Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ሬስ ኢንጂነሪንግ ከባድ ማሽነሪዎች ላይ የጂፒኤስ መሣሪያዎችን መግጠም ጀመረ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ሬስ ኢንጂነሪንግ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ያስመጣቸው የነበሩ የከባድ ማሽነሪዎች መቆጣጠርያ መሣሪያዎች (ግሎባል ፖዚሽኒግ ሲስተም – ጂፒኤስ) በኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ችግር ሳቢያ ተቀናጅተው መሥራት ባለመቻላቸው አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውን አስታወቀ፡፡ የድርጅቱ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ መንግሥቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ ሲያስመጣቸው የነበሩ ማሽኖች እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በነፃ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ቢሆንም፣ በተፈጠረው ክፍተት የሦስት ዓመት ጊዜው እንዲሁ ባክኗል፡፡

  ‹‹በሌላው ዓለም ጥቅም ላይ ከዋለ ቆይቷል፡፡ በእኛ ግን ብዙም አይታወቅም፡፡ አዲስ ቴክኖሎጂ ነው፤›› የሚሉት አቶ ፈቃዱ፣ አማራጭ መንገድ በመጠቀም አገልግሎቱን መስጠት እንደተጀመረ ገልጸዋል፡፡ መሣሪያዎችን በከባድ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ በመግጠም በሳተላይት አማካይነት በመቆጣጠር ማንኛውንም የማሽኑን እንቅስቃሴ ማወቅ የሚያስችል መረጃ ለተቆጣጣሪው በሞባይል ስልክ መልዕክት በመላክና በኮምፒዩተር በኩል መረጃ በማስተላለፍ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መሣሪያዎቹ አዲስ በምናስመጣቸው ማሽኖች ላይ ሁሉ ይገጠማሉ፡፡ በፊት የመጡ ማሽኖች ላይም ማስገጠም ይቻላል፡፡ መሣሪያዎቹ በነፃ የሚገጠሙ ሲሆን ለሦስት ዓመታት  ነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በወር እስከ አሥር ዶላር በመክፈል አገልግሎቱን መጠቀም ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ የማሽኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጤንነት፣ በሰዓት ምን ያህል እንደሠራ፣ የተጠቀመው የነዳጅ መጠንና የመሳሰሉትን መረጃዎች መስጠት መቻሉ ባለሀብቶች ንብረታቸውን በቀላሉ እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1965 የተቋቋመው ሬስ ኢንጂነሪንግ በኢትዮጵያ የአሜሪካውን ኩባንያ የካተርፒላር ምርቶችን ሲያከፋፍል ቆይቷል፡፡ ተጨማሪ ብራንዶችን የእርሻና የግንባታ ማሽኖችን ከሜሲ ፈርጉሠን፣ ከፐርኪንሥ፣ ከፎርድ፣ ከትሪማንና ከሌሎችም ድርጅቶች ተቀብሎ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ማከፋፈል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ዶዘር፣ ግሬደር፣ ኤክስካቫተር፣ ኮምፓክተር፣ ጄኔሬተር፣ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ ሐርቨስተርና የመሳሰሉትን ማሽነሪዎች ያስመጣል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም በየዓመቱ ከ200 በላይ ማሽኖችን አስመጥቷል፡፡ ሳሊኒ፣ ሶል ኮንስትራክሽን፣ ሳትኮምና ሌሎችም ትልልቅ ድርጅቶች ደንበኞቹ ናቸው፡፡

   በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በሐዋሳ ቅርንጫፉን ከፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከ500 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡ እንደ አቶ ፈቃዱ ገለጻ ማሽኖቹን የሚያቆዩበትና ክምችት የሚይዙበት መጋዘኖች ባይኖሩትም ትዕዛዝ ሲኖር ወዲያው በማስመጣት እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የመለዋወጫ መሣሪያዎችን በተመለከተ 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት ክምችት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

  ለደንበኞቹ ከሚሰጠው አገልግሎት መካከል የቅድመ ሽያጭ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ በቅድመ ሽያጭ አገልግሎት ለደንበኞች ከመሣሪያ አጠቃቀም ጀምሮ ስለማሽኑ ሊያውቋቸው የሚገቡ ቁም ነገሮችን ማሳወቅ፣ ለደንበኞችና ለሠራተኞች ሥልጠና መስጠት፣ ምርታማነታቸውን ከማሳደግ አንፃር ሊጠቀሙት ስለሚገባቸው የማሽን ዓይነት መምከር እንዲሁም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅ ይገኝበታል፡፡

  በዚህ መሠረትም ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀውና ከጥቅምት 10 እስከ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በቆየው የማሽነሪዎች ዐውደ ርዕይ ላይ ደንበኞቹን ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከሆኑ ትራክታይፕ ትራክተር፣ ሐይድሮውሊክ ኤክስካቫተር፣ ሞተር ግሬደርዊል ሎደርና ከመሳሰሉት አዲስ ሞዴል ማሽኖች ጋር ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ ‹‹ማሽነሪዎችን የምናስመጣው ገበያ ላይ ያለውን ፍላጎት በማጥናት ነው፡፡ ስለዚህም ጥናታችንን ከወዲሁ ጀምረናል፤›› ያሉት አቶ ፈቃዱ፣ አጋጣሚው ምርታማነትን ለማሳደግ ዓይነተኛ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ባለው የገበያ ፍላጎትም ዶዘር፣ ኤክስካቫተር 329 እና 336 ተፈላጊነታቸው ከሌሎቹ እንደሚልቅ ገልጸዋል፡፡

  እንደ እሳቸው ገለጻ የድርጅቱ ካፒታል 703,567,500 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በቅርቡም ራቅ ባሉ አካባቢዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክት ቀርጾ ለመተግበር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባም በአውቶሞቲቭና በእርሻ አጠቃላይ የሽያጭና ከሽያጭ በኋላ አገልግሎት የሚሰጥ ዋና መሥሪያ ቤት ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች