Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ምርምር ተስፋና ትግል እስከ ኢንዱስትሪው መንደር

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንደበተ ርቱዕ የሆኑት የ57 ዓመቱ አርሶ አደር አበበ ደገፋ ከመኖሪያ ቤታቸው ጋር ኩታ ገጠም ከሆነው ስንዴ ማሳቸው አጠገብ ቆመው ‹‹ዛሬ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆን ለአካባቢዬ ሞዴል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፤›› እያሉ ለእንግዶቻቸው ያስረዳሉ፡፡ በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው የቦሩ ሌንጫ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር፣ ለምርት የተቃረበውን የቢራ ገብስ በማስመልከት ከአዲስ አበባና ከክልል ከተሞች ከተወጣጡ በግብርናና ተዛማጅ ሥራ ላይ ካሉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥራ የጀመረበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት ባለሙያዎቹ የጉዞ ዓውደ ጥናት ተዘጋጅቶላቸው በአገሪቱ ተዘዋውረዋል፡፡

ለአካባቢያቸው ‹‹ሞዴል›› አርሶ አደር እንደሆኑ በሙሉ ልብ የሚናገሩት አቶ አበበ፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር ካሉት 17 የምርምር ማዕከላት አንዱ በሆነው የቁሉምሳ ምርምር ማዕከል ተሻሽሎ የወጣውን አዲስ የስንዴ ዝርያ በ1.75 ሔክታር ማሳ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሞክረውታል፡፡ በተመራማሪዎች ‹‹ኪንግበርድ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ምርጥ ዘር እስካሁን የደረሰበት ዕድገትና ፍጥነት በአርሶ አደሩ አስደሳች ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ በፊት ያመርቷቸው ከነበሩ የስንዴ ዝርያዎች የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ለተመራማሪዎችና ለባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

‹‹ለብዙ ዓመታት ከምርምር ማዕከሉ የሚለቀቁ የስንዴም ሆነ ሌሎች አዳዲስ ዘሮችን ዘርቼ አመርታለሁ፡፡ ከተመራማሪዎች የሚሰጠኝን ምክርና ትምህርት ከልቤ አዳምጬ በደንብ አከናውናለሁ፡፡ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች በተነገረኝ መሠረት ስለምጠቀም ከሁሉም ማሳዎች የማገኘው ምርት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ ሞዴል ለመሆን ችያለሁ፤›› በማለት ስኬታቸውን ይመሰክራሉ፡፡

በየጊዜው አገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ቴክኖሎጂዎች ላይ ምርምር በማካሄድ የተሻሻሉ የግብርና ውጤቶችን ጥቅም ላይ የማዋልና የማስተዋወቅ ሥራዎች በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከምሥረታው ጀምሮ ባለፉት 50 ዓመታት በአገሪቱ ከሚገኙ የግብርና ተቋማትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ከ1,100 በላይ የሚሆኑ በሰብል፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ለማቅረብ ስለመቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ የምርምር ሥራዎች ከላይ በተጠቀሱት መስኮች ላይ እየተካሄዱ ሲሆን፣ በተለይ የሰብል ዝርያዎች ላይ የመጨረሻ የሙከራ ምርት የተጀመረባቸው የተሻሻሉ ዝርያዎችም ይገኛሉ፡፡

ለአብነት ያህል በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ተዳቅሎና ተሻሽሎ ‹‹ኮራ›› በሚል ስያሜ የተሻሻለ የጤፍ ዝርያ ለምርት ተለቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቁንጮ የተባለው የጤፍ ዝርያ በምርምር ተሻሽሎ የተለቀቀ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ኮራ የጤፍ ዝርያ፣ በምርምር ተቋሙ የእርሻ መሬት ተፈትሾ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ መተግበር ጀምሯል፡፡ ድርቅን በመቋቋም ችሎታው፣ በምርታማነቱና በአጭር ጊዜ ለምርት መድረስ በመቻሉ የተሻለ ዝርያ ለመሆን በቅቷል፡፡ የኮራ ጤፍን በማሳ በመዝራት ለመጀመርያ ጊዜ በማምረት ላይ የሚገኙት በሎሜ ወረዳ በማኅበር የተደራጁ አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ በዚሁ ወረዳ ደካቦራ በተባለው ቀበሌ የጫጫ ዘር አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር በ1.175 ሔክታር ማሳ ላይ የኮራ ጤፍን አምርተው ለሌሎች አርሶ አደሮች የዘር ሽያጭ ለመፈጸም በመጨረሻው የምርት ሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡

የማኅበሩ ሰብሳቢ አርሶ አደር ይርዳው ሔዬ ሲያብራሩ፣ ‹‹ይኼን ዘር ዘግይተን ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር የዘራነው፡፡ የክረምቱ ዝናብ ዘግይቶ በመጀመሩ ነበር እኛም የዘገየነው፡፡ ነገር ግን አሁን እንደምታዩት ፈጥኖ ከማደጉ ባሻገር ያፈራውን ፍሬ ስታዩት ፈጣን ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

ምንም እንኳ የመጨረሻ ውጤቱ ‹‹እንደ አየሩ ፀባይ›› የሚወሰን ቢሆንም፣ ከአዲሱ የጤፍ ዝርያ በሔክታር ከ40 እስከ 42 ኩንታል እንደሚጠብቁ አርሶ አደሩ ተስፋቸውን በመስክ ጉብኝቱ ወቅት አስረድተዋል፡፡

የኅበረት ሥራ ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት በደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል የተለቀቁ የጤፍ፣ የሽምብራ፣ የምስር፣ የማካሮኒና የፓስታ ስንዴዎችን ጨምሮ የዶሮ ዝርያዎችን ከማዕከሉ ተቀብሎ ለአባላቱና ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ቀደም ብለው ከተለቀቁ የጤፍ ዝርያዎች በአማካይ ከ30 እስከ 35 ኩንታል በሔክታር ሲያመርቱ መቆየታቸውን የሚገልጹት ደግሞ አቶ አዩ ለሚኢርጎ የሎሜ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ናቸው፡፡

‹‹ከዚህ በፊት ከምርምር ማዕከሉ የተለቀቁ እንደ ቁንጮ ዓይነት የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን የወረዳችን አርሶ አደሮች በመዝራት የተሻለ ምርት አግኝተዋል፡፡ የኮራ መምጣት ደግሞ አብላጫ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ምርታማነትን እያሳደግን አንገኛለን፤›› የሚሉት ምክትል ኃላፊው፣ 80 በመቶ የአካባቢው አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንደሆኑም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የደብረ ዘይት ምርምር ማዕከል እስካሁን በአገር አቀፍ ደረጃ ከተለቀቁት 31 የጤፍ ዝርያዎች 26ቱን በምርምር አውጥቶ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች አዳርሷል፡፡ በሎሜ ወረዳ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ የሰብል ዘሮች መካከል የስንዴ ዘር አንዱ ነው፡፡ ለማካሮኒና ለፖስታ የሚሆነው የዱረም ስንዴ፣ የማንጉዶ፣ የህዳሴ፣ የቀቀባ እንዲሁም የደንደአ የተባሉ የስንዴ ተለያይነት ያላቸው ዝርያዎች ለምርት ሥራ ውለዋል፡፡

በሌሎች የምርምር ማዕከላትም የተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ቀደም ብሎ ተለቀው ከነበሩትና አሁንም በምርምር ሒደት ላይ የሚገኙትን ጨምሮ የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ በአገሪቱ ያለው ዓመታዊ አማካይ የምርታማነት ዕድገት 21 በመቶ መድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡

በተሻሻሉ ዝርያዎች በመታገዝ ላይ ያለው የግብርናው ዘርፍ በዋነኛነት አትኩሮቱ በምግብ ራስን ለማስቻልና ከውጭ የሚገባ የግብርና ምርትን በአገር ውስጥ በማምረት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈለገውን የጥሬ ዕቃ ግብዓት ማሟላት ነው፡፡ ከተቋሙ በተገኘ መረጃ መሠረት የጤፍ ምርታማነት ከስምንት ወደ 20 ወይም 25 ኩንታል፣ በቆሎን ከ20 ወደ 70 ወይም 80 ኩንታል፣ ስንዴን ከ12 ወደ 40 ወይም 50 ኩንታል፣ ድንችን ከ80 ወደ 250 ወይም 300 ኩንታል በሔክታር ማሳደግ መቻሉን ያሳያል፡፡ በእንስሳት ዘርፍም ከፍተኛ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያስቀምጣል፡፡

መንግሥት እስከ 2017 ዓ.ም. አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማሳደግ ሲያቅድ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ለማሻገር የሚለው የዕቅዱ ዋና መነሻ ነው፡፡ በዚህም የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ የኢንዱስትሪውን የግብዓት ፍላጎት ማሟላትና ከግብርናው ዘርፍ የሚገኘውን ምርት በኢንዱስትሪ በኩል እሴት በመጨመር የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማገዝ በመንግሥት የታቀደ የሥራ መስክ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ደካማ አፈጻጸሞች ተብለው ከተለዩት ውስጥ ከግብርናው ዘርፍ የሚጠበቀውና ለኢንዱስትሪው ዕድገት ቁልፍ ማነቆ የነበረው የግብዓት አለመሟላት ነበር፡፡ በዕቅድ ዘመኑ ለፋብሪካዎችና በአጠቃላይ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ የሰብልና ሌሎች የግብርና ውጤቶች ላይ ምርታማነትና ጥራትን ሊያሻሽሉ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶች ቢሠሩም፣ በአብዛኛው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚጠይቀውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማሟላት ባለመቻሉ የዕቅድ ዘመኑ ተግዳሮት ሆኗል፡፡

ለአብነት ባለፈው ዓመት ከተስተዋሉትና ዘንድሮም ሙሉ ለሙሉ መቀረፍ ያልቻሉ ዋና ዋና ችግሮች ከታዩባቸው ንዑስ ዘርፎች መካከል የዳቦ ዱቄት እንዲሁም የማካሮኒና ፓስታ ፋብሪካዎች፣ የብቅል ፋብሪካዎችና ብዛት ያላቸው የግብርና ግብዓት የሚፈልጉ አምራች ፋብሪካዎች የግብዓት እጥረት ተቸግረው ይታያሉ፡፡

በፋብሪካዎችም ሆነ በአርሶ አደሩ በኩል የሚፈለገውን የግብዓት መጠን ለማቅረብ እንዲቻል የግብርና ምርምር ተቋማት ተፈላጊ ዝርያዎችን፣ በምርታማነታቸውም ሆነ በጥራታቸው የተሻሉ ብዜቶችን አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ከምርምር ተቋማት ውጪ ወደ አርሶ አደሩና ወደ ኢንዱስትሪው በስፋት ሊደርሱ እንዳልቻሉ የዘርፉ ተመራማራዎች ይስማሙበታል፡፡

ለምሳሌ በቁልምሳ ምርምር ማዕከል ሥር የሚገኘው የበቆጂ ንዑስ ማዕከል በተለይ ለቢራ ጠመቃ የሚፈለገው የብቅል ገብስ ላይ ምርምር በማካሄድ በጥራቱም ሆነ በምርታማነቱ የተሻለ ዝርያ በማፍለቅ ምርምሩን አጠናክሯል፡፡

ለብቅል የሚሆን ገብስ በአገሪቱ በብዛትም ሆነ በጥራት በበቂ ሁኔታ ሊመረት ባለመቻሉ ለብቅል ፋብሪካዎች ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ መቆየቱን የዘርፉ ተዋናዮች  ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡

የአሰላ ብቅል ፋብሪካና ጎንደር የሚገኘው የዳሸን ብቅል ፋብሪካ የሚፈልጉትን ያህል ለብቅል የሚያስፈልግ ገብስ በአገር ውስጥ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ ከውጭ ለማስገባት ከመገደዳቸው ባሻገር ከአቅም በታች ብቅል እያመረቱ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የብቅል ገብስ አቅርቦት ኃላፊ አቶ መኮንን አበራ ለሪፖርተር እንደሚገልጹት፣ በአገሪቱ ያለው የብቅል ፍላጎት በፍጥነት እያደገ መጥቶ ወደ 1.2 ሚሊዮን ኩንታል የደረሰ ሲሆን፣ ዓመታዊ ዕድገቱ 20 በመቶ ሆኗል፡፡ ‹‹በእኛ ፋብሪካ አሁን እየተመረተ ያለው ብቅል በዓመት 360 ሺሕ ኩታል ሲሆን፣ በጎንደር ያለው ፋብሪካ 160 ሺሕ ኩንታል እያመረተ ነው፡፡ በጋራ 520 ሺሕ ኩንታል ብቅል ነው የሚመረተው፡፡ ሁለታችን ከአጠቃላይ ፍላጎት እያመረትን ያለነው 50 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ቀሪው የሚሸፈነው ከውጭ በምናስገባው ነው፤›› በማለት በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ይተነትናሉ፡፡

እንደ አቶ መኮንን ከሆነ፣ የአሰላ ብቅል ፋብሪካ አሁን ያለውን አቅም በአምስት ዓመት ውስጥ በሁለት እጥፍ ለማስፋፋት ያቀደ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያለው የግብዓት እጥረት ግን የፋብሪካው ዋነኛው ሥጋት ሆኗል፡፡

‹‹በዕቅዳችን መሠረት ፋብሪካችንን ለመገንባትና ለማስፋፋት ከሁለት ዓመት የበለጠ አይወስድብንም፡፡ ነገር ግን የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ ትልቁ ሥጋታችን ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ለብዙ ጊዜያት የቆየውን የቢራ ገብስ እጥረት ለመቅረፍ የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ቀደም ብሎ የተሻሻለ ዝርያን አውጥቶ በማባዛት የገብስ ምርታማነትን ለማሳደግ በፕሮጀክት ደረጃ ተሞክሮ ተስፋ እንደታየበት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ አበራ ይገልጻሉ፡፡

ይህንን የተጋሩት የብቅል ፋብሪካው ኃላፊ ከምርምር ማዕከሉ ጋር በጋራ የሚተገበረው ፕሮጀክት ተስፋ ሰጭ ቢሆንም፣ የዘር ዓይነቶቹ የጥራት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ በመምጣቱ ብዙ መዝለቅ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በተለይ ሚሶካል የተባለው ዝርያ ላይ መጀመርያ ተስፋችንን ብንጥልበትም ከተማ ከሚገባው ዝርያ አንፃር ጥራቱ እየወረደ በመምጣቱ ይኼንን ዝርያ ሙሉ በሙሉ ባንተወውም በአብዛኛው አለመጠቀሙን እየመረጥን ነው፡፡››

የፋብሪካው ተወካይም ሆኑ የቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎችና ኃላፊዎች ፋብሪካዎች የሚፈልጉት ጥራትና ከፍተኛነት የዝርያዎች ደረጃ ዝቅተኛ መሆን ላይ የሚስማሙ ሲሆን፣ ከማዕከሉ በተጓዳኝ በሆለታና ሌሎች የምርምር ማዕከላት የተሻሉ ዝርያዎችን በማምጣት የምርት ዘሮች እየተራቡ ነው፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ዝርያዎች ችግር የሆነው በፍጥነት ወደ አርሶ አደሩ ለመድረስና የሚፈለገውን ምርትና ግብዓት ማግኘት አለመቻል መሆኑን የአሰላው ብቅል ፋብሪካ ኃላፊ ጠቁመዋል፡፡ ቢያንስ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የአገሪቱ አጠቃላይ የቢራ ገብስ ፍላጎት ወደ 1.6 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚያሻቅብ የሚገልጹ ትንበያዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ብቅል ፋብሪካዎች የሚፈለገውንና ጥራት ያለውን ብቅል ለማምረት የቴክኖሎጂ ችግር ባይኖርባቸውም፣ በአገር ውስጥ ይኼንን ሊያሳኩ የሚያስችላቸው ግብዓት ስላላገኙ ከውጭ የተሻለ ጥራት ያለው ገብስ እያስገቡ ይገኛሉ፡፡

በአገር ውስጥ ካሉት መካከል ሆለክርና ሳቢና የተባሉ ዝርያዎችን እንደሚጠቀሙና ጥራታቻው ጥሩ የሚባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሚሲካል ለሚባለው ዝርያ ሙሉ በመሉ ስላልተማመኑ ከመጀመርያ ሁለቱ የተሻሉ ዝርያዎች ጋር በመቀየጥ ለብቅል ምርት እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡

የብቅሉን ጥራት የሚያወርደው በመሆኑ ሚስካልን በመቀነስ፣ የተሻሻሉ ባሏቸው ዝርያዎች ላይ ብዙ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሥር ከሰደደው የግብዓት እጥረት ባልተናነሰ መልኩ የብቅል ፋብሪካው ሌላው ፈታኝ ችግር በአገር ውስጥ የሚመረተው ገብስ የመግዣ ዋጋ ከውጭ ከሚገባው አኳያ ውድ መሆኑ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ለአብነት ያህል ፋብሪካው 176 ሺሕ ኩንታል ገብስ ከውጭ ያስገባ ሲሆን፣ የመጫኛ ዋጋን ጨምሮ አንድ ኩንታል የተበጠረ ገብስ በ910 ብር ወጪ አስገብቷል፡፡ ‹‹ነገር ግን ያልተበጠረውና ገብስ ከ10 እስከ 15 በመቶ ብጣሪ ሊወጣለት የሚችለውን ምርት ከአገር ውስጥ እስከ 1,010 ብር ከፍለን እየገዛን ነው፡፡ እንግዲህ ከ10 እስከ 15 በመቶ ብጣሪ ቢወጣው እንኳ ከአገር ውስጥ የምንገዛው ገብስ በአማካይ እስከ 1,200 ብር ድረስ የሚያስወጣ ነው፡፡ ይኼም ከአገር ውስጥ የምንገዛው ገብስ ከውጭ ከምናስገባው ገብስ አኳያ የ300 ብር ልዩነት አለው ማለት ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹በአገር ውስጥ የምናመርተው ምርት በጥራት ከተሻለው የውጭው ገብስ በዋጋ መብለጡ ከዓለም አቀፉ ገበያ ጋር ተወዳዳሪ እንዳንሆን ያደርገናል፡፡ በጥራት በኩል ልዩነት ባይኖርም እንኳ አሁን ያለው የ200 እና 300 ብር ልዩነት ከውድድር ውጪ ያደርገናል፡፡ ስለዚህ በአገር ውስጥ ምርታማነትን በብዛትም ሆነ በጥራት በማስፋፋት የመሸጫ ዋጋውን ልናወርደው ይገባናል፤›› ብለዋል፡፡ የአቶ መኮንንን ሥጋት የሚጋሩት በቁልምሳ ማዕከል የማኅበራዊ ኢኮኖሚክስ ተመራማሪ ዶ/ር ቶሎሳ በበኩላቸው፣ አርሶ አደሩን የመደገፍና ምርታማነቱን የማሳደግ ሥራዎችን አንድ ላይ በማስኬድ በሒደት ዋጋውን ማውረድ እንደሚቻል ያምናሉ፡፡

‹‹አርሶ አደሮቻችንን እንደግፍ፡፡ ያመረቱትን ምርት እኛው ስንቀበላቸው ያድጋሉ፡፡  ምርታማነቱ እያደገ ሲሄድ ዋጋውም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ዘለቄታውን ነው ልናስብ የሚገባው፤›› በማለት ይመክራሉ፡፡

የቁሉምሳ ምርመር ማዕከልና የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የአቅርቦት ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ተቀናጅተው እየሠሩ ነው፡፡ ከዝርያ ማውጣት ጀምሮ በአርሶ አደሩ ተመርቶ ለገበያ እስኪቀርብ እንዲሁም ግብይት እስኪፈጸም ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራን ነው በማለት ስለሚሠሩት ሥራ አብራርተዋል፡፡

ፋብሪካውና ማዕከላቱ የጋራ የምርምር ፕሮጀክቶች ተዘጋጅቶ በአምስት ዓመት ውስጥ ከውጭ ዘር በማምጣትና ከአገር ውስጥ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል የተሻሻሉ ዝርያዎች ወጥተዋል፡፡ አምስት ዝርያዎች እስካሁን የተለቀቁ ሲሆን፣ የተወሰኑት ለምርት ደርሰው ወደ ብቅልነት ተቀይረዋል፡፡ ለፋብሪካ መላካቸውም ታውቋል፡፡

የብቅል ፍላጎቱ በ20 በመቶ እያደገ በመሆኑ፣ የብቅል ፋብሪካ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ቢሆንም የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱን የግድ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ ብቅል ከማስገባት ይልቅ ገብስ አስገብቶ መሥራት አዋጪ ቢሆንም ብቅልን አገር ውስጥ ማሟላቱ አስፈላጊ በመሆኑ የአሰላ ብቅል ፋብሪካን ማስፋፋቱ የግድ እንደሆነ አቶ መኮንን ያምኑበታል፡፡

ፋብሪካዎች በበኩላቸው ያለባቸውን የብቅል እጥረት በመቀነስ የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ለብቅል የሚሆናቸውን የገብስ ዘር ከውጭ በማስገባት በገበሬዎች በኩል ማስመረት ጀምረዋል፡፡

በቢራ ገበያው ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ካላቸው ቢራ አምራቾች አንዱ የሆነው ሄኒከን ከዓመታት በፊት ከመንግሥት ለገዛቸው የበደሌና የሐረር ቢራ ፋብሪካዎች በተጨማሪ በቅርቡ ለገበያ እያቀረበ ባለው የዋልያ ቢራ የሚፈልገውን የብቅል ግብዓት ለማሟላት ለቢሾፍቱ፣ ለአድአ አካባቢዎችና ለአርሲ አካባቢ ገበሬዎች ዘር በማደልና በማኅበር ተደራጅተው የሚያመርቱትን ገብስ መልሶ በመግዛት የብቅል ፍላጎቱን ለማሟላት ካለፈው ሁለት ዓመት ጀምሮ እየሠራ ነው፡፡ ነገር ግን ፋብሪካው ያስመጣው ዝርያ በኋላ አንዳንድ አርሶ አደሮች ከስምምነት ውጪ ለሌላ ቢራ አምራቾች እየሸጡበት መሆኑን ወቀሳ አሰምቷል፡፡

የሃይኒከን ኢተያ ቢራ ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ጋሮምሳ እንደተናገሩት፣ ሄኒከን ከሥራው ውጪ ቢራ ከማምረት አልፎ ከውጭ የተባዛ ዘር በማስመጣት አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ ወርዶ ዘር እያከፋፈለ መሆኑን በግብርና ምርምሩ 50ኛ ዓመት የመስክ ጉብኝት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ከቢራ ፋብሪካዎች በተጨማሪ የስንዴ ምርትን በግብዓትነት የሚጠቀሙ አምራች ኩባንያዎችም ተመሳሳይ የአቅርቦትና የጥራት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ ተስተውሏል፡፡ ለአብነትም ያህል በአሰላ ከተማ የሚገኘው ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ሲሆኑ፣ በስንዴ እጥረት የሚፈለገውን የአቅሙን ያህል ለማምረት መቸገሩን የፋብሪካው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

በተለያዩ የምርምር ማዕከላት በተደረጉ ጉብኝቶች የግብርናው ክፍል በእሱ ላይ ተመሥርቶ እንዲያድግ የሚጠብቀው ኢንዱስትሪው ገና ሰፊ ርቀት እንዳላቸው ተወስቷል፡፡

ምንም እንኳ የተሻለ ምርታማነት ሊሰጡ የሚችሉ የዘር ዓይነቶች ላይ የሚደረገው ምርምር ተስፋ ሰጪና አመርቂ ቢመስልም፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ አርሶ አደሩ በስፋት የማዳረስ ውስንነት መኖሩ ተስተውሏል፡፡ በምርምርም ሆነ ቴክኖሎጂውን በማስፋፋት ረገድ ጥረቱ በጉልህ ባይታይም ከሞዴል አርሶ አደሮች ብዙም አልዘለለም የሚል አስተያየት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አንፃር የግብርናው ኢኮኖሚም ፈታኝ ሥራ እንደሚጠብቀው ከወዲሁ ባለሙያዎች እየተነበዩ ይገኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች