Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በጋራ ኔትወርክ በመጠቀም በርካታ ብሮድካስተሮች አንድ ጣቢያ አቋቁመው መሥራት ይችላሉ››

አቶ ግዛው ተስፋዬ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕግና የማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

አቶ ግዛው ተስፋዬ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕግና የማስታወቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ብሮድካስቲንን ሽግግር ለማድረግ ሥራ የጀመረው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ሒደቱ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ 22 የግልና የሕዝብ ብሮድካስተሮች ይኖሯታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ሒደት ጋር በተያያዘ ረቂቅ የሚዲያ ፖሊሲና ሕግ ተዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ሚኪያስ ሰብስቤ አቶ ግዛውን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሚዲያ ሕግን የሚያሻሽል አዲስ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህን ማድረግ ያስፈለገው ለምንድነው?

አቶ ግዛው፡- ረቂቁ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ቀርቧል፡፡ የተዘጋጀበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ብሮድካስቲንግ በመሸጋገሯ ነው፡፡ ሽግግሩ የራሱ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በሥራ ላይ ባለው ሕግ ላይ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ከፈቃድ አሰጣጥና ከአዳዲስ አገልግሎቶች አመራር ጋር በተያያዘ ለውጥ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- በረቂቅ አዋጁ ላይ የተካተቱት አንኳር ጉዳዮች ምንድናቸው?

አቶ ግዛው፡- በአናሎግ ብሮድካስቲንግ አንድ የቴሌቪዥን ብሮድካስተር ራሱን ችሎ የማሠራጫ መሣሪያ ገዝቶ ማሠራጫውን ይገነባል፡፡ ፕሮግራምም ራሱ ያዘጋጃል፡፡ ስለዚህ የሚሰጠው ፈቃድ የተቀናጀ ፈቃድ ነው፡፡ በዲጂታል ብሮድካስቲንግ ግን ብሮድካስተሩ ለቴክኖሎጂ መጨነቅ አይኖርበትም፡፡ በጋራ ኔትወርክ በመጠቀም በርካታ ብሮድካስተሮች አንድ ጣቢያ አቋቁመው መሥራት ይችላሉ፡፡ በአንድ ማሠራጫ ጣቢያ ከ20 እስከ 22 ጣቢያዎች ስለሚኖሩ ብሮድካስተሩ ይዘት ብቻ ነው አዘጋጅቶ የሚያሠራጨው፡፡ ይህ የቴክኖሎጂና የጥገና ወጪውን ይቀንስለታል፡፡ አስፈጻሚውና ተቆጣጣሪው አካልም እንደ አዲስ ይቋቋማል፡፡

ሪፖርተር፡- የመሠረተ ልማት ግንባታውን የሚያስፈጽመው ማነው? ረቂቁ መፅደቅ ብቻ ከቀረው ግንባታው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ግዛው፡- ሽግግሩ ሚዲያን ለማስፋፋት በተለይም የቴሌቪዥን ብሮድካስትን ለማስፋፋት ያለመ ነው፡፡ ይህ ለኅብረተሰቡ አማራጭ ይፈጥራል፡፡ ለንግዱ ማኅበረሰብም ዕድል ይፈጥራል፡፡ በተለይ የመዝናኛውና የማስታወቂያ ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ግንባታውን የሚያስፈጽመው የብሔራዊ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ነው፡፡ ሁሉም ብሮድካስተር የማሠራጫ ጣቢያ ለመገንባት አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ የጋራ ኔትወርክ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ኤጀንሲው በ2007 ዓ.ም. ጨረታ አውጥቷል፡፡ ጨረታው እየተገመገመ ነው፡፡ መንግሥት ለግንባታው ምንም ዓይነት በጀት አልመደበም፡፡ በብድር ነው እየተሠራ ያለው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ሒደቱ የዘገየው ከምዝበራ ጋር በተገናኘ ነው የሚሉ አሉ፡፡

አቶ ግዛው፡- ሒደቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በሚጠናቀቅበት በ2007 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት ነበር፡፡ ነገር ግን በጀት አልተመደበለትም ነበር፡፡ በመሆኑም ዕቅዱ ተከልሷል፡፡ በጀት ባልተመደበበት ሁኔታ ምዝበራ ሊካሄድ አይችልም፡፡ አሁንም በብድር የሚገዛው መሣሪያ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲመረት ነው የታቀደው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ለመፈጸም አቅም ያላቸው ባለሀብቶች አሉ?

አቶ ግዛው፡- ይህን የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው ለብሮድካስት ባለሥልጣን ነው፡፡ ነገር ግን በዋናነት ሽግግሩ እየተመራ ያለው በብሔራዊ ዓቢይ ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ከብሮድካስት ባለሥልጣን፣ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተዋቀረ ነው፡፡ በ2003 ዓ.ም. ነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው፡፡ ኮሚቴው በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን አቅም ገምግሟል፡፡ ግምገማው አቅም እንዳለ አረጋግጧል፡፡ ከውጭ የማስገባት ዕቅድ የለም፡፡ በመንግሥት ድጎማ እዚሁ መመረት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ሪፖርተር፡- የመሠረተ ልማት ግንባታው በአጠቃላይ ምን ያህል ገንዘብ ይጠይቃል ተብሎ ይገመታል?

አቶ ግዛው፡- የበጀቱ ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ወጪ እንደሚጠይቅ ተገምቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ብድሩን ከየት ለማግኘት ነው የታቀደው?

አቶ ግዛው፡- ከውጭ ባንኮች ነው የታቀደው፡፡ በጨረታው የሚሳተፉ አካላት ብድሩንም ይዘው ይመጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕግ የግሉ ዘርፍ በቴሌቪዥን አገልግሎት እንዳይሰማራ ባይከለከልም፣ በተግባር የመንግሥት ሞኖፖሊ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ሽግግሩ ደግሞ የመጣው ባለፉት አምስት ዓመታት ነው፡፡ እስካሁን የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ያልኖረው ለምንድነው?

አቶ ግዛው፡- ወደ ዲጂታል ብሮድካስት የመሸጋገር ጉዳይ የምርጫ ነገር አይደለም፡፡ በዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኅብረት አሠራር መሠረት አገሮች እ.ኤ.አ. እስከ 2015 ድረስ የአናሎግ ቴክኖሎጂን ወደ ዲጂታል እንዲያሸጋግሩ ይገደዳሉ፡፡ ይህ ሽግግር እንዳለ እየታወቀ ለግሉ የብሮድካስተር ፈቃድ መስጠት ኪሳራ ማብዛት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መሠረተ ልማቱ በመንግሥት ከተገነባ በኋላ ፕሮግራም ብቻ አዘጋጅቶ በማሠራጨት እንዲጠቀም ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ከዚያ በፊትስ ጥያቄውና ብቃቱ ነበር ወይ? እንዲሁ ይነሳል እንጂ ቀርቦ ያመለከተ የለም፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለስድስት የሕዝብ ብሮድካስተሮች ፈቃድ ለመስጠት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ ለአዲስ አበባና ለአማራ ክልል ፈቃዱ ከተሰጠ በኋላ ለሌሎች የተከለከለው በተመሳሳይ ምክንያት ማለትም የሚደርሰውን ኪሳራ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የብሮድካስት ኔትወርኩን የሚያስተዳድር የመንግሥት የልማት ድርጅት ይቋቋማል፡፡ ይህ ከአቅም ጋር የተገናኘ ነው ቢሉም፣ ሌሎች አካላት ግን በሥርጭቶቹ ላይ መንግሥት ተዘዋዋሪ ቅድመ ኅትመት ቁጥጥር እንዲያደርግ የተመቻቸ አሠራር እንደሆነ ይተቻሉ፡፡

አቶ ግዛው፡- ብሮድካስተሩ ቻናል ተከራይቶ ይዘት ያሠራጫል፡፡ ራሳቸው ጣቢያ ገንብተው የሚያሠራጩበት አሠራር በአደጉ አገሮች አለ፡፡ ይኼ ከአቅም ጋር የሚመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመረጠችውና በብዙ የአፍሪካ አገሮች የሚተገበረው አሠራር በአንድ ድርጅት የተገነባው የብሮድካስት ኔትወርክን ተቆጣጣሪው አካል እንዲያከፋፍል በማድረግ የሚፈጸም ነው፡፡ በሁለቱ መካከል የጥቅም ግጭት እንዳይኖር ይደረጋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ተመሳሳይ አሠራር ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ የሚዘጋጀውን ፕሮግራም የልማት ድርጅቱ የመቁረጥ ሥልጣን አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ ‘ሴንሰርሺፕ’ ወይም ቅድመ ኀትመት የይዘት ቁጥጥር ሥጋት ሆኖ ሊነሳ አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- አቅም ያለው ማሠራጫ ጣቢያ የሚገነባ ግለሰብ ቢመጣ ሕጉ እኮ ይከለክለዋል?

አቶ ግዛው፡- ካሉት ሁለት አማራጮች አንዱ ተወስዷል፡፡ ነገር ግን የጋራ ማሠራጫ ጣቢያ መጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብትን የሚገድብ አይሆንም፡፡ ሁሉም ብሮድካስተር የማሠራጫ ጣቢያ ቢገነባ የአገር ሀብት ነው የሚባክነው፡፡ ወደፊት አቅም ሲገነባ ሕጉን ማሻሻል ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አትራፊዎች ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበር መንግሥት እንዲያውም ድጎማ እንዲያደርግ ነው የሚጠበቀው፡፡ አስተዳደሩን የልማት ድርጅት ማድረግ ከሚዲያ ኢንዱስትሪው ለማትረፍ የታለመ አያስመስለውም?

አቶ ግዛው፡- አትራፊ ቢሆንም ትርፍን ብቻ ታሳቢ አድርጎ ወይም ገቢ ለማግኘት ብቻ የሚሠራ አይሆንም፡፡ የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት ለማሳካት ዓላማ አድርጎ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለምን ያህል የግል ቴሌቪዥን ብሮድካስተሮች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዷል?

አቶ ግዛው፡- በአጠቃላይ 22 አዳዲስ የቴሌቪዥን ብሮድካስተሮች ይኖሩናል፡፡ ይህም የግል ወይም የንግድና የሕዝብ ብሮድካስተሮችን ይጨምራል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕጉ አልፎ አልፎ የመንግሥት በሚለው ላይ የሕዝብ፣ የሕዝብ በሚለው ላይ ደግሞ የመንግሥት ሚዲያ እያለ ያስቀምጣል፡፡ ሁለቱ አንድ ናቸው እንዴ?

አቶ ግዛው፡- የሕዝብ ሚዲያ መባል ነው ያለበት፡፡ ችግሩ የአርትኦት ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በብሮድካስቲንግ አዋጁ ላይ ከተቀመጡት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ገደቦች መካከል ከሥነ ምግባርና ሞራል፣ ከብሔራዊ ደኅንነትና ከስም ማጥፋት አንፃር የተዘረዘሩት ገደቦች ለትርጉም የተጋለጡ ናቸው ተብለው ይተቻሉ፡፡ አሁን ለውጥ ይኖራል?

አቶ ግዛው፡- በመሠረቱ ገደቦቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ የወንጀል ሕጉም ከአንቀጽ 42 እስከ 47 ድረስ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች ይደነግጋል፡፡ በተግባር በእነዚህና በአዋጁ በተቀመጡ ገደቦች አተረጓጎም ላይ ችግር አልገጠመንም፡፡

ሪፖርተር፡- በረቂቁ አዋጅ ላይ የሙያ ሥነ ምግባር ደንብ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሥነ ምግባር ደንብ አዘጋጅተው የሚዲያ ካውንስል በማቋቋም ሒደት ላይ ናቸው፡፡ ግንኙነታቸው እንዴት ነው የሚሆነው?

አቶ ግዛው፡- ሚዲያ ራሱን በራሱ በመቆጣጠር በኃላፊነት እንዲሠራ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አሁን በአገሪቱ ጠንካራ የሚዲያ ካውንስልና የሙያ ማኅበር አልተፈጠረም፡፡ በሕጉ ላይ የተቀመጠው በብሮድካስት አገልግሎት የሚሰማሩ አካላት ሊኖራቸው ስለሚገባው የሙያው የሥነ ምግባር ደንብ ነው፡፡ መደራረብ አይኖርም፡፡ የሚዲያ ካውንስሉ ተደራጅቶ ከወጣ በጋራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሕጉ የወሰን ስፋት ማኅበራዊ ሚዲያን ይጨምራል?

አቶ ግዛው፡- የመቀበያ መሣሪያዎች ውህደት በቴክኖሎጂው ሽግግር አማካይነት ተፈጥሯል፡፡ በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔትና በሞባይል ስልክ ተመሳሳይ ይዘትና አገልግሎት ስለሚገኝ ቁጥጥሩ መስፋት ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ይህ ሶሻል ሚዲያን አይጨምርም፡፡ በተመሳሳይ ዩቲዩብና ኢሜይልንም አይጨምርም፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የግል የኅትመት ሚዲያው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይህን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለማሻሻል ምን ታቅዷል? ምንስ መደረግ አለበት ይላሉ?

አቶ ግዛው፡- ለግል ወይም የንግድ ጋዜጣና መጽሔት ባለሥልጣኑ የሚሰጠው የምዝገባ አገልግሎት ነው፡፡ የሚመዘገቡት ብዙ ቢሆኑም በሥራ ላይ የቀጠሉት ግን ውስን ቁጥር ነው ያላቸው፡፡ ባለሥልጣኑ ከመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ ባጠናነው ጥናት ዋናው ችግር የገቢ እጥረት ነው፡፡ የአከፋፋዮች ጫናና የሥራ ቦታ ችግርም እንዲሁ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እየሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ ወጣቶችን አደራጅቶ በማከፋፈል ሥራ ማሰማራት አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ በዘርፉ ጥሩ ለሠሩ ማበረታቻ ለመስጠትም ታቅዷል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ረቂቅ የሚዲያ ፖሊሲም ተዘጋጅቷል፡፡ የፖሊሲው ይዘት ርዕዮተ ዓለማዊ ጫና የሚያደርግ እንደሆነ ተተችቷል፡፡ ርዕሱ ራሱ ‘የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና ስትራቴጂ’ ነው የሚለው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው ሊበራል የሆነና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ያለገደብ ከፈቀደበት ሁኔታ አንፃር ነፃነቱን የሚያጠብ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

አቶ ግዛው፡- ከዚህ ቀደም በነበሩና በሥራ ላይ ባሉ የተለያዩ ሰነዶች ላይ ፖሊሲው በፊትም ነበር፡፡ አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተካሄደበት በኋላ የሚዳብር ነው፡፡ አንድ ሚዲያ ዞሮ ዞሮ የሚመስለው የአገሪቱን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ነው፡፡ በአንዳንድ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የሚነገረው የቢዮንሴ የጫማ ቁጥርና የሜሲ ምግብ ነው፡፡ ይኼ ሕገወጥ ስላልሆነ ባለሥልጣኑ አያስቆመውም፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ቅሬታ አለው፡፡ ሚዲያ ሁሌም ተቀባይነት የሚኖረው ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ሲነሳ ነው፡፡ ልማታዊ ሚዲያ ሌሎች እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮችም ያለፉበት ሒደት ነው፡፡ ካደጉ በኋላ ግን ሊበራል ሆነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሊበራል አመለካከት ማራመድ መብት በመሆኑ እሱን የሚያራምዱ የግል የኅትመት ውጤቶች አሉ፡፡ ፖሊሲው የእነዚህን ሚዲያዎች ህልውና ሁሉ አደጋ ላይ የሚጥል ነው ተብሎ ነው የሚተቸው፡፡

አቶ ግዛው፡- እሱ እኮ ገና ረቂቅ በመሆኑ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ የሕዝብ ብሮድካስተር የመንግሥት ሕዝብ ግንኙነት መሆን የለበትም ብሎ የተነሳ ፖሊሲ ነው፡፡ የንግዱ ብሮድካስተርም ምን መሥራት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት የለብህም የሚል ገደብ አያስቀምጥም፡፡ ምን ሚና አለው? ምን ሚና መጫወት አለበት? የሚለውን ነው ለማስቀመጥ የሞከረው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ማንም የመሰለውን ሐሳብ መያዝ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ፖሊሲው ይህን የመገደብ ዓላማ የለውም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች