Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የሆቴል ኢንዱስትሪው በክልሎችም መስፋፋት እንዳለበት ተጠቆመ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ደረጃቸውን የጠበቁ  ባለኮከብ ሆቴሎችን ማስፋፋት ወሳኝ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የቱሪዝም መስህቦች ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ በመሆናቸው ጎብኚዎች የሚፈልጓቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች በየአካባቢው እንደልብ አለመገኘታቸው ለዕድገቱ እንቅፋት መሆኑን የጠቆመው ዓለም አቀፉ ጎብኚዎችንና ሆቴሎችን በድረ ገጽ የሚያገናኘውና ጆቫጎ የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ጥቅምት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ ይህንኑ አቅርቧል፡፡

  ‹‹በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ባለኮከብ ሆቴሎች ማሠራት የሚችል አቅም አለ፡፡ ይሁን እንጂ ባለሀብቶች ትኩረት አልሰጡትም፤›› ያሉት የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ የጆቫጎ ቅርንጫፍ  ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኢስተል ቨርዲና ናቸው፡፡ እንደ ቨርዲና ገለጻ፣ የአገሪቱ የቱሪዝም መስክ የወደፊት ተስፋ ይታይበታል፡፡ በዚህ ረገድ አገሪቱ የብዙዎችን ትኩረት መሳብም ችላለች፡፡ ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም የተፈጠረውን  ዕድል ተጠቅመው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሻሻል የተደረገው እንቅስቃሴ እምብዛም አጥጋቢ አይደለም፡፡

  በኩባንያው ሪፖርት መሠረት የባለአንድ ኮከብ ሆቴል አገልግሎት የሚፈልጉ ጎብኚዎች አራት በመቶ፣ ባለሁለት ኮከብ ሆቴል ፈላጊዎች 25 በመቶ፣ ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ፈላጊዎች 33 በመቶ፣ ባለአራት ኮከብ 28 በመቶ፣ እንዲሁም ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ፈላጊዎች ቁጥር ዘጠኝ በመቶ ነው፡፡ ሪፖርቱ የልዩ ልዩ አገልግሎቶች ተፈላጊነትን በተመለከተም እንዲሁ በመቶኛ ለይቶ አስቀምጧል፡፡ 68 በመቶ የሚሆነው ጎብኝ የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት፣ 24 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የመዋኛ ገንዳ ያላቸው ሆቴሎችን ሲፈልግ፣ ስምንት በመቶ የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ክፍሎች እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡ አገሪቱ ካሉባት ችግሮች አንፃር መሥፈርቶቹን ለማሟላት የባለድርሻ አካላት ሆቴሎችን በማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራትን በመጨመርና የአገሪቱትን እምቅ የቱሪዝም መስህብ በበቂ በማስተዋወቁ ረገድ ሰፊ ጥረት እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

  ጆቫጎ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡ በአገር ውስጥ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት በሰባት ወር ጊዜ ውስጥም ከ500 በላይ ሆቴሎች ጋር አብሮ ለመሥራት ችሏል፡፡ በአፍሪካም ከ25,000 በላይ ከሚሆኑ ሆቴሎች ጋር ይሠራል፡፡ በእስያም ከ80,000 በላይ ሆቴሎች ጋር አብሮ እየሠራ ሲሆን፣ ከአውሮፓ ሆቴሎች ጋር የሥራ ግንኙነት እንዳለውም ተገልጿል፡፡

  ጆቫጎ ማንኛውም ግለሰብ ከአንድ ከቦታ ቦታ ለጉብኝት በሚንቀሳቀስበት ወቅት በሚጓዝበት አካባቢ ስለሚገኙ ሆቴሎች ዝርዝር መረጃ የሚያቀርብ ድረ ገጽ ነው፡፡ የአገልግሎት ክፍያውን የሚያገኘውም ከሆቴሎች ሲሆን፣ ክፍያው እንደየስምምነታቸው ይለያያል፡፡ በዚህ መሠረትም ከፍተኛው ኮሚሽን 30 በመቶ ዝቅተኛው 20 በመቶ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ በፈረንሣይ የሚገኘው ጆቫጎ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

  ግብርና መር የሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከቱሪዝም 9.3 በመቶውን ድርሻ ያገኛል፡፡ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ ነው፡፡ ይህም ቢባል መንግሥት ያቀደውን መጠን ለማግኘት ሳይቻለው ቆይቷል፡፡ አንድ ሚሊዮን ጎብኝዎች ይመጣሉ ተብሎ ሦስት ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ቢታሰብም ይህ አልተሳካም፡፡ የዓለም የጉዞና የቱሪዝም ምክር ቤት እንዳስታወቀው የአገሪቱ ቱሪዝም 3.6 በመቶ የሚሆነውን የሥራ ዕድል ለዜጎቹ ፈጥሯል፡፡

  በአኅጉሪቱ ቅርሶች በማስመዝገብ የቀዳሚነቱን ደረጃ ከያዙት ስድስት አገሮች መካከል የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ባስመዘገበችው የቅርስ ብዛት ትመራለች፡፡ ምንም እንኳ በየዓመቱ የሚታየው ዕድገት መልካም ቢሆንም፣ አገሪቱ ካላት እምቅ የቱሪዝም መስህብ አኳያ ዕድገቱ ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ በ2009 ዓ.ም. በእጥፍ ለማሳደግ የታቀደ ሲሆን፣ ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ መንግሥት ከባድ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች