንደ ወንድምም እንደ ጓደኛም መስመር የቀየሰልኝ ጋሽ አባተ መኩሪያ ነው፡፡ ቴዎድሮስን እንድሠራ የመረጠኝ እሱና ደራሲው ነበሩ፡፡ አይሆንም ብልም መርጠንሃል ተባልኩ፡፡ ‹‹ኦቴሎ›› እና ‹‹ቴዎድሮስ›› ከአራት ዓመት በላይ ተሠርቷል፡፡ በተለይ ቴዎድሮስ አስመራ፣ አሰብ፣ ምፅዋና ሌሎችም ቦታዎች ቀርቧል፡፡ 1984 ዓ.ም. ወደ ብሔራዊ ቴአትር መጣሁና ኤዲፐስ ንጉሥን ተጫወትኩ፡፡ በ1967 ዓ.ም. ባሬስታ ሆኜ የተጫወትኩበት፣ ‹‹ባለካባና ባለዳባ›› በ1986 ዓ.ም. ዳግም ሲመጣ የምጓጓለትን ጋሽ ተፈሪ የሚጫወተውን ቦታ አገኘሁ፡፡ የተሰማኝ ደስታ ወደር አልነበረውም፡፡ በሕይወቴ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ከአብዬ መንግስቱ ‹‹ባለካባና ባለዳባ›› ከጋሽ ፀጋዬ ‹‹የከርሞ ሰው››ን እወዳቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አፄ ቴዎድሮስን ጨምሮ አራት ጊዜ ንጉሥ ሆነህ ተውነሃል፤ ንግሥና ምን ዓይነት ስሜት ይሰጥሃል?

ፍቃዱ፡- ንጉሥ ሆኖ መተወን ጥሩ ነው፡፡ ሰው ይሰግዳል፡፡ አክብሮቱን ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የሌሎችን ትወና እንደተመልካችም ማየት ይቻላል፡፡ ንጉሥ ለመሆን የሚያስመርጠው ግርማ ሞገስ ነው፡፡ በእኔ እምነት ሞገስ የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስጫወት የአንዱ ባህሪ በሌላው እንዳይመጣ እሠጋ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቴዎድሮስና ኤዲፐስ ተመሳሳይ እብደት፣ ጩኸት ነበራቸውና የአንዱ ወደ አንዱ እንዳይመጣ እጨነቅ ነበር፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር የተወሰኑ ሰዎችን ፕሮፋይል ይጽፍ ነበር፡፡ ስለኔ ‹ፍጹም ራሱን ቀይሮ ሌላ ሰው ይሆናል፤ አንዳንዴ ሲስቅ ብቻ ፈቃዱን ትንሽ አየውና ወዲያው ይጠፋብኛል› ብሎ ጽፏል፡፡ ለነገሩ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ስለምወድ የምጫወተው የእውነት ነበር፡፡ ገፀ ባህሪው ሲሰጠኝ ጎንደር ሄጄ ዘዬውን ለመቅሰምና መቅደላ ድረስ ሄጄ ምን ሊሰማኝ እንደሚችል ማወቅ ፈልጌ ነበር፡፡ ስላልተሳካልኝ በራሴ ስሜት ቀጠልኩ፡፡ አስተሳሰባቸውን፣ የተነሱለትን ዓላማ ስለማከብር ለቴአትር ሳይሆን የእውነት ነበር የምጮኸው፡፡ ጆሮዬን አሞኝ በሹሩባዬ ስር የሚፈስ ነገር ነበር፡፡ ስተኩስም በቅርበት ተኩሼ፣ ተሽከርክሬ በቄንጥ ነበር የምወድቀው፡፡ ብዙ ሰው ቴዎድሮስን የምናውቃቸው በፈቃዱ ነው የሚል አስተያየት ነበረው፡፡ በወቅቱ መኪና ስላልነበረኝ ንጉሥ ሆኜ ሠርቼ ቦርሳዬን አንጠልጥዬ በእግሬ ስሄድ፣ ቴዎድሮስን ሆኖ የሚሠራው አይደል እንዴ? ይሉኝ ነበር፡፡ መድረክ ላይ ንጉሥ ተኩኖ ለቡና መጠጫ እንኳን የሚታጣበት ጊዜም ነበር፡፡ አንድ ግሮሰሪ አለች ባለቤቱ ፍራንክ ከሌለኝ እንቁላል ቅቅል በሚጥሚጣ ያቀርብልኛል፡፡ አፕሬቲቭ ወይም ጅን እየጠጣሁ የነ ጥላሁን ገሠሠን ሙዚቃ እየሰማው የሚሰማኝ ሐሴት ቀላል አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል ተመስለህ መጫወት የምትፈልገው ንጉሥ አለ?

ፍቃዱ፡- እንደዚህ አልተመኘሁም፡፡ አፄ ቴዎድሮስን መጫወት ብፈልግም ከባድ ኃላፊነት ስለነበር ጨንቆኝም ነበር፡፡ ከአገራችን ጀግኖች አፄ ምኒልክን መሆን አልችልም፡፡ መሆን የምችለው ቴዎድሮስን ብቻ ነው፡፡ ጉልበታም ስለነበሩ ራሴንም መፈተኛ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ካንተ በፊትና በኋላም አፄ ቴዎድሮስን የተጫወቱ ተዋንያን አሉ፤ እንዴት ታያቸዋለህ?

ፍቃዱ፡- ጌትነት እንየው ‹‹የቴዎድሮስ ራዕይ››ን ልዩ አድርጎ ጽፎታል፡፡ ጋሽ አባተ እንደሚሠራው በብዙ ሕዝብ የመጠቀም ዘዴ አለው፡፡ ሱራፌል ተካን ሳይ ራሴን የምመለከት ነበር የሚመስለኝ፡፡ በጣም ጎበዝ ነው፤ በስሜት ነበር የሚሠራው፡፡ አድናቆቴንም ነግሬዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት የንግሥና በዓል ሲከበር፣ በተለያየ ሙያ ያሉ ግለሰቦች አፄ ቴዎድሮስን እንዴት እንደሚያዩዋቸው ሲጠየቁ ያንተ ምላሽ ምን ነበር?

ፍቃዱ፡- ያኔ አልተጠየቅኩም፡፡ የሆነ ዓመት ላይ ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለእሳቸው የተለያዩ ምሁራን ሲናገሩ በጣም አዘንኩ፡፡ እዛ መገኘቴንም አልወደድኩትም ነበር፡፡ ስለእሳቸው የሚሰጡት አስተያየት ተራ ሽፍታ የመንደር ወሮበላ እንደሆኑ ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የጠራኝ ሰው ‹አንተ በሙያህ እንድታበረክት እንጂ አስተያየት እንድትሰጠን አልነበረም› አለኝ፡፡ እኔ እንደእናንተ አልተመራመርኩም፤ ስሜቴን ነው የተጫወትኩት፡፡ ስለእሳቸው ባነበብኩት ከተለያዩ ሰዎች በምሰማው ተነስቼ ያለኝን ፍቅር ነው የገለጽኩት አልኩ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ብቻ ነበሩ ጥሩ ነገር የተናገሩት፡፡ ከጊዜ በኋላ ልክ ያልሆነ ነገር አጉልቶ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ወይ ለጥሩ፣ አልያም ለመጥፎ ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ያለው ስሜት ከአገር ወዳድነት፣ ከአገር አንድነት ጋር ይያያዛል፡፡ እሳቸው ምልክት ናቸው፡፡ ወደ ላይ የምንመለከተውና የምናከብረው ታዲያ ማንን ነው? ብዙ ክፉ ነገር ሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲያ ያደረጋቸው የሁኔታው አስገዳጅነት ነው፡፡ ሁሉም ባለበት ዘመን ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት የየራሱን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ባለ ጉዳይ›› ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ከብዙዎች ህሊና አይጠፋም፡፡ ድራማው ያነሳቸው የመሬት ጥያቄና ሌሎችም ጉዳዮች ዛሬም ሊነሱ የሚችሉ ናቸውና ‹‹ባለጉዳይ›› ወደ ቴሌቪዥን ቢመለስ መልካም ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?

ፍቃዱ፡- አሁንም እንደዛ ዓይነት ችግር አይጠፋምና ቢደገም ጥሩ ነው፡፡ ‹‹ባለጉዳይ›› የተጻፈበትና የቀረበበት መንገድ ልዩ ስለሆነ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እንደ ማንኛውም ካለው ምልልስ ጎን ለጎን በልባችን ስለ አንድ ሰው የምናስበውና ሰውየው ፊት የምንናገረውን የተለያየ ነገር በአንድ ጊዜ ያስተላልፋል፡፡ ያነሳውም ጉዳይ ትልቅ ነበር፡፡ የመሬትና ቦታ ጉዳይ ነው፡፡ የነበሩ ቴክኒካል ችግሮችን አስተካክሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የጻፈው ነቢይ መኰንን ሲሆን፣ አበበ ባልቻና እኔ ሆነን እንዲሠራ ስንጠይቅ በወቅቱ የነበሩት የቴሌቪዥን መምሪያ ኃላፊ አቶ አማረ አረጋዊ እንዲሠራ ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ያኔ ስንሠራው አቶ አማረ ጥረት አድርገው በቴሌቪዥን ባልተለመደ በትዕይንት መልኩ (በኤፒሶድ) ትንሽም ቢሆን እንዲከፈለን አድርገዋል፡፡ መመስገን ይገባቸዋል፡፡ የሚያሳዝነኝ ሥራው ውጪ አገር ተሽጧል፡፡ በንቀትና በድፍረት የእኛ የተዋንያኑ ፎቶ ወጥቶበት በሲዲ ‹‹ኦል ራይትስ ሪዘርቭድ›› ብሎ አንዱ ደፋር አሜሪካ ውስጥ ሸጦታል፡፡ ይኼን በደል ዓለም እንዲሰማው እፈልጋለሁ፡፡ ለማን አቤት ይባላል፡፡ እኛ ያልተጠቀምንበት ሕገወጥ ስርቆት መሆኑንም መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ሙሉ የቴአትር ዶክመንት የማይገኘው ገና ለገና ይሸጣል በሚል ፍራቻ ነው፡፡ እዚህ እየተሠራ አውሮፓ ወይም ሌላ ቦታ ይታያል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሬዲዮ ትረካዎችህ መካከል ‹‹ሞገደኛው ነውጤ››፣ ‹‹ወንጀለኛው ዳኛ›› እና ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ይጠቀሳሉ፡፡ ከተረካቸው መጻሕፍት ካሉ ገፀ ባህሪያት የማትረሳው ማንን ነው?

ፍቃዱ፡- ‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› ፈታኝም ስለሆነ ደስ ይለኛል፡፡ የገጠር ሰዎች ለመጠየቅ ሲመጡ ወይም ገጠር ስሄድ የአነጋገራቸውን ዘዬ አውቃለሁ፡፡ ደራሲው አበራ ለማም ጎበዝ ነው፡፡ የነበረውን እውነት ነው የጻፈው፡፡ ነውጤ ግብርናውን ብቻ የሚያውቅ ንፁህ ፍጡር ነው፡፡ ጓደኛህን ገድለሃል ተብሎ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከዳኛው ጋር የነበረውን አለመግባባት የሚተርክ ነው፡፡ ትረካውን መልሼ ሳደምጠው ይገርመኛል፡፡ ‹‹ግራጫ ቃጭሎች›› ላይ መዝገቡ የሚገርመኝ ገፀ ባህሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኪነ ጥበቡ ያሉ የአንተ ዘመን ባለሙያዎችን እንዴት ትገልጻቸዋለህ?

ፍቃዱ፡- እየጀመርኩ ሳለሁ በጣም ዝነኛ ከነበሩት አንዱ ወጋየሁ ንጋቱ ነው፡፡ በሙያም አርአያዬ ነበር፡፡ ራሱን ለሚሠራው ነገር ያስገዛ ነው፡፡ ደበበ እሸቱ፣ አውላቸው ደጀኔ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ተስፋዬ ሳህሉ ጋር የመጫወት ዕድል ገጥሞኛል፡፡ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ሲራክ ታደሰ፣ ተክሌ ደስታ፣ ዓለሙ ገብረአብ፣ ትሩፋት ገብረየስ፣ ዓለምፀሐይ ወዳጆ፣ ዓለማየሁ ታደሰ፣ ሙሉአለም ታደሰ፣ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ፈለቀ አበበ፣ መሠረት መብራቴና ሌሎችም በጣም ጎበዝ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሁሉንም አልጠራሁም ግን ብዙ ባለሙያዎች ተፈጥረዋልና ያስደስታል፡፡ ሁሉም የየራሳቸው መወደጃ ወዝ አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ተወልደህ ያደግክባትን አራት ኪሎ እንዴት ትገልጻታለህ?

ፍቃዱ፡- አራት ኪሎ ቆንጆ ሰፈር ነው፡፡ እኔ የተወለድኩት ጅሩ ሰፈር ነው፡፡ ብዙ ጐምቱ ጐምቱ ሰዎች ይኖሩባት የነበረ፣ የአገር ሽማግሌ ያሉባት ናት፡፡ የኔ አባት አንዱ ትልቅ የዕድር ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ ተክለማርያም ኪዳኔና ሌሎችም ታላላቅ ሰዎች ነበሩበት፡፡ ቀስ እያሉ በዕድሜአቸው ሲያልፉ አዝን ነበር፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የየራሳቸው ወግና ልማድ ነበራቸው፡፡ በደመራና በሌላም በዓል በየቤቱ መጠራራቱ፣ እየበሉ እየጠጡ መጫወቱ፣ እኛ ልጆች ሆነን ከመጋረጃ ወይም ግድግዳ ጀርባ ቁጭ ብለን በቀዳዳ ስናያቸው አስታውሳለሁ፡፡ አራት ኪሎ ብዙ የአራዳ ልጆች ነበሩባት፡፡ ዳንስ ቤት፣ መጠጥ ቤት ይበዛ ነበር፡፡ እኔ በልጅነቴ ከቤት እየጠፋሁ ቤተ መንግሥቱ አካባቢ ኳስ፣ ቁማር እስከ ምሽት ድረስ እንጫወት ነበር፡፡ ወወክማም እያመሸሁ ሲኒማ እመለከት ነበር፡፡ ሰኞ ቦናንዛ፣ ማክሰኞ ዘ ሴንት፣ ረቡዕ ዘ ፊውጂቲቭ፣ ሐሙስ ሚሽን ኢምፖሲብል፣ ዓርብ ስታር ትሬክ፣ ሀዋይ ፋይቭ ኦ፣ ቅዳሜ የሳምንቱ ታላቅ ፊልም እሑድ ሬስሊንግ እየከሰከስኩ አምሽቼ በፓርላማው በኩል በእግር ቤቴ እገባ ነበር፡፡ በዛ መሀል የድንች ወጥ ይሸተኝ ነበር፡፡ ጨዋታ ላይ ስለምግብ ስለማናስብ ሲሸተኝ ይርበኝና ወደቤቴ እሮጣለሁ፡፡ አራት ኪሎ ሥጋም እንደልብ ነበር፡፡ አማርጦ በትንሽ ገንዘብ ይገዛ ነበር፡፡ ዛሬ አንድ ኪሎ ሥጋ 250 ብር ነው፡፡ ያኔ በ25 እና 50 ሳንቲም የሚሸጥ ቅንጥብጣቢም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡‑ በ1994 ዓ.ም. የኪነ ጥበብና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት ከተሰጣቸው አንዱ ነህ፤ ሽልማቱ ላንተ እንዲሁም ሌሎች በሙያው ላሉ ምን አስተዋጽኦ አለው?

ፍቃዱ፡‑ ሽልማቱ መጀመሩ ጥሩ ነበር፡፡ ሁለት ጊዜ ተካሂዶ ተቋረጠ እንጂ ቢቀጥል ብዙ ሰዎች ይኼን አጋጣሚ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሙያተኛው እሸለማለሁ ብሎ ተስፋ አድርጐም ነበር፡፡ ሲቋረጥ ሰው ሁሉ ጠብቆ የነበረው ነገር ቆመ፡፡ ሽልማት በአገር አቀፍ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር አስቸጋሪ ነው፡፡ የሽልማት ድርጅትም መቋቋም አለበት፡፡ አሁንም እንደዛ ዓይነት መንፈስ ያለው ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ እኔ ዕድለኛ ሆኜ ተቋዳሽ መሆን ችያለሁ፡፡ ያን የመሰለ ዕድል የሚገባቸው ባለሙያዎች አሁንም አሉ፡፡ ያኔ እኔን ማስታወሳቸውና መምረጣቸው ትልቅ አደራና ሞራልም ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ቀደም ባሉ ጊዜአት የነበረውና የአሁኑ የኢትዮጵያ ቴአትርን ገጽታ እንዴት ታነጻጽረዋለህ?

ፍቃዱ፡‑ በፊት ብዙ ትልልቅ ክላሲካልና ታሪካዊ፣ እዚህ ዘመን ላይ ይቆማሉ የማይባሉ ቴአትሮች ይሠሩ ነበር፡፡ እነ‹‹ባልቻ አባ ነፍሶ››፣ ‹‹ሼክስፒር›› ‹‹ዳዊትና ኦርዮን››ንን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ቴአትር መድረክ የሚመጥኑ ብዙ ቴአትሮች ተሠርተዋል፡፡ አሁን ላይ ይኼ ቴአትር ባይታይ የሚባል ዓይነት ቴአትርም ይሠራል፡፡ ሕዝቡ ግን ያያል፡፡ ብዙ ታሪካዊ ቴአትሮች ሲሠሩ አላይም፡፡ ቢሠሩም ዕድሜአቸው ትንሽ ነው፡፡ በቅርቡ ካሉት ‹‹የቴዎድሮስ ራዕይ››ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሰው ስሜትም የተገደበ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ አሁን ብዙ ሰው የሚያስቅ ቴአትር ነው የሚወደው፡፡ ሲኒማውም ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ የተጀመረ ሰሞን ፊልሞችም ይታዩ ነበር፡፡ አሁን ርእሳቸው ራሱ የማይስብ የወረዱ ሥራዎች ይታያሉ፡፡ ከወንድሜ ጋር ‹‹የበጋ መብረቅ›› የሚል ፊልም ሠርተን ነበር፡፡ ሰው በሞተ ስሜት ላይ ሆኖ ነው የመጣው፡፡ እኔ ቴአትር ስጀምር ለፍራንክ ሳይሆን ለስሜት ነበር፡፡ የአሁኑ አስተሳሰብ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ጥበብን ለጥበብ መሥራት የሚለው ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ቴአትር ቤቶች ውስን ከመሆናቸውም በላይ ያሉትም በእድሳትና በተለያየ ምክንያት ይዘጋሉ፤ ቴአትሮች ከአዲስ አበባ ወጥተው የሚታዩበት አጋጣሚም ጠባብ ነው፤ ይኼን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

ፍቃዱ፡‑ አዳራሾች መሠራት አለባቸው፡፡ ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ግን የተደበቁ ጸሐፍት የሚወጡበት መንገድም መኖር አለበት፡፡ አይዶል ሙዚቀኞችን እንደሚያወጣው ማለት ነው፡፡ ቴአትር ቤት ሲዘጋ ተጽእኖ የሚፈጥረው ያሉት አዳራሾች ትንሽ ስለሆኑ ነው፡፡ ስብሰባ ሲደረግ ወይም ሌላ ፕሮግራም ሲኖር ደግሞ ቴአትሩም ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ለቴአትር ብቻ የሚሆኑ እንደ ብሔራዊ ቴአትር ያሉ አዳራሾች መሥራት መፍትሔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ በሙያህ የማትረሳውና በጣም የተደሰትክበት ቅጽበት የቱ ነው?

ፍቃዱ፡‑ የተደሰትኩት የምፈልገው ሙያ ውስጥ ገብቼ እንደተሳካልኝ ሲሰማኝ ነው፡፡ እንደሚሰካልኝ እገምት ነበር፡፡ ማግኘት የሚገባኝን ባላገኝም ሕዝቡ ሲወደኝ ደስ ይላል፡፡ ቴአትር አልቆ ተመልካች ሲያጨበጭብልኝ ደመወዜን የተቀበልኩ ያህል ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡‑ በብሔራዊ ቴአትር ጡረታ ከምትወጣበት ዓመት ላይ አምስት ዓመት ተጨምሮልሃል፤ ከዚህ ጐን ለጐን በቴሌቪዥን እየተላለፈ ያለው ‹‹መለከት›› ድራማ አለ፤ በቀጣይስ ምን አቅደሃል?

ፍቃዱ፡‑ በጭራሽ አላቅድም፡፡ ማቀድ የተውኩት ብዙ ህልም ያላቸው ከጐኔ ያሉ ጓደኞቼ ሲያልፉ ነው፡፡ የማድረው በፈጣሪ ቸርነት ነውና የማስበው አሁን ላይ ስላለው ብቻ ነው፡፡ አሁን ብዙም አላርፍም፤ በተቻለ መጠን ግን ማረፍ እፈልጋለሁ፡፡ በእኔ ጊዜ የነበረውን ለማወቅ የሚፈልጉ ወጣቶች አሉ፡፡ እነሱን መምከርም አለ፡፡ የምንም ነገር ሱሰኛ እንዳይሆኑ ለማድረግም እሞክራለሁ፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...